አባል:Shenkut Ayele

ከውክፔዲያ
                                                         አማራ ከእምነት መጠሪያነት እስከ ብሔር መጠሪያነት ያለዉ የትርጉም ሂደት ፤ ( 213.55.106.166)
                                                    ዋናዉን /ኦርጅናል/ ሰነድ ለማንበብ የሚከተለውን ዌብሳይት ይጫኑ 
                     http://www.iwooket.com/wp-content/uploads/2012/09/The-Concept-of-Amhara-from-religious-name-to-ethinic-name.pdf 

አማራ ማለት ምን ማለት ነው? የተለያዩ ሰዎች የራሳቸውን መልስ ሊሰጡ ሲሞክሩ ይስተዋላል። አማራ የሚለው ቃል መነሻው የተለያየ እነደሆነ ለማብራራት የሚሞክሩ ወገኖች አሉ። ለምሳሌ አማራ ማለት ያማረ፣ የተዋበ እያሉ ለማብራራት የሚሞክሩ ወገኖች አሉ። ሁለተኞቹ ወገኖች ደግሞ አማራ ማለት በተራራ ላይ የሚኖር ህዝብ ማለት ነው ሲሉ ትንታኔ ይሰጣሉ። ከእነዚህ ወገኖች ውስጥ በታሪክ አጋጣሚ አገር እንዲመሩ ያስቀመጣቸው መንግስቱ ሀይለማሪያም አንዱ ናቸው።

ይሄን የመንግስቱን ንግግር እንደቁም ነገር ወስደው አማራ ማለት በተራራ ላይ የሚኖር ህዝብ ነው ሲሉ የሚያነበንቡ ሰዎችም ሞልተውናል። መንግስቱ ሀይለማሪያም ምናልባት አማራ ማለት በተራራ ላይ የሚኖር ሀዝብ ነው ሲሉ የተናገሩት አንድም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተራራ ላይ ስለሚኖር በኢትዮጵያ ውስጥ በተራራ ላይ የማይኖር ህዝብ ስለሌለ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድ ስለሆነ ኢትዮጵያዊ ሁሉ አንድ ነው በማለት የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ አስበው ሊሆን ይችላል።

አንድም ሰዉዬዉ ኮሚኒስት ናቸዉና አማራ የሚለዉን ታሪክ ከክርስትና ታሪክ ጋር ያለዉን ቁርኝት በማላቀቅ አማራ የሚለዉን ከተራራ ጋር ብቻ በማገናኘት የሚነሳባቸዉን የአማራ ህዝብ ጨቋኝ ነዉ የሚለዉን የብሄር ሙግት ጥያቄ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ በትንታኔያቸዉ ክርስትናዉንም አስቀረተዉ አማራ የሚባል ጨቋኝ መደብ አለ እያሉ የሚከሱዋቸዉን ተዋጊዎችም አፍ ለማሲያዝ አስበዉ የተናገሩት ሊሆን ይችላል። አንድም ሰዉዬዉ ወታደር ናቸዉና አማራ ማለት ምን ማለት ነዉ የሚለዉን ጥያቄ ለመመለስ ሙሉ መረጃ ስላጡ የተናገሩት ጉዳይ ሊሆን ይችላል። በዚያም ተባለ በዚያ አማራ ተራራ ላይ የሚኖር ህዝብ ነዉ የሚለዉን ሀሳብ አጥልቀዉና አግዝፈዉ ያስተጋቡት መንግስቱ ሀይለማሪያም ናቸዉ። ሆኖም ተራራ የሚለዉ ቃል አማራ ከሚለዉ ቃል ጋር እንዴት እንደሚገናኝ ወደ ኋላ ላይ እናያለን።

በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሃዲስ ኪዳን እንደሚነበበዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ከአብርሃም እስከ ሙሴ ፣ ከሙሴ እስከ ሰሎሞን ከሰሎሞን እስከ ኢዬሱስ ክርስቶስ መወለድ ድረስ በእግዚብሄር የሚያምን እና የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ ሲጠባበቅ የነበረ ህዝብ ነዉ። ይሄን በምሳሌ ለማስረዳት ካስፈለገ የሙሴን እና የኢትዮጵያዊዉ ካህን ዮቶርን የመጽሀፍ ቅዱስ ታሪክ ማንበብ ይገባል። ኢትዮጵያዊዉ ዮቶር ለሙሴ ሴት ልጁን ዳረለተ። ይሄ ኢትዮጵያዊ ዮቶር ካህን ነበር። ስለሆነም ሙሴ ከግብጽ የወጣዉን ህዝቡን በምን አይነት ሁኔታ ሊመራዉና ሊያስተዳዶረዉ እንደሚገባ የስራ አመራር ሳይንስን /ማኔጅመንት ሳይንስን/ ያስተምረዉ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም የካህኑ የዮቶር ወንድ ልጅ ደግሞ የቃል ኪዳኑ ታቦት ቦታ መሪ ሆኖ ታቦቱ የሚያርፍበትን ቦታ እየቀደመ ይመራና ይመርጥ ነበር። ዘጽአትን ያንብቡ።


