አባል:ዮናስ ጥላዬ

ከውክፔዲያ
Jump to navigation Jump to search

ቴዎድሮስ ጥር ፮ ቀን ፲፰፻፲፩ ዓ.ም. ሻርጌ በተባለ ቦታ ቋራ ውስጥ፣ ከጎንደር ከተማ በስተ ምዕራብ ተወለዱ። የተወለዱትም አገሪቷ በባላባቶች ተከፋፍላ በምትመራበት- ዘመነ መሳፍንት በሚባለው ወቅት ነበር። አባታቸው ደጃዝማች ኃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ የቋራ ገዢ ነበሩ። ዓፄ ቴዎድሮስ በህጻንነታቸው የቄስ ትምህርት ከቀሰሙ በኋላ፣ የአጎታቸውንና በኋላም ለጥቂት ጊዜ የ ጎጃሙን ጦር መሪ የ ጎሹ ዘውዴ ን ጦር ተቀላቀሉ። በዚሁ የውትድርና ዘመናቸው ከፍተኛ ችሎታን ማስመዝገብ ስለጀመሩና ዝናቸው ስለተስፋፋ በ፲፰፻፴፱ ዓ.ም. በወይዘሮ መነን ሊበን አምዴ አነሳሽነት የልጇን የራስ አሊ አሉላ ን ልጅ፣ ተዋበች አሊ ን ተዳሩ፤ እንዲሁም በደጃዝማች ነት ማዕረግ የቋራ አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ። ቴዎድሮስ ግን በ፲፰፻፵፬ ዓ.ም. አጠቃላይ የዘመነ መሳፍንት ሥርዓትን በመቃወም በሰሜናዊ ባላባቶች ላይ ዘመቻ ጀመሩ። በኒህ ተከታታይ ዘመቻወች የገጠሟቸውን ባላባቶች ስላሸነፉ፣ መጀመሪያ የ ራስ ማዕረግን በኋላም የ ንጉሥ ማዕረግን በአንድ ዓመት ውስጥ ተቀዳጁ። በየጊዜው በሚያደርጉት የተሳካ ዘመቻ የዘመኑን ባላባቶች ኃይል በመሰባበር የካቲት ፫ ቀን ፲፰፻፵፯ ዓ.ም ንጉሥ ካሳ - ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ተብለው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሆኑ። ሥርዓተ ንግሡ የዘመነ መሳፍንት መቃብር በመሆን የዘመናዊ ኢትዮጵያን ታሪክ "ሀ" በማለት ጀመረ። ዓፄ ኃይለ ስላሴ እስከ ፈጸሙት ድረስ ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ሥራም በዚሁ ወቅት ተጀመረ። ዓፄ ቴዎድሮስ ሰሜናዊ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አንድ ለማድረግ የሞከሩት፣ አጠቃላይ በታሪክ የሚታወቀውን የኢትዮጵያ ክፍል ነበር - ለዚህም ዋቢ ወደ ወሎና ወደ ሸዋ ያደረጓቸው ዘመቻወች ይጠቀሳሉ። በዘመነ ንግሣቸው ዓፄ ቴዎድሮስ አገሪቱን የሚያሻሽሉ ሥርዓቶችን ለአገራቸው አስተዋውቀዋል። ከነዚህም ውስጥ፡ ባርነትን የሚያግድ አዋጅ፣ የመጀመሪያው መንገድ ግንባታ፣ የሥርዓተ ንዋይና የፖለቲካ ሥርዓቱን በማዕከላዊ መንገድ ማዋቀር፣ የባላባት የተከፋፈለ "ሁሉ-በሁሉ-ጦርነት ሥርዓት"ን በማስቀረት ብሔራዊ ውትድርናን ማስተዋወቅ ይጠቀሳሉ። በዘመነ መሳፍንት እንደልባቸው ይፈልጡ ይቆርጡ በነበሩ ባላባቶች ዘንድ እኒህ ለውጦች እጅግ የተጠሉ ሆኑ። በ፲፰፻፶ ዓ.ም. ብዙወቹ ባላባቶች አመጽ ማነሳሳት ጀመሩ። በ፲፰፻፶፪ ዓ.ም ንጉሠ ነገሥቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ርስት የነበረውን መሬት ለገበሬወች በማከፋፈላቸው ከሃይማኖት መሪወች ጋር ተጣሉ። ይህን ተከተሎ በየቦታው አመጽ በሚነሳበት መካከል አውሮፓ ውያን ሚሲዮኖችም ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር በተነሳሳ አለመግባባት ምክንያት በዓፄው ታሰሩ። በመጋቢት ወር ፲፰፻፷ ዓ.ም ላይ የ እንግሊዝ መንግሥት በሮበርት ናፒየር የሚመራ፣ በጊዜው እጅግ ግዙፍ የተባለ ኃይልን አሰናድቶ አውሮፓውያን እስረኞችን ለማስፈታት ጦር ላከ። መጋቢት ፭ ቀን ፲፰፻፷ ዓ.ም ይህ ጦር በመቅደላ ምሽግ ላይ በሚገኘው፣ በአመጽ በተዳከመ የንጉሱ ጦር ላይ ጥቃት አደረሰ። በውጊያው መሃል ንጉሠ ነገሥቱ እጃቸውን እንዲሰጡ ቢጠየቁ እስከመጨረሻው አሻፈረኝ በማለት በሽጉጣቸው እራሳቸውን ገድለው በጀግንነት አለፉ። ዓፄ ቴዎድሮስ ያሰቡትን ለውጦች በሙሉ በተግባር ቢፈጽሙ ኖሮ በእርግጥም ታላቅና የሰለጠነ ሀገር መሪ ሊሆኑ ይችሉ እንደነበር ታሪክ ተመራማሪወች ይስማማሉ። ዕቅዳቸው በዚህ መልኩ ቢሰናከልም፣ እጅግ ድንቅ መሪ፣ የተዋጣላቸው ወታደርና የተባበረች ዘመናዊ አገር ራዕይ አብሳሪ እንደነበሩ ያሰሯቸው አውሮጳውያን ሳይቀር ሳይመሰክሩ አላለፉም። የዙፋን ስማቸው «ቴዎድሮስ»ን የወሰዱት ከፍካሬ ኢየሱስ ከተገኘ ትንቢት ነበረ። በዚያው ትንቢት በኩል፣ በዓለም መጨረሻው ክፍለ ዘመን፣ ተወዳጁ፣ የጥንቱ ዘመን ንጉስ ቀዳማዊ ቴዎድሮስ እንደገና ተነስቶ አገሪቱን ለ፵ ዓመታት ይገዛል የሚል ነበር። "ቴዎድሮስ" የሚለው ስም ከግሪክ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም «ጤዎስ ዶሮስ»፣ 'የአምላክ ስጦታ' ማለት ነው። የቤተሰብ ታሪክ ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ የዓፄ ቴዎድሮስ እና እቴጌ ጥሩወርቅ ልጅ ዓጼ ቴወድሮስ የቋራ አስተዳዳሪ የነበሩት ደጃዝማች ኃይለ ጊዮርጊስ ወልደ ጊዮርጊስ (ባጭሩ ኃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ ) ልጅ ናቸው። እናታቸው ወይዘሮ አትጠገብ ወንድበወሰን ሲባሉ አመጣጣቸውም ከ ጎንደር ከተማ ባላባቶች ነበር። የወይዘሮ አትጠገብ እናት ወይዘሮ ትሻል ስትባል የ በጌምድር ክፍል መሳፍንት ዘር ነበረች፣ በአባቷ በኩል አያቷ ራስ ወዳጆ በዘመናቸው ከፍተኛ ተሰሚነት የነበራቸው ባላባት ነበሩ። የወይዘሮ አትጠገብ ድህነት በታሪክ መጻህፍት በተደጋጋሚ የሚጠቀስ ቢሆንም አመጣጡ እንዲህ ነበር፡ የህጻኑ ቴወድሮስ አባት ደጃች ሃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ ከሱዳኖች ጋር በተነሳ ጦርነት በጀግንነት ሲወድቁ እናት ገና ሁለት አመት የሆነውን ልጇን ይዛ ከቋራ ወደ ጎንደር ከተማ ሄደች። በዚህ ወቅት ሁለተኛ ላታገባ በመቁረብ ልጇን ብቻዋን ማሳደግ ግድ አላት። አንዳንዶች በዚህ ምክንያት እራሷን ለማስተዳደር ኮሶ ትሸጥ ነበር ሲሉ ጸሃፊው ጳውሎስ ኞኞ ወይዘሮ አትጠገብ መቼውንም ኮሶ አትሸጥም ነበር ይላል (ኮሶ ትሸጥ ነበር የሚለው የልጁ ጠላቶች ፈጠራ ወሬ ነበር በማለት ያስረዳል)። ሆኖም ቀረ ህጻኑ ቴወድሮስ በድህነት እንዳላደገ ሁሉም የታሪክ ጸሃፊያን ይስማማሉ። አንድ ለናቱ ቴወድሮስ በእናቱ በኩል እህትም ሆነ ወንድም አልነበረውም። የወደፊቱ አጼ ቴዎድሮስ በ፲፰፻፴፱ ዓ.ም. ተዋበች አሊ የተባለችውን የዘመነ መሳፍንት ታላቅ ባላባት፣ የራስ አሊ አሉላ ን፣ ልጅ አገባ። ተዋበች በጊዜው የ፲፭ ዓመት ወጣት የነበረች ሲሆን ቁንጅናዋና አስተሳሰቡዋ በጊዜው በነበሩ ሰወች ዘንድ የተደነቀ ነበር። ሁለቱ በፍቅር በመውደቃቸው ቴወድሮስ በአባቷ ራስ አሊና በአያቷ እቴጌ መነን ላይ ሲያምጽ ባሏን ትደግፍ ነበር። አጼ ቴወድሮስ የሚስታቸውን መታመም ከዘመቻ መልስ በ፲፰፻፵፰ ዓ.ም ላይ ከሰሙ በኋላ እቴጌ ተዋበች በ፲፰፻፶ አረፉ። በኃዘኑ ወቅት እስቲ ጠይቁልኝ እርቃ ሳትሄድ እትጌ ተዋበች ሚስት እናት ገረድ? ብለው እንደተቀኙ በታሪክ መዛግብት ሰፍሮ ይገኛል። ከሁለት ዓመት ሀዘን በኋላ በ፲፰፻፶፪ ዓ.