ቆምጬ ኣምብው

ከውክፔዲያ

ቆምጬ አምባውደርግ ጊዜ የቢቡኝ ወረዳ አስተዳዳሪ የነበሩ ሰው ናቸው ።

የቆምጬ አምባው- ቃለ-ምልልስ (በአበባየሁ ገበያው)24 December 2014 at 14:25 የሶሻሊዝምን ርዕዮተ ዓለም በ1960ዎቹ ማብቂያ ላይ በአገራችን ያስተዋወቁት የደርግ ባለስልጣናት ሶሻሊዝምን የተረዱት የ70 ዓመቱ አዛውንት የጐጃሙ ቆምጬ አምባው በተረዱት መንገድ ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያ ታሪክ አሁን ከምናየው ፍፁም የተለየ ይሆን ነበር፡፡ ለእሳቸው ሶሻሊዝም ማለት ሠርቶ ማሰራት ነበር፤ ሶሻሊዝም ሜዳ ተራራውን አረንጓዴ ማልበስ ነበር፤ ለእሳቸው ሶሻሊዝም ብዙ ት/ቤት፣ ክሊኒክ፣ ወፍጮ ቤት፣ መገንባት ሌባን ማጥፋት ነው፡፡ በደርግ ዘመን ለ13 ዓመት የተለያዩ ወረዳዎችን ያስተዳደሩት ቆምጬ፤ በሠሯቸው በርካታ የልማት ሥራዎችና ብልሃት በታከለበት የአመራር ችሎቻቸው ከመንግስትም ከህዝብም ተወዳጅነት እንዳገኙ ይናገራሉ፡፡ እሳቸው ያልተናገሯቸው ብዙ ነገሮች እየተፈጠሩ በስማቸው እንደሚነገሩ አዛውንቱ ቢናገሩም እራሳቸው በትክክል የፈፀሟቸውም ቢሆኑ ከፈጠራዎቹ የሚተናነሱ አይደሉም፡፡ በሃላፊነት በሚመሩት ወህኒ ቤት የነበሩትን በጣታቸው እየፈረሙ ደሞዝ የሚበሉ ያሏቸውን ፖሊሶች በ60 ቀን ማንበብና መፃፍ እንዲማሩ የፈጠሩት ብልሃት ተጠቃሽ ነው፡፡ ኰሎኔል መንግስቱ ሃ/ማርያም በሥራቸው ተደስተው ሽጉጣቸውን ሲሸልሟቸው አልተቀበሉም - ከሽፍታ ያስፈታሁት 18 ሽጉጥ አለኝ በማለት፡፡ በምትኩ ግን ለህዝቡ መብራትና ውሃ እንዲገባለት ጠይቀዋል፡፡ በትውልድ አገራቸው በጐጃም ያገኘቻቸው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ሰፊ ቃለ-ምልልስ ያደረገችላቸው ሲሆን አንባቢያን የእኒህ መለኛ አብዮተኛ ታሪክ ከነለዛቸው ይደርሳቸው ዘንድ ቃለምልልሱን እንደወረደ አቅርበነዋል - ከአነጋገር ዘዬአቸው ጋር፡፡


የት ተወለዱ? መቼ?

የተወለድኩት በጠላት ወረራ ዘመን ነው፡፡ በጐዛምን ወረዳ ማያ አንገታም ቀበሌ ገበሬ ማህበር፣ አባላይ በተባለ ቦታ ሜዳ ላይ ተወለድኩ፡፡ እናቴም አባቴም አርበኛ ናቸው፡፡ ስወለድ ማን እንበለው እያሉ ሲመካከሩ ሳለ አንድ አውሮፕላን ትመጣና ክምር ስታቃጥል፣ አባቴ አነጣጥሮ ቢተኩስ ተንከታክታ ወረደች፡፡ ያን ጊዜ ቆምጬአምባው እንበለው፤ ይኼ ልጅ ገዳም ነው ተብሎ ነው ስም የወጣልኝ፡፡

ለትምህርት እንደደረስኩ እዚያው ቀበሌ አንገታም ጊዮርጊስ የቄስ ትምህርት ተምሬ፣ ዳዊት ፆመድጓ ጨርሼ ወደ ቅኔ ቤት ገባሁ፡፡ በሽታ እንደገባ አባቴ ከቅኔ ቤት አውጥተው ወሰዱኝ፡፡ በ15 ዓመቴ የሰባት ደብር የጐበዝ አለቃ ሆንኩኝ፡፡

ቆምጬ ማለት ምን ማለት ነው?

ደፋር፣ ጠንካራ፣ ቆራጥ ማለት ነው፡፡

በሸዋ ግን ትርጉሙ ሌላ መሰለኝ. . .

አዎ፡፡ በእኔ በኩል ግን ቆምጬ ማለት ታይቶ የሚታለፈውን የሚያውቅ፣ ታይቶ የማይታለፈው ላይ ቆራጥ እርምጃ የሚወስድና ሩህሩህ፣ የዋህ ማለት ነው፡፡

ወጣትነትዎ እንዴት አለፈ?

በወጣትነቴ የቤተሰብ ተጽዕኖ ነበረብኝ. . . ሰው ፊት ጠላ መጠጣት አይፈቀድልኝም፤ ውሃ እንኳን ጭልጥ አድርጎ መጠጣት እንከለከላለን፡፡ ስንበላ አፋችሁን ገጥማችሁ አፋችሁን አታጩሁ፤ እየተባልን ነው ያደግነው፡፡ አባቴ ቅዳሴ አስቀድሼ ወጥቼ መሃራ አያስቀምጡኝም ነበር፡፡ ..መሃራ መብላት ያለበት አቅም ያጣ፣ ቤቱ የሚበላው የሌለው ነው፡፡ አንተ ሁሉ ነገር ቤትህ ሞልቶ የተረፈህ ስለሆንክ ምንም እንዳትቀምስ.. እባላለሁ፡፡ ሰርግ ስንሔድ የአባቴን መሣሪያ ይዤ ከበስተጀርባው ነበር የምቀመጠው፡፡ እህል በወሰክንባ(ሞሶብ) ነበር የሚመጣልኝ፡፡ ጨዋታ አምሮኝ ከጉብላሊቱ(ህጻናት) ጋር መደባለቅ አይፈቀድልኝም፡፡ ከፍተኛ ተጽዕኖ ነበረብኝ፡፡ በፆም ቀን ከስምንት ሰዓት በፊት ስንበላ ከተገኘን እንደበደባለን፡፡ የገና ጨዋታ፤ ፈረስ ግልቢያ፣ ዋና፣ አውሬ አደን ምን ልበልሽ ያልተሳተፍኩበት የለም ...ከሁሉም ግን ደስ የሚለኝ አደን ነበር፡፡

ምን አድነዋል?

ድኩላው፣ አሳማው፣ ሚዳቋው. . . በለሴ ሆኖ ወደ እኔ ይመጣል፡፡ በቃ ሆ እያልን አገሬ ይዤ እገባለሁ፡፡ ከሰው የተጣላሁ እንደሆን አባቴ አይለቀኝም ነበር፡፡

የደብር አለቃ ሳለሁ ሰው ሲጣላ ባውቀውም ባላውቀውም አስታርቅ ነበር፡፡ በዚያውም የስብሰባን ጥቅምና የአንዳንድ ነገሮችን ሁኔታ ማየት ጀመርኩ፡፡

ስለትዳርና ቤተሰብ ይንገሩኝ. . .

አስር ልጆች አሉኝ፡፡ ባለቤቴ አሁን ያለችት የልጆቼ እናት ናት፡፡ ለሷ የእኔ እና የእሷን ስምንት ስምንት የቀንድ ከብት አማተን ደርሰን ሃብታም ሆነን፤ ኋላ ገንዲ በሽታ መጣና ከብቱን ሲፈጀው ተበሳጨሁና ወደ ጐጃም ጠቅላይ ግዛት መጣሁ፡፡ የምክትል ፀሃፊነት ፈተና ተፈተንኩና አለፍኩ - ጃናቢት በተባለች ስፍራ፡፡

ደሞዙ ጥሩ ነበር?

25 ብር ነው፡፡ ማለፌን ከሰማሁ በኋላ አንድ አህያ ተልባ፣ አንድ አህያ ኑግ ጭኜ ወደ ደብረማርቆስ ገበያ ወጣሁና ቦጋለ በረዳ የሚባል ቦታ ሸጥኩት፡፡ ከዚያ ምክትል ፀሃፊነት አለፍኩ አልኩና ሁለት አዝማሪ ጥሩ ብዬ፣ ሹመቴን እያነሳሳ ሲዘፈን ሲጠጣ ሲበላ ታደረ፡፡ ጥቂት ብር ቀረችኝ፡፡ ማለዳ የሹመት ደብዳቤውን ልቀበል አውራጃ አስተዳደሩ ጋ ስሄድ የወረዳው ገዢ ቀኝ አዝማች ረታ ፈረደ ይባላሉ ..አንተ ነህ ምክትል ፀሃፊ የተሾምከው?.. አሉኝ፡፡ አለባበሴም ደህና ነው ያን ጊዜ፤ ንቁ ነኝ፡፡ ..አዎ.. አልኳቸው፡፡

..አንተማ የዋናው የከበርቴ ልጅ አይደለህ፤ ሰባት ጉልት እያሳረሳችሁ፤ አንተን አንቀጥርም! በል ውጣ ከቢሮዬ.. አሉኝ፡፡ ተበሳጨሁ ገንዘቤን ጨርሻለሁ፤ ሌላ አማራጭ ሳፈላልግ በደብረማርቆስ ወህኒ /ቤት ለወታደርነት ቅጥር የተለጠፈ ማስታወቂያ አየሁ፡፡ ወዲያው እለቱን ተመዝግቤ አለፍኩ፡፡ ሲያዩኝ በቁመትም በክብደትም እኩል መጣሁ፡፡ ወደ ማሰልጠኛ ላኩኝ፡፡ ከማረሚያ ቤት አስተዳደር ወታደሮች አስራ ሰባት፣ ከፖሊስ ሰባት ነበር የተመለመለው፡፡ እዚያ ተደባልቀን ስንማር በፀባይ፣ በተኩስ፣ ህግ በማወቅ አንደኛ ወጣሁ፡፡የዚያን ጊዜው አገረገዥ ደጅአዝማች ፀሃይ እንቁ ኃይለስላሴ፣ የምስክር ወረቀት ሲሰጡ ..በወታደራዊ አቋም፣ በፀባይና በተኩስ ወታደር ቆምጬአምባው ይልማ አንደኛ.. ብለው ሸለሙኝ፡፡ ኮሎኔል አሰፋ ወንድማገኘሁ ከሚባሉ ከወህኒ ቤቱ አዛዥ ጋር ጠሩኝና ..ከአስራ ሰባቱ ወታደር አንተ በጣም ጠንካራ ነህ፤ ወደፊትም እናሳድግሃለን.. አሉና ሃምሳ ብር በግሌ ሰጡኝ፡፡ የወህኒ ቤቱ /ቤት የእስረኞች የህግ አማካሪና የጠቅላይ ግዛቱ ወህኒ ቤት ጠበቃና ነገረ ፈጅ አደረጉኝ፡፡ ኮልት ሽጉጥም ሸለሙኝ፡፡

