Jump to content

ቅልልቦሽ

ከውክፔዲያ

ቅልልቦሽ የኢትዮጵያ ህጻናት በጠጠር የሚጫወቱት ሲሆን አጨዋወቱም አንዱዋን ጠጠር ወደአየር በማጉናት እሱዋ ባየር ላይ እያለች የተቻለን ያክል ጠጠር ከመሬት ማፈስ ነው። ባየር ላይ ያለችው ጠጠር ስትመለስ በተጫዋቹ እጅ "መቀለብ" ወይም "መያዝ" ይኖርባታል። ሳትያዝ መሬት ላይ ከወደቀች፣ ጨዋታው አለቀ ማለት ነው። ጨዋታው "ጠጠር" በመባልም ይጠራል።

ብዙ አይነት የቅልልብልቦሽ ጨዋታዎች ሲኖሩ፡ በጣም የታወቀው "ዓይጥ አለብሽ" በመባባል የሚጫወቱት ነው። ልጆቹ ሁለት ወይም ሶስት ይሆኑና፡ አምስት ቆንጆ ድብልብል ጠጠሮች፡ ስፋትና ርዝመታቸው ከግማሽ ኢንች የማይበልጡ፡ ይለቅሙና መሬት ይቀመጣሉ። ቀድሞ "ብጀ" ያለ መጀመርያ ይጀምራል። ብጀ ማለት ብጀምር ማለት ነው። ያንን ለማለት እሽቅድምድም ነው።"ብቀ" ያለ ከርሱ የሚከተል ነው ማለት ነው፡፡ ብቀ ማለት ብቀጥል ማለት ነው። ሁለት ልጆች እኩል "ብቀ" ካሉ በድምጽም ቢሆን ቀድሞ "ብ!" ከአፉ የወጣው ሰው ሁለተኛነቱን ያገኛል። "ብቀጣጥል!" ያለ ሶስተኛ ነው። "እንጀራ ብጋግር!" ያለ አራተኛ ነው። አምስተኛ ካለ "ወጥ ብሰራ!" ብሎ ተራውን ያሳውቃል። በዚህ ተራ ተስማምተው ጀማሪው ይጀምራል።

አጨዋወቱም አራት ደረጃ አለው፤ አራቱንም ደረጃ የሚጫወተው፡ በአንድ እጁ ብቻ ነው፦

የመጀመርያው፡ አንድዮሽ ነው። አምስቱን ጠጠሮች መሬት ላይ ይበትናል። አንዱዋን ያነሳል። ሲያነሳም ሌላ ጠጠር መጭረፍ/መንካት የለበትም፡ ከነካ ለሁለተኛው ያስረክባል ተራውን። ካልነካ ግን፡ ባነሳት ጠጠር አራቱንም፡ ተራ በተራ "ይበላል"- ማለትም፡ መብያ ጠጠሩን ወደላይ እየወረወረ፡ አንድ በአንድ በእጁ እያነሳቸው ይቀልባል። አንዱን ሲበላ፡ ሌላውን ከነካ፡ ወይም ቀድሞ የበላውን ከጣለ፡ "አጣ" ይባልና፡ ተራውን ለቀጣዩ ያስረክባል።

ሁሉንም ከበላ ግን፡ ወደሁለትዮሽ ተራ ያልፋል።አ ምስቱንም ጠጠር እንደመጀመርያው ይበትናል። ሲበትን ግን በጣም እንዳይራራቁ ማድረግ አለበት። ምክንያቱም፡ ሁለቱን አንድ ላይ፡ ሁለቱን አንድ ላይ ነው የሚቀልባቸው፤ ከተራራቁ መቅለብ ላይችል ነው። ከበተናቸው በሁዋላ መብያ ጠጠሩን መርጦ ያነሳል። ከዚያም ሁለት ሁለቱን ይበላል።

ሶስተኛው ተራ "እንቡጥዮሽ" ይባላል። መብያ ጠጠሩን ወደላይ ወርውሮ፡ አራቱን ጠጠሮች አንድ ላይ መሬት ላይ እንደተሰበሰቡ ደምድሞ ቁጭ ያደርጋቸውና፡ የወረወረውን ይቀልባል። ከዚያም፡ መብያውን ወደላይ ወርውሮ፡ ያስቀመጣቸውን አራቱንም በአንዴ ይበላል። አንዲት ጠጠር ከወደቀችበት አጣ ይባልና ተራውን ለቀጣዪ ያስረክባል። ከበላ ግን፡ "አይጥ" ይልና፡ በተቻለ መጠን አምስቱንም ጠጠሮች ከእጁ ጀርባ ወርውሮ ያስቀምጣቸዋል። አንዱዋ ወይም ሁለቱ ተፈናጥረው ቢወድቁ ችግር የለም። ሶስት ወይም ከዚያ በላይ ከወደቀበት ግን፡ አይጡን በሌሎቹ ላይ ማስቆጠር አይችልም። ካልወደቁበት ግን፡ ከእጁ ጀርባ ወደ እጁ ፊትለፊት መልሶ ይቀልባቸውና፡ ያስቆጥራል ማለት ነው- አይጦቹን! መጀመርያ በብቀው ላይ፡ ከዚያም ሁለተኛ ዙር አንድዮሽ፡ ሁለትዮሽና እንቡጥዮሽ ተጫውቶ በብቀጣጥሉ ላይ፡ ወ ዘ ተ... እያለ እስኪያጣ ድረስ ማስቆጠሩን ይቀጥላል።

ጨዋታው ለመዝናናት ጥሩ ሲሆን፡ አይጥ ባስቆጠሩ ቁጥር እየደመሩ ስለሚሄዱ፡ በዚያው ሂሳብ ይማራሉ።