ም ዓፄ ቴዎድሮስ ከሁለተኛ ሚስታቸው ጋር ተገናኙ። «ደራስጌ ቤተክርስቲያን ውስጥ ተቀምጠው ሳለ አንድ ወታደራቸው ወደ ርሳቸው ቀረበና «ጌታየ፣ አንዲት ሴት አገኘሁ፣ ፊቷም እንደ ፀሐይ የሚያበራ ነው።» ልጅቱም በኋላ ወደ ቤተመንግሥት ቀረበች፣ ስሟም ጥሩነሽ ውቤ ፣ የደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም ልጅ ነበረች። ንጉሱም አይተዋት "እውነትም ወርቅ ናት" በማለት አገቧት። በዚህ ወቅት ንጉሠ ነገሥቱ አባቷን ራስ ውቤን አስረዋቸው ነበር። ራስ ውቤ የ ሰሜን፣ወልቃይት ፣ፀገዴ ፣ትግራይ፣ ሰራየ ፣ ሐማሴን ና አንጎት (ሰሜን ወሎ) አስተዳዳሪ ሲሆኑ ከዓፄ ፋሲለደስ የሚወለዱ ስለነበሩ ለንጉሥነት የሚገዳደሩ ነበሩ። የጥሩወርቅ (ጥሩነሽ) እናት ደግሞ ወይዘሮ ላቂያየ የተባሉ የትግራይ መሳፍንት ዘር ነበሩ። ከኒህ ሚስታቸው ደጃዝማች ዓለማየሁ ቴዎድሮስ የተባለውን ከሁሉ በላይ የሚወዱትን፣ እርሳቸውን እንዲተካ ያጩትን ልጅ ወለዱ። ዓፄ ቴዎድሮስ በአጠቃላይ ፬ ጊዜ ሲያገቡ ፮ ወንድና ፫ ሴት ልጆች ነበሯቸው፣ እነርሱም፦ ወንድ ልጆች ሴት ልጆች ያልተረጋገጠ ፩) ራስ እንግዳ ቴወድሮስ - (የተዋበች ወይም እንግዳወርቅ? ልጅ) 1833 ላይ የተወለዱ። በመቅደላ ጦርነት የተገድሉ። 3ቱ ልጆቹ በእንግሊዞች የታሰሩ። ፩) ወይዘሮ አልጣሽ ቴዎድሮስ -- (ከሁለተኛ ሚስት) መጀመሪያ ጊዜ ከዳግማዊ ምኒልክ ጋር ጥር 1856 ላይ በመቅደላ የተዳሩ። ሁለተኛ ጊዜ ከራስ ባሪያው ጳውሎስ ፣ የትግራይ መስፍን ጋር ተጋቡ። ጥቅምት 1882 አረፉ ፩) ፒተር ኡስቲኖቭ - የእንግሊዙ ታዋቂ ጸሃፊ፣ ተዋናይና ድራማ ሰሪ ፒተር ኡስቲኖቭ ቅድም አያቱ የቴወድሮስ ሴት ልጅ እንደነበረች ይናገራል። [2] ተመራማሪወች ቅድም አያቱ እሳተወርቅ የተባለች መቃዶ የተባለ የጎንደር ወታደር ልጅ ናት ይላሉ። [3] ፪) ራስ መሸሻ ቴወድሮስ - (የተዋበች ልጅ) 1840 ላይ የተወለዱ። ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ን ከመቅደላ እንዲያመልጡ የረዱ። በአባታቸው የደጃዝማችነት ማዕረግ ተሰጧቸው በኋላ በዳግማዊ ምኒልክ ራስ የሆኑ። ልጆቻቸው ደጃዝማች ካሳ መሸሻ - የጎንደር አስተዳዳሪ ፪) ስማቸው ያልታወቀ ፫) ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ - (የጥሩነሽ ውቤ ልጅ) 1853 ላይ የተወለዱ። ሊድስ፣ ዮርክሻየር፣ እንግሊዝ አገር በ1870 ዓ.ም ያረፉ። ፫) ስማቸው ያልታወቀ ... ልጅ አላማ ጉዋሉ ን ያገቡ ፬) ልጅ ኃይለማርያም ቴዎድሮስ - (ሁለተኛ ሚስት) ፭) ልጅ ይማም ቴዎድሮስ -- (ላቀች ወይም ጣይቱ) ፮) ልጅ ተሰማድንገት ቴዎድሮስ -- (ሁለተኛ ሚስት) ወጣቱ ኃይሉ ካሳ ውልደትና ትምህርት ቤት ካሳ ኃይሉ በ1811 ዓ.ም. አባታቸው ሃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ በሚያስተዳድሩት ቋራ፣ ከእናታቸው ወይዘሮ አትጠገብ ተወለዱ። [4] ቋራ በምዕራቡ ኢትዮጵያ ከሱዳን ድንበር የሚገኝ ሲሆን በዘመኑ ከሱዳኖችና ክግብፆች ዘንድ ብዙ ወረራ ይደርስበት የነበር ክፍል ነው። [5] ደጅ አዝማች ሃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ ከሱዳን ጋር በተደረገ ጦርነት ሲያልፉ፣ በ1813 ዓ.ም ወይዘሮ አትጠገብ ህጻኑን ቴወድሮስ ይዘው ወደተወለዱበት ጎንደር ከተማ ተመለሱ። [6] ወይዘሮ አትጠገብ በነበራቸው ገቢ መጠን ልጃቸውን በጥሩ ሁኔታ ማሳደግ ስላልቻሉ ክንፉ ሃይሉ ህጻኑን ቴወድሮስ በጎንደርና በጣና ሃይቅ መካከል በሚገኘው ቸንከር በተባለ ቦታ የተክለ ሃይማኖት ገዳም ለትምህርት ላኩት። ቀጥሎ የሆነውን በጊዜው የነበር ደብተራ ዘነበ እንዲህ ሲል ይዘግባል፡ በልጅነትዎ፡ቸንከር፡ትምርት፡ሲማሩ፡ከገዳሙ።ደጃች፡ማሩ፡በደምቢያ፡ሸፈቱ።ያነ፡ጊዜ፡የቤጌ፡ምድር፡ሁሉ፡ገዢ፡ እራስ፡ይማም፡ነበሩ። ደጃች፡ማሩን፡ለማሳደድ፡በመጡ፡ጊዜ፡ገዳሙን፡ሰበሩት። አብረው፡የሚማሩዋቸውን፡ ፵፰አሽከሮች፡ሰልቦ፡ልጅ፡ካሳን፡ትቷቸው፡ሄደ፡በውስጥ፡ሳሉ። [7] ይህም በህጻኑ ላይ የማይጠፋ የአይምሮ ጠባሳ ትቶ ያለፈ ኩነት ነበር። [8] ህጻኑ ወደ አጎቱ ወደ ደጃዝማች ክንፉ ቤት ተመልሶ በአጎቱ ቤት የአስተዳደርን፣ የወታደራዊ ዘዴንና ስልትን ተማረ። [9] ማንበብና መጻፍን በዚሁ ወቅት በሚገባ ተለማመደ። [10] የወደፊቱ ቴወድሮስ እጅግ ማንበብን የሚወድ ሰው ነበር፣ የኢትዮጵያን ጥንታዊና ጊዜያዊ ድርሳናትን፣ የአውሮጳን ጥንታዊ እና ጊዚያዊ ታሪክ በደንብ እንዳጠና መረጃ አለ።[9] የ ሼክስፒርን ስራወችና መጽሃፍ ቅዱስ ን ሳይቀር እንዳጠና በጊዜው የነበሩ አውሮጳውያን ሳይመዘግቡ አላለፉም። ለነበረበት ዘመን በደንብ የተማረ ሰው ነበር።[9] በሽፍትነት ወራት ቴወድሮስና ሽፍቶቹ የ ደምቢያ አስተዳዳሪ የነበሩት ደጃዝማች ክንፉ ምንም እንኳ ቴወድሮስን ለዘመቻ ይዘውት ቢውጡም ግዛታቸውን ከካሳ ይልቅ መኮንን ለተባለ ልጃቸው ለማውረስ በመፈለጋቸው ግንኙነታቸው የሻከረ ሆነ። በ1839 ደጃች ክንፉ ካረፉ በኋላ የክንፉ ሁለት ልጆችና ካሳ ሆነው የ ዳሞት ና ጎጃም ገዢ በነበሩትን ደጅ አዝማች ጎሹ ዘውዴን ጦርነት ገጥመው ተሸነፉ። ልጅ ካሳ በጦርነቱ ባይማረክም ብዙ ወራት በሽሽት ከቆየ በኋላ የአሸናፊውን ደጃች ጎሹን ጦር በመጨረሻ ተቀላቀለ [11] ። ምንም እንኳ የውትድርና ብቃትን ቢያሳይም በደጃች ጎሹ ሰራዊት ውስጥ እድገትን ስላላገኘ ወደ ቋራ ተመለሰ።[12] ። ሆኖም ወይዘሮ መነን ሊበን አምዴ አጠቃላይ ደምቢያ ን የግሏ ርስት አድርጋ ነበር።[13] በዚህ ምክንያት የመነን ሊብን ተወካይ ገዢወች ወጣቱን ካሳ ከቋራ እንዲለቅ ይወተውቱት ነበር። ካሳም የተነጠቀውን የአባቱን ርስት ለማስለመስ ያለው አማራጭ አመጽ በመሆኑ ወደቆላ ወርዶ ሸፈተ። [9] ካሳ እንደሌሎች ሽፍቶች ሳይሆን በደግነቱና በፍርድ አዋቂነቱ እራሱን ለየ። ለምሳሌ በሽፍትነት የሚያገኘውን ገንዘብ ለገበሬወች እያከፋፈለ ሞፈርና ቀንበር እንዲገዙ ይረዳ ነበር።[9] ይህ አይዞህ ባይነትና ደግነት ለወጣቱ የፖለቲካ መሰረት ሲያስገኘው ከጊዜ ወደጊዜ ደጋፊወቹ እንዲበራከቱ አደረገ። [13] በ12 ሰወች የተጀመረው አመጽ በጥቂት ጊዜ 300 ጦረኞችን ሰበሰበ።[9] ተከታዮቹ እየበዙ ሲሄድ በጣም የተሳካ የጦር ስልት መከተል ጀመረ፣ ስልቱም እንዲህ ነበር፡ ያልተጠበቀ ዘመቻውን ቀን ላይ ካወጀ በኋላ ከ5 እስከ 600 ፈረሰኞቹ ጋር ሆኖ ሌሊቱን ሲጓዝ ያድርና ጠዋት ላይ ጠላቶቹ ላይ በድንገት ይደርሳል።[14] ዱብዳው ጦርነትም በካሳ አሸናፊነት ይፈጸማል። በዚህ ሁኔታ በ1829 ዓ.ም. የካሳ ጦር ሱዳን ጠረፍ ደረሰ። የፖለቲካ ሰው የካሳ ሽፍቶች በነጋዴወች ላይ የሚያካሂዱት ጥቃት በተዘዋዋሪ የእቴጌ መነንን (በጊዜው የ ሳልሳዊ አጼ ዮሃንስ ባለቤት) የቀረጥ ገቢ ቀነሰ። [15] በዚህና እየጎላ በመጣው የካሳ ዝና ምክንያት የ የጁ ባላባት ምን እንዲያደረጉ ግራ ገባቸው። ችላ እንዳይሉት ችሎታ አለው፣ እንዳይወጉት ጥሩ ተዋጊ ነው። [16][17] ስለሆነም ወይዘሮ መነን ለቴወድሮስ በመስፍን ማዕረግ የልጇን የራስ አሊ አሉላ ን ጦር እንዲቀላቀል ጋበዘችው። [13] ካሳም ያለውን ጥንካሬ ግምት ውስጥ በማስገባት ለመነን ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የራሱን ሰራዊት እንደያዘ የቋራ አስተዳዳሪ ሆኖ ተሰየመ። በዚያውም የራስ አሊን ልጅ ተዋበች አሊን በ1839ዓ.