ከእስረኞች ጋር ስለነበርዎ ግንኙነት ያጫውቱኝ፡፡

እስረኛው አንዳንድ ጊዜ ..ምግብ ጠቆረ.. ይልና ያድማል፡፡ ..እኛ መነገጃ አይደለንም.. ይላል፡፡ የጐጃም ጠቅላይ ግዛት በሙሉ፣ የ35 ወረዳና የሰባቱ አውራጃ እዚሁ ነበር የሚታሰረው - የመተከል፤ የቤንሻንጉል፤ የባህርዳር ሁሉ ማለት ነው፡፡ እስረኛው ሲያድም እኔ ሽጉጥ ታጥቄ በመሃላቸው እገባና ..እናንተን ያሰራችሁ ሰው አይደለም፤ ያሰራችሁ እግዚአብሔር ነው፡፡ እዚህ እኮ የምትፀልዩበት፣ የምትማፀኑበት፣ ፍርድ እናግኝ ብላችሁ የምትለማመኑበት ነው፡፡ የጐጃም ሰው ሆዳም አይደለም ምግብ አነሰኝ ብሎ አይናገርም፡፡ አናንተ ቆሎ፣ በሶ፣ በግም ፍየልም አሳርዳችሁ ትበላላችሁ፤ አገራችን ተሰደበ.. ብዬ ያንን ጠቆረ አንበላም ብለው የተውትን ጥቁር እንጀራ እነሱ መሃል ሆኜ ቆርሼ እበላዋለሁ፡፡ ያንዜ ያጨበጭባሉ፡፡ ከዛ በኋላ አድማው ይበተናል፡፡ ..አሁን ትፈታላችሁ ግማሻችሁ በአመክሮ፤ ግማሾቻችሁ ደግሞ ፀባያችሁ ጥሩ ከሆነ ሚያዚያ 27 በአርበኞች ድል በዓል ወይም ሐምሌ 16 በጃንሆይ ልደትና ጥቅምት 23 በጃንሆይ የዘውድ በአል ትፈታላችሁ፡፡ እንቢ ካላችሁ ግን ችግር ላይ ትወድቃላችሁ.. ስላቸው በጀ ይላሉ፡፡ የጣቢያው አዛዥ ንግግር ስለማያውቅበት ቀጠሮ ስጡኝ ብዬ እኔ ነበርኩ የማናግራቸው፡፡

ለእስረኛው ያወጡት ህግ ነበር ይባላል?

ህጉ እያንዳንዱ እስረኛ ሰውነቱን በሳምንት አንድ ቀን ፀጉሩን ዕለት ዕለት እንዲታጠብ የሚል ነው፤ አሽቶ የሚያጥበው በወር 1 ብር ከፍሎ ሰው ራሱ ይቀጥራል፡፡ እስረኛው ገንዘብ ነበረው፡፡ ሞልቶታል፡፡ ከዚያ አሰልፋቸውና ከኪሴ ነጭ መሀረብ አውጥቼ የአንዱን ደረት አሸት አድርጌ ..ይሄው እድፍ አለው ውጣ.. እለዋለሁ፡፡ ንፁህ ሆኖ ያገኘሁትን ደግሞ አንድ ብር አወጣና እሸልመዋለሁ፡፡ ያን ጊዜ እስረኛው ሁሉ ንፁህ ለመሆን መሯሯጥ ነው፡፡ የመኝታቸውን ዳትም ክፍላቸው እየገባሁ እፈትሽ ነበር፡፡ ይሄን አይተው ደጃዝማች ፀሃይ (በ1958) የደ/ማርቆስ ቤተመንግስት ሲሰራ ..ይሄ ጐበዝ ልጅ ነው፤ ጠንካራ ሰራተኛ ነው.. ብለው ወሰዱኝና እንደገና ተሸለምኩ፡፡

ንጽህናውን ያልጠበቀ እስረኛስ? ቅጣት አለው?

አዎ ይቀጣል፡፡ አስር የችግኝ ጉድጓድ አስቆፍረዋለሁ፤ በግቢው ውስጥ የፍራፍሬና የአትክልት ስፍራ ስለነበረ እሱንም አስቆፍራቸዋለሁ፡፡ ሰው ገድሎ የታሰረውን ግን ወታደሩ ስራ አናሰራም ብሎ ይቃወመኛል፤ መሳሪያ ነጥቆን ይሄዳል በሚል፡፡ ..በያዝከው መሳሪያ አጨማደህ አትጥለውም፤ እንግዲህ በእግር ብረት ታስሮ አይሞትም.. እልና፤ የገደለውን ሁሉ ሰብስቤ ..ኑ ተንቀሳቀሱ ይሄ ስራ የእናንተ ነው፣ አካልና አእምሮአችሁን አስተባብራችሁ በሞራል የጠነከራችሁ እንድትሆኑ ስሩ.. እላቸዋለሁ፡፡ በጣም ይወዱኛል፡፡ ፍ/ቤት ለስራ ስሄድ ባዶ ወረቀት ካገኘሁ ሰብስቤ አመጣና አንዳንዱን በሽልማት እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘመድና ለምሽት ደብዳቤ መጠጣፊያ፡፡ ከዚያ ፊደል ሠራዊት የሚባል መሰረተ ትምህርት ተቋቋመ፡፡ በደጃዝማች ፀሃይ ጊዜ፣ አቶ ሸዋቀና የተባሉ የትምህርት ሚኒስቴር ሃላፊ፣ የጠቅላይ ግዛቱን ወህኒ ቤት እሱ ነው ማስተባበር የሚችለው አሉና እኔን ሾሙኝ፡፡ ማንበብ መፃፍ የማይችል፤ በጣቱ እየፈረመ የሚበላ ፖሊስ ሞልቷል - ያኔ፡፡ አዳራሽ ላይ ሰበሰብኩና እስከ ስልሳ ቀን ድረስ ማንበብና መፃፍ ካልቻላችሁ ሚስጢር ነው የምነግራችሁ ..ትባረራላችሁ.. ተብሏል አልኳቸው፡፡ (ሳቅ) መንግስት አቋም ይዟል፤ ማታ ማታ ልጆቻችሁ ቤት ውስጥ ያስተምሯችሁ አልኳቸው፡፡ ማንበብ መፃፍ የማይችል ሠራዊት በፍፁም አይሆንም፤ እየተባለ ነው ስላቸው. . . ማታ ማታ ጥናት ነው፣ ማንበብ ነው፡፡ ሲፈተኑ ደህና ናቸው፡፡ ..ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘኢትዮጵያ.. ብዬ ብላክ ቦርዱ ላይ ፃፍኩና ገልብጡ አልኳቸው - እንዳለ ፃፉት፡፡ በዚህም ተሸለምኩ፡፡

አብዮቱ ሲፈነዳ በአንድ ቀበሌ ውስጥ ህዝቡ ስለሚያውቀኝ የአብዮት ጥበቃ የፍርድ ዳኛ ሸንጐ ውስጥ ገባሁ፡፡ በደብረማርቆስ በድሮው ቀበሌ 8 ዳኛ ሆንኩ፡፡ ስራዬ እርቅ ነበር - ይቅር ተባባሉ ማለት፡፡ ፍርድ የሚሻውን ደግሞ ፍርድ እያሰጠሁ እየቀጣሁ በሬድዮ አስነግራለሁ፡፡ ጉልታዊ አገዛዝን እየኮነንኩ፤ የሠራተኛውን መደብ ንቃ እያልኩ የተናገርኩ እንደሆነ መልእክቴ ሁሉ በሬድዮ ይሰማ ነበር፡፡

በአፄ ኃይለስላሴ ጊዜ ከሽፍቶች ጋር ተደራድረሃል ይባላል?

የገበሬው አመ በሚባልበት በነ ባምላኩ ጊዜ፣ እነ ደጃዝማች ፀሃይ ከደ/ማርቆስ ይነሱ በሚባል ጊዜ ከብፁዕ አቡነማርቆስ ጋር ደብረወርቅ ሄጃለሁ፡፡ ገበሬው ሰው ቆምጬን ያውቀዋል ብሎ ለከኝ፡፡ በኢሊኮፍተር ነበር የሄድነው፡፡ ከዛ ከኢሊኮፍተሩ ላይ ስንወርድ ከርቀት አነጣጥረው የብፁዕ አቡነ ማርቆስን ቆብ ይመቱታል፤ ..ጐንበስ ይበሉ ጐንበስ ይበሉ.. አልኳቸው፡፡ በኋላ እንደ ምንም ወጣን፡፡

በዚያን ወቅት እንግዲህ ሀገሩ ሁሉ ሸፍቶ ነበር፡፡ ወንበዴ በወንበዴ ሽፍታ በሽፍታ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ማነው አሁን እነሱ ጋ ሄዶ እርቅ የሚለምን ተብሎ አገር ይታመሳል ..እኔ እሄዳለሁ ምን ችግር አለው.. ብዬ ሽጉጡንም፣ ኡዚ አቶማቲክ ጠመንጃም ይዤ በመሃላቸው ገባሁና ..ደህና ዋላችሁ፤ ደህና ዋላችሁ.. ስል ሁሉም ተነስቶ ሰላም አለኝ፡፡

ሽፍቶቹ?

እህሳ! ያ ሁሉ ሽፍታ እኮ ታስሮ የተፈታ ነው፡፡ በእስር ቤት ውስጥ ሁሉም ነበር የሚያውቀኝ፡፡ በኋላ ከፊታቸው ቆሜ ንግግር አደረኩ፡፡ ..እናንተ ብቻችሁን አትችሉም፡፡ ሃገር ልታስደበድቡ ነው፤ ክቡር ዘበኛ መጥቷል፡፡ ዛሬ ምላሻቸውን እንፈልጋለን መልሱን አምጣ ተብዬ ነው.. ስላቸው ..አንተማ የሀገራችን ልጅ ነህ ሌላ ቢሆን በጥሰን በጣልነው ነበር፡፡ በእስር እያለን ከሚስታችን ከዘመዳችን እያገናኘህ ብዙ የረዳኸን ነህ፡፡ አሁንም የምትለንን እንሰማለን፤ ጦርነት አንፈልግም፤ እኛ የምንፈለገው አንድ ብር ከሃምሳ ግብር እንዲነሳልንና ደጃዝማች ፀሃይ እንዲወርዱልን ነው.. አሉኝ፡፡ እዚያው ያሉትን ቁጭ ብዬ ፃፍኩና ..መልስ እስክናመጣላችሁ ወደ ቤታችሁ ግቡ፡፡ እርሻም እረሱ፤ የመጣውም ጦር ይመለስ፤ ጳጳሱም መጥተው ተኩሳችሁ ልትገሏቸው ነበር፡፡ እግዚአብሔር ነው ያወጣቸው፡፡ አሁን እሳቸው ሊያስታርቁ ቢመጡ ሊያስተኩሱ እንደመጡ ሁሉ እንዲህ ታደርጉ? እኔም ደሞ የሀገር ሰው ነህ፤ ወንድም ነህ ተብዬ ተመርጬ ነው የመጣሁ፡፡ የተከበሩ አቶ መኮንን እውነቴን፤ የተከበሩ በከፋ የኔነህን ታውቋቸዋላችሁ አይደል? በአምስት አመት የጠላት ወረራ ዘመን ከደጃዝማች በላይ ዘለቀ ጋር አብረው የነበሩ፣ የደጃዝማች በላይ ዘለቀን ማህተም ይዘው ይፉ የነበሩ ናቸው. . . ጠላትን ያርበደበዱ የነበሩ፡፡ ዛሬ ደግሞ አስታራቂ ሆነው መጡ፡፡ በሉ እነሱ ይምጡና ሰላም በሏቸው.. አልኳቸው፡፡ ..በቃ እሺ...... ወታደር እንዳይመጣ እነሱ ይምጡ.. አሉ፡፡ ይዤአቸው ሄድኩ፡፡ ብቻ ወዲህ ወዲያ ብለን ደጃዝማች ፀሃይ ወረዱ፡፡ ሰላም ሰፈነ፡፡

የደርግ መንግሥት እንዴት ተቀበለህ?