በብሉይ ኪዳን እንደዮቶር በመሳሰሉ ካህናት መሪዎች ሲመራ የኖረዉ የኢትዮጵያ ህዝብ በሃዲስ ኪዳን ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስን ከአለም ህዝብ ቀድሞ ለመቀበል ዋና ተሰላፊ ሆነ። አማራ የሚል ቃል በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥ እንዴት እንደተነሳ ወደ ሚያብራራልን የታሪክ ክፍል ይዞልን የሚዘልቀዉም ይሄዉ የክርስትና እምነት ታሪክ ጉዳዮ ነዉ። ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተወለደ እና እንደ ተሰቀለ በ30ዎቹና በ40ቹ አመታት ዉስጥ /በአንደኛዉ ክፍለ ዘመን/ ጃንደረባዉ ኢትዮጵያዊ ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ነበር /የሃዋርያት ስራ 8፡28-42 ተመልከት/። ወደ ኢየሩሳሌም የሄደዉም ቀድሞ ለሚያመልከዉ ለእስራኤል አምላክ ለመስገድ ነበር። ጃንደረባዉ ብቻ ሳይሆን በርካታ ኢትዮጵያኖችም በእስራኤል አምላክ ያምኑ ነበር። ማለትም በዚያን ሰአት የኢትዮጵያ ህዝብ በአብዛኛዉ የአይሁድ እምነት ተከታይ ነበር። ለዚህም ነዉ ንግስት ሳባ ሳትቀር ልቤ ጥበብን ናፍቃለችና ወደ ሰሎሞን ልሄድ እነሳለሁ ያለችዉ። ጥበብ ማለቷ የእግዚአብሄርን መንፈሳዊ ሚስጥር ጨምሮ የሚያብራራ የንግግር ፈሊጥ ነዉ። ጥበብን ፍለጋ ማለቷ የእግዚአብሄርን እምነት፣መንፈስ፣ እና ሚስጥር ፍለጋ ማለቷ ነዉ።/መጽሀፈ ጥበብን፣ መጽሃፈ ምሳሌን እና መጽሃፈ መክብብን ተመልከት።/


በርግጥ የጃንደረባዉ ወደ እስራኤል መሄድ የመንፈስ ቅዱስ ሚስጢርና ጥሪ እንዳለበት የአንደምታ መጽሃፍ ያብራራሉ። ለጊዜዉ የዚህን የመንፈስ ቅዱስ ጉዳይ በዚህ ላይ እናቁመዉና ወደተነሳንበት ታሪክ እንዝለቅ። ይህን ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ የብሉይ ኪዳን መጽሃፍ ሲያነብ ፊሊጶስ ቢያገኘዉ ስለክርስቶስ አስተዉሎቱ ምን ድረስ እንደሆነ ጥያቄ ጠዬቀዉ። ጃንደረባዉም እንደማያቅ/ምንም ግንዛቤ እንደሌለዉ መለሰ። ፊሊጶስም የኢዬሱስ ክርስቶስ አስተምህሮትን ሰበከለት። ማለትም ኢትዮጵያዊዉን ጃንደረባ ክርስቲያን አደረገዉ።


ይህ ጃንደረባ ወደ ሀገሩ ተመለሰ። የቀደመ ዘመን ክርስቲያኖች በመንፈስ የሚቃጠሉ፣ የእዉቀትም ሀብታሞች፣ ለክርስቶስ ፍቅር በሙሉ ልባቸዉ የተንበረከኩ ነበሩና ጃንደረባዉ ሀገር ቤት ሲመለስ የስብከት ስራዉን ቀጠለ። በነገራችን ላይ ይህ ጃንደረባ በዚያ ጊዜ የነበረዉ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣን ነበር። የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ እየጠበቁ በእስራኤል አምላክ ያምኑ ለነበሩ ኢትዮጵያዊያን የክርስትናን ነገር ሰበከላቸዉ። ጃንደረባዉ ባለስልጣንም ነበርና በርካታ ትልልቅና ሀያላን ባለስልጣኖች ክርስትናን ተቀበሉ። ሆኖም ሌሎች በርካታ ሀያላን እና ትልልቅ ባለስልጣኖች የለም አሁን የተወለደዉን ክርስቶስን አንቀበልም ሲሉ ተቃወሙ።


እናም የኢትዮጵያ ሰዉ እሁለት ተከፈለ። አንዱ ቡድን የአይሁድነትን እምነት ይዞ የቀጠለ ሌላዉ ቡድን ደግሞ ክርስትናን የተቀበለ። ክርስቶስን ለተቀበሉ ወገኖች መጽሃፍ ቅዱሰ አንድ የሚለዉ ሀይለ ቃል አለ። እናንተ በእግዚብሄር በክርሰቶስ በኢየሱስ አርነት ወጥታችኋል ፣ ነጻ ናችሁ የሚል። እናም ክርስትናን የተቀበሉ ወገኖች እኛ ነጻ ህዝቦች ነን ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ነጻ የወጣን ወገኖች ነን ሲሉ ለእራሳቸዉ ስም አወጡ። አም በሂብሩና በግእዝ ህዝብ ማለት ነዉ። ሐራ ማለት ደግሞ ነጻ/ከፍታ/ ማለት ነዉ። አንድ ላይ አምሐራ ማለት ነጻ ህዝብ ላይ ወይም በመንፈስ ከፍታ /የመንፈሳዊ ተራራ ላይ/ የተሳፈረ ህዝብ ማለት ነዉ። /የንቡረ እድ ኤርምያስ ከበደ መጽሃፍን ኢትዮጵያ የአለሙ መፋረጃ የሚለዉን ተመልከት/። እንዲሁም ኢትዮጵያ በመጽሃፍ ቅዱሰ የሚለዉን የሚኒልክ መጽሃፈን አጣቅስ/።

