Jump to content

ታደሰ ኃይለሥላሴ

ከውክፔዲያ

ኢንጂነር ታደሰ ኃ/ሥላሴ (Tadesse HaileSelassie)

የቀድሞ በርታ ኮንስትራክሽን መሥራች ኢንጂኔር ታደሰ ኃ/ሥላሴ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ። ኢንጂኔር ታደሰ ኃ/ሥላሴ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ80 ዓመታቸው የካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም. በሞት ተለይተዋል፡፡ ሥርአተ ቀብራቸው በአራዳ መናገሻ ቅዱስ ጊዩርጊስ ቤተ ከርስቲያን ተፈጽሟል፡፡

የሕይወት ታሪክ

ኢንጂኔር ታደሰ ኃ/ሥላሴ ተክለ ከእናታቸው ከወ/ሮ እልፍነሽ ወልደመድህን እና ከአባታቸው ከአቶ ኃ/ሥላሴ ተክለ በቀድሞ አርሲ ክ/ሀገር ዶዶታ ወረዳ ሊጋባ ከተማ ጥቅምት 14 ቀን 1933 ዓ.ም.ተወለዱ፡፡ እደሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በአካባቢው ት/ቤት ትምህርት በመከታተል ላይ እያሉ፤ በ1940 ዓ.ም. ክቡር ትዕዛዝ ወልደ ጊዩርጊስ ወልደ ዮሐንስ ወደ አዲስ አበባ አምጥተው በተፈሪ መኮንን ት/ቤት አስገብተው እየከፈሉላቸው እንዲማሩ አድርገዋል፡፡ እዚያው ት/ቤት አዳሪ በመሆን እስከ 12 ክፍል ድረስ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ በመቀጠል በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ በ1953 ዓ.ም. የምህድስና ኮሌጅ በመግባት በ1957 ዓ.ም. ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ተመርቀዋል፡፡ በት/ቤት በነበሩበት ጊዜ ጀምሮ በነበራቸው የአገር ፍቅር የተነሳ በወቅቱ በነበረው ""ተምሮ ማስተማር" በሚባል ፕሮግራም ቀዳሚ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ከቀ.ኃ.ሥ. ዩኒቨርስቲ እንደተመረቁ፣ ልምድ ለማግኘት በቀን ሙያተኛነት በመቀጠር፤ አሁን ዋናው ፖስታ ቤት ያለበት ህንጻ በሚገነባበት ጊዜ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ላይ እየታዩ ደረጃ በደረጃ እስከ ፕሮጀክቱ ዋና መሐንዲስነት ድረስ አገልግለዋል፡፡ በመቀጠል ታደሰ ኃ/ሥላሴ ኮንስትራክሽን በሚል የራሳቸውን አቋቁመው ነበር፡፡ ድርጅቱን በማሳደግ ከኢንጂኔር ብርሃነ አባተ ጋር በመሆን በርታ ኮንስትራክሽን ኃ/የተ/የግ/ማህበርን አቋቋመዋል፡፡ አገር በቀል የሆኑ ተቋራጮች ሲመሠረቱ ከቀደምቶቹ አንዱ በመሆን፤ በርታ ኮንስትራክሽን በተለያዩ የመንገድ ሥራዎች ለምሳሌ ፡- ብቸና ሞጣ፣ ጅማ ጭዳ፣ ሰርዶ አፍዴራ፣ ጋሸና ላሊበላን ገንብተዋል፡፡

ፋብሪካዎችም ገንብተዋል ለምሳሌ፡- የሐረር ቢራ ፋብሪካ፣ ሜታ ቢራ ፋብሪካ፣ ለቱሪስት መዳረሻ የሚሆኑ ታሪካዊ ቦታዎች ውስጥ በባህር ዳር "ጣና ሐይቅ" በጎንደር "ጎሃ" በላሊበላ "ሮሃ" በአክሱም "የሃን" በሒልተን ሆቴል ደረጃ የሆኑ አራት ሆቴሎችን ገንብተዋል፡፡ በሰፋፊ የመስኖ ሥራ ተግባራትም ተሳትፈዋል፣ ለምሳሌ የአሚባራ መስኖ ፕሮጀክት፡፡ ኢንጂኔር ታደሰ ኃሥላሴ ስለ አገር ልማት የነበራቸው ሕልም ከፍ ያለ ነበር፡፡ በተለያዩ መድረኮች ለአገር ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ ሃሳቦችን አቅርበዋል፤ ያገባኛል የሚሉ ወገኖችም በሃሳባቸው ዙሪያ እንዲወያዩ አድርገዋል። በተጨማሪ ኢንጂነር ታደሰ ኃሥላሴ ስለ አገር ልማት ጽሑፎችን ለሕዝብ በተደጋጋሚ አበርክተዋል፡፡ እንዲሁም በዚሁ ጥረት በህዝብ ሚዲዎች ብዙ ገለጣዎችን አከናውነዋል፡፡ ኢንጂኔር ታደሰ ኃ/ሥላሴ ያቀርቧቸው የነበራቸው የልማት አስተያየቶች ላይ ተመርኩዞ በ2011 ዓ/ም በተመሠረተ የመሐንዲሶች የጥናት ቡድን፡ በ2050 ኢትዮጵያ በልማት የት ልትደርስ ትችላለች በሚል በተዘጋጀ መድረክ እውቅና ተሰጥቷቸው ተሸልመዋል፡፡ ኢንጂኔር ታደሰ ኃ/ስላሴ በጣም ግልጥና በጣም ቅን ግለሰብ ነበሩ፡፡ እሳቸውን መሰል ቅን ሰው ማግኘት ያዳግታል፡፡ ኢንጂነር ታደሰ ኃ/ሥላሴ ሚያዝያ 1967 ዓ.ም. ከወ/ሮ ሂሩት አማረ ጋር ትዳር መሥርተው ለ46 ዓመት እስከ እለተሞታቸው ድረስ በፍቅር አብረው ኖረዋል፡፡

ምንጭ ጌጡ ተመስገን፡- (የኢትዮጵያ ሲቪል መሐንዲሶች ማህበር)