በደርግ ሥርዓት ሌባ፣ ሴሰኛ፣ ገንዘብ የሚያታልለው፣ ጥቅም ፈላጊ ፓርቲውን አይቀላቀልም ነበር፡፡ እንጃ! በኋላ አበላሽተውት እንደሆነ አላውቅም፡፡ የመደብ ትግሉን ለመቀላቀል የሚፈልግ ሰው የግል ማህደሩ ይታያል፡፡ እኔ በመጀመርያ በሙሉ ፈቃደኝነት ማመልከቻ የፃፍኩት ..የኢትዮጵያ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራምን ተቀብያለሁ፤ ከሰፊው ህዝብ ጥቅም ይልቅ የራሴን ጥቅም አላስቀድምም፤ ከራሴ ጥቅም ይልቅ የሰፊውን ህዝብ ጥቅም አስቀድማለሁ፣ እየተማርኩ ከአብዮቱ ጋር ለመቀላቀል ፈቃደኛ ነኝ.. ብዬ፡፡ ማመልከቻዬ ተመረመረ፤ ጀርባዬን አስጠኑኝ - በደህንነቶች፤ በጐረቤት፡፡ በኋላ በቀበሌ የጥናት ክበብ ውስጥ አስገቡኝ፡፡ በመንግሥት ሥራ ተወጥሮ የጥናት ክበቡ ላይ ያልተገኘ እንኳን ይሰረዛል፡፡ መማር ግድ ነበር፡፡

ትምህርቱ ምንድን ነው?

የካፒታሊስት ስርዓትና፤ የሶሻሊስት ስርዓት ምንድን ነው? ጠቃሚው የትኛው ነው? በሚል ነበር፡፡ ከዛም የሠራተኛው መደብ ንቅናቄ በጀርመን በአሜሪካ ምን ይመስላል የሚለውን. . . ከዛም የምትበይው፣ አረማመድሽ፣ ንቃትሽ፣ ንግግርሽ ሁሉ ይገመገማል፡፡ የገባው ሁሉ አይዘልቅም፡፡ ልክ መንገድ ላይ መኪና እንደሚጥለው ፌርማታ ላይ እየተራገፈ ይሄዳል፡፡ ከብዙ ምልምሎች ጥቂቶች ቀረን፡፡ . . . እኔ እዚህም ምስጉን ነበርኩ፡፡

ምስጉንነትህን ማን ነገረህ?

ጓድ መንግሥቱ ናቸዋ! አፍና ተግባር ይሉኝ ነበር፡፡ አንደዜ እሳቸው በምሠራበት አቸፈር አካባቢ መጥተው ሳለ. . . እኔ አላውቅም ነበር እንደሚመጡ፡፡ የከብቶችን አዛባ እዝቅ ነበር፡፡ ኮረኔል ዘለቀ ..ና ሰላም በል ና ሰላም በል.. አሉኝ፡፡ ሸሚዜን ወደ ላይ ሸበሸብኩና ስጨብጣቸው ..ጓድ ቆምጬ አስተዳድሩ ተባለ እንጂ አዛባ ይዛቁ ተባሉ.. አሉኝ፡፡ ..ጓድ መንግስቱ፤ እኔ ካልሠራሁ ሌላው ስለማይሰራ ነው.. አልኳቸው፤ ዞረው ሁሉን አዩ፡፡ በቆሎው፣ በርበሬው ደርሷል፡፡ በቆሎውን ሸለቀኩና አንዱን ወታደር እንካ ጥበስ አልኩት፡፡ በኋላ ጠብሶ ሲሰጠኝ እንኩ አልኳቸው፤ ሰበር አድርገው እሸቱን በሉ፡፡ ቀሪውን ለአጃቢው ሰጠሁት፡፡ ያሉት ሁሉ አንዳንድ በቆሎ በሉ፤ ቆሎ በኑግ ከመንደር መጣ፡፡ ጠላ በዋንጫ ቀዳሁና እኔ መጀመሪያ ..ፉት.. አልሁና ሰጠኋቸው፡፡ ..ለምን ነው? ለምን ነው? ዝም ብለው ያምጡት አሉኝ.. መቸም ኸዱ ብዬ አላማቸውም፡፡ ..ለምን ቀመሱት ጓድ ቆምጬ ያምጡት በሉ.. አሉኝ ..አይ የጎጃም ባህል ነው፡፡ ማንም እንዲህ ሲሰጥ ቀምሶ ነው ሚሰጥ፤ እንቆቆ ወገርት መድኃኒት ሲሰጥ እንኳን ቢሆን ቀምሶ ነው፤ የሀገሩን ባህል ለማንፀባረቅ ነው.. አልኳቸው፡፡ በኋላ በርበሬ ጧ ብሎ ደርሷል፤ ይዩት ብዬ እሱን አሳየኋቸው፡፡ ጓድ ካሣ ገብሬ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴሩ ወፍራም ነበሩ፤ እኔ አላውቃቸውም ነበር፡፡ እንደዛሬው ቴሌቪዥን የለም፡፡ ሳያቸው ሆዳቸው ቦርጫቸው ሌላ ነው ..እስዎም አሁን ኮሚኒስት ተብለው ነውን?.. አልኳቸው፡፡ መሀረባቸውን ከኪሳቸው አውጥተው እምባ በእምባ እስቲሆኑ ድረስ ከት ከት ከት ብለው ሳቁ፡፡

አንተስ ቀጭን ነበርክ?

በጣም፡፡ ይኸውልሽ ወንበዴ እየመጣ ሁልጊዜ ተኩስ ነው፡፡ ሀሳብ ነበረብኝ፡፡ በዚያ የተነሳ ሃሳቡ ነው መሰለኝ በጣም ቀጭን ነበርኩ፡፡ በኋላ ጓድ መንግሥቱ ..እስቲ የወረዳውን ተፈጥሯዊ ገታና አጠቃላይ ሁኔታ አምጣ.. አሉኝ፡፡ ..አውራጃ አስተዳዳሪው ጓድ መስፍን አለ አይደል.. አልኳቸው፡፡ ..ከወረዳው መስማት ነው የምንፈልግ.. አሉ - እሳቸው፡፡ ያለውን ነገር ሁሉ ቁጭ አደረኩላቸው፡፡ በመሠረተ ትምህርት ቅስቀሳው አንዳንዶች አትማሩ እያሉ እየቀሰቀሱብን ነው እንዲያውም አስራ ሁለተኛ ክፍል የጨረሰውን ሥራ ሳያሲዙ እያሉ እንደሚያሳምፁና ወረዳውም በከፍተኛ ሁኔታ ኋላ ቀር መሆኑን፣ የመብራትና የውሃ ችግር መኖሩን፣ የአቸፈር ልጅ ለአብዮቱ በየተራራው እንደሚዋጋ ሃቁን ስነግራቸው ..እነዚህ ወረበላዎች ምን እያሉ ነው የሚቀሰቅሱ.. አሉኝ፡፡ አይ ይሄን የነገርኩዎን ነው አልኳቸው፡፡ የወረዳውን ለእኛ ተውት፤ ግን ነገሩ በውይይት ቢፈታ አልኳቸው ..በውይይት ሲሉ ምን ዓይነት ነው?.. አሉኝ፡፡ ..ሰውን የሚያጣላው የስልጣን ጥያቄ ነው ጓድ ሊቀመንበር.. አልኳቸው፡፡ ..ለመሆኑ እርቅና ድርድር ቢጀመር ትኩረት ሰጥተው ይከታተሉታል.. አሉኝ፡፡ ..አዎ.. አልኳቸው፡፡ ..እንዴት.. አሉኝ፡፡ ..በክቡር አቶ አማኑኤል አምደሚካኤል የሚመራ ቡድን ሦስት ጊዜ ሂዶ እርቁ ከሸፈ፡፡ በሬዲዮ የሰማሁትም የኢትዮጵያ መንግሥት እምቢ አለ የሚል ነው.. አልኳቸው፡፡ ..ለማንኛውም ጥሩ ግንዛቤና የሀገር ፍቅር አለህ፡፡ አፍና ተግባር ትክክል ሆኖ ያየሁት ባንተ ነው.. አሉኝ፡፡ ተዚያም ሽጉጥ አውጥተው ..ገንዘብ የለኝም.. አሉና ሊሰጡኝ ሲሉ ..ኧረ እኔ ተሽፍታ ያስፈታሁት አስራ ስምንት ሽጉጥ አለ፡፡ እንደውም ከቸገራችሁ ውሰዱ አልፈልግም.. አልኳቸው፡፡ ..ታዲያ ምንድነው የሚፈልጉት.. ሲሉኝ ..መብራት እና ውሃ ለሰፊው ህዝብ.. አልኳቸው፡፡ ጓድ ፍቅረስላሴ ወግደረስ አብረው ነበሩ፡፡ ..ጓድ ፍቅረሥላሴ፤ ቀን ሰጥቼሀለሁ. . . በተገኘው ገንዘብ ሁሉ መብራትና ውሃ እንዲገባ.. ብለው መመሪያ ሰጡልኝ፡፡ ስልሳ ቀን ሳይሞላ መብራትና ውሃ ገባ፡፡

ለአስተዳዳሪነት የተመደብክበት የመጀመሪያ ቦታ የት ነበር?