ም. አገባ። [18] አዲስ ማዕረግ የተጎናጸፈውን የልጁን ባል ራስ አሊና እናቱ ወይዘሮ መነን ድሃ አደግነቱን አስመልክተው ንቀት በተሞላው መልኩ ያስተናግዱት ነበር። ከዚህ በተረፈ የመነን ርስት የሆነ ደምቢያም የቋራን ክፍሎች ስለያዘ የቋራ ገቢ በጣም አንስተኛ ነበር። በዚህና መስል ምክንያቶች በሚስቱ ድጋፍ በመነን ላይ አመፀ፣ ስሙንም አባ ታጠቅ በማለት ደምቢያን ወረረ። [19] የቴወድሮስን ወርራ አድገኛነት ያልተረዳችው ወይዘሮ መነን በደጅ አዝማች ወንድይራድ የሚመራ አንስተኛ ሃይል አድርጋ ጦር ላከችበት። ይህ ጦር ሁለት ጊዜ በቴወድሮስ ተሸነፈ። በምስራቅ፣ በጎጃም መነንና ልጇ አሊ በጦርነት ተጠምደው ስለነበር የጎንደር ከተማን ለቀው ወደጎጃም ጦራቸውን ይዘው ዘመቱ። [13] የተገኘውን አጋጣሚ በመጠቀም ጥር 1840 ላይ የጎንደር ከተማን ቴወድሮስ ተቆጣጠረ። [13] የራሱን ባለስልጣኖች በከተማው ላይ ከሾመ በኋላ ለአሊ ይገባው የነበርውን ግብር ሰበሰበ፣ ቀጥሎም ከነገስታቱ ጎተራና ከከባቢውም መንደሮች እህልን መዘበረ። [15] ከጎጃም መልስ፣ በጣና ሃይቅ በስተሰሜን በተደረገ ጦርነት እቴጌ መነን ጭኗ ላይ ቆስላ ከባሏ ከሳልሳዊ አጼ ዮሃንስ ጋር በቴወድሮስ ታሰረች። [13] እኒህ እሰርኞችን ለማስለቀቅ በተደረገ ውይይት ቴወድሮስ የ ደጅ አዝማችነትን ማዕረግ ከራስ አሊ አገኝ። እንዲሁም ደምቢያ ለቋራ ተመልሰ። በአንጻሩ ቴወድሮስ የአሊን ሰራዊት ልዋሃድ ተስማማ። [15] ቴወድሮስ የመጀመሪያው የዘመናዊ ጦር መሳሪያ ውጊያ የገጠመው በዚሁ በደጅ አዝማችነት ወራት ነበር። ደባርቅ ላይ ሰፍሮ የነበረውን በሙሃመድ አሊ የሚመራ የግብጽ ወራሪ ሃይል ለማጥቃት ከ16፣000 ሰራዊት ጋር መጋቢት 1840 ላይ ዘመቻ አድርጎ፣ ምንም እንኳ የርሱ ሃይሎች ቁጥር ከግብጾቹ ቢበልጥም በግብጾቹ ዲሲፕሊንና ዘመናዊ ጦር መሳሪያ ምክንያት ተሸነፈ። ይህ ጉዳይ ቴወድሮስን እጅጉን ያስደነቀ ኩነት ነበር።[15] ከዚህ በኋላ ነበር ቴወድሮስ ዘመናዊ ጦር መሳሪያን ለማግኘትና ዘመናዊ የጦር ስልትን ለመማር ከፍተኛ ፍላጎት ያደረበት። [20] ጦርነትና ንግሥና ከትንሹ አሊ ጋር ጥል የቴዎድሮስ ጦር ግንባሮች ከ1845 እስከ 1847 የምሽግ ቅጥሮች በፋሲል ግቢ፣ ጎንደር ከተማ ቴወድሮስ ከሱዳን ጋር ለጦርነት በወጣበት ወቅት ቋራ ላይ ይዘርፉ የነበሩትን አማጺወች ሲመለስ ቀጣ። በዚህ መንገድ የቋራ ግዛቱን ካጸና እኋላ ከከባቢው ተገዳዳሪወች ይበልጥ ጠነከረ። [17] ጥር 1840 ላይ ራስ አሊ ቴወድሮስ ወደ ደብረ ታቦር እንዲመጣ ለሁለተኛ ጊዜ ቢልኩበትም ባለመሄዱ በሁለቱ መካከል የመጀመሪያው ጥል ታየ።[20] ከ1841- 42 ለተወሰነ ጊዜ በአገው ምድር ዘመቻ ካደረገ በኋላ ወደ ቋራ ተመለሰ።[17] 1844 ላይ ከራስ አሊ ጋር ፊት ለፊት በመጋፈጥ ወደ ዙፋን የሚያደርገውን ጉዞ ጀመረ። ከዚህ ዓመት በኋላ ታላላቅ የዘመነ መሳፍንት ባላባቶችን ተራ በተራ በመውጋት አሸነፋቸው። በኒህ ጦርነቶች "የላቀ የውጊያ ስልትንና ጥበብን" በማሳየት ወታደራዊ ብቃቱን አስመዘገበ። [21] በ1844 መጨረሻ አካባቢ ከራስ አሊ ጋር የገባውን ውል ሙሉ በሙሉ በማፍረስ ራስ አሊ ወደ ጎጃም ሊያደርገው በነበርው ዘመቻ እንደማይሳተፍ አስታወቀ።[20] ራስ አሊም ለብዙ ወራት ጦር በመላክ ቴወድሮስን በቋራ ውጊያ ገጠመው 7። በስተመጨረዣ መስከረም 1845 ላይ አሊ ጎሹ ን የቋራ ገዢ አድርጎ በቴወድሮስ ላይ ሾመበት።[22] ይህ አዲሱ ሹም ቴወድሮስን ለመግጠም ወደቋራ ከሰራዊቱ ጋር ተመመ። በዘመነ መሳፍንት ላይ ጦር ስለመክፈቱ ጥቅምት 27፣ 1845 ላይ ቴወድሮስ የድሮ አለቃውን የጎጃም ባላባት ደጅ አዝማች ጎሹ ዘውዴን በ ጉር አምባ ጦርነት ገጥሞ አንድ ቀን ሙሉ በተደረገ ውጊያ ደጅ አዝማች ጎሹ ስለወደቁ በቴወድሮስ አሸናፊነት ተጠናቀቀ። [21] ይህ በጊዜው እንደ ታላቅ ድል የታየ ሲሆን ጉር አምባ ለጎንደር ከተማ በጣም የቀረበ ቦታ ስለነበር የቴወድሮስን የወደፊት ምኞት ያመላከተ ጦርነት ነበር። በዚህ ድል የተደናገጠው ራስ አሊ ምንም እንኳ ከቴወድሮስ የዕርቅን መልዕክት ቢላክለትም የጎንደር ከተማን ለቆ ወደ ደብረ ታቦር አመራ። ቴወድሮስ ብዙም ሳይቆይ የጎንደር ከተማን ያዘ። [22] ራስ አሊ ደብረ ታቦር ላይ ሆኖ የ የጁ ን፣ የ ወሎና የትግራይ ን ጦር አንድ አድርጎ ቴወድሮስን ለመውጋት ለ3ቱም ክፍሎች ጥሪ አደረገ። [23] ጥር 1945 ላይ የትግራዩ ባላባት ደጅ አዝማች ውቤ ከራስ አሊ ጋር ትብብር እንደፈጠሩ ሰማ፡ ይህ በዘመኑ የሁለት ታላላቅ የተባሉ ሰራዊቶች ቅንጅት ነበር። መጋቢት ላይ የጠላት ጦር ወደርሱ እየመጣ እንደሆነ መረጃ በማግኘቱ ከጎንደር ከተማ 3ሰዓት የእግር ጉዞ ላይ ባለው በ ጎርጎራ ቢሸን ላይ ሰራዊቱን አሰፈረ። ሚያዚያ12፣ 1845 ላይ በዚሁ ቦታ በተደረገ ጦርነት በየጁው ደጅአዝማች ብሩ አሊጋዝ የሚመራው ጦር እንዳለ ተደመሰሰ። በዘመነ መሳፍንት ላይ ጦርነት የከፈተው ካሳ በጦርነቱ የራስ አሊንና የደጅ አዝማች ውቤን ሶስት ደጅ አዝማቾች ገደለ።[22] ከዚህ ድል በኋላ ወደ ጎንደር ከተማ ተመልሶ የተቀሩትን ሁለቱን መሪዎች ፣ ውቤንና አሊን፣ ለመደምሰስ ይዘጋጅ ጀመር። ግንቦት 1845 ላይ ደብረ ታቦር ላይ ዘመቻ አድርጎ ከተማይቱን መዘበረ። አማቱን ራስ አሊንም ቢያሳድደው ጎጃም ላይ መሸገ።[22] ቀጥሎም በሰኔ29፣ 1845 ላይ አይሻል በተባለ ቦታ ጦርነት ገጥመው ቴወድሮስ ራስ አሊን አሸነፈ፣ እቴጌ መነን ሊበንንም ማረከ። የ አይሻል ጦርነት በዘመኑ እጅግ በደም የጨቀየ አስክፊ ጦርነት ነበር።[23] ብዙ ታሪክ አጥኝወች ይህ የአይሻል ጦርነት የዘመነ መሳፍንት ማብቂያ እንደሆነ ይስማማሉ። [24] [25] ከዚህ በኋላ ሁሉ በሁሉ ጦርነት የሚከፍትበትና ሃይለኛ ባላባቶች ተቀራምተው አገሪቱን የሚያስተዳድሩበት ዘመነ መሳፍንት አበቃለት። በዚህ ወቅት እንደ ጥንቱ አንድ ጠንካራ ሰው ከሌሎች ልቆ አገሪቱን የሚያስተዳድርበት ሁኔታ ተፈጠረ። [23] ከአይሻል ጦርነት በኋላ ራስ አሊ ወደ የጁ ሸሹ፣ 1848 ላይ በዚያው በየጁ አረፉ።[23] ከ18ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀመሮ የገነነው የየጁ ሃይልና የራስ አሊ ጥንካሬ አይሻል ላይ አበቃ። [26] ከዚህ ድል በኋላ ቴወድሮስ የመላው ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ መሪ ቢሆንም ቅሉ አጠቃላይ መሪ ለመሆን የተቀሩትን የሰሜን ባላባቶች ማሸነፍ ነበረበት። ግንቦት 1846 አምባ ጄበል ላይ ከጎርጎራ ቢሸን ጦርነት አምልጦ የነበረውን ብሩ ጎሹን ተዋግቶ በመማረክ ለሚለቀጥሉት 14 አመታት እስረኛው አደረገው።[27] ትንሽ ቆይቶም ቴወድሮስ የላስታውን ፋሪስ አሊን ደመሰሰ።[22] ከአቡነ ሰላማ ጋር ስምምነት፣ የደራስጌ ጦርነት የተዋበችና የንጉስ ቴወድሮስ መቁረብ በወቅቱ ዙፋን ላይ ለመውጣት አንድ ቀሪ እንቅፋት በቴዎድሮስ ላይ ተጋረጠ፣ እርሱም የሰሜኑ ደጃዝማች ውቤ ነበር። ከአይሻል ጦርነት በኋላ ራሱ ውቤ ከቴወድሮስ ጋር እርቅን በመሻት የተለያዩ ስጦታን ላከለት። ቴዎድሮስ በላስታና በጎጃም ቀሪ ዘመቻወችን ሲያደርግ ከኋላው በሰሜውን ውቤ ጦር እንዳይከፍትበት ሲል የውቤን ስጦታወች ተቀበለ። [27] በዚህ ስምምነት መሰረት የቴዎድሮስ ሰራዊት ትግራይን መልቀቅ ጀመረ ሆኖም ግን አቡነ ሰላማ ከትግራይ ወደ ጎንደር እንዲመጡ አደረገ።