Jump to content

አቡነ ተክለ ሃይማኖት

ከውክፔዲያ
አቡነ ተክለሃይማኖት
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ጳጳስ
ስም ፍስሐ ጽዮን በኋላ ተክለሃይማኖት
የተወለዱበት ቀን ታኅሣሥ ፳፬ ፲፩፻፺፯
የትውልድ ቦታ ቡልጋ
የአባት ስም ቅዱስ ጸጋዘአብ
የእናት ስም ቅድስት እግዚእ ኃርያ
የአቡን ስያሜ በእስክንድሪያው አቡነ ቄርሎስ
ያረፉበት ነሐሴ ፳፬[1]
ንግሥ ነሐሴ ፳፬
የሚከበሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንኮፕት ቤተክርስቲያን የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥንክሳር


አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቡልጋ ደብረ ጽላልሽ ወይም ዞረሬ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የሰበካ ክልል ከአባታቸው ከካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ቅድስት እግዚእ ኃረያ መጋቢት ፳፬ ቀን ተፀንሰው፤ በ፲፩፻፺፯ ዓ.ም ታኅሣሥ ፳፬ ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በሦስት ቀናቸው ከእናታቸው እቅፍ ወርደው «አሐዱ አብ ቅዱስ፣አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ» ብለው ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ ወላጆቻቸውም ፍስሐ ጽዮን አሏቸው፡፡ ትርጓሜውም የጽዮን ተድላዋ ደስታዋ ማለት ነው፡፡ አስደናቂ ገድላቸውን ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ

በወላጅ አባታቸው በካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብ ግብረ ዲቁናን ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ሲያጠኑ ቆይተው በአሥራ አምስት ዓመታቸው ከእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ /ጌርሎስ/ ዲቁናን ተቀብለዋል፡፡ በዚህም ቅድስት ቤተክርስቲያንን በወጣትነት ዕድሜያቸው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

ከዕለታት በአንዱ ቀን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከጓደኞቻቸው ጋር ወደ ዱር አደን ሄደው ሳለ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ ለኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ሐዲስ ሐዋርያ አድርጎ መረጣቸው። ስማቸውንም «ተክለ ኃሃይማኖት» አለው፡፡ ትርጓሜውም የኃይማኖት ፍሬ ማለት ነው፡፡

አባታችንም ሐዋርያዊ ጉዟቸውን ሲጀምሩ

«አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደተከፈተ ተውኩልህ . . . ደካማ ለሆንኩ ለእኔ ያለ አንተ የሚያፀናኝ የለም። ለምፍገመገም ለእኔ ያለ አንተ ደጋፊ የለኝም። ለወደቅሁ ለእኔ ያለአንተ የሚያነሳኝ የለም። ለአዘንኩ ለእኔ ያለአንተ የሚያረጋጋኝ የለም። ለድሀው ለእኔ ያለ አንተ መጠጊያ የለኝም፡፡»

/ገድለ ተክለ ሃይማኖት ምዕ ፳፰ ቁ ፪ - ፫

ይህን ብለው ትሕትና በተሞላበትና በተሰበረ ልብ ወደ ፈጣሪያቸው ከለመኑ በኋላ በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገራት ከኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ፣ ከክህደት ወደ ሃይማኖት መልሰዋል፡፡ በዚህም የተነሣ ለኢትዮጵያውያን ብርሃን ፀሐይ ተብለዋል፡፡

አስደናቂ ገድላቸውን ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ

ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን ክታቡ ስለ ቅዱሳን መንፈሳዊ ተጋድሎ ሲገልፅ:-

  • «እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሱ» /ዕብ. ምዕ ፲፩ ቁ ፴፫ / እንዳለ አባታችን ቅዱስ ተክለ ሃይማኖትም በመንፈሳዊ ተጋድሎ እንዲሁም በትህትና በተአምራት አላዊ የነበረውን ንጉሥ ሞቶሎሚን ወደ ክርስትና መልሰዋል፡፡
  • «ጽድቅን አደረጉ» እንዳለው አባታችን ወንጌልን በተጋድሎ ሕይወታቸው ተርጉመዋል፡፡
  • «የአንበሶችን አፍ ዘጉ» ምዕ ፲፩ ቁ ፴፫ /ምዕ ፲፩ ቁ ፴፬ /እንዳለው አባታችንም የአውሬውን ፥ የዘንዶውን ራስ ቀጥቅጠዋል።
  • «ከሰይፍ ስለት አመለጡ» እንዳለው አባታችንም ሞቶሎሚ ከወረወረው ጦር በተአምራት ድነዋል፡፡
  • «ከድካማቸው በረቱ» እንዳለው አባታችንም ያለ ዕረፍት በብዙ ተጋድሎ በጾምና በስግደት በብዙ መከራ በርትተዋል፡፡

ይህን ሁሉ ገድልና ትሩፋት እየፈጸሙ ዕረፍታቸውም በደረሰ ጊዜ ደቀመዝሙሮቻቸውን «ልጆቼ ሆይ ሁሉም መነኮስ መንግሥተ ሰማይ ይገባል ማለት አይደለም፤ ዓለምን በሚገባ የናቀ ብቻ ይገባል እንጂ መጀመሪያ የእግዚአብሔርን ጽድቁን ብቻ ፈልጉ፤ ጾምጸሎትን አዘውትሩ፤ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ ትእዛዛቱንም አጥብቃችሁ ጠብቁ እያሉ ይመክሯቸው ነበር. . .» በኋላም «ለዓለም ጨው ለራሴ አልጫ ሆንኩ፤ ለዓለም ብርሃን ለራሴ ጨለማ ሆንኩ፣ ከእውነተኛው ዳኛ ከጌታዬ ፊት ስቆም ምን እመልሳለሁ?» እያሉ በፍጹም ትህትና እና በልዩ መንፈሳዊ ተመስጦ ይጸልዩ ነበር፡፡

በመጨረሻም አባታችን በነሐሴ ፳፬ ቀን ዕረፍታቸው ሆነ። በዚህም መሠረት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ለእኚህ ዕረፍታቸው በእግዚአብሔር ፊት ለከበረና ብዙ ክብር ለተሰጣቸው ለጻድቁ ተክለ ሃይማኖት በየዓመቱ በነሐሴ ፳፬ ቀን በዓለ ዕረፍታቸውን በታላቅ ድምቀት ታከብራለች፡፡ እኛንም ከጻድቁ ረድኤት በረከት ይክፈለን፡፡

በበለጠ ለማወቅ ስለ አባታችን ሰፊውን ገድላቸውን ማንበብ እጅግ አርጎ ይጠቅማል ።

ደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን የምክሖ ደናግል ማርያም ወጣቶች መንፈሳዊ ማኅበር አዲስ አበባ


ስብሐት ለእግዚአብሔር


  1. ^ ታሪካቸው በኢትዮጵያ ሥንክሳር በነሐሴ ፳፬ የሰማዕታትና ቅዱሳን ታሪክ ውስጥ ይነበባል