ቢቡኝ ነበረ፡፡ ቢቡኝ ማለት እስታሁንም አረንጓዴ ትርዒት ማለት ነው፡፡ በሄድኩበት ወረዳ የተፈጥሮ ሀብት እንክብከቤ በማድረግ የደን መራቆት እንዳይኖር ሳልታክት እሠራ ነበር፡፡ ከዚያ ደግሞ ሁለት እጅ እነሴ ወረዳ ነው የሰራሁ፡፡ እዛም እንደዚያው ደብረ ወርቅ ተዛውሬ አበት አለፍ የሚባል ተራራ አለ፤ የሬዲዮ መገናኛ ያለበት ነው፡፡ እዚያ ወጥቼ ሳየው ተራራውን ገበሬው እህል ያበቅልበታል፡፡ አጠናሁና ..እዚህ ላይ ደን እንትከል.. አልኩ. . . ..ከብት ይበላዋል.. አሉ፡፡ ..በፍፁም! እኔ እዚው መሳሪያዬን ይዤ እተኛለሁ እጠብቀዋለሁ ግዴለም.. አልኩ፡፡ በበሬ አረስነ አስተከልነ፡፡ ከዚያ በስብሰባ ላይ ..እንግዲህ ልብ አድርጉ የብሔራዊ አብዮታዊ የምርት ዘመቻን ሳንይዝ መንግሥት ያወጣው መመሪያ ግቡን አይመታም፡፡ ሊመታ የሚችለው እኛ ስንሠራ ነው.. እንደ አሁኑ የ5 ዓመት መርሃ ግብር እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ ..በሥራ ቀን ቤት ተቃጥሎብህ፣ ጥይት ተተኩሶብህ ካልሆነ በስተቀር እዚህ ከተማ ሲያወደለድል የሚገኝ ሰው ቢኖር ደን ተከላ ነው የምልከው.. ብዬ አወጅኩ፡፡ ሰው ሲመጣ ይያዛል፤ ደን ተከላ ይላካል፡፡

የዚያንዜ ያስተከልሁት ችግኝ ዛሬ አድጎ መብራት ኃይል ለመላው ኢትዮጵያ ከዚያ እየቆረጠ ነው ሚወስድ፡፡ ወደ 6 ማሊዮን ብር ተሸጧል፡፡ ምን እንደሰሩበት እንጃ! በኋላ ዶ/ር ገረመው ደበሌ ለጉብኝት መጥተው አይተው በጣም ተደሰቱ፡፡ ወደ 50ሺ ብር የሚሆን ለግብርናው ሽልማት ሰጡ፡፡

የቀለም ትምህርት እስከ ስንት ዘልቀሃል?

ደብረ ኤልያስ እስከ ስድስተኛ ክፍል ተምሬአለሁ፤ ደብረ ወርቅ እስከ ዘጠኝ ተምሬ በተልዕኮ 12ኛ ጨረስኩ፡፡ ከዛም ፖለቲካ ት/ቤት አስገቡኝ፡፡ ..ይሄን የመሰለ ልማት እየሠራ በትምህርት ቢታገዝ የበለጠ ውጤት ያመጣል.. ተባለ፡፡ ተዚያ ቀደም ይከለክሉኝ ነበር፡፡ የሚልኩኝ ችግር ባለበት ወረዳ ነው፡፡ ችግር ሲኖር እሱ ይሂድ ነው የሚባል፡፡ እኔ ሄጄ እግሬ እንደደረሰ ህዝቡን ሰብስቤ ..ከመንግሥት ጋር ያለህ ፀብ ምንድነው? በል ተናገር.. እለዋለሁ . . . ..ጠባችን ከመንግሥት ጋር አይደለም፤ ከሊቀመንበሩ ጋር ነው.. ይላል፡፡ ..እሱ ነው ጠላትህ ይሄው አወረድኩልህ፤ ሌላ ምረጥ.. እለዋለሁ፡፡ ይኸነዜ አዳሜ ወክ ይላል፡፡ አንድ የማልረሳው ምሳሌ ብነግርሽ አንደዜ የገበሬዎችና አምራቾች የህብረት ሥራ ላይ መሬት ከልለው ገበሬውን ባዶ አስቀርተውት አገኘሁ፡፡ ..ምንድን ነው.. ስላቸው ..ዛሬማ ቅልጥ ያለ ተኩስ አለ.. አሉኝ፡፡ ..ለምን?.. አልኩ፡፡ ..አምራቾች የሚያበሉትን ሳር እናብላ ብለው.. አሉኝ፡፡ አንድ የሚበጠብጥ ካድሬ ነበር ይሄን ሁሉ የሚያደርገው፡፡ የራሴን እርምጃ ወስጄ ወደ ሌላ ቦታ አዛወርሁት፡፡

ሌባን ለማጥፋት ሸፍተህ ነበር ይባላል. . .

ዋ! እህሳ! ልክ ነው፡፡ አስር ዓመት ሙሉ የሸፈተ አንድ ኃይለኛ ሽፍታ ነበር፡፡ አንደኛውን በቃ ሃይለኛ ነበር፡፡ ..ግዴለህም ግን.. ብዬ አባብዬ ብልክበት ..እነ ደጃዝማች ደምስ ያልነኩኝ ማን ነው እሱ!.. ብሎ ናቀኝ፡፡ የወረዳውን ህዝብ ሰበሰብኩና ሳበቃ ..የምንሄድበት ቦታ አለ፡፡ ወታደር የሆንክ ወደ ኋላ ሁን.. አልኩ፡፡ ሽማግሌዎች ነበሩ፡፡ የሀገሩ ሰው ለእሱ አብሮ ይተኩስብናል፡፡ ብቻ ተጠንቅቀን ደረስን፡፡ ከሌቱ በ10፡00 ሰዓት ቤቱን ከበብነው ..እታኮሳለሁ.. አለ፡፡ ጠመንጃውን አቀባብሎ ሁለት የጣሊያን ቦምብ ይዞ፤ በሁለት ወታደር ታጅቦ መጣ፡፡ ሰላምታ እየሰጠ. . . እንግዲህ ከበነዋል፡፡ ማምለጫ የለም. . . ሁሉንም እየጨበጠ ሲመጣ እኔ ሰላም እለውና ..ያዝ!.. ስላችሁ በላዩ ላይ ተከመሩ ብዬ ወታደሮችን መክሬያቸው ነበር፡፡ እኔ ጋ ደርሶ ሰላም ሲለኝ ..ያዘው.. ብዬ ስል ያዙት ..ወይኔ ወይኔ!.. አለ፡፡ እጅ እግሩን ጠፍረን አሰርነው፡፡ ..እንግደለው.. አሉ፡፡ ..የለም ይሄ አይደረግም፡፡ እንኳን ይሄንና ሶማሊያ፣ ግብፆች፣ ቱርኮች፣ ጣሊያንና እንግሊዞች አገራችንን ሲወሩ እንደዚህ አድርገው እጃቸውን ሲሰጡ አይገደሉም፡፡ ይሄማ ወንድማችን ነው፤ አስረን ነው የምናስተምረው፤ እሺ ብሎ አንደዜ እጁን ሰጥቷል.. አልኳቸው፡፡ ተዚያማ ምኑን ልንገርሽ፡፡ ሌላ ሆነ . . .ተፎከረ ተሸለለ. . .

የተለያዩ መፈክሮች እያፃፍክ ትሰቅል ነበር?

መስቀል ነው! . . . ..ከሌባ ጋር እንዳትጋቡ፤ ለሱ የሚድርለት ራሱ ሌባ ነው.. የሚል መፈክር ነበረኝ፡፡ የጦር መሣሪያዬን አነግትና በየኼድኩበት ስለ ጉቦ፣ ስለ ሥርዓቱ አስተምራለሁ፡፡ እና ደግሞ ሰውም ይሰማኛል ..ምን ልታደርግ መጣህ.. ስለው ..ልማር፤ ህግ ላውቅ ነው የመጣሁ.. ይለኛል፡፡ ከሌላው ወረዳ ይልቅስ ብዙ ሽፍቶች እጃቸውን የሚሰጡት በእኔ ወረዳ ነበረ፡፡ በቴሌግራም በሬዲዮ ..እንዲህ ያለ ሽፍታ እጅ ሰጥቷል.. ብዬ አስነግራለሁ፤ ሰላማዊ መሆኔን እነግራለሁ፡፡ የራሴኮ ቴሌግራም ነበረኝ፡፡

ማን ሰጠህ?

መንግሥት ነዋ! በዚያን ወቅት እነ ሰልጣን አለሙ የተባሉ ጋዜጠኞች ነበሩ ስራዬን ሁሉ የሚያስተላልፉልኝ፡፡ እናም ..የእሱን ሥራ ተናገሩለት፤ ሌት ተቀን ነው የሚለፋው.. ተብዬ ድጋፍ ተሰጠኝ፡፡ በኋላ አንድ ጊዜ የቡሬ አስተዳዳሪ የነበረ መቶ አለቃ ሙሉ የሚባል ሰው፣ ጓድ ቆምጬ የሚያስተዳድሩት ማቻከል ወረዳ 80ሺ ኩንታል እህል አስገብቶ አንደኛ ወጣ ተብሎ ሲነገር ቢሰማ ..የለም! አፈር ጭኖ ነው እንጂ እህል ጭኖ አይደለም.. ብሎ አስወራብኝ፡፡

ለምን?

ምቀን ይዞት፡፡ በኋላ 4 ወፍጮ ተሸለምን፡፡

በአንተ ስም ነው የተሰየመው ይባላል...

አዎ /ሳቅ/ ቆምጬ ወፍጮ ነው የተባለው፤ እንዲያውም ወፍጮው ሲነሳ ሁሉ ..ቆምጬ ተንደቀደቀ.. ይባል ነበር፡፡ ዛፍም አለ ..ቆምጬ ዛፍ.. የሚባል፡፡ ዳቸና ገብርኤል ውስጥ ነው ያለው፡፡ ሰው አይነካውም፡፡ ..ይሄ ከደረቀ ለዚህ እግር አልጠቀመውም.. ብዬ እተክለዋል፡፡ እኔን መስሎ ስለሚታየው ሰው ዛፉን ይንከባከበዋል፤ በምሔድበት ሁሉ መጋቢትም ይሁን የካቲት ቆፍሩ እልና ..ይሄ ዛፍ ይድረቅና እያንዳንዳችሁን አደርቅችኋለሁ.. እያልሁ አስፈራራቸዋለሁ፡፡ የህዝብም ግም የአገርም ግም የለውም፡፡ የትም ወረዳ ሂጂ ..አንድ የሆነ ሰው ክፉ ነው፣ ገዳይ ነው፣ በመሪዎች ላይ አደጋ ይጥላል.. ሲባል ልትሰሚ ትችያለሽ፡፡ ግን ውሸት ነው፡፡ መሣሪያውን ወይም እጮኛውን ካልቀማሽው፣ ሰውየውን ዝቅ ካላደረግሽው፣ ባለሞያውን ካከበርሽው ምንም አይልም፡፡ፖለቲካ ት/ቤት ባለሥልጣኑን ጉድጓድ አስቆፍራቸው ነበር፡፡