[17] አቡነ ሰላማ ከግብጽ የመጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን ፓትሪያርክ ነበሩ። ደጅአዝማች ውቤ እራሳቸውን ለማንገስ ከግብጽ ያስመጧቸው ነበሩ። የቴወድሮስ አላማ አቡነ ሰላማን ከርሱ ዘንድ በማድረግ የቤተክርስቲያኗን ፈቃድ ለማግኘትና አገሪቷን እንደገና ለመገንባት ነበር።[27] ወዲያውም ቴወድሮንና አቡነ ሰላማን የሚያግባባ አንድ አላማ ተገኘ ፡ አንዲት ጠንካራ ቤ/ክርስቲያን በአገሪቱ እንዲኖር ማድረግ። በዘመኑ ሶስት ልደት የሚባል ትምህርት ተነስቶ ይህን ሃሳብ በሚያነሱና በተዋህዶ ተከታዮች መካከል ከፍተኛ ክርክር ነበር። [28] ይህን ክፍፍል ለማስወገድ ሐምሌ 1846 ላይ በቴዎድሮስ የሚመራ የ አምባ ጫራ ጉባኤ ተጠራ። [27] ለተዋህዶ ተቃዋሚወች ቴወድሮስ ጠየቃቸው፡ "አቡነስ ሰላማን እንደመሪያችሁ ታውቁታላችሁ?" እነርሱም ለስወ "አዎ" አሉት። ያን ጊዜ መልሶ ጠየቃቸው፡ "እንኪያስ ልጆቼ ከአቡኑ የተለየ የሚያስተምሩ መናፍቅ ናቸው ።" ከዚህ በኋላ ለ3 ቀን ያለምግብና መጠጥ ትቷቸው ሄደ፣ ከዚህ በኋላ ጥፋታቸውን አመኑ። [29] ከዚህ ስምምነት በኋላ የሶስት ልደት ትምህርት ኑፋቄ ተባለና የተዋህዶ ትምህርት የአገሪቱ ብቸኛ ትምህርት ሆነ ። እኒህን ለውጦች በመፈጸሙ ከአቡነ ሰላማ ጋር ያለው ግንኙነት እጅግ ጥሩ ሆነ። በ1846 መጨረሻወቹ ቴዎድሮስ ንጉስ ተብሎ በአቡነ ስላማ ተቀባ። [30] ቴዎድሮስና ተዋበችም ጋብቻቸውን ህጋዊ በማድረግ ቆረቡ።[31] የቴዎድሮስን ንጉስ መሆን ደጅአዝማች ውቤ ሊቀበለው አልቻለም። ስለሆነም ቴወድሮስን ለመውጋት ዝግጅት ማደርግ ጀመረ። [32] በዚህ ምክንያት ቴዎድሮስ ያለመንም ችግር ሰሜንን በመውረር ከትግራይ የካቲት 9፣ 1847 የተነሳውን ውቤን ደራስጌ ላይ ገጠመው። ደራስጌ የደጅ አዝማች ውቤ ዋና ከተማ የነበር ቢሆንም በዚህ ጦርነት ተሸነፈና ተማረከ። ከሁለት ቀን በኋላ ቴወድሮስ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት ተብሎ አክሊል ጫነ። በደራስጌ ማርያም ዘውድ ስለመጫናቸው ከብዙ መራራ ትግል በኋላ የሰሜን ተፎካካሪወቹን ያስወገደው። [32] ንጉስ ካሳ ሃይሉ የካቲት 11፣ 1847 ዓ.ም. ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብለው ዘውድ ጫኑ፣ ስማቸውም ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ተባለ።[24] ስርአተ ንግሱ የተከናወነው በደራስጌ ማርያም ቤተክርስቲያን ሲሆን የዓለምን ተገልባጭ ዘይቤ በሚያሳይ መልኩ ይኸው ቤ/ ክርስቲያን ደጃዝማች ውቤ ለራሳቸው ስርዓተ ንግስ ሲሉ ያስሩት ነበር፣ ስርዓተ ንግሱንም የፈጸሙት አቡነ ሰላማ ሲሆኑ እኒሁ ጳጳስ ከግብጽ በደጅ አዝማች ውቤ ለራሳቸው ንግስና የመጡ ነበሩ። [24] አጼ ቴዎድሮስ ንግስናቸውን ያወጁበት ሰገነት፣ስሜን ጃናሞራ፣ደረስጌ ማርያም አጼ ቴወድሮስ 1847፣ በደራስጌ ማርያም ዘውድ ሲጭኑ፡- ቀይ ቆብ የደፉት አቡነ ሰላማ ሲሆኑ ከንጉሱ አጠገብ ተዋበች አሊ ትታያለች። ስዕሉ ከዚያው ዘመን የመነጨ በኋላ ከአድዋ ቤ/ክርስቲያን ወደ እንግሊዝ የተወሰደ አጼ ቴዎድሮስ በመጀመሪያወቹ የአገዛዝ ዘመናቸው ራሳቸውን ከሰሎሞናዊው ስርወ መንግስት የተለዩ እንደሆነ ለማሳየት ሞክረዋል ይህም በዘመነ መሳፍንት የደረሰው የግብረገብና ፖለቲካ መላሸቅ ምክንያት ስርወ መንግስቱ በህዝቡ ዘንድ ዋጋው ረክሶ ነበር [33] ። በዚህ ምክንያት የአጼ ቴወድሮስ የመጀመሪያወቹ የአገዛዝ ዘመናት ከ1270ዓ.ም. ይኩኖ አምላክ ጀምሮ ሲወርድ ሲዋርድ የመጣውን የአገሪቱን አሰራር በጭንቅላቱ የደፋ ነበር። ሆኖም ግን በኋላ ላይ አጼ ቴዎድሮስ በእናታቸው የአጼ ፋሲለደስ ዘር እንደሆኑ ለማሳየት ሞክረዋል፣ ስለሆነም በአጠቃላይ መልኩ በአሁኑ ዘመን የሰለሞናዊ ስርወ መንግስት አካል እንደሆኑ ይጠቀሳል [34] ። የአጼ ቴዎድሮስ ዙፋን ላይ መውጣት በ1845 በአይሻል ጦርነት ተጀምሮ የነበረውን የዘመነ መሳፍንት ስርዓተ ቀብር አጠናቋል። ብዙ ታሪክ ተመራማሪወች የካቲት11፣ 1847 የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ጅማሬ እንደሆነ ይስማማሉ 2። ሪቻርድ ፐንኸርስት እንደጻፈ፡"የካሳ ሃይሉ ከፍ ማለት አዲሱን የኢትዮጵያ ታሪክ የከፈተ ክስተት ነበር 3"። አጼ ቴዎድሮስ የዙፋን ስማቸውን የመረጡት ከ ፍካሬ እየሱስ ሲሆን ይህ መጽሃፍ የሚያትተው ስለሚመጣው አለምና በ15ኛው ክፍለ ዘመን ስለነበረው በዘመኑ ኢትዮጵያውያን ዘንድ እጅግ ተወዳጁ ስለነበር ንጉስ ቀዳማዊ አጼ ቴወድሮስ ስርዓት እንደገና በኢትዮጵያ መንሰራፋት ነበር። ይሄው የጥንቱ ንጉስ፣ ምንም እንኳ የአገዛዙ ዘመን እጅግ አጭር ቢሆንም፣ የፈጸመውም ጥሩ ተግባራት በታሪክ ጅረት ተሽርሽሮ ቢጠፋም በጥንቶቹ ኢትዮጵያውን ዘንድ ምንጊዜም የማይረሳ ተወዳጅ ንጉስ ነበር። ከሰራቸው ስራወች አንዱ ከይኩኖ አምላክ ጀምሮ ለቤተክርስቲያን ሲወርድ ሲዋርድ የመጣውን የቤተክርስቲያን መሬት ለገበሬወች ማከፋፈሉ ነበር። በፍካሬ እየሱስ መሰረት፣ ቀዳማዊ ቴዎድሮስ እንደገና ከሞት ይነሳና ፍትህና ሰላም አስፍኖ "ሁሉም ከሚፈጠረው ደስታና ሰላም ተካፋይ" የሚሆንበት ግዛት ያንሰራፋል የሚል ነበር [35][36] ። በ1830ዎቹ የዘመነ መሳፍንት ጦርነቶች በተሰቃየው ህዝብ ዘንድ ይህ የ ፍካሬ እየሱስ ትንቢት ከመንደር መንደር የገነነ ነበር። [30] አጼ ቴዎድሮስ፣ ይህ "የአገሪቱን የታሪክ አቅጣጫ የሚቀይር" የሚመጣው ንጉስ ነኝ ብለው ያምኑ እንደነበር ለማመን አይከብድም 7። በስርዓተ ንግሳቸው ላይ ባደርጉት ንግግር አገሪቷን አንድ ለማድረግና እንደገና ለመገንባት ያላቸውን ከፍተኛ ፍላጎት ገልጸዋል። የቴወድሮስን የህይወት ታሪክ የጻፈው ስቬን ሩቤንሰን አፄ ቴወድሮስ ስልጣን ላይ ሲወጡ በአይምሮአቸው ውስጥ የነበረውን ዕቅድ እንዲህ ሲል ይዘግባል፡ "የቴዎድሮስ ስሜት እንደቀደሙት ነገስታት ሳይሆን የተለየ ነበር፡ ለእርሱ የባላባቶች ትርምስ፣ የግብረገብ መላሸቅ፣ የቴክኖሎጂ ኋላቀርነት የአገሪቱን መኖር ጥያቄ ውስጥ የጣሉ ጉዳዮች ነበሩ። ያወጃቸው ለውጦች፣ የተከተላቸውና ሊተገብራቸው የፈለጋቸው ፖሊሲወች፣ እያንዳንዱን ችግር ለመፍታት ያሳየው እልከኝነት፣ የሚያሳዩት የንጉሱ አላማ ብሔራዊ ተሃድሶና አገሪቱን ወደ ዘመናዊ አገር ማሻገር እንደነበር ነው [37] " የቴወድሮስ መንግስት፡ አንድነትና ሥልጣኔ ዘመቻ ወደ ወሎና ሸዋ በ1848 የቴዎድሮስ ግዛት ወሎን፣ ጎንደር ን፣ ትግራይን፣ ጎጃም ን፣ ሸዋ ን እና እንዲሁም ከፊል ኤርትራን ያጠቃልል ነበር ወታደር አጼ ቴዎድሮስ ከሁለት አመት የማያቋርጥ ዘመቻ በኋላ የነገሱት አጼ ቴወድሮስ ለማረፍ አልፈለጉም፣ እንዲያውም ዋናዋና ታላቁ ግባቸውን እውን ለማድረግ ወደ ደቡቡ ታሪካዊ የኢትዮጵያ ክፍል መዝመት ግድ አላቸው 9። የሰሜኖቹን ባላባቶች በማሸነፍ ብቻ አለመታቀባቸው በታሪክ ጸሃፊው ባህሩ ዘውዴ ዘንድ ንጉሱ "ሰፋ ያለ ራዕይ" እንደነበራቸው የሚያሳይ ሆኖ ተገኝቷል። [24] የደራስጌው ስርዓተ ንግስ የዘመነ መሳፍንትን ማብቃት ሲያሳይ የሸዋውና የወሎው ዘመቻ በአንጻሩ በአጼ ምንሊክ የተጠናቀቀውን የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ማዕከል ወደ ደቡብ ማምራት አመላካች ነበር [24] ። የወሎና የሸዋ በራስ መተዳደር በርግጥም ንጉሱ የነበራቸውን የማዕከላዊ አንድ ኢትዮጵያ ራዕይ አደጋ የጣለ [38] ስለሆነ ዘመቻው ግድ የሚል ነበር [39] ። በመጋቢት ፲፰፻፵፯ ዓ.