በሌባ ጣትሽ አታሳዪኝ

ከውክፔዲያ

በሌባ ጣትሽ አታሳዪኝ

(53) አለቃ እጓሯቸው ዱባ ተክለዋል። ዱባውም አድጎ ፍሬ ይዟል። ፍሬውም ጎምርቶ (አሽቷል ) እሱንም ጧት ማታ እየተንከባከቡ ይጠብቃሉ። ከጎረቤታቸው አንዲት በሌብነት የሰለጠች ጋለሞታ ነበረች። አንድ ቀን ጧት ወደ ቤተክርስቲያን ሲሄዱ አይታ ቀጥፋ ወሰደችባቸው። ሲመለሱ ዱባቸውን ያጡታል አዝነውና ተናደው ወይ ዱባዬ እያሉ ሲቃትቱ ያቺ አልማጭ ሌባ ከቤት ወጥታ «ምን ሆኑ አለቃ?» አለቻቸው። እሳቸውም «ዱባዬን ጉድ ሆንኩ ተሰረቅሁ» ይላሉ። እሷም ያዘነች በመምሰል ከንፈሯን እየመጠጠች የዱባው ፍሬ የነበረበትን ስፍራ በሌባ ጣታ እያመለከተች «አዎ አለቃ ትላንትና እዚህ ነበር እኔም አይቼዋለሁ» ስትል እሷ እንደሞጨለፈችው አውቀው «ተይው ልጄ በሌባ ጣትሽ አታሳዪኝ» ብለው ስርቆቷን ነገሯት።