መሠረተ ትምህርትን ምሁራኑን ይዤ አቅዳለሁ፡፡ ..እናንተ መሀይምነትን ማጥፋት አለባችሁ.. እላቸዋለሁ፡፡ ለመምህራኑ ስኳር፣ ብርድ ልብስ የሚያስፈልጋቸውን እሰጣቸዋለሁ፡፡ ከሊቀመንበሩ በላይ የገጠሩ መሪ የማደርገው መምህሩን ነበረ፡፡ ባለሙያውን ልዩ ሥልጣን እሰጠዋለሁ፡፡ በደብረ ምጥማጥ አንድ መምህር ነበረ፡፡ ወጥሮ ያዛቸው፡፡ ትምህርት ላስተምራችሁ ባለ ያላደረገውን ..በሬ ሰረቀን . . .እንዲህ አደረገን.. አሉና ከበው ይዘው አመጡት፡፡ ..ነው? ሰረቀ?.. አልኳቸው፡፡ ..አዎ.. አሉኝ፡፡

..በአለም ላይ መምህር መቼ ነው ሌባ ሲሆን ያያችሁት?.. አልኩና ይዘውት የመጡትን ሰዎች አሰርኳቸው፡፡ መምህሩን ይዤው ወደ ከሰሱት ሀገር ሄጄ ..እውነቱን አውጡ! ካልሆነ በጊዜ ቀጠሮ እያንዳንድህን ወህኒ ቤት ነው ምለቅህ.. አልኳቸው፡፡ ጎጃም ዱር የሚባል ቦታ አለ፡፡ አካፋና ዶማ አስያዝኩና ማስቆፈር ጀመርኩ፡፡ ሲቆፍሩ ውለው አዳራሽ ውስጥ እንዲያድሩ አደረግሁ፡፡ ተዚያማ . . . . . . ..አያ! ጌታችን ተሳስተናል.. አሉኝ፡፡ ..ጌታ እግዚአብሔር ነው፡፡ አቶ ቆምጬ (ጓዱ ቆምጬ) ብለህ ጥራኝ፡፡ ጌታህ እየሱስ ክርስቶስ እንጂ እኔ አይደለሁም.. አልኳቸው፡፡ ..አንተም እርፍ ይዘህ ታርሳለህ፣ እኔም አርሳለሁ፡፡ አንተ የምታጭደውን እኔም አጭዳለሁ፡፡ እኔ ህይወትህንና ንብረትህን ለማስጠበቅ መንግሥት የላከኝ ሰው ነኝ እንጂ አንተንና እኔን የሚለየን የለም.. አልኳቸው፡፡ ..ውሸታችንን ነው፡፡ መሠረተ ትምህርት እያስተማረ አላስቀምጥ ስላለን ነው ይቅርታ.. አሉ፡፡ ዋና ቀንደኞችንና ሊቀመንበሩን ወህኒ ሰደድኩና ..ይህንን መምህር አክብረህ መሪነቱን፣ መምህርነቱን፣ ሰው የሚለውጥ መሆኑን፣ ለብሔራዊ አብዮታዊ የምርት ዘመቻ ከፍተኛ እድገት አዋጭ መምህሩ መሆኑን አውቀህ አክብረው፡፡ እኔን በትምህርት ይበልጠኛል.. አልኩ፡፡

ሰው እንዲማርና መሠረተ ትምህርት እንዲያድግ ህዝቡን ሌላ ያሳመኑበት መንገድም ነበር . . .?

አይሄ (ሳቅ). . . ይኼውልሽ አንድ ዮናስ የሚባል ልዥ ነበር፡፡ የወረዳ አስተዳዳሪ ነው፡፡ እና ገጠር አይወድም፡፡ ገጠር ከሄደ አተር አስቆልቶ ሲበላ ነው የሚከርም፡፡ የገበሬውን ቦሃቃ፤ ምግቡን ንፁህ አይደለም እያለ ያነውራል፡፡ እኛ ደግሞ ገበሬ የበላውን ነው የምንበላ፡፡ ድንችም ቆሎም የተገኘውን እንበላለን፡፡ ዶ/ር ፋሲል ናሆም የጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ህግ አማካሪ፤ ቀደምም የመንግሥቱ ኃ/ማርያም አማካሪ የነበሩ በሄሊኮፕተር ወደ ፓዊ ሲሄዱ ..ቆምጫ አምባው ማለት ወታደር ነው እንጂ መምህር አይደለም፤ እንዴት ነው ነገሩ? በመሠረተ ትምህርት አንደኛ ወጥቷል፤ በፀረ ስድስት ክትባት ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሸልሞታል፡፡ ሽልማት በሽልማት ነው ስልቱ ምንድን ነው?.. ሲሉ ይሄ ዮናስ ያልኩሽ ሰው ..እሱማ ቢቡኝ ወረዳ ሂዶ፤ መሠረተ ትምህርት ያልተማረ መፃፍ ማንበብ ያልቻል ቡዳ ነው፤ ቡዳ ስለሆነ እንዳትድሩለት፤ ውሃም እንዳታስቀዱት ብሎ አወጀ.. ብሎ ነገራቸው፡፡ በቃ ያን ይዘው እንዲህ አለ ይሉኛል፡፡. . . ..ያው እኔ በእቅድና በስልት ነበር የምመራ፡፡

በእርስዎ ስም የሚነገሩ ብዙ ቀልዶች አሉ... የሶሻሊዝም አፍቃሪ ነበሩ ይባላል?

ያ ሥርዓት ተለውጧል ብዬ የምተወው አይደለም፡፡ በተመስጥኦ ነበር የተቀበልኩት፡፡ ግንባር ቀደምትነት የሚሰጠው ለሠራተኛው ስለነበር በጣም ነበር ያራመድኩት፡፡ በሠራተኛውም በዕደ ጥበባቱም፡፡. . . ..ሦስቱ ጣምራ ጠላቶቻችን እነማን ናቸው.. ብላችሁ ቆምጬን ብትጠይቁት ..ያው አብዮት አደባባይ ተሰቅለውላችኋል!.. ይላል ይላሉ - የግልብጥ ሲወራ፡፡ (ሌኒን፣ ማርክስና ኤንግልስ ለማለት ነው) ፈተና ቀርቦ ..የብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ፕሮግራም ለምን አስፈለገ? ለምን ቀጥታ ሶሻሊዝም አልሆነም?.. ተብሎ ሲጠየቅ ..ታዲያ ቆምጬ አምባው ነው የከለከላችሁ ከሆነ አታደርጉትም!.. ብሎ መለሰ ይላሉ፡፡ ሊቢያና ቻድ ተጣልተው ነበረ፡፡ ፕሬዚዳንት ሊቀመንበር ጓድ መንግሥቱ ሊያስታርቁ ሄደው ሳይሳካ ቀረ፤ ..አንተ በፖለቲካ መጥቀኸል ሌት ተቀን ታነባለህ፡፡ ንባቡን አንበልብለኸዋል፡፡ እንግዲህ በአንተ አተያይ ሊቢያና ቻድ እንዴት ናቸው?.. ብለው አቶ ካሣዬ አራጋው ሲጠይቀው ..አይ! ለምን ሥራ ያስፈቱኛል? ሊቢያና ቻድን ሊቀመንበር መንግሥቱ ያልሆነለትን ከደብረወርቅ ቆምጬ አምባው ሄጄ ላስታርቅ ነው?.. ብሎ አለ አሉኝ፡፡ አንደዜ ደሞ እኔ ራሴ ዝርፊያ ትተው አገር እንዲጠብቁ ያስታጠኳቸው ሌቦች ነበሩ፡፡ እኔ ከማስተዳድረው አካባቢ ለቀው ሌላ ቦታ ሲዘርፉ ተገኙ፡፡ በኋላ ጠራሁና አረቄ እያጠጣሁ ..እንዴት ነው . . . እኔ በማህበር በሰንበቴ በእድር እከታተላችኋለሁ፡፡ ግን ስርቆውን አልተዋችሁምና.. አልኳቸው፡፡ ..አይ እስዎን መደበቅ ማለት እግዚአብሔርን መደበቅ ማለት ነው፡፡ ከቢቡኝ ህዝብ እኮ አንሰርቅም ከዳሞት ነው የምንሰርቀው.. አሉኝ፡፡ ..እንግዲህ ያ ህዝብ አይደለም? እነማናችው አብረዋችሁ ያሉ?.. ብዬ ስጠይቃቸው ነገሩኝ፡፡ . . . የተባሉትን ጠራሁና መከርኳቸው፡፡ ሌላው ደሞ በትምህርት ቤት ጎበዝ የሆነ ተማሪ ወደ ጦር ሜዳ አልክም፡፡ መምህር አላዘምትም ..ስብጥር አድርገው.. ስባል ..አልክም! ማን ያስተምር? ህዝቡ ይነሳብኛል.. እላቸዋለሁ፡፡ ሌባውን ነው መርጬ የምልከው፤ ..ሌባው ህዶ ሰልጥኖ ሞያ ቀስሞ ይመጣል.. ነው የምል፡፡

አንድዜ ደሞ የአንዱ የአውራጃ አስተዳዳሪ ከነበሩ አቶ መስፍን አበረ ጋር አንግባባም ነበር፡፡ ምክንያቱ ፖለቲካ ነው፡፡ ማልሬድ የተባለ የፖለቲካ ድርጅት አባል ነበሩ፡፡ እኔ ደግሞ አብዮታዊ ሰደድ ለተባለው ድርጅት አባል ነበርኩ፡፡ በምልመላ ተጣላነ፡፡ ታክቲክና ስትራቴጂ በመቀየስ የፖለቲካ ሥራውን አቀላጥፈው ነበርና በርካታ አባላቱን ወሰድኩበት፡፡ ኋላ ነደደዋ! ጠላኝ፡፡ ኋላ ምን ልበልሽ አጥረገረገኝ፡፡

..ከሃምሳ ጦር በላይ ቢቡኝ አብሮህ ውሏል፡፡ ፖለቲካ ሰውን ሥራ እያስፈቱ እንደዚህ ማድረግ አይደለም፡፡ አንተ ያልተማርክ መሀይም... . . ስድብ በስድብ ተዚያ በቴሌግራም ጻፈለኝ፡፡ ሳየው ንዴቱ ገባኝ፡፡ ፖለቲካ ደግሞ ወንድማማች ያጋድላል እንኳን ስድብ፡፡ ኋላ. . . ማንነቱን ጠቅሼ ተንትኜ አሳየሁታ!!

ምን ብለው?

ስፍለት. . . ..አባቴ ፊታውራሪ አምባው ይባላል፡፡ ግራዝማች ናቸው፡፡ የርስዎ አባት ደሞ ደጃዝማች አበራ ይማም ይባላሉ፡፡ ሚያዚያ 30 ቀን 1942 ዓ.ም. ዳንግላ (ሸፍተው) ወረራ አካኸዱ፡፡ ዳንገላንም የወረሩበት ምክንያት ሹመት ቀረብኝ ብለው ነው፡፡ አባትዎ ሲሸፍቱ የእኔ አባት ፊታውራሪ አምባ በሽማግሌ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወርጠዋቸው ..አቸፈርን በአውሮፕላን አታስደብድብ እጅህን ስጥ.. ብለው መክረዋቸው እጃቸውን ሰጡ፡፡ እጃቸውን ሲሰጡ ጃንሆይ አስረው አሰቃዩዋቸው፡፡ ፊውዳል እኔ አይደለሁም፤ እስዎ ነዎት፡፡ እሰዎስ ቢሆኑ የጃንሆይ መንግሥት እንዳይቀለበስ በፓርላማ ሲሟገቱ አልነበረ? እኔ የአንዱ ጉልት ገዢ ልጅ ነኝ፡፡ ደሞስ ማህይም ማለትዎ?! ማህይምስ እስዎ፡፡ በእጅ መፃፍ አቅቶዎት በታይፕ የሚጽፉ.. ብዬ ስልክባቸው ወከክ አሉያ፡፡ ብቻ እንዲያ እንዲያ ተብሎ ታረቅነ፡፡

በሥልጣን ዘመንዎ ያሰሯቸው ት/ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎች እስቲ ንገሩን?