ም በፆም ወቅት አጼ ቴዎድሮስ ወደ ወሎ ዘመቻ አደረጉ።[24] ምንም እንኳ ይህን ዘመቻ ወሎ ውስጥ ይገኙ የነበሩት ፯ ጎሳወች ተባብረው ለማሸነፍ ቢሞክሩም የቴዎድሮስ ሰራዊት በመስከረም ፲፪ ቀን ፲፰፻፵፰ ዓ/ም መቅደላን በመቆጣጠር ድል አደርጋቸው።[24] መቅደላ እንግዴ በኋላው ዘመን የአጼ ቴወድሮስ የመንግስት ማዕከልና ዋና ምሽግ የሆነ ነው [24] ። የወሎ ዋና ዋና መሪወች ከተማረኩ በኋላ አመጽ እንዳያስነሱ በቴወድሮስ መቅደላ ላይ ታሰሩ። [39] የወሎው ድል ለአጼ ቴወድሮስ ትልቅ ስልታዊ ጠቀሜታ ነበረው ምክንያቱም ወደ ሸዋ በሚያደርጉት ዘመቻ የኋላቸው ለጥቃት አይጋለጥምና። [40] ሸዋ በዚህ ወቅት ከዘመነ መሳፍንት ትርምስ የተገላገለ ክፍል ስለነበር ከሰሜኑ ኢትዮጵያ በተለየ መልኩ ሰላም የሰፈነበትና ሃብታም ነበር። [41] ጥቅምት 1848 ላይ በድንገት የአጼ ቴዎድሮስ ሰራዊት ከወሎ ተነስቶ ሸዋ ገባ።[39] የንጉሰ ነገሥቱ ሰራዊት ድንገተኛ አመጣጥ የሸዋን ሰራዊት ስለከፋፈለው በጥቅምት አጋማሽ ላይ በአጼ ቴዎድሮስና ንጉሥኃይለ መለኮት ሣህለ ሥላሴ ሠራዊት መካከል በተደረገ ጦርነት የአጼው ጦር የ ባለወርቅ ጦርነት ተብሎ የሚታወቀውን ውጊያ ድል አደረገ። ዘመቻው ባጠቃላይ ፭ ወር የፈጀ ነበር። [24] መንዝ ግድም ና ኤፍራታ በቴዎድሮስ ስር ሲወድቁ ሌሎች የሸዋ ክፍሎች ግን በሰይፉ ሣህለ ሥላሴ ፣ የ ንጉሥ ኃይለ መለኮት ወንድም መሪነት የቴዎድሮስን ጦር በመከላከል ቆዩ [24] ። በራስ ዳርጌ የሚመራው የንጉሠ ነገሥቱ ጦር ህዳር 1848 ላይ በበረከት ጦርነት አሸነፈ [42] ። በመካከሉ ኅዳር ፱ ቀን፣ ንጉሥ ኃይለ መለኮት በሕመም አረፉ። በዚህ ምክንያት የሸዋ ወታደሮች ዓላማ የንጉሡን ልጅ ምኒልክን ከቴዎድሮስ እጅ ተከላክሎ ማዳን ሆነ። ሆኖም ግን ልጅ ምኒልክ በቴዎድሮስ እጅ በመውደቁና ቴዎድሮስም እንደልጃቸው ሊያሳድጉት ቃል በመግባታቸው የካቲት ፲፰፻፵፰ ዓ/ም ላይ አንኮበር ሲገቡ በቀሳውስትና አንኮበር መሪወች ዘንድ ተቀባይነትን አገኙ።[41] ቀጥሎም ንጉሰ ነገስቱ በጊዜው የነበረውን የሸዋ አስተዳደር በመቀየረ መርድ አዝማች በሚለው የጥንት ማዕረግ የንጉሥ ኃይለ መለኮት ወንድም የነበሩትን ኃይለ ሚካኤል የሸዋ አስተዳዳሪ አድርገው ሾሙ። [43] ለ፪ መቶ ክፍለ ዘመን ተከፋፍሎ የነበረውን የኢትዮጵያ ግዛት አጼ ቴዎድሮስ በ፫ አመት ዘመቻ በንዲህ መልኩ አንድ አደረጉ 11። በ፲፰፻፵፰ ዓ/ም አጋማሽ ላይ ሸዋ ን ጎጃም ን ወሎን ትግራይ ንና ጎንደር ን አንድ ላይ በመግዛት፣ በ፵፯ ዓመታቸው፣ የዘመነ መሳፍንት የመጨረሻ ባላባትና የአዲሱ ዘመናዊ አገር የመጀመሪያ ንጉሠ ነገሥት ለመሆን በቁ። በዚህ ወቅት የአገሪቱ ዋና ከተማ ከጎንደር ወደ ደብረ ታቦር ተዛውሮ ነበር 9። የአዲሱ ንጉሠ ነገሥት የመጀመሪያ ስራዎች የቴዎድሮስ መነሳት የዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክ መጀመሪያ ነው፣ ለዚህም ምክንያቱ የፈጸሟቸው ለውጦች ናቸው [43] ። ከርሳቸው በፊት ከነበሩ ነገሥታት በተለየ መልኩ ቴዎድሮስ አገሪቱን ወደ ዘመናዊ አገር ለማሻገር ያሳዩት ፍላጎት ንግሰ ነገሥት በነበሩበት ወቅት የነበራቸው ወጣትነትና።[44] ከአደጉበት ከቋራ ነባራዊ ሁኔታ የመነጫል። ቋራ በዘመኑ ከሱዳን የማያቋርጥ ውጊያ የሚደረግበትና በዚያ የሚኖረው ህዝብ ከመካከለኛው መንግስት የሚያገኘው ምንም እርዳታ ስላልነበር ህዝቡ እጅግ የተሰቃየበት ነበር።[45] ቀሳውስቱም ቢሆን በጎጥ ተከፋፍለው የየራሳቸው ሃይማኖታዊ ስርዓት በመተለም የተዋህዶ ቤተክርስቲያናን ከብዙ ቦታ ለመክፈል የሚገዳደሩበት ዘመን ነበር።[45] የገጠሩም ክፍል በባላባቶች የርስ በርስ ጦርነት የተሰቃየ ነበር።[45] የአገሪቱ ሁኔታ ንጉሰ ነገስቱ ዘመነ መሳፍንትን ለማጥፋት እንዲነንሳሱ አደረገ። [44] በጊዜው የነበረው የእንግሊልዙ ቆንጽላ ዋልተር ፕላውዴን ንጉሰ ነገሥቱ የኢትዮጵያን ቀደምት ታላቅነት ለመመለስ ዋና አላማ እንዳላቸው ሳይመዘግብ አላለፈም፣ በፕላውዴን አስተሳሰብ ይሄ የንጉሰ ነገስቱ ዋና አነሳሽ አላማ ነበር።[46] ከዚህ አንጻር የቴዎድሮስ የንግስና መጀመሪያ አመታቶች በብሄራዊ ፍትሕ፣ ርህራሄና የደሃ አደጎችን ህይወት በማሻሻል ላይ ያተኮረ ነበር። [30][47] ቴዎድሮስ ቀደምት የአገሪቱ መንገድ ሰሪ ነበር።[48] በዜና መዋዕሎችና የውጭ አይን እማኞች መሰረት ቴዎድሮስ በራሱ በእጁ መንገድ በመስራት ሌሎች እንዲከተሉት ይመራ ነበር።[48] ንጉሱ ከ"ሌት እስከ ምሸት በራሳቸው እጅ ድንጋይ ይፈነቅሉ እንዲሁም ጎርባጣውን ክፍል ያቃኑ" ነበር። በምሳሌ የሚመራው ቴዎድሮስ እርሱ እየሰራ ሌሎች ተከታዮቹ ሊበሉም ሆነ ሊያርፉ አይደፍሩም ነበር። [48] ሌሎች መንገድ ሰሪወችንም እጅግ ይረዳ ነበር። ደብተራ ዘነብ እንዲህ ሲል ይዘግባል፡ ቴዎድሮስ ቀደምት የተንሰራፋውን የባሪያ ንግድ ስርዓት ያጠቃ ንጉስ ነበር [50] ። በዚህ ወቅት ባሪያ መሸጥም ሆነ መለወጥ እንዲሁም ማጓጓዝን የሚያግዱ ብዙ ድንጋጌወችን ንጉሱ በማወጅ ቀደምት የባርነት ስርዓት ተቃዋሚ ንጉስ ሆነ። [29] ለምሳሌ ጎጃም፣ ባሶ ውስጥ ባደረገው ዘመቻ በገበያው የተገኙ ባሪያወችን በነጻ ለቋል። ወሎ ውስጥ የተማረኩ ባሪያወች እንዳይሸጡ አግዷል። [50] ሆኖም ግን ከህጉ ውጭ በኮንትሮባንድ ውስጥ ለውስጥ በአገሪቷ ዳርቻወች ባሪያ መሸጡና መለወጡ አላቆመም። [29] ከባህል አንጻር የአማርኛ ስነ ጽሁፍ በኒሁን ንጉሥ ዘመን ማደግና መሻሻል አሳይቷል። ከፍተኛው የመንግስት ስራ በአማርኛ ይካሄድ ነበር።[50] ዜና መዋእላቸውን በአማርኛ ለመጀሚርያ ጊዜ ያስጻፉ ንጉሥ ነበሩ። [51] ፣ ከዚህ በፊት በ ግዕዝ ነበር። ከዚህ በኋላ አማርኛ የአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ሆነ። [52] ።ቴዎድሮስ ከግዕዝ ይልቅ ሰወች በሚረዱት አማርኛ መጽሃፍ ቅዱስ እንዲተረጎም አደርጉ።[48] የመጀመሪያው የጂዖግራፊያ መጽሃፍ በአማርኛ የታተመውም በኒሁ ንጉስ ዘመን ነበር። ህዝቡ ለጋብቻ ከፍተኛ ዋጋ እንዲሰጥም በጣም ጥረት አድርገዋል፣ እራሳቸውም በአንድ ሴት በመወሰን መሪ ምሳሌ ለመሆን ሞክረዋል። [48] ከቴዎድሮስ በፊት ይሰራበት የነበረውን ከወገብ በላይ እራቁት መሆን የአለባበስ ዘዴን በማስቀረት ሹሞች በጥሩ ሁኔታ እንዲለብሱ አድርገዋል። በአጠቃላይ ህዝቡ የሃይማኖትና የባህል ህጎችን አጥብቆ እንዲከተል ጥረት አድርገዋል። [48] ከአስተዳደር ስልት አንጻር ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ እስከፈጸሙት ድረስ የነበረውን አገሪቱን በማዕከላዊ ሃይል የማስተዳደር ስራ ጀምረዋል። በአዲሱ ስርዓት መሰረት የግብር እና የፍርድ ባለስልጣናት ከማዕከላዊ መንግስት ደመወዛቸውን እንዲያገኙ ተደረገ፣ ይህም በየቦታው የነበሩ ባላባቶችን የመፍለጥ የመቁረጥ ሃይል የቀነሰ ተግባር ነበር።