አቡነ ሽኖዳ “የመንፈስ አርነት” ተብሎ ወደ አማርኛ በተተረጎመ መጽሃፋቸዉ ስለተራራና መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ሰፊ ማብራሪያ ከመጽሃፍ ቅዱስ እያጣቀሱ አቅርበዋል። ተራራ የመንፈስ ነጻነት ምሳሌ ነዉ፣
በተራራ ላይ በምንቆምበትና በምንጸልይበት ጊዜ መንፈሳችን ከአካላችን በላይ ስለሚገዝፍ የመንፈስ ልዕልና ይኖረናል ሲሉ ያበራራሉ። በምሳሌነትም የኢየሱስ ክርስቶስን እና የሙሴን ወደ ተራራ ወጥቶ የመጸለይና የመጾም ሚስጥር ያነሳሉ። 

በዚህም ተራራ በመጽሃፍ ቅዱስ የመንፈስ ነጻነት ተደርጎ እንደሚወሰድና ከአይሁድነት እስከ ክርስትና ያሉ እምነቶች ተራራን/ከፍ ያለ ቦታን/ ለቤተ እግዚአበሄር መስሪያነት ለምን እንደሚመርጡት ያብራራሉ።

ይሄዉ የአቡነሸኖዳ ትንታኔ በሀገራችንም እዉነት በመሆኑ በክርስቲያኖች ቤተክርስቲያን አሰራር ላይ በብዛት ይንጸባረቃል። ያን ያስተዋለ ጸሃፊ ሚስጥሩ ሳይገባዉና በርካታ የክርስቲያን አካባቢዎች በተራራማ ቦታዎች ለሚገኙ አማራ/ክርስቲያን/ ማለት ተራራ የሚወድ ህዝበ ነዉ ስለዚህም በተራራ ላይ የሚኖር ህዝብ ነዉ ሲል የጻፈዉን ይዘዉ አንዳንድ ወገኖች አማራ ማለት በተራራ ላይ የሚኖር ህዝብ ነዉ የሚል ድምዳሜ ይሰጣሉ። መንግስቱ ሀይለማሪያምም ያስተጋቡት ይህችኛዋን ሀሳብ ነዉ።

ሆኖም በሀገራችን በኢትዮጵያ በክርሰትናና በአይሁድ እምነት መካከል ትግሉ ቀጠለ። አንዱ አንድ ጊዜ የበላይ ሲሆን ሌላ ጊዜ ደግሞ አንዱ ሲዳከም። በዚህ ሂደት ዉስጥ አንዱ ወገን በሌላዉ ላይ አሰቃቂ ግፍ ይፈጽም ነበር። ክርስቲያኖቹ በራሳቸዉ ወገን ላይ ግን ከአይሁድ እምነት አልላቀቅም ባለዉ ላይ ግፍ ሰርተዋል። የአይሁድ እምነት ተከታዮቹም ክርስቲያን በሆነዉ የራሳቸዉ ወገን ላይ ግፍ ሰርተዋል። በዚህ ሂደት ዉስጥ የተነሳቸዉ ዮዲት ጉዲትም ክርስቲያኖችን እስገድዳ የአይሁድ እምነት እንዲከተሉ አድርጋቸዋለች። ከዮዲት ጉዲት ያመለጡ ክርስቲያኖች ግማሾቹ ከአክሱም ወደ ደቡብ የቀሩት በአክሱም ዙሪያና ከአክሱም ወደ ሰሜን ተበታትነዋል።

የዮዲተ ጉልበት ምድር አንቀጥቅጥ ነበርና ክርሰቲያኖቹ በቦታም ሆነ በቋንቋ መደበቂያ ማዘጋጀት ነበረባቸዉ። በዚህ ሂደት ዉስጥ ከግእዝ ብዙም የመይርቁትና ከግእዝ የተወለዱት የአማርኛና የትግርኛ ቋንቋ በተለያዬ ስነምህዳር ተበታትኖ ይኖሩ በነበሩት ክርስቲያኖች እየዳበሩ እንደመጡና ወደተለያዬ ቋንቋ እንደሄዱ ታሪክ ያስረዳል። በሂደትም ሁለቱ ቋንቋዎች የራሳቸዉን ቅርጽ እዬያዙ መጡ። ከአንድ ህዝብ ሁለት ቋንቋ ተወለደ ማለት ነዉ።