በተለያዩ አካባቢዎች የተለያየ ሥልጣን ነበረኝ፡፡ በአውራጃ አስተዳዳሪነት ብትይ በወረዳ አስተዳዳሪነት. . . ቢቡኝ አስር ት/ቤት አሰርቻለሁ፤ ከሕዝቡ ጋር ነው የምሠራው፡፡ ከመንግሥት የምፈልገው ቆርቆሮና ሚስማር ብቻ ነው፡፡ ጤና ጣቢያ በቢቡኝ ወረዳ ውስጥ አሰርቻለሁ፡፡ ቆንተር ስላሴ (ወይን ውሃ ከተማ ት/ቤት ጤና ጣቢያ) የሚባል አገር አለ፡፡ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት የጓድ ብርሃኑ ባየህ አገር ናት፡፡ እነሱ እንኳን በሄሊኮፕተር ወርደው አይተዋታል፡፡ አንደዜ ወባ ህዝቡን ፈጀው፡፡ ክሊኒክ ሠራን በዚያ ወቅት ወባ ጠፋች፡፡ በቢቡኝ ወረዳ ኮረብታ አማኑኤል ክሊኒክ ተሠርቷል፡፡ ጎማጣ (የጎልማሶች ማሰልጠኛ ጣቢያ) ገነባን፡፡ ሁለት እጁ አነሴሞ ሌላ ጎማጣ፣ አስራ አምስት ት/ቤቶች፣ አስራ አምስት የአገልግሎት የህብረት ሥራ ማህበራት አንደኛ ደረጃ ት/ቤት፤ የመንግሥታዊና የሕዝባዊ ድርጅቶች ቢሮ ስፖርት ሜዳ አሠራሁ፡፡ ቢቡኝ ዘጠኝ የህብረት ሥራ አገልግሎት ማህበራት፤ ሁለት የበግ ማርቢያ አዳራሾች፣ የደን ተከላ፣ ጎማጣ አሰርቻለሁ፡፡ እናርጅ እናውጋ ወደ ዘጠኝ የአገልግሎት የህብረት ሥራ ማህበር፤ አንድ የስፖርት ሜዳ አሰርቼ ..ኢትዮጵያ ትቅደም.. የተባለውን ውድድር፣ ሰባቱን አውራጃዎች 35 ወረዳዎችን አስተናግዷል፡፡ መብራት፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ ጤና ጣቢያ፣ ደን፣ አስር ት/ቤት፣ ጤና ጣቢያ፣ ሦስት ክሊኒክ፤ ፈለገ ብርሃን የተባለ ቦታም አንድ ት/ቤት፣ አንድ ጤና ጣቢያ፣ ክሊኒክ አሰርቻለሁ፡፡ አቸፈር ውስጥ የህዝብ መድኃኒት ቤት፤ አምስት ት/ቤት፣ ሦስት ጤና ጣቢያ፣ መብራትና ውሃ፣ ደን ልማት ይህን ሁሉ ሠርቻለሁ፡፡ ትምህርትን በተመለከተ በኢትዮጵያ ከነበሩት ከአምስት መቶ ሰባ ስድስት ወረዳዎች ደብረ ወርቅ አንደኛ፣ ፈለገ ብርሃን ሁለተኛ ወጣ፡፡ ማቻከል በፀረ ስድስት ክትባት አንደኛ ወጥቶ ከጤና ጥበቃ ተሸልሟል፡፡ በደን አያያዝም ከግብርና ሚኒስትሩ ከዶ/ር ገረመው ደበሌ ተሸልመናል፡፡ በ13 ዓመት ጊዜ ይሄን ሠራን፡፡ በሠራነው ስቴዲየም ስፖርት ኮሚሽን 30ሺ ብር ሸልሞን በሥራ ብዛት ሳንወስደው ቀርተናል፡፡

ስቴዲየሙ ደረጃውን የጠበቀ ነበር?

ምን ማለትሽ ነው? ራሴ እኮ ነኝ ቆሜ ያሰራሁት፡፡ ወረዳ አስተዳዳሪ ነበርኩ፡፡ ህዝቡን ሰብስቤ በጉልበትና በዶዘር አስተካከልኩት፡፡ ራሴ ነኝ ዶዘሩን እየነዳሁ መሬቱን እደለድል የነበረ፡፡ ጓድ ካሳዬ አራጋው መጥተው አዩንና ..በአጠቃላይ ከሁሉም ወረዳ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ በማህበራዊ እንቅስቃሴ ተወዳዳሪ የለህም.. ተባልኩ፡፡ /ሳቅ/ ስብሰባ ላይ ምን ይናገራል ብለው የተገላቢጦሽ የሚፈሩኝ እኔን ነው፡፡ ..ኮከብ ወረዳ አስተዳዳሪ!.. ተብዬ ነው አልኩሽ የተሸለምኩት፡፡

ብዙ ጊዜ ስለሚሸለሙ አንዳንድ ባለሥልጣናት እርስዎን የሚያኮስስ ነገር በአደባባይ ይናገሩ ነበር የሚባለው እውነት ነው?

የነበረው መንግሥት ወዳጅም ጠላትም ነበረው፡፡ ጠላቶች በጦርነት አይደለም የሚያሸንፉ፡፡ ማዳከም፣ መቦርቦር፣ የሚወጣውን እቅድና ፕሮግራም አለመፈም፣ ማንኮላሸት ነበር ሞያቸው፡፡ ምን ሆነ መሰለሽ? . . . እናርጅ እናውጋ ወረዳ ውስጥ ነው፡፡ ብዙ ህዝብ ተሰብስቧል፡፡ የቅባት፣ የጥራጥሬ እህል አለ፡፡ እና ይህን የሚያነሳልን መኪና አጣን፡፡ ብጮህ ብጮህ የሚሰማኝ አጣሁ፡፡ ..የተሰበሰበውን እህል ምስጥና አይጥ እየበላው ስለሆነ ይታሰብበት.. የሚል መረጃ በጋዜጣ ላይ አስወጣሁ፡፡ ንግድ ሚኒስትሩ ሰው ልከው ሲያዩት ሌላ ሆኖ ተከምሮአል፡፡ ለጓድ ካሳዬ አራጋው ነገሯቸው፡፡ በአንድ በኩል ህዝቡ እየተራበ ነው፤ አዲስ አበባ ህዝቡ ምግብ አምጡልን እያለ ነው፡፡ ..ለምን አይነሳም.. ብዬ በጋዜጣ ሳወጣ ጠሉኝ. . . እዚያ ያለው የቀጠና ኃላፊ ..እንደዚህ አድርገህ ስም ታጠፋለህ.. አለኝ፡፡ ..እናንተ ናችሁ ፀረ ህዝብ.. አልኩት፡፡ ማቻከል ወረዳ ተዛውሬ እንደዚሁ በጋዜጣ አስወራሁ፡፡ የመንግሥት ማዕከላዊነት አልጠብቅም ሪፖርት አደርጋለሁ፡፡ ካሳዬ አራጋው ..እኔ ብሰማው.. አሉኝ፡፡ ..እስዎ ምን መኪና አለዎት.. አልኳቸው፡፡ ..ቢፈልጉ ያባሩኝ አርሼ መብላት የምችል ነኝ.. ስላቸው ..ስለሠራህ ለምን አባርርሃለሁ?.. አሉኝ፡፡ ..እንግዲያስ ለእኔ ለምን አትነግረኝም አይበሉኝ፡፡ ቢፈልጉ ይጥሉኝ በማስተዋወቂያ ክፍሉ እቀበቅባቸዋለሁ.. አልኳቸው፡፡ አንደዜ ደሞ የቤተ መንግሥቱ ጋዜጠኛ አሰፋ ሽበሸ ደውሎ ..ጓድ መንግሥቱ በጣም ይወዱሃል፡፡ ቆራጥ መሪ ነው የሚሉህ፡፡ አይዞህ በርታ፤ ሁሉ ሰው እንዳንተ ቆራጥ ቢሆን ነው የሚሉ ጋዜጣውን እያነበቡ.. አለኝ፡፡ እንዲያውም አንደዜ . .. ባህርዳር ቤዛዊት ቤተመንግስት ጓድ ሊቀመንበር አስጠሩኝና ..እስቲ ንገረኝ ህዝቡ ምንድን ነው የሚል?.. አሉኝ ..አይ . . . ህዝቡ መዋጮ በዝቶበታል፡፡ የልዩ መዋጮ ሃያ ብር፣ ግብር ሃያ ብር፣ በዛብን እያለ ነው፡፡ በርግጥ ህዝቡ እስዎን ይወድዎታል.. አልኳቸው፡፡ ..ሚኒስትሮችም ነገሩን አለባብሰው ምንም ችግር የለም ነው የሚሉዎት፡፡ መረጃ ቢያገኙ ጥሩ ነው.. አልኳቸው፡፡ ..እንደዚህ ደፍሮ የሚነግረኝ የለም.. አሉኝ ይሄን አልረሳውም፡፡ በሌላ ጊዜ ደሞ ጓድ ካሳዬ ሲነግሩኝ ፕሬዚዳንቱ ..ጓድ ቆምጬ ደህና ናቸው?.. ነው የሚሉ እንጂ ..ጐጃም ደህና ነው ወይ.. አይሉም አሉ፡፡ እሳቸውን የሚጠላ እኔን አይወደኝም፡፡

ሬዲዮና ጋዜጣ ላይ ስምዎት በየጊዜው ይጠቀስ ነበር የሚባለውስ?

ቢቡኝ ወፍጮ የለም፡፡ ርዕሰ ከተማው ወፍጮ አያውቅም፡፡ ከህዝቡ ላይ 15ሺ ብር አወጣሁና ..እስኪ አንድ ወፍጮ ከተማው ላይ እናድርግ፡፡ ሴቶች፣ እርጉዞች፣ ደካሞች፣ እየለፉ ነው.. ብዬ ካስማማሁ በኋላ ወፍጮውን ከአዲስ አበባ የሚያመጣልኝ አጣሁ፡፡ በዚያን ሰዓት ችግሬን በሬዲዮ አስነግሬ ያንን 15ሺ ብር ባንክ አገባንና አንድ ግለሰብ ወፍጮውን ከአዲስ አበባ ገዝቶ አመጣልን፡፡ በኋላ ሬዲዮው ..ወፍጮ ተተከለ . . . ወፍጮውን መርቀው የከፈቱት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ጓድ ቆምጬ ናቸው.. ብሎ አወራ፡፡

ያኔ አርስዎ የት ነበሩ?