[53] የሆኖ ሆኖ ንጉሡ የገዥውን መደብ ሙሉ በሙሉ አልቀየሩም፣ አንድ አንድ ገዥወች በነበሩበት እንዲቀጥሉ አድርገዋል። [43] ለምሳሌ የትግራይ ገዥ የነበሩት ደጅ አዝማች ሰባጋዲስ ዘር የሆኑትን ካሳ ምርጫ ን በትግራይ ሾሙ፣ እንዲሁም የንጉስ ሳህለ ስላሴ ዘር የሆኑትን ሃይለ ሚካኤል ን በመሾም በየቦታው የነበሩትን የሃይል ማዕከላት በነበሩበት እንዲጸኑ አድርገዋል። [43] በአንዳንድ ክፍሎች የራሳቸውን ዘመዶች ስልጣን ያወጡበት ሁኔታ ይገኛል፣ ለምሳሌ ራስ እንግዳን በጎጃም[54] ። ይህ ስርዓት በመጀመሪያ እጅግ የተሳካ ነበር ምክንያቱም በዘመነ መሳፍንት እንኳ ሳይቀር ጠንካራ ባላባቶች ለንጉሳዊው ስልጣን የመገዛት ባህርይ ያሳዩ ነበርና። ከሸዋ መርዕድ አዝማች ሃይለ ሚካኤል በየጊዜው ወደ ንጉሱ የጓዙ ነበር። ትግራይ ደግሞ ለንጉሱ ዋና የገቢ ምንጭ ነበር (200፣000 ማሪያ ቴሬሳ በአመት)፣ ከበጌምድር የሚያገኙት 50፣000 ማሪያ ቴሬሳ ብቻ ነበር።[54] ሆኖም ግን አንድ አንድ ጥቃቅን ባላባቶች አመጽ ለማስነሳት መመኮራቸው አልቀረም፣ ስለሆነም ንጉሱ ሰራዊቱን ማሻሻል እንዳለባቸው ተገነዘቡ። አጼ ቴዎድሮስ በራሳቸው እጅ እየቆፈሩና እያስቆፈሩ እንዲሁም በዲናሚት እይደለደሉ መንገድ ሲያሰሩ ዘመናዊ ሠራዊት ሠራዊቱ በፖለቲካው ውስጥ ባለው መሰረታዊ ተፅዕኖ ምክንያት ንጉስ ቴዎድሮስ በዚህ ክፍል ላይ ብዙ ትኩረት አድርገዋል። እራሳቸውን ከስሎሞኑ ስርወ መንግስት በመጀመሪያ የአገዛዛቸው ዘመን በማራቃቸው ብቸኛው ወደላይ የሚያወጣቸው መሰላል የውትድርና ብቃት እንደሆነ ጠንቅቀው ተረዱ። [54] አገራዊ ሠራዊቱን ለማጠናከርና ብሔራዊ አንድነትን እውን ለማድረግ፣ ዋልተር ፕላውዴን "ታላቁ ለውጥ" ያለውን አጼ ቴዎድሮስ አከናወኑ 9። ይህ ታላቅ ለውጥ በ3 አብይ ክፍሎች ላይ ያተኮረ ነበር፡ ፩.መዋቅር ፪.ዲሲፕሊንና ፫.ትጥቅ ናቸው። [54] እኒህ ለውጦች ከሞላ ጎደል የተወደዱና ለብዙ ድሎች ያበቃቸው ሲሆን ስልጣናቸውንም ለማንሰራፋት አይነተኛ ምክንያት ናቸው። እኒህ ለውጦች የአገሪቱ ዜጎች በ"አንጻራዊ ደህነነት" እንዲኖሩ ረድተዋል 9። ከመዋቅር አንጻር ከዘመነ መሳፍንት ሲወርድ የመጣውን የተከፋፈለ የባላባቶች ሰራዊትን በአንድ ብሔራዊ ሰራዊት ቀይረዋል። [53] ከተለያዩ ክፍለ ሃገሮች የመጡት ወታደሮች በንጉሠ ነገሥቱ በተዋቀረ አንድ የጦር ክፍል ስር ተደራጁ። [55] እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ ሰራዊት የሚሰራበት የ አስር አለቃ ፣ የ ሀምሳ አለቃ ና መሰል ማዕረጎች የተፈጠሩት በዚሁ ዘመን ነበር።[55] ንጉሡን የሚያጅቡትን ወታደሮች ቁጥር በመቀነስ፣ የዚህን ክፍል እዳተኝነትን ቀነሱ። [55] ወታደሮች ከዚህ በኋላ ቋሚ ደሞዝ ተቆርጦላቸው ስለሚተዳደሩ የሰፈሩበትን ቦታ መበዝበዝ በህግ ተከለከሉ።[55] በ ፊውዳሉ ስርዓት ወታደሮች በረገጡበት ቦታ ያሉ ገበሬወች ምግብና መኝታ እንዲያቀርቡ ይገደደዱ ነበር።[53] ይህ ሁኔታ በንጉሠ ነገሥቱ አጥብቆ የተከለከለ ነበር። [55] ይህን በሚያሳይ መልኩ ለምሳሌ አንድ ገበሬ የ12 ጫጩት እናት የሆነችን ዶሮ እንዲያርድ በንጉሱ ወታደር ይገደዳል። ድርጊቱ ንጉሱ ድረስ ቀርቦ በዳኝነት ከታየ በኋላ ወታደሩ በሞት ሲቀጣ ገብሬው ላም ተሰጥቶት እንዲሄድ ተደረገ። [53] በዚህ ዘመን ወታደሮች ቀለብ የሚባል ገቢ ከንጉሱ የሚሰፈርላቸው ሲሆን ከዚህ ውጭ ማንም ገበሬውን ያስገደደ ወታደር ከፍተኛ ቅጣት ይቀጣ ነበር።[53] ንጉሡ በሠራዊቱ ዘንድ እንደ ብረት የጠነከረ ዲሲፕሊን ለማቋቋም ሞክረዋል። [55] ለምሳሌ ወደ ወሎ ባደረጉት ዘመቻ ያለትዕዛዝ ጦርነት የሚገቡ ወታደሮች ያለርህራሄ ይገደሉ ነበር።[55] በሸዋው ዘመቻ እርስ በርስ ሽኩቻ ያሳዩ ወታደሮች በሙሉ በጥይት ተደብድበዋል። [55] ባህሩ ዘውዴ እኒህ ድርጊቶች ደም መፋሰሱ እንዲባባስ በማድረግ ብዙ ጥቅም አላመጡም ያላል።[55] ሆኖም ወታደሩ በራሱ ፈቃድ ብዙ ጥፋት እንዳያደርግ ረድቷል። [53] አብዛኛው የአጼ ቴዎድሮስ ሰራዊት ጦር መሳሪያ ከጦር ሜዳ የተማረከ ነበር [55] ። ቆይተው ግን ከአውሮጳ ቴክኖሎጂ በማስመጣት በኢትዮጵያ ምድር ላይ የመሳሪያ ማምረቻ ለማቋቋም ሞክረዋል። [55] ለዚህ ተግባራቸው እንዲረዳ የአውሮጳ ሚስዮኖችን በጋፋት፣ ደብረታቦር ሰብስበው መሳሪያ እንዲሰሩ አደርጉ ከዚህ ትይዩ ትምህርት ቤት በማቋቋም ጥበቡን ተማሪወች እንዲቀስሙ አደረጉ።[50] የመጀመሪያው ትክክለኛ የመሳሪያ ዝርዝር የተገኘው ከመቅደላ በአጼ ቴዎድሮስ ዘመን ነበር፡ 15 መድፎች ፣ 7 አዳፍኔዎች ፣ 11፣063 ጠመንጃዎች፣ 875 ሽጉጦች ፣ 481 ሳንጃዎችና ጥይቶችን ያጠቃልላል።[50] ውስጣዊ ተቃውሞና ግርግር አስቸጋሪው የኢትዮጵያ ቤ/ክርስቲያንን ሽግግር አጼ ቴዎድሮስ ያሰቡትን ለውጥ በተግባር ለመፈጸም ቋሚ የተረጋጋ የመዋዕለ ንዋይ መሰረት እንደሚያስፈልጋቸው ተገነዘቡ [56] ። በዘመኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክርስቲያን ከሁሉ ግምባር ቀደም ሃብታም ድርጅት ነበር።[57] አጼ ቴዎድሮስ የ ተዋህዶ ን ትምህርት ስለደገፉና አቡነ ሰላማ ም ይህ ጉዳይ ስላስደስታቸው በቴዎድሮስና በቤተክርስቲያን መካከል የነበረው ግንኙነት በመጀመሪያው የንጉሱ ዘመን መልካም ነበር። 17፣[56] ። በፖለቲካው አንድነት እንደሚፈልጉ ሁሉ በሃይማኖቱም አንድነትን ማየት ይፈልጉ ነበር።[56] የቴዎድሮስ መስቀል በዘመኑ ቴዎድሮስ እጅግ ሃይማኖተኛና የጋብቻን አንድ ለአንድ መጽናት የሚያክብሩ፣ የቤተክርስቲያን ክፍፍልን የሚቃወሙና እንዲሁም "ከክርስቶስ ውጭ እኔ ባዶ ነኝ" የሚሉ መሪ ነበሩ። በዚህ ምክንያት ከቤተ ከርስቲያን ጋር የነበረው የመጀመሪያ ግንኙነት ጥሩ የነበር ቢሆንም የቴዎድሮስና የአቡነ ሰላማ (እንዲሁም መላው የቤተክርስቲያኒቱ ቀሳውስት) ግንኙነት ቀስ እያለ እየተበላሸ ሄደ፣ ለዚህም ምክንያቱ ቤተክርስቲያኒቱን ለመለወጥ ያደረጉት አንድ አንድ ተግባር ነበር። ከቤተክርስቲያን ጋር ያለው ጥል በተለይ ፈጦ የወጣው የመሬት ይዞታን ለማሻሻል ያቀዱትን ሃሳብ ባሰውቁ ጊዜ ነበር። ለምሳሌ በ1848 ዓ.ም. ቀሳውስቱን ሰብስበው እንዲህ አሏቸው፡" እኔስ ምን ልብላ፣ ወታደሮቸስ? ግማሹን መሬት የመስቀል መሬት ብላችሁ ትወስዳላችሁ፣ ግማጩን ደግሞ ሪምና ገዳም 19፣[56] "። መሬቱን ለግብር ከፋይ ገብሬወች በማከፋፈል አገሪቱ ላይ ሊያካሂዱት ላሰቡት መሻሻል ወጭ ቋሚ ገቢ ለማግኘት ነበር። 1852 ላይ የመሬት የዞታ ማሻሻሉ ስራ በከፊልም ቢሆን ተከናወነ በዚህ ወቅት የቤ/ክርስቲያን መሬት በከፊል ለገበሬወች አከፈፋሉ።[58][56] ይህም በፍካሬ እየሱስ ላይ እንደተጠቀሰውና በእውን እንደነበረው ቀዳማዊ ቴዎድሮስ ስራ ነበር። በዚሁ አመት የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ከሁለት ቄሶችና ሶስት ዲያቆኖች በላይ እንዳይሆን ደነገጉ። [57][59] ከዚህም በላይ ደብተራነትን ከነአካቴው ለማጥፋት እንዳሰቡ ገለጹ። [59] ብዙ ደብሮች ከአስፈላጊ በላይ የሰው ሃይል ሲኖራቸው ነገር ግን ከግብር ነጻ ስለሆኑ የአገሪቱን ሃብት በከንቱ ያባክናሉ፣ ይህም አጼ ቴዎድሮስ አጥብቀው የተቃወሙት ስርዓት ነበር [60] ። ንጉሱ በወግ አጥባቂ ቀሳውስት ላይ ያላቸውን መጸታዊ ንቀት ሲገልጹ "ዱላቸውን ከመንደር መንደር እየጎተቱ ያለ ምንም ስራ የሚያውደለድሉ [61] " ይሏቸው ነበር። ሆኖም ቀሳውስቱ አርፈው የንጉሱ ተጠቂ መሆን አልቻሉም። በ1856 ዓ.