ሌላዉ በግራኝ መሃመድ ዘመን የተፈጠረዉ የታሪክ ክስተትም በሀገራችን አለ። ግራኝ መሃመድ በመላ አገሪቱ ያሉ ቤተክርስቲያኖችን ሲያቃጥልና ሲያጠፋ አክሱም ጺዮንን እና ሌሎች ታላላቅ ታቦታትን ከግራኝ መሃመድ ለማሸሽ ከትግራይ፣ ከወሎ፣ከጎጃም፣ ከጎንደር፣ ከሸዋ፣ ከጉራጌ አካባቢና ከሌሎች የክርስቲያኖች መኖሪያ አካባቢ ክርስቲያኖች ወደ ዘዋይ ደሴት ተሰደዱ። እነዚህ ክርሰቲያኖች ግማሾቹ በዚያዉ በደሴቲቱ ላይ ሰፈረዉ ቀሩ። በሂደትም እነዚህ ክርስቲያኖች ከሌላዉ ክርስቲያን ህዝብ ጋር ለረዥም ጊዜ ተቆርጠዉ ስለቆዩ የራሳቸዉ ቋንቋ ኖራቸዉ እነሱም የዝይ ሰዎች ተባሉ። ቋንቋዉ ለግዕዝ፣ለአማርኛ፣ለትግርኛና ለጉራጌኛ በጣም ቅርብ ቋንቋ ነዉ። ሆኖም ሁሉን ህዝብ በዘርና በጎሳ ህሳቤ ካላስቀመጠ ምድር የምትጠፋ የሚመስለዉ ዘመንም እነዚህንም ወገኖች የራሳቸዉ ብሄር ያላቸዉ ናቸዉ ሲል አሁን በብሄር ፈረጃቸዉ። አሁን እነዚህ ወገኖቻችን የዝይ ብሄር ተብለዉ ተፈርጀዋል።

ወደ ጥንታዊዉ ታሪክ እንመለስ። ከዮዲት ጉዲት ሞት በሁዋላ ያገገመዉ ክርስቲያን ቀደም ሲል ይግባባበት የነበረዉ የግዕዝ ቋንቋ እየተዳከመና በሂደት የተወለደዉ አማርኛና ትግሪኛ የጋራ መግባቢያዉ እየሆነ መጣ። በተለይም አማራ ሳይንት በሚባለዉ /ድሮ ላይ ኮመዝ ዛሬ ወሎ በሚባለዉ/ አካባቢ አድጎ እየተንሰራፋ የመጣዉ አማርኛ እንደ መግባቢያ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን የማንነት መገለጫ እስከመሆን ደርሶ በአሁኑ ሰአት አማራ የሚባል ብሄር አለ ወይስ የለም የሚለዉን ወይይት እስከማስነሳት ደረሷል። አማራ የሚባል ህዝብ ሳይኖር እንዴት አማርኛ የሚባል ቋንቋ ሊኖር ይችላል? የሚለዉ የክርክር መነሻ አማራ የሚባል ህዝብ አለ ወደሚል ድምዳሜ የሚወስድ እየሆነ መጥቶአል።


የንቡረዕድ ኤርምያስ መጽሃፍ በስፋትና በጥልቀት እንደሚያስረዳዉና ሌሎች የታሪክ መጽሃፍት እንደሚያረጋግጡትም አማራ የሚለዉ ጽነሰሀሳብ በኢትዮጵያ ምድር ክርስትናን የሚከተሉ ወገኖች መለያ /መጠሪያ ቃል እንጅ የአንድ የተለዬ ደምና ጉሳ ስም አልነበረም። ክርስቲያን የሆኑ የትግራይ፣የአገዉ፣የጉራጌ እንዲሁም የሌሎች ኢትዮጵያዉያዉያን የወል ስም እንደነበረ አጥልቀዉና አጠንክረዉ ያብራራሉ። በምሳሌነትም ንጉስ ላሊበላ አገዉ ነበሩ። ሆኖም በእሳቸዉ ዘመንም ሆነ ፣ ከእርሳቸዉ በፊትም ሆነ፣ ከእርሳቸዉ ብኋላ የነበረዉ ህሳቤ አማራ ማለት ክርስቲያን ማለት ስለነበረ አማራነትን ማለትም ክርስትናን ሲያስፋፉና የኢትዮጵያዉያን የመንግስት ሀይማኖት እንዲሆን ሲሰሩ ነበር።

የሰለሞናዊ ስርዎ መንግስት የሚባለዉ መሰረታዊ ጭብጡ የሰለሞንን አምላክ የተቀበለና ከሰለሞን አምላክ በደም ሳይሆን በመንፈሳዊ ልጅነት የአመራር ጥበብን ያገኘ ማለት መሆኑን የኢትዮጵያዊያን ታሪክ የስረዳል። ኢትዮጵያዊያን ክርስቲያኖች እስካሁን ድረስ እኛ እስራኤል ዘነብስ ነን ሲሉ የሚደመጡት የእስራኤልን ደም በማጣቀስ አይደለም።የእስራኤልን አምላክ በመቀበልና በመከተል እንጅ። ያ የእስራኤል አምላክ በብሉይ ኪዳን የነበረዉና በሃዲስ ኪዳን የተወለደዉ ኢየሱሰ ክርስቶስ ነዉ። ያን አምላክ እፊትም እናምነዉ ነበር አሁንም እናምነዋለን ሲሉ እኛ እስራኤል ዘነብስ ነን ይላሉ። እስራኤል ዘነብስ መሆን የመንፈሰና የእምነት ትስስር ነዉና ለማንኛዉም በክርስቶስ ለሚያምን ወገን ክፍት ነዉ ሲሉ ያስተምራሉ።