/ሳቅ/ እዚያው ቢቡኝ፡፡ ኋላ . . . ምን አሉ መሰለሽ . . . ..ቆምጬ አምባው ከአዲስ አበባ ወደ ቢቡኝ በመኪና ሲመጣ ..ስማ አንተ ሹፌር አንደዜ አቁም.. ህዝቡን ደሞ አንደዜ ጫ በሉ እሻ. . . እሻ.. ብሎ ..ጓድ ቆምጫምባው ማለት እኔ ነኝ.. አለ አሉ፡፡ ኩራት፣ ትቢት፣ ጉበኛ፣ ምቀኛ፣ መዝባሪ አትሁኝ ብቻ፡፡ ህዝቡ ይወድሻል፡፡ አንድ ጊዜ እናርጅ እናውጋ ወረዳ ፈለገ ብርሃን ከተማ ክሊኒኩን ጓድ ቆምጬ አምባው መርቀው ከፈቱ ይልና እኔ በማላስተዳድርበት በቡሬ ሽኩዳድ መረቀ ብሎ ጋዜጠኛው ተሳስቶ አወራ፡፡ አስተዳዳሪው ለነጓድ ካሳዬ ስልክ ደወለና ..ይኼ እንዴት ይሆናል.. ብሎ አበደ፡፡ ..አይ! ጓድ ቆምጬ በሬድዮ ሁልጊዜ ይናገራል፤ የልማት ሰው ነው፤ እንግዲህ ጋዜጠኞች ይወዱታል እሱም ይወዳቸዋል፤ ጋዜጠኞች ተሳስተዋል ቆምጬን አንከስም.. ይሉታል፡፡ ባህርዳር ስብሰባ ላይ ስንገናኝ ..አምባገነን.. አለኝ፡፡ ..ዋ! አምባገነን የሚለውን ትርጉም እወቅ አንተ! እኔ እንደ አንተ ምስኪን አስተዳዳሪ ነኝ! የሚሰጠኝን መመሪያ፣ እቅድና ፕሮግራም አቀላጥፌ እሰራለሁ፡፡ ቆምጬ አምባው መረቀ አለና እኔ ምን ላድርግህ?.. አልሁት፡፡

በአንድ ወቅት ደግሞ ቢቡኝ ውስጥ የራሴን ቢሮ ወረዳውን አስተባብሬ አብሬ ጭቃ እያቦካሁ እመርጋለሁ፡፡ አያየኝም መስሎታል አንዱ ሌላውን ጐተት አድርጐ ..እህ! ይሄ ከማርቆስ የመጣው ውራጌ አስተዳዳሪ አይደለ . . ... ብሎ ሲያወራ ሰማሁ... ..አንተ በመጨረሻ ስትሄድ እኔን እንድታገኘኝ.. ብዬ አንዱን እንዲጠብቀው አዘዝሁበት፡፡ ..ስራ መሥራት ውራጌ ያስብላል አንተ? እኔ የተንጠራራሁ የአንዱ ፊታውራሪ ልጅ ነኝ፤ በል ወዲህ ና!.. አልኩና መቶ ጉድጓድ አስቆፈርሁት፡፡ በሌላ በኩል ደሞ እኔ በዛ አካባቢ ስሾም በኢህአፓም በሌብነትም ተይዞ እስር ላይ የነበረውን ሁሉ ጠራሁና እየጠየቅሁ ፈታሁ... ግን ያን ሳደርግ ቅ እያስሞላሁ ስለማንነቱ እንዲገል እየጠየቅሁ ነበር፡፡ ከዚያ ወደ ሁለት መቶ የሚሆን ኢህአፓ ቆምጬ ሊጨመድደኝ አይደል ብሎ እርሻውን እየተወ ሄደ፡፡

በኢህአፓ ጊዜ የገጠመዎት ችግር ነበር አሉ. . .?

አዎ! ወረዳውን አልነግርሽም፡፡ ብቻ በዚያ አካባቢ የጠነጠነ አንድ ሽፍታ አለ፤ አንዱ ቤት ገባሁ፡፡ ከዚያ ነገሩ ደስ ስላላለኝ ወታደር ልኬ ሌላ ቤት እንዲዘጋጅልኝ አድርጌ ወደ ሌላ ቤት ተዛወርሁ፡፡ መጀመሪያ የነበርኩበትን ቤት ..ቆምጬ አምባው.. ብሎ ፎክሮ ያን ሳር ቤት በእሳት አጋየው፡፡ በኋላ ግን ሰነባብቶ ያው ሰውዬ ሌላ ቦታ ተይዞ ተቀጣ፡፡ አንድዜ ደሞ ሽፍቶቹ መከሩ እኔን ለመግደል...፡፡ በስብሰባው ላይ ከሽፍቶች ጋር አብሮ የዋለው ሰውዬ... ቢሮዬ መጥቶ ሰላም አለኝ፡፡ ..ላይህ ነው የመጣሁ እንዲያው ግን ደና ሰንብተሃል . . . ደህና ነህ ደህና ነህ?.. ሲለኝ ቆይቶ ..ስብሰባ ተደርጐ ሽፍቶች እንግደለው ብለው መክረዋል.. አለኝ፡፡ ሰማሁት፡፡ ሚኒሽር ጠበንጃ ሸለምኩት፡፡ እነዚያን የሽፍታ አለቆች ሁለቱን በሚኒሽር! አይላቸው መሰለሽ. . . (ሳቅ)፡፡ ገዳዩ እኔ ነኝ አላለኝም፤ ይሄን ያደረገው እስር ቤት ሳለ የሰራሁለትን ውለታ ቆጥሮ ኖሯል፡፡ ... ግን መጥቶ ..ተደመሰሱኮ.. አለኝ፤ ..እኔ ገደልኳቸው.. አላለኝም፡፡ እኔም አንስቼ 50 ጥይት ሰጠሁት፡፡

የየካቲት 66 የፖለቲካ ትምህርቱስ?

እዛማ ስድስት ወር ነው የተማርኩ፡፡ ..ለምንድነው እኔ የማልማር? . . . አርሶ አደሮች እረዳለሁ፡፡ ሠራተኛ መደብ እረዳለሁ፤ ልማት ሠራሁኝ ምን ቸገራችሁ ት/ቤት ብትልኩኝ.. አልኩ፡፡ እላይ ድረስ ጮህኩ፡፡ እውነትም ለምን አይገባም? ይገባዋል ትምህርት . . . ተብዬ ገባሁ፡፡ የጎንደር፣ የወሎ፣ የጎጃም ሁሉ የትምህርት ቤቱ የልማት ኮሚቴ አስተባባሪ አደረጉኝ፡፡ ጄነራሉን ባለሥልጣኑን ሳይቀር አበባ መትከያ ጉድጓድ ጠዋት ጠዋት አስቆፍረዋለሁ፡፡ ዳይሬክተሩ ጋር ሂደው ..በቁፋሮ ፈጀን.. ብለው ተናገሩ፡፡ ..ይሄ ሪሰርች ነው.. ተባሉ፡፡ እኔ ቱታ ለብሼ ውሃ ነበር የማጠጣ፡፡ እነሱ ወርቃቸውን ሌዘራቸውን ለብሰው ይሸልላሉ፡፡ አቶ በጋሻው አታላይ ለእያንዳንዱ ካድሬ ሁለት ሁለት ኩንታል ቡና ለስንቅ ሰጥተዋቸው ነበር፡፡ እኔ ያችው ደሞዜ ናት፡፡ እና እነሱ ቢራቸውን ይጠጣሉ፡፡ ቆፍሩ ስላቸው መች ሚሰሙኝ ሆኑ. . . ደግሞ በትምርቱስ የዋዛ መሰልሁሽ? ሌት ተቀን አጠና ነበር፡፡

ትምህርቱ አይከብድም ነበር?

ኧሯ አይከብድም! የሚታወቅ አይደል፡፡ በጣም ቀላል ነበር፡፡ የኢንፔሪያሊስቱና የሶሻሊስቱን ሁኔታ ነው፡፡ ይሄ ቄስ ትምህርት ረድቶኛል፡፡ በኋላ ምርቃቱ ላይ ለገሠ አስፋው መጡና ተህዝቡ ፊት ቆመው ..ጓድ ቆምጬ አምባው አንደኛ.. ብለው የኮምኒስቶች መጽሐፍት /የቼኮዝላቫኪያ፣ የሶቬት ሕብረት/ ሽልማት በሽልማት . . . አያረጉኝ መሰለሽ!

ውጭ አገር ሄደዋል?

ኧሯ! ማን ሰዶኝ፡፡ መቼም መላ አለው ብለው ችግር ባለበት እኮ ነው የሚልኩኝ!

በኢህአዴግ ስርዓትስ?

... አቶ ታምራት ላይኔ ደሞ ምን አለኝ መሰለሽ? ..አቶ ቆምጬ ጥፋት የለብዎትም፡፡ የልማት ሰው ነዎት፡፡ ወደፊትም ልማት ይስሩ.. ብለው እስዎ ዲግሪ የለዎትም አዲስ አበባ በዲግሪና ዲፕሎማ ነው የምንመድብ፤ ቢሆንም እዚህ ይሁኑ ሲሉኝ እኔ አገሬ ጐጃም ናፍቆኛል ልሄድ አልኩቸው...

በኢህአዴግ ታስሬ ስፈታ... እሰራበት ወደነበረው አካባቢ ስሜን ወስደው ህዝቡን ጠየቁት፤ ህዝቡ ጥሩ አስተያየት ሰጠልኝ፡፡ ..ኧረ እንዲያውም . . . አሁንም ይምጣልን . . . ይኼ ሁሉ ልማት የሱ ነው.. አሉ፡፡ አሁንም ተህዝቡ ጋር ነኝ፡፡ የቀይ መስቀል የቦርድ አባል እኮ ነኝ - በህዝብ ተመርጬ፡፡

እንዴት ከእስር ተፈቱ?