ም. አቡነ ሰላማ እስከታሰሩ ድረስ ቤተክርስቲያኗ በአቡኑ መሪነት በንጉሱ ላይ ተቃውሞ አነሳች። [59] የቀሳውስቱ ዋና ማጥቂያ ስልት የንጉሱን "ነጣቂ"እንጂ "ህጋዊ ንጉስ" አለመሆን ማስታወስ ነበር።[57] የአጼ ቴዎድሮስ ሰራዊት ሲገሰግስ ውስጣዊ ግርግር የጎጥ አመጾች አስተዳደሩ ማዕከላዊ እየሆነ በሄደ ቁጥር የሃይላቸውን መሸርሸር የተረዱት የየጎጡ ባላባቶች ጦር ማንሳት ጀመሩ። የጎጃሙ ተዳላ ጓሉ፣ የወልቃይቱ ጢሶ ጎበዜ ፣ የሸዋወቹ ሰይፉ ሳህለስላሴ ና በዛብህ፣ የወሎዎቹ ደጃዝማች ሊበን አምዴ አመጽ አስነሱ።[62] በዋግሹም ጎበዜ የሚመራው የላስታ ጦር ጭራሽ ጎንደርን ለጥቂት ጊዜ ለመቆጣጠር ቻለ፣ ሰሜን ና ወገራ ም እንዲሁ ለአመጽ ተነሳሱ።[63] በመጀመሪያዎቹ የቴዎድሮስ ዘመናት የትግራዩ ደጃዝማች ካሳ ምርጫ ከሌሎቹ ባላባቶች በተለየ መልኩ ለአዲሱ ንጉስ ክብርና ታማኝነት ያሳይ ነበር።[64] በዚህ ወቅት የንጉሠ ነገሥቱ ጦር ሰራዊት ከሁሉ የተሻለ ስለነበር ሁሉኑም አመጽ በሃይል ለመቆጣጠር ቻለ።[65] የንጉሱን ሰራዊት መመገብ የሰለቻቸው ገበሬወች ግን ባንጻሩ ለአመጹ መበረታታት አስተዋጾ አደረጉ።[57] በየጊዜው የሚካሄደው ዘመቻም ለድህነትና ለህዝብ ማለቅ ከፍተኛ አስተዋጾ እያደረገ መጣ። [57] በዚህ መካከል የአገሪቱን ብሄራዊ መከላከያ ለማጠናከር አጼው ያወጡት የግብር ስልት አዲሱን ስርዓት ከገበሬወች ዘንድ ሙሉ በሙሉ ለየው ። [66] እኒህ ተቃውሞወች ከተራ ሰውነት ተነስተው አገሪቱን ለማሳደግና ፍትሃዊ ስርዓት ለማስፈን በሞከሩት አጼው ዘንድ አሳዛኝ ነበሩ። [57] በ1850ወቹ ንግሡ በዛ ያሉ አመጾችን በትግሬና በበጌምድር ለማፈን ቻሉ። ታህሳስ 1852 የሰሜኑ ክፍል አመጽ ዋና አዛዥ የነበረውን አገው ንጉሴ ን ወግተው ገደሉ። በ1857 መቅደላ ያደገው ወጣቱ ምኒሊክ ምንም እንኳ ንጉሱን ቢወድም ከመቅደላ አምልጦ ሸዋ በመግባት የግዛቱን ኢ-ጥገኝነት አወጀ።[67] ጎበዝ የተሰኘው የድሮው የላስታ መሪ ልጅ የላስታ መሪ በመሆን ስልጣኑን አወጀ፣ ትግራይም እንዲሁ በካሳ ምርጫ ስር ወደቀ።[67] ከ1858-59 ንጉሱ የጢሶ ጎበዜን ጦር በጎንደርና የ ተድላ ጓሉን ሃይሎች በጎጃም ለመቆጣጠር ብዙ ዘመቻወን አካሄዱ። በነዚህ ዘመቻወች ብዙ ወታደሮች ከንጉሱ እየከዱ አመለጡ። [68] በ1859 በንጉሱ ሙሉ ቁጥጥር ስር የነበረ አካባቢ ቢኖር በጌምድር ነበር 72። ጥቅምት 1860 ላይ ቴዎድሮስ ደብረታቦርን አቃጥለው ወደ መቅደላ በመሄድ እስከ እለተ ሞታቸው ድረስ ኑሮአቸውን በዚያ አደረጉ።[69] አጼ ቴዎድሮስ ያቀዱት እና ለመተግብረ የፈለጉት አገር በተግባር መስራት አልቻለም። [70] ንጉሱ የሃገራቸውን ህዝብ ምንጊዜም ላለመበደል ቢፈልጉም የፖለቲካውንና የፍትሃዊ ስርዓቱን ቅጥ ለማስተካከል አይነተኛ አማራጭ የወታደራዊ ሃይል በመሆኑ ብቻ ጦር መክፈት ግድ እንዳላቸው ሳይናገሩ አላለፉም። [70] ከባህር ጠረፍ በርቀት የመሰረቱት መቅደላም እንደ ትግራይና ሸዋ በፍጥነት ዘመናዊ ጦር መሳሪያን ሊያገኝ አልቻለም። [46] የንጉሱ በጣም ጠንካራ ወታደራዊ ዲሲፕሊን(ግብረ ገብ) ብዙዎቹ ወታደሮች እንዲከዱ አደረገ። [62] ባንድ ወቅት የአጼው ሰራዊት ከመቶ ሺህ በላይ የነበር ሲሆን በ1858 ከአስር ሺህ ብዙ አይበልጥም ነበር።[62] በቁም እስር የነበሩት አቡነ ሰላማ በ1859 ሲሞቱ አጠቃላይ ክርስቲያኑ ክፍል በቴዎድሮስ ላይ ከፍተኛ ጥላቻን አሳየ። [71] በአገሪቱ የነበረው የተቃውሞ መጠን ከማየሉ የተነሳ አጼ ቴዎድሮስ ከደብረታቦር መቅደላ ባሰሩት መንገድ እንኳ ሳይቀር በሰላም መንቀሳቀስ አልቻሉም።[62] በ1859 መጨረሻ ይሄው መንገድ እጅግ አደገኛ እየሆነ በመምጣቱ ንጉሰ ነገስቱ በመቅደላ ሙሉ በሙሉ ተወሰኑ። [62] የሃይማኖት ግርግር በንጉሱና በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን መካከል የነበረው ግንኙነት እየተበላሸ ቢሄድም ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር የነበርው ግንኙነት የከፋ ነበር። በመጀመሪያ፣ ፕሮቴስታንቶች፣ ካቶሊኮች፣ እስላሞች፣ እና ፈላሻወች የሃይማኖት ነጻነት ተፈቅዶላቸው ይኖሩ ነበር። [58] ሆኖም የአገሪቱ ውስጣዊ ሁኔታን መበላሸት ተከተሎ ፣ ሚሲዮኖችና ሌሎች ሃይማኖቶች ጫና እየበዛባቸው ሄደ። ንጉሰ ነገሥቱ ለአገሪቱ አዲስ አይነት ቴክኖሎጂን ለማስተዋወቅ ከነበራቸው ፍላጎት አንጻር በንግሱና በፕሮቴስታንት ሚሲዮኖች የነገረው የመጀመሪያ ግንኙነት መልካም ነበር። [31] እንደ ካቶሊኮች የግለሰቦችን ሃይማኖት ለመቀየር ሳይሆን የቤተክርስቲያኒቱን ውስጣዊ አሰራር ለመቀየር ስለሚፈልጉ ፕሮቴስታንቶች በንጉሱ ዘንድ በጥሩ አይን ይታዩ ነበር። [72] በ1847 ከስዊዘርላንድ የተላኩ ወጣት እጅ ጥበብ አዋቂ የፕሮቴስታንት ሚስዮኖችን ለማስተናገድ ንጉሱ ቃል ገቡ። [73] እኒህ ሚስዮኖች በአማርኛ የታተሙ የሃይማኖት መጽሃፍትን ይዘው የመጡ ሲሆን፣ ቴዎድሮስ ግን የፈለጉት የጦር መሳሪያወችን ነበር፣ ሆኖም ቀረ ግን ንጉሱ ለኒህ ሚሲዮኖች ጥሩ አቀባበል አደረጉላቸው።[73] በንጉሱ ፈቃድ መሰረት እኒህ ሚሲዮኖች የሰበካ ስራቸው ክርስቲያን ባልሆነው ክፍል ብቻ እንዲወስኑ ሲደረግ፣ የእጅ ጥበብ ስራቸው ግን ንጉሱ በፈለጉት መጠን ጥራት አልነበረውም።[72] ሚሲዮኖቹ የእጅ ጥበብ አዋቂ ቢሆኑም ንጉሱ ላሰማራቸው ስራ ግን የተለማመዱ አልነበሩም። [73] በ1853 አካባቢ በንጉሱ አግባቢነት አንስተኛ አዳፍኔ ሰርተው ሲያቀርቡ ወዲያው መድፍ እንዲሰሩ ከንጉሱ ዘንድ ጥያቄ ቀረበላቸው። [74] ምንም እንኳ እኒህ ነገሮች ንጉሱን ቢያስደስቱም ፕሮቴስታንቶች ሌሎች አውሮጳውያን ላይ ይደርስ ከነበረው ጭቆና ተቋዳሽ ከመሆን አልተረፉም። [72] ለዚህ ምክንያቱ ለምሳሌ የፕሮቴስታንት ሰባኪ የነበረውን ሄንሪ ስተርን ንግሱ ላይ የሚናገራቸው በጊዜው የሚያስቆጣ ንግግር ይጠቀሳል። [72] ለምሳሌ ሄነሪ ስተርን ባሳተመው መጽሃፉ ላይ የንጉሱ እናት በጣም ደሃ ከመሆኗ የተነሳ "ኮሶ ትሸጥ ነበር" ይህም በንጉሱ ዘንድ እጅግ የሚያስቆጣ ነበር።[75] ስለሆነም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ብዙዎቹ ሚሲዮኖች (ከሄንሪ ስተርን ጨምሮ) በመቅደላ ታሰሩ። [72] በአንጻሩ ከካቶሊኮች ጋር የነበረው ግንኙነት ምንጊዜም ብልሹ ነበር፣ ለዚህም ምክንያቱ ሁለት ነበር፦ ፩) ካቶሊኮች በስሜኑ በኩል የነበራቸው ተጽዕኖ የንጉሱን ስልጣን የሚገዳደር ነበር ፪) ከፈረንሳይ ሃይል ጋር የነበራቸው የጠበቀ ግንኙነት ነበር [76] ። ጃኮቢና ጉስቲኖ የተሰኙ ካቶሊኮች በአንድ ወገን አቡነ ሰላማ በሌላ ወገን ባስነሱት የግል ጥል ምክንያት አጼ ቴዎድሮስ ካቶሊኮቹን በ1846 ከአገር ሲያባርሩ ኢትዮጵያዊ ደጋፊወቻቸውን እንዲታሰሩ አደርጉ።[76] በዚህ ምክንያት ካቶሊኮች፣ በተለይ ፈረንሳይ ንጉሱን ከስልጣን ለማሰወገድ መዘጋጀት ጀመሩ።