ክርስትና በ4ኛዉ ክፍለዘመን የመንግስት እምነት ለመሆን የደረሰዉና ሀይለኞቹ እነ አብርሃና አጽብሃ ክርስቲያን ካልሆኑ በቀር መምራት ስለማይችሉ የዘመኑን ግዴታ ተቀብለዉ ክርስቲያን በመሆን አክሱምና ሸዋ ላይ ተቀምጠዉ የኢትዮጵያን ህዝብ ሲያስተዳድሩ የነበረዉ ቀድሞ በክርስትና ማስፋፋት ላይ በርካታ ስራዎች በሁሉም ኢትዮጵያዊ ወገኖች ስለተሰራ ነዉ። አንዳንድ የታሪክ ጸሃፊዎች ግን ክርስትና በአራተኛዉ ክፈለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ ገባ ፣ በአራተኛዉ ክፍለ ዘመንም የመንግስት ሀይማኖት ሆኖ ታወጀ ሲሉ ከተጠይቅ የራቀ ትንታኔ ያቀርቡልናል። እዉነታዉ ግን ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ በጃንደረባዉ አማካኝነት/ 34 ዓም/ ገበቶ ፣ በርካታ ትግልን ከአይሁድነት እምነት ጋር አድርጎ እየተስፋፋ መቆዬቱ ነዉ። ክርስቲያን ሳይሆኑ የቆዩት እነ አብርሃና አጽብሃም ክርስቲያን/አማራ/ ሆነዉ ሀገሪቱን የመምራት እድላቸዉ ሰፊ እንደሆነ ስለገባቸዉ እራሳቸዉን ክርስቲያን/ አማራ/ በማድረግ ኢትዮጵያን መርተዋል። እነዚህ የሌላ እምነት ይከተሉ የነበሩ ሰዎች ክርስትናን እስኪቀበሉ ድረስ አማራ አልነበሩም ክርሰትናን ሲቀበሉ ግን አማራ ሆኑ።

በቅርቡም በአጼ ምኒልክ ዘመን እነ እራስ ሀብተጊዎርጊስ የክርስትና እምነትን እየተቀበሉ ክርስቲያን /አማራ/ ሆኑ ይባል እንደነበረ የታሪክ መጽሀፍት ያወሳሉ። እራስ ሀብተጊዎርጊስ ቢፈልጉ ኖሮ ክርስቲያን/አማራ/ ስለሆኑ ከአጼ ምኒሊክ ሞት ብኋላ ከፍተኛ ስልጣን እና ሀይል ስለነበራቸዉ ንጉሰ ነገስት ሊሆኑ ይችሉ ነበር። ይህም ማለት እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ክርስቲያን የሆኑ የትግራይ፣የአገዉ፣የጉራጌ ፣ የኦሮሞ እንዲሁም የሌሎች ኢትዮጵያዉያዉያን የወል ስም አማራ /ክርስቲያን/ ነበር ማለት ነዉ። ንቡረ እድ ኤርምያስ ከበደ ይሄን እዉነት በመጽሃፋቸዉ በጥልቀት አፍታትተዉ አቅርበዉታል። በኢትዮጵያ ምድር የሰሎሞናዊ ስረወ መንግስትነት ዘር አለኝ ለማት መጀመሪያ ጉልበት ሊኖርህ ይገባል፣ ቀጥሎ ደግሞ ክርስቲያን ልትሆን ይገባሃል። በቃ ይሄዉ ነዉ። የሰለሞን ስረወ መንግስት የሚባልለት ሀቅ ሲሉ በአንድ ወቅት የአክሱም ንቡረእድ የነበሩት ኤርምያስ ከበደ ያስረዳሉ።

አዉሮፓዊ ጸኃፊያን እና ክርስቲያን ያልሆኑ ወገኖች ግን ይህ ተጠይቅ አንድም ግራ ይሆንባቸዋል ወይም ደባና ተንኮል ሆኖ ይገለጥላቸዋል። እንዴት ሰዉ ሁሉ የሰሎሞንን የጥበብ አምላክ ስለተቀበለ የሰለሞን ዘር አለኝ ሊል ይችላል። በእምነት ይቻላል። ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳለዉ በእሱ የሚያምን ሁሉ የእርሱ የብልቶቹ አካል ሲሁን እያንዳንዱ ክርስቲያን ወንድም አማች ነዉና። ኢትዮጵያን ክርስቲያኖች በቀደመዉ ዘመን ይሄን እምነትና አስተሳሰብ አጥልቀዉ አራምደዉታል። የተለያዩ ወገኖችና ጎሳዎችንም በአንድ የክርስትና ጥላ ስር ለማሰባሰብና የጋራ ማንነት ለመፍጠር ነጻ ህዝብ /አምሓራ / የሚለዉን ጽንሰሀሳብን ያለገደብ ሲያራምዱት ኖረዋል።

እዚህ ጋር ሲደረስ ታዲያ ክስና ወቀሳ ከበርካታ ወገኖች ይነሳል። በተለይም ይህ ሀሳብ እንደ እሬት የሚመራቸዉ ወገኖች Amharanization/አማራ የማድረግ ሂደት/ ሲሉ አጥብቀዉ ይከሳሉ። ይሄንኑ ክርስቲያን/አማራ/ የሚለዉን ህሳቤ ለማንኛዉም ክርስቲያን ስም አድርጎ የመስጠት ሂደትን የአማራዎች ደባና ተንኮል፣ የሌሎችን ማንነት ማስጣል ሲሉ በምሬት ያስረዳሉ። ሆኖም ይሄን ትችትና ወቀሳ ይሄኛዉ ትዉልድ ሊመልሰዉ የሚችል አይመስለኝም። ወይም ሊወቀስበት የሚገባ ጉዳይም ነዉ ብዬ አላምንም። የቀደሙ ሰዎች አማራ ማለት ክርስቲያን ማለት ነዉ ብለዉ እስከተስማሙ ድረስ/ወይም በጉልበት እስካሳመኑህ ድረስ በዚያ ዘመን የነበርህ ሰዉ ብትሆንም ያኛዉ ትዉልድ ያደርግ የነበረዉን እያደረግህ መቀጠልህ አይቀርም። በዘመናቸዉ በነበረዉ ህሳቤ መሄድ መብታቸዉ ነበርና። ወደኋላ ሄዶ ማን ነዉ ይህ አስተሳሰባችሁ ስህተት ነዉ ሊላቸዉ የሚችለዉ? ከቀደመ ዘምን ጋር ተሙዋግቶ ያን ዘመን ማሸነፍ ይቻል ይሆን?

ከላይ የተብራራዉ ታሪክ እንዳለ ሆኖ ይሄዉ አማራ የሚለዉ ቃል በሂደት ወደ ብሄር መጠሪያነት ለመድረስ መቻሉንም እናስተዉላለን። ከዚሁ የብሄር ስያሜነት ጋርም ተያይዞ አማራ ከሚለዉ እሴት እና የጋራ ማንነት ጋር የተለያዩ ወገኖች ሰፊ ትግል እና ፍጭት አድርገዋል። እንደሚታወቀዉ በሂደት አማራ የሚለዉ ህሳቤ የክርስትና እትምነትን የሚገልጸ ሀሳብ ሳይሆን አማርኛ ቋንቋን በአፍ መፍቻነት የሚናገሩ ወገኖች ስም እየሆነም መጥቶአል። ለምሳሌ ድንገት ሳያስቡት አማራ ተብሎ በተፈረጀዉ ወገን ላይ በተከታታይ በተደረገበት ጥቃት የተበሳጩት ፕሮፌሰር አስራት መአህድን ባቋቋሙበት ወቅት ለመሆኑ አማራ ማለት ምን ማለት ነዉ የሚል የዱብ እዳ ጥያቄ ሲነሳባቸዉ አማራ ማለት አማርኛ የሚናገር ሁሉ ነዉ ሲሉ ነበር የመለሱት።

ለዘመናት የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንደተነተኑ የኖሩት ፕሮፌሰር መሰፍን ግን አሁን አማራ የሚለዉ ቃል ለብሄር መጠሪያነት መሰጠቱ ያበሳጫቸዋል። የክህደት ቁልቁለት በሚለዉ መጽሃፋቸዉ እነ ንቡረእድ ኤረምያስን እያጣቀሱ አማራ የሚለዉ ስም የጉሳ ስም አለመሆኑን ለማስረዳት መከራቸዉን አይተዋል። አንዳንድ ጸሃፊዎች የፕሮፌሰሩ ጽሁፍ የአማራን ህዝብ ማንነት መጋፋት ነዉ ሲሉ የምት መልስ ጽፈዋቸዋል። በጣም የተበሳጨዉ እስክንድር ነጋም ፕሮፌሰር መስፍን በአማራ ህዝብ ላይ ደባ እየሰሩ ነዉ፣ አማራ የራሱ የብሄር ማንነት ያለዉ ህዝብ ሆኖ ሳለ እንዴት ማንነቱን ከሀይማኖት ጋር በማያያዝ ማደበዘዝ ይቻላል የሚል እልህ አዘል ጽሁፍ መጻፉም ትዝ ይለኛል። አሁን አሁን የሚነሳዉ ክርክር ደግሞ አማራ የሚባል ብሄር አለ ወይስ የለም የሚል ነዉ? የሶሽዎሎጂና አንትሮፖሎጅ ምሁራን አንድ ህዝብ ብሄር የሚባለዉ ምን ምን ሲያሟላ ነዉ ብለዉ ይጠይቃሉ። ለዚህም መልስ አላቸዉ። አንድ ህዝብ ብሄር የሚባለዉ 1. የጋራ ስነልቦና 2. ኩታ ገጠም መልከአምድር 3. የጋራ ቋንቋ 4. የጋራ ባህል/ባህለ ማህበራዊ ተቋማትን ጨምሮ 5. የጋራ ታሪክ 6. ተደጋጋፊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሲኖረዉ መሆኑን ያብራራሉ። ይሄን አሳማኝ መከራከሪያ ጭበጥ በማንሳት አማራ የሚባል ህዝብ አንደ ብሄር ነዉ እንጅ ክርስቲያን የሆኑትን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የሚወክል ስም አይደለም በማለት የሚከራከሩ ወገኖች በርካታ እየሆኑ የመጡ ይመስላል። በዚያም ተባለ በዚህ ግን አማራ የሚለዉ ቃል ግልጽ ታሪካዊ መነሻዉ የክርስትና ሀይማኖት ወደ ኢትዮጵያ የገባበት ሁኔታና ሂደት ነዉ። በርግጥም አንድ ወቅት በሁሉ ነገር አንድ የነበሩት የአዳም ልጆች በምድሪቱ ላይ አየበዙና እየሰፉ ሲመጡ የተለያዬ ነገድና ጎሳን እንደፈጠሩት ሁሉ በእኛም አገር ይሄዉ ሁኔታ መፈጠሩ የሚያስደንቅ ላይሆን ይችላል። በአንድ ወቅት አማራ /ነጻ ህዝብ፣ክርስቲያን ህዝብ/ የሚለዉ ስያሜ በሂደት ይሄዉ ስም ሌላ ጽንሰሀሳብ የሚያካትት ሆኖ መምጣቱ አያስገርምም።