የደርግ ባለስልጣናት በሙሉ ማህደራችን ተሰብስቦ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ተልኮ ነበር፡፡ ..በቃ ቀልጬ ቀረሁ.. አልኩኝ፡፡ የጠ/ሚ /ቤት ብዙ ብሄራዊና አለማቀፋዊ ስራ አለበት... የእኔ የአንድ ተራ ሰው ጉዳይ ልብ ተብሎ አይታይም ብዬ አስቤ ነበር፡፡ 3 ዓመት ከ7 ወር ታስሬ ተፈትቻለሁ፡፡ ጉዳዩን እንዲያዩልኝ ስጠይቅ ለረጅም ጊዜ ሲያደርጉብኝ ጊዜ እንዴት አልኩና የጡረታዬን ጉዳይ ልጠይቅ የማህበራዊ ዋስትና ሃላፊውን ሳናግር ..አቶ ቆምጬ እንኳን እግዚአብሄር አስፈታዎት... ይቀመጡ... በሉ ወተት ሻይ.. ሲለኝ ፆም ነበር ..አይ ይቅርብኝ.. ስለው... ..ምነው ያን ጊዜ ሳይበሉ ኑረው ነው?.. አለኝ... ..ኧረ እኔስ በልቻለሁ.. አልኩ፡፡ ተሳሳቅን፡፡ ጉዳዩን እንዲያዩልኝ ስል... ወዲያው ተፎ ተሰጠኝ፡፡ ..ወደፊት ምን ይሰራሉ?.. ሲሉኝ ..እርሻ . . ሹመኞች ሁሉ ሞጣዎች ናቸው፡፡ ያውቁኛል.. አልኳቸው፡፡ ..አያሳርስዎትም.. አሉኝ፡፡ ..ዋ!ምን ብለው? ምን በሰራሁ... ? አልኳቸው፡፡ ..መጓጓዣ ገንዘብ ልስጥዎት?.. አሉኝ... ..ጐጃም ሞልቶ የል ባዲሳባ? አልኳቸው፡፡ ሦስት መቶ ብር... እምቢ ብለው ሰጡኝ፡፡

አሁን በምን ሙያ እየተተዳዳሩ ነው?

አሁን በጡረታ ስገለል ..ነገረ ፈጅ ነበርኩ የጥብቅና ፈቃድ ስጡኝ.. አልኳቸው፡፡ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት. . . የጥብቅና ፈቃድ ሰጠኝ፡፡ መቼም ለጡረታ መደጐሚያ ይበቃል፡፡ ጎጃምማ ..እሱም ወንድ፣ እኔም ወንድ፣ ከማን አንሼ ነው ጠበቃ ምገዛ?.. ይላል፡፡ ለጥብቅና ሥራ ሸጋ አዲስ አበባ ነው፡፡ የኛ ሰው ነገር አዋቂ ነኝ ብሎ ጠበቃ ማቆም ዝቅተኛነት ይመስለዋል፡፡ እና እንዳልሁሽ እርቅ ሥሠራ ነው የምውለው፡፡ በአኩሪው ባህላችን መሠረት ስናስታርቅ ነው የምውል፡፡ አሁን በእድር በማህበራዊም ሆነ በተለያየ የማህበራት አስተባባሪና መሪ ነኝ፡፡

በኢህአዴግስ አልተሸለሙም?

ምክትል ጠ/ሚ አዲሱ ለገሠ ..የመልካም አስተዳደር የሰላምና የዲሞክራሲ እድሮችን በመምራት ባደረጉት አስተዋጽኦ ተሸላሚ.. የተባለ ጊዜ አግኝተውኝ ..አቶ ቆምጬ፣ ከሦስት መንግሥት የሚበሉ፤ በሃይለ ሥላሴ፣ በደርግ፣ በኢህአዴግም . . ... አሉ፡፡ እኔስ ምኔ ሞኝ!. . . ..ሁሉም እኮ የኢትዮጵያ ተወላጅ ናቸው፡፡ መንግሥት ይለወጣል፣ አገር ነው የማይለወጥ.. አልኳቸው፡፡ ሳቁ፡፡ ..ሰምቻለሁ ሥራዎትን፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ሰውን አስተምሩት፡፡ ሽማግሌ ነዎት፡፡ ትልቅ ሰው ነዎት፡፡ ይለፋሉ፡፡ አይዞዎት.. አሉኝ፡፡ እንዲሁ አንደዜ የደ/ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ሲመረቅ ንግግር እንዳደርግ ተጋብዤ ተናገርኩ፡፡ ..ብሔር ብሔረሰቦች የሚተዋወቁበት ኮሌጅ ተሰራልነ፡፡ የሠራችሁልን መማሪያ ቤት የኛ ነው፡፡ ቧንቧው መስኮቱ እንዳይሰበር እንጠብቃለን፡፡ ከሌላ አገር የመጣ ደባል ፀባይ ካለ እኛ ጎጃሞች አንፈልግም፤ ጉሮሮውን አንቀን ለፍርድ እናቀርባለን.. አልኳቸው፡፡

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ስላለው የፖለቲካ ሁኔታ ምን ይላሉ?

ኢትዮጵያ ውስጥ የማያባራ ጦርነት ነበር፡፡ ያኔ ፕሬዚዳንቱን ..ሥልጣን አጋሩ፤ ተደራደሩ.. ብያቸው ነበር ግን ..ድርድር የለም.. ብለው እምብኝ አሉ ፕሬዚዳንቱ፡፡ የሚገርምሽ በደርግ ወቅት ጦሩ እንዳይዋጋ የሚቀሰቅስ ሙዚቃ ነበር፡፡

..አሁን የእኔ መኖር፤ መኖሩ ነው ወይ፤

ጉች ጉች ያለ ጡት አንድ ቀን ሳላይ.. የሚል ቅስቀሳ ወጣቱ ይሰማ ነበር፡፡

ጦር ሜዳ?

እህሳ፡፡ በጦር ሜዳ ቅስቀሳ ሲደረግበት ወጣቱ በቃ እዚያ መቆየት አይፈልግም፡፡ በቃ እየተወ መምጣት ጀመረ፡፡ ሽንፈቱ አየለ፡፡ ሌላው ጦርነቱ ደግሞ የአንድ አገር ጦርነት ነበረ፡፡ ያው አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት አሸንፏል፡፡ ነገር ግን ያንዜ የነበረው ጦርነት ታሪካዊ ተብሎ አይያዝም፡፡ ሁለት ወንድማማቾች ነበሩ የተቃመሱ፡፡ የእርስ በርስ ጦርነት ስለሆነ፡፡ ታሪካዊ ጦርነት የምትይው ከኤርትራ፣ ከሱማሌ፣ ከጣልያን፣ ቱርኮች፣ ግብፆች፣ እንግሊዞች ጋር የነበረው ጦርነት ማለት ነው፡፡ አንድ ጦርነት ታሪካዊ የሚባለው ጦርነት በሚያውቁ ሳይንቲስቶች፣ የጦር ጠበብቶች ሲገመገም ነው፡፡

አሁን ያለው ለሰላም ለዲሞክራሲ፣ ለመልካም አስተዳደር የቆመ አስተዳደር ነው ቢባልም ከላይ የወጣው መመሪያ ትክክል ሆኖ ሳለ ከታች ግን ይሸራረፋል፡፡ ከታች ያየሽ እንደሆን መመሪያዎች፣ ህገ መንግሥቱ፣ ሌሎች ነገሮች እየተሸራረፉ ይገኛሉ፡፡ ተቆጣጥሮ ለማስተካከል ጥብቅ ክትትል ያስፈልጋል፡፡

በኢህአዴግ ዘመን በምርጫ ለምን አልተወዳደሩም?

አይ!. . . መንግሥታት በሥልጣናቸው የሚመጣባቸው አይወዱም፡፡ እኔም ደሞ ከእንግዲህ የአገር ሽማግሌ ነኝ፡፡ ተመርጠሽ ፓርላማ በምትገቢበት ጊዜ ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ሊኖርሽ ይገባል፡፡ ለነገሩ ለተሳትፎም መማር ጥሩ ነው፡፡

ግን ትምህርቱን ለምን እስከ ዲግሪ አልገፉበትም?

እህ እንግዲያ! እኔ በተልዕኮ በህግ የጥብቅና ዲፕሎማ ይዣለሁ፡፡

ጠ/ሚ መለስ ዜናዊን አግኝተዋቸው ያውቃሉ?

ኧረ የለም፡፡ ጠ/ሚኒስትሩን የማመሰግናቸው የኢትዮጵያና የኤርትራን ጦርነት በአሸናፊነት በመወጣታቸው ነው፡፡ የቀድሞ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ በሚያስተዳድሩ ጊዜ የሶማሌ ጦር ..አዋሽ ነው ድንበሬ.. ብሎ መጥቶ ነበረ፡፡ ለወሬ ነጋሪ ሳይቀር እንደ አገዳ ክምር ተቃጠሏ! ጠ/ሚ መለስም ቢሆኑ ጦርነት ባይፈልጉም ጦረኞችን ለመከላከል የሚያደርጉት የሚደንቅ ነው፡፡ ይህም ደግሞ አፄ ቴዎድሮስ፣ አፄ ዮሐንስ ህይወታቸውን የሰውት ንብረት ጠፍቷቸው ንብረት ፍለጋ ሳይሆን ሀገር ለመጠበቅ ነው፡፡ ያው በእኔ በኩል ጠ/ሚኒስትሩን ባገኛቸው ግን ጎጃም ውስጥ እነ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ ደራሲ ዮፍታሔ ንጉሴ፣ ደራሲ ዶ/ር ሃዲስ አለማየሁ፣ የቅኔው ባለቤት በአለም የታወቀው አድማሱ ጀምበሬ. . . የተወለዱበት አገር ደብረ ኤልያስ ይባላል፡፡ በደብረ ኤልያስ ..አባይ ፍል ውሃ.. 44 ዓይነት ምንጭ ውሃ የሚፈልቅባት ናት - ለብለብ፣ ሙቀት፣ እሳት አለንጋ፡፡ ታዲያ ሰው ለመፈወስ በበረሃው እየሄደ በውሃ ጥም እስከ 300 ሰዎች ሞተዋል፡፡ በጫካ ገብተው መንገዱ ጠፍቷቸው፡፡ እና ጠ/ሚኒስትሩ እግዚአብሔር ከዚያ ሁሉ ሽምቅ ውጊያ፤ አሁንም ቢሆን አንዳንድ ከፍተኛ መሰናክሎች አጋጥሟቸው የተወጡት በእግዚአብሔር ሃይል ስለሆነ . . . የእነዚህን ታላላቅ ሰዎች አገር ..አባይ ፍልውሃን.. ባለችዎት አቅም በእግዚአብሔር ብየዋለሁ ያሰሩልን፡፡ ..አባይ ፍልውሃ.. መንገዱ ቢሠራ ከፍተኛ የእምነበረድ ክምችት፣ ከፍተኛ የብረት ምርት፤ የቅባትና የሰሊጥ እንዲሁም፣ የበርበሬ ምርት በብዛት ያለበት ነው፡፡ ከደ/ኤልያስ አባይ ፍል ውሃ 17 ኪ.ሜ ርቀት ነው ያለ፡፡ እና እባክዎ ይሄንን ያሰሩልን . . . በፃድቃን በሰማዕታት በደናግል በመነኮሳት . . . ይዠዋለሁ፡፡

በመጨረሻ ምን ይላሉ?

መልካም ዘመን ለኢትዮጵያ ሕዝብ፡፡ ከአዲስ አበባ ድረስ ደ/ማርቆስ በመምጣት ቃሌን ተቀብላችሁ በጋዜጣችሁ ስላስተላለፋችሁ አዲስ አድማሶችን አመሰግናለሁ፡፡


ይህ ቃለ-ምልልስ በሁለት ክፍሎች በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ታትሟል፡፡ ቃለ-ምልልሱን ያገኘነው በጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው መልካም ፈቃድ ነው፡፡ እናመሰግናለን፡፡