[76] አገው ንጉሴ የተሰኘው የ ሰሜን መሪ ንጉሱን ለመውጋት እና ዘመናዊ ጦር መሳሪያ በተለዋጭ ለማግኘት እንደሚፈልግ ሲሰማ በፓሪስ ደስታ ሆነ።[72][31] አገው ንጉሴ ከካቶሊኮችና ከፈረንሳይ ባገኘው ድጋፍ መሰረት ሃይሉን በትግራይ ማጠናክር ጀመረ። [58] ሆኖም በ1852 ላይ በጦርነት ተሸንፎ ተገደለ።[72] አጼ ቴዎድሮስ ከመስሊሞች ጋር የነበራቸው ግንኙነት ለየት ያለ ነበር። ምንም እንኳ ሙስሊሞች ሃይማኖታቸውን በነጻነት እንዲያካሂዱ ንጉሱ ቢፈቅዱም ወደ ኦሮቶዶክስ ክርስትና እንዲለወጡ ግን ይደግፉ ነበር። የአጼ ቴዎድሮስ አባት የተገደሉት በሱዳን መስሊሞች ቢሆንም ቅሉ የሃይማኖት ነጻነታቸው ግን እንደተጠበቀ እንዲቀጥል ፍላጎታቸው ነበር። ሆኖም በአገዛዛቸው መጨረሻ ከሙስሊሞች ጋር የነበረው ግንኙነት የሻከረ ነበር፣ ለዚህ ምክንያቱ ሁለት ነበር፤ አንደኛው የ ኦቶማን ግዛት በቀይ ባህር መንሰራፋትና የሙስሊም ነጋዴወች ባሪያ ንግድ ነበር።[71] ባሪያ ንግድ በንጉሠ ነገሥቱ አዋጅ መሰረት ወንጀል ነበር። ስለሆነም በሚያዚያ 1856 ዓ.ም. እስልምና በግዛቱ ሲከለከል፣ ይህን ጉዳይ በመቃወም ስራ ያቆሙ ሙስሊሞችኑን ንጉሱ ይቀጡ ነበር።[71] ዲፕሎማሲና የአውሮጳውያን መታሰር የክርስቲያን ትብብር ህልም ቀይ ባህር ላይ የተነሰራፋው የኦቶማን ቱርክ ግዛት ለአጼ ቴዎድሮስ ዋና አደጋ ነበር የንጉሰ ነገስቱን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በ፫ ዋና ኩነቶች ተጽዕኖ ደርሶበታል፦ በቴዎድሮስ ዘመን አገሪቱ በቱርክና ግብጽ ሃይሎች የተከበበች ስለነበር ከዚህ መከበብ እራስን ለማዳን ከአውሮጳውያን ጋር የክርስትና ትብብር ለመፍጠር ንጉሰ ነገሥቱ ፈቃድ ማሳየት ከአውሮጳ የመጡ መናኛ/ሰነፍ ዲፕሎማቶች በንጉሱ ዲፕሎማሳዊ ጥረት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማድረግ በተለይ በብሪታኒያ ዲፕሎማቶች የተሰሩ «ማመን የሚያስቸግሩ ስህተቶችና መልዕክት አለማድረስ»[77] ናቸው። አጼ ቴዎድሮስ በግል ደረጃ ከነበራቸው የጠበቀ ሃይማኖታዊ እይታ ውጭ ስለ ዘመኑ የአውሮጳ እርስ በርስ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረትና ግንኙነት የጠለቀ መረጃ አልነበራቸውም። የአጼ ቴዎድሮስ የዲፕሎማሲ ደብዳቤወች እንደሚያሳዩት ለንጉሱ የሃይማኖት ጉዳይ ለዲፕሎማሲው ጥረት ዋና ጉዳይ ነበር፣ ከአውሮጳውያን ጋር ትብብር በመፍጠር የግብጽን እስላማዊ ሃይል ለመመከት የነበራቸውን ፍላጎት የዚሁ ሃይማኖታዊ ዲፕሎማሲ አካል ነበር።[78] ስለሆነም ክርስቲያን እንግሊዝ ከሙስሊም ቱርክ ጋር ወግና ክርስቲያን ሩሲያን በክሪሚያ ጦርነት እንደወጋች ሲሰሙ ለንጉሱ እጅግ እንግዳ ሁኔታ ነበር። በተረፈ የዘመኑ የአውሮጳ ቤተመንግስቶች በዘረኛነት የተሸበቡ ስለነበር ለነሱ «አንድ የአፍሪቃ ንጉስ ከተራ የጎሳ አለቃነት ባለፈ አይታይም ነበር» [79] ፤ ይህም እውነታ ለንጉሱ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የተደበቀ ነበር። ከውጫዊ አደጋ በተረፈ ውስጣዊ አመጽ ሲነሳም እንዲሁ ዲፕሎማሲን በመጠቀም ብሄራዊ ድጋፍ ለማግኝገት ንጉሱ ሞክረዋል4። ከአውሮጳ አገሮች የቴክኖሎጂ እና የወታደራዊ ድጋፍን መጠየቅ የዚህ ዲፕሎማሲ አካል ነበር።[71] የፈረንሳዮች መልስ ንጉሱ የካቶሊክ ሚሲዮኖች በአገሪቱ እንዲዘዋወሩ ከፈቀዱ ድጋፉን እንደሚሰጡ ነበር፣ ሆኖም ግን ይህን ጉዳይ ንጉሱ እንደማይፈቅዱ አስቀድሞ የታወቀ ስለነበር «ድጋፍ ከመከልከል» ጋር ምንም ልዩነት አልነበረውም።[80] ሩሲያኖች በክሪሚያ ጦርነት ተዳክመው ስለነበር ለንጉሱ ድጋፍ መላክ አልቻሉም።[80] በዚህ ምክንያት በክሪሚያው ጦርነት መነሳት የተበሳጩት ቴዎድሮስ። [80] በኋላ ያሰሩትን መድፍ ሴባስቶፖል በማለት ለሩሲያኖቹ ጦር ሜዳ ማስታወሻ ሰየሙ። [80] በዚህ ትይዩ ከሙስሊም አገሮች ጋር፣ በተለይ ከግብጽ ጋር፣ የነበረው ግንኙነት እየተበላሸ ሄደ። በ1848፣ የ አሌክሳንድሪያ ፓትሪያርክ ቄርሎስ ለጥየቃ ወደኢትዮጵያ በመጡበት ጊዜ አቡነ ሰላማ ፣ በንጉሱ ስም፣ ግብጽ ወታደራዊ እርዳታ እንድታደርግ ጠየቁ። የቆብጡ ፓትሪያርክም የንጉሰ ነገሥቱ አምባሳደር በካይሮ ለመሆንና ጥያቄውን ለማቅረብ ተስማሙ[81] ። ሆኖም ይህ ጉዳይ ንጉሱ ሳይሰሙ በሁለቱ የሃይማኖት መሪወች መካከል የተከናወነ ስለነበር ንጉሰ ነገሥቱ የተደረገውን ጉዳይ ሲሰሙ ሁለቱንም ግብጻውያን እስር ቤት ከተቷቸው። [78] በዚ ሁኔታ ነገሮች ቀጥለው ፓትሪያርክ ቄርሎስ ህዳር 1849 ላይ ሲፈቱ አቡነ ሰላማ በታሰሩበት 1859 አረፉ።[82] ከዚህ ጎን ዋድ ንምር ለተሰኘው ሱዳናዊ የ ማክ ንምር ልጅ ንጉሰ ነገስቱ እርዳታ ያደርጉ ነበር። ይሄ ሰውና አባቱ በግብጾች ላይ የሚካሄድ ሱዳናዊ አመጽ መሪ ነበሩ። ስለሆነም የአጼ ቴዎድሮስ ድጋፍ በአካባቢው የነበርውን የግብጽን ሃይል ለመነቅነቅ ከነበረ አቅድ የመነጨ ነበር።[78] ይሁንና ከምዕራቡ የአገሪቱ ክፍል ከሚመጣው የግብጾች ጸብ ይልቅ ቴዎድሮስን ከአውሮጳውያን ጋር ለመስራት የገፋፋቸው በምስራቅ ከቀይ ባህር የሚመነጨው የቱርኮች አደጋ ነበር።[78] የቴዎድሮስ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በአብዛኞቹ አውሮጳውያን ሃይሎች ዘንድ አወንታዊ ምላሽ አለማግኘቱን ተከትሉ ንጉሱ ከእንግሊዞች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ለመፍጠር ፈቀዱ።[78] በተለይ ለዚህ ፍላጎት ዋና መንስኤ የነበረው ሊቀ መኩዋስ ብለው ከሰየሙት ሊቀመኳስ ጆህን ቤል እና የእንግሊዝ የመጀመሪያ ቆንጽላ በኢትዮጵያ ዋልተር ፕላውዴን ጋር የነበራቸው ቅርበት ነበር።[78] በኒህ ሁለት ሰወች ምክንያት ንጉሱ ለብሪታንያ ከፍተኛ አድናቆትና ክብር የነበራቸው ሲሆን ነገር ግን ከእንግሊዞች ዘንድ ተገልባጭ ፍቅርና አድናቆት አልነበረም። [78] የሆነው ሆኖ በመጨረሻ ንጉሱ የጠበቀ ግንኙነት ለመፍጠር የፈለጉት አገር ዋና ጠላታቸውና የመውደቃቸው ምክንያት ሆኖ አረፈው። የእንግሊዝ ዲፕሎማሲ መበላሸት ጥቅምት 29፣ 1854 ላይ አጼ ቴዎድሮስ ሁለት ተመሳሳይ ደብዳቤወችን ለእንግሊዟ ንግስት ቪክቶሪያ ና ለፈረንሳዩ ናፖሊዮን ሳልሳዊ ላኩ። የደብዳቤያቸው ፍሬ ነገር የቱርኮች በኢትዮጵያ ግዛት መኖርን የሚቃወምና እነርሱን ከኢትዮጵያ ምድር ለማባረር ድጋፍ እንዲሰጡ ነበር። [83] ደብዳቤው በ1854 የእንግሊዝ ቆንጽላ በኢትዮጵያ ተብሎ በተሾመው ካፕቴን ካሜሮን አማካኘት የተላከ ነበር። በዚሁ ደብዳቤ ንጉሠ ነገሥቱ ጆን ቤልና ዋልተር ፕላውዴን ለንጉሱ የገቡትን ቃል አስታውሶ ንግስት ቪክቶሪያ የንጉስ "ታላቅ ንግስት" እንደሆነችና "የክርስቲያኖች ወዳጅ" እንደሆነች ያስታውሳል። [83] በዚህ ምክንያት እንግሊዝን እንደሚወዱ በደብዳቤው አስፍረዋል። [83] ከዚህ በተጨማሪ የቱርኮች በኢትዮጵያ ባህር ወደብ ላይ መንሰራፋት በቀይ ባህርል ላይ ጉዞ እንዳያደርጉ የሚከለክልና አምባሳደርም እንዳይልኩ ያደረጋቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።[84] ከአውሮጳዊ እስረኞቹ ውስጥ ጥር 12፣ 1854 ላይ የቴዎድሮስ ደብዳቤ ለንድን ቢደረሰም። [84] የታቀደውን አላማ አልፈጸመም። ለዚህ ምክ