አንድ የነበሩ ህዝቦች ወደ ሁለት ነገድ ሊሰነጠቁ ይችላሉ። ለምሳሌ የቤተ እስራኤላዊያን/ፈላሻ/ ፈላሻ ታሪክ የዚህን ሂደት እዉነት ያረጋግጥልናል። ከላይ አንዳነሳንዉ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ የኢትዮጵያ ህዝብ የአይሁድ እምነት ተከታይና የክርስትና እምነት ተከታይ ተብሎ ሁለት ተከፈለ። በዚህ የሀይማኖት መከፋፈልም የተነሳ አንድ የነበረዉ ህዝብ ሁለት የተለያዬ ማንነት ተላብሶ እርስ በእርሱ ክፉኛ ተጎዳዳ። በተደረገዉ የእርስ በእርስ በቀልና መጠፋፋትም በእጅጉ የተራራቀ ስነልቦና ተፈጠረ።

በሂደት ክርስቲያኖች የበላይነቱን ሲጨብጡ የገዛ ወገኖቻቸዉን ከብዙ ነገር አገለሎዋቸዉ፣ለዩዋቸዉ። ፈላሻ በማለትም ክርስቲያኖቹ የራሳቸዉ ወገኖች የሆኑትን የአይሁድ እምነት ተከታይ ወገኖቻቸዉን አፈለሷቸዉ/ለዩዋቸዉ። ፈላሻ ሲሉም የተለዩ ወገኖች እንደሆኑ ጫና በማድረግ፣መሬት እንዳያገኙ በማድረግ፣ ከዋና ዋና የሀገሪቱ ከተሞች እንዲሸሹ በማድረግ አፈለሱዋቸዉ። በግዕዝ ፈላሻ ማለት የፈለሰ፣የተለዬ ወገን ማለት ነዉና ፈላሻ ብለዉ በመሰዬም ከፍተኛ ጫና አሳደሩባቸዉ። በዚህ ጫናም በርካታ የአይሁድ እምነት ተከታዮች ክርስቲያን/ወይም በዚያን ዘመን አነጋገር አማራ እንደሆኑ ታሪክ ይመሰክራል። እንቢ በእምነታችን እንጸናለን ያሉ ኢትዮጵያዊያን የአይሁድ እምነት ተከታዮች ደግሞ በኢትዮጵያ ምድር ቢኖሩም የባእድነት ስሜት እየተሰማቸዉ የተለዩ ወገኖች እንደሆኑ ቀጠሉ።

እስራኤል እንደ ሀገር ተመስርታ የሰዉ ሀይል ቁጥሯ ጉዳይ ያሳስባት ነበርና በመላዉ አለም ያሉ የአይሁድ እምነት ተከታዮችን ስታሰባስብ የእኛን ኢትዮጵያዊ ወገኖችም እስራኤላዊ ናቸዉ ብላ ለኢትዮጵያ መንግስታት ጥቂት ጥቂት ፍርፋሪ ጣል እያደረገች ህዝባችንን ማጋዝ ጀመረች። ኢትዮጵያዊያን የአይሁድ እምነት ተከታይ ወገኖች እስራኤላዊ ናቸዉ የተባለዉ ከእስራኤል አይሁዳዊ እምነት ተከታዮች ጋር ባላቸዉ የእምነት ትስስር ከሆነ ያስማማናል። በደም አንድነት ነዉ የሚለዉ ግን ስህተት ነዉ። ከመላዉ አለም የተሰበሰቡት የአይሁድ እምነት ተከታዮች በአብዛኛዉ ተመሳሳይ ነጭ መልክ ሲኖራቸዉ ከኢትዮጵያ የሄዱት ግን መልካቸዉ ኢትዮጵያዊ ነዉ። አዎን ኢትዮጵያዊ መልኩ ኢትዮጵያዊ ነዉና እነዚህ ወገኖቻችን መልካቸዉ ፍጹም ኢትዮጵያዊ የሆነ ነው::

ይህም ማለት እነዚህ የይሁድ እምነት ተከታይ ወገኖቻችን በደረሰባቸዉ የመገለል ታሪከ፣ ባላቸዉ የእምነት ቁርኝት የተነሳ የእስራኤልን ምድር ናፈቁ እንጅ በደምስ ኢትዮጵያዊ ናቸዉ። ከዚህ ታሪክ ጋር የተያያዘ አስተምህሮት በኢትዮጵያ ተዋህዶ ክርስትና እምነት ዉስጥ ላለ ሰዉ የሚገባዉ የስነልቦና ቁርኝት ከእስራኤል ምድር ጋር የሚተሳሰር ጉዳይ አለ። እሰራኤል ዘ ነብስ የሚለዉ ጥልቅ ጉዳይ አለ። ከትንቢተ ኢሳያስ የመጽሃፍ ክፍል ዉስጥ ያዕቆብ ሆይ ኢትዮጵያን አስራት አርጌ ሰጠሁሁ የሚለዉን አባባል በምዘዘ የክርስቶስ የኢየሱስን አምላክነት የተቀበለዉን ሰዉ ሁሉ እስራኤል ዘነብስ የማድረግ ስነልቦና አለ። ሥለሆነም የአይሁድ እምነት ተከታዮችም ሆኑ የክርስትና እምነት ተከታዮች ከእስራኤል ጋር ልዩ የስነልቦና ቁርኝተ አላቸዉ። ይሄ ማለት ግን እነዚህን ወገኖች ኢትዮጵያዊ ሳይሆኑ እስራኤላዊ ያደርጋቸዋል ማለት አይደለም። ሰዎቹ በደም ፍጹም ኢትዮጵያዊ ናቸዉ።

