ሳህሌ ደጋጎ

ከውክፔዲያ

ኮሎኔል ሣህሌ ደጋጎ ከእናታቸው ከወይዘሮ ደጊቱ ፈይሣ እና ከባላንባራስ ደጋጎ አለቤ አብራክ በ1923 ዓ/ም በምዕራብ ወለጋ ልዩ ስሙ ነጆ ከተባለው ሥፍራ ተወለዱ። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በነቀምት አንደኛ ደረጃ እና በአዲስ አበባ ተፈሪ መኮንን ት/ቤት ዘመናዊ ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ በነበረው ልዩ የውትድርና ፍቅር በቀድሞ 1ኛ ክፍለ ጦር በኋላም ማዕከላዊ ዕዝ ተብሎ በተጠራው የክ/ዘበኛ የጦር ክፍል ውስጥ በ1942 ዓ/ም ተቀጥሯል። በነበረው ሙያዊ ብቃትና ወታደራዊ ሥነ ሥርዓት አክባሪነት ከተራ ወታደርነት በአንድ ጊዜ የሃምሳ አለቅነት ማዕረግ ማግኘት የቻለው ሣህሌ፤ በሂደት እስከ ኮሎኔል ደረጃ ደርሷል። ወደ ሙዚቃ ቀማሪነት፣ ዜማና ግጥም ደራሲነት እንደዚሁም ወደ የማዕከላዊ ዕዝ የሙዚቃ ባንድ ኃላፊነት ከመሸጋገሩ በፊት በእግረኛ ባንድ ውስጥ “ክላርኔት” የተሰኘው የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዎች የነበረው ሣህሌ ደጋጎ፣ የሙዚቃን ትምህርት የቀሰመው ከፈረንሣዊው መምህሩ ሙሴ ኒኮ መሆኑን የሕይወት ታሪኩ ላይ ተጠቅሷል። ከክላርኔት በተጨማሪ “አኮርዲዮን፣ አልቶ-ሳክስፒያኖ” የተሰኙትን የሙዚቃ መሣሪያዎችንም በብቃት ይጫወት ነበር።

በጠቅል ራዲዮ ጣቢያ (በተቋቋመ ጊዜ ) በአኮርዲዮን ጥዑም ዜማ ለጣቢያው አድማጮች ሲያንቆረቁር ከነበሩት የሙዚቃ ሰዎች መካከል ሣህሌ ደጋጎ የመጀመሪያው ነበር። ከእነ ሻለቃ ግርማ ይህደጎ፣ ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ እና ከሻለቃ ባሻ ገብረዓብ ተፈሪ ጋር በመሆን የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራን ስም እፁብ ድንቅ በማድረጉ በኩል የበኩሉን ሚና ተጫውቷል። ግጥምና ዜማ ደራሲ ከመሆኑም ባሻገር የአጫጭር እና ረዣዥም ድራማዎች ፀሐፊ የነበረው ሣህሌ፣ «ሁለገብ የታሪክ ማኅደር» ያሰኘውን ተግባር በሕይወት ዘመኑ አከናውኗል።

ክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠ ከተጫወታቸው ሙዚቃዎች ውስጥ “ስቆ መኖር”፣ “እውነት ማሪኝ”፣ የሚሉትን ግጥሞች፣ “ዋይ ዋይ ሲሉ”፣ “ውሸት ለመናገር”፣ “ልብሽን ለአፈርሰው”፣ “ኮቱሜ”፣ የሚሉትን ዘፈኖች ግጥምና ዜማዎች የደረሰው ሌ /ኮሎኔል ሣህሌ ደጋጎ እንደሆነ ይታወቃል።

ከዚህም ሌላ ለድምፃዊት ብዙነሽ በቀለ “አይወጣኝም ክፉ ነገር” በሚል የዘፈነችውና በብዙኀን ዘንድ ተወዳጅነት ያለውን (“ወደመጣሁበት ምድር፣ እስክመለስባት በክብር፣ ሰውን ከማስደሰት በቀር፣ አይወጣኝም ክፉ ነገር፣ ...” ) ሙዚቃውን ያቀናበረው ሌ /ኮሎኔል ሣህሌ ነው። ሌ /ኮሎኔል ሣህሌ “ፍላጎቴ”፣ “ምን ነበር”፣ “ምንድነው ትዝታህ”፣ ... የተሰኙትን የብዙነሽ በቀለን ዘፈኖች ያቀናበረ ሲሆን፣ “ከንቱ ሥጋ” የሚለውንና ሌሎችንም ዘፈኖችዋን ግጥም ደርሶላታል። “አታሳየኝ ጭንቁን”፣ “የፍቅር ወጋገን”፣ “ቃልኪዳን”፣ “በብር አይጋዛም”፣ “ፍቅርህ ቀሰቀሰኝ”፣ … የተሰኙትን ዜማና ግጥሞች ያዘጋጀው ሣህሌ ደጋጎ እንደነበረ ይታወቃል።

“ሰው ከተሰማራ” በተሰኘው ዘፈኗ ለምትታወቀው ለድምፃዊት መንበረ በየነ ደግሞ “እንዴት ከረማችሁ” የሚለውን ዘፈን ግጥም የደረሰው ሌ /ኮ /ል ሣህሌ ነበር። “የቆራጡ መሪ ፍሬው ጎመራ” የተሰኘውንና ለቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ላቀነቀነችው ለድምፃዊት ውብሻው ስለሺ ደግሞ “ይህ ነው ጌትነት”፣ “የምድር ፈተና” የተሰኙትንና በ 1966 ዓ /ም የታተሙትን ዘፈኖችዋን ያቀናበረላት ሌ /ኮሎኔል ሣህሌ ደጋጎ ነበር።

በዕድሜ ዘመን የኪነ ጥበብ አገልግሎት የክብር ሜዳሊያ እና የ 20 ሺህ ብር ተሸላሚ የሆነው ሣህሌ ደጋጎ፤ የ 30፣ የ 20 እና የ 10 ዓመት የረዥም ዘመን አገልግሎት የወርቅ፣ የብርና የነኀስ እንደዚሁም የተዋጊ ወታደርነት የደረት ዓርማ ኒሻን ተሸለሚም ነበር። ሙዚቃ ቀማሪው ሣህሌ ደጋጎ ከባለቤታቸው ከወ /ሮ ወይንሸት ተክሉ 4 ሴት እና 3 ወንድ ልጆችን አፍርቶ የ 10 ልጆች አያት ለመሆን በቅቷል። በቀብር ሥነ ሥርዓቱም ላይ ከቤተሰቡ ውጪ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ወዳጅ ዘመዶቹ፣ የቀድሞ የሥራ ባልደረቦቹ እና አድናቂዎቹ፣ የመኖሪያ አካባቢያው ሰዎች ተገኝተው በዕንባ ሸኝተውታል። የአበባ ጉንጉንም አኑረዋል።

ኢህአዲግ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ .ም . ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረ በኋላ ሌ /ኮሎኔል ሣህሌ ደጋጎ ለሰባት ወራት በጦላይ የጦር ማሠልጠኛ ማዕከል ታስሮ እንደነበር ይታወቃል።

በዚህ አጋጣሚ ለመላው የሌተናል ኮሎኔል ሣህሌ ደጋጎ ቤተሰብ አባላት፣ ለወዳጅ ዘመዶቹ እና ለአድናቂዎቹ ፈጣሪ አምላክ ልባዊ መጽናናትን እንዲሰጥ እንመኛለን ።