የአይሁድ እምነት ተከታዩም/ፈላሻ መባል የሚታወቀዉ/ ሆነ ክርስቲያኑ ኢትዮጵያዊ በዘሩም ሆነ በዜግነቱ ኢትዮጵያዊ ነዉ። ምናልባት በአለም ላይ የታሪክ እሴቷን ሁሉ ሳታገናዝብ የራሷን ህዝብ ሌላ ህዝብ ነዉ ብላ ያልሆኑትን በደም ቤተእስራኤላዊያና ናቸዉ ብላ ወደ እስራኤል የላከች ብቸኛ አገር ኢትዮጵያ ሳትሆን አትቀርም። ለነገሩ ያሏትን ዜጎች በተገቢዉ መንገድ ወደ ብልጽግና ማድረስ እስካልቻለች ድረስ ብዙ ምርጫ ያላት አትመስልም። ለፍርፋሪ ዜጎቿን ከመለወጥ ዉጭ። እርስ በእርስ ለመገዳደል የጦር መሳሪያ ለማግኘት ዜጎቿን ለእስራኤል የሸጠች አገረ ኢትዮጵያ ብቻ ነች። የታሪክ ምሁራንም አፋቸዉን ለጉመዉ እዉነታዉን ሳያብራሩ ዝምታን መርጠዋል።

ወደ ነጥባችን ስንመለስ አማራ የሚለዉ ቃል መጀመሪያ የነበረዉንና ከክርስትና ጋር የነበረዉን ቁርኝት ይዞ የሚቀጥል አልሆነም። ዋና ዋና ምክንያቶቹም፤ 1. የእስልምና ሀይማኖት ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ብኋላ በሂደት በርካታ ክርስቲያን/አማራ/ የነበሩ ኢትዮጵያዉያን እምነታቸዉን በተለያዬ ምክንያት ወደ እስልምና መለወጣቸዉ። 2. በጠቃላይ ሀይማኖት በሂደት ተለዋዋጭ መሆኑ፤ ይሄም ማለት በልዩ ልዩ ምክንያት አንድ ህዝብ የተለያዩ ሀይማኖቶችን በተለያዬ ወቅት ሊይዝ ይችላል። በአንድ ወቅት የማያምን የነበረዉ ወደ አይሁድነት፣ ከዚያም ወደ ክርስቲያንነት ከዚያም ወደ እስልምና፣ ከዚያም ወደ ሌላ ወደ አዲስ እምነት ከዚያም ተመልሶ ወደ አለማመን ሊመጣ ይችላል። ከዚህ ሁሉ ሂደት ብኋላም ተመልሶ ክርስቲያን ሊሆንም ላይሆንም ይችላል። 3. አንድ ህዝብ ከልዩ ልዩ ህዝቦች ጋር በሚያደርገዉ መስተጋብር የደም፣የባህል፣የእምነት፣ የስነልቦና፣የመልከአምድራዊና፣ የፖለቲካ ብልጽግናዉ እያደገና እየበለጸገ ስለሚመጣ ጥንት የነበረዉ ማንነት በአዲስ መልክ እየጎለመሰ እና እየሰፋ ስለሚመጣ የመጀመሪያዉ ቅርጹ መለወጡና መሻሻሉ አይቀርም 4. በህዝቦች መካከል በሚደረገዉ መስተጋብር ጦርነቶችና መፈቃቀሮች በሚፈጥሩነት ዉህደት አንዲሁም መበታተን አንድ ህዝብ እንደገና ማንነቱን እየፈጠረ፣ እያደሰና ወይም ጨርሶ አዲስ ማንነት እየገነባ የትዉልድ ጉዞ ስለሚያደርግ 5. በዬወቅቱ የሚፈጠሩ የፖለቲካ ርዕዮተ አለሞች የተለያዬ ማንነትን እያላበሱት የነበረዉን ይበልጥ እያሰፉት ወይም በአዲስ የተኩት ስለሚመጡ

ከላይ በተጠቀሱት ምክንያት አማራ የሚለዉ የቃሉ መነሻና አሁን ያለዉ ትርጉም ፈጽሞ የተለዬ ሆኗል። ስለሆነም በአሁኑ ወቅት አማራ የሚለዉ በሶሾሎጂስቶች ትንታኔ መሰረት ብሄር ማለትም የጋራ ስነልቦና ፣ ኩታ ገጠም መልከአምድር፣ የጋራ ቋንቋ ፣የጋራ ባህል/ባህለ ማህበራዊ ተቋማትን ጨምሮ/ ፣የጋራ ታሪክ እና ተደጋጋፊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ያለዉ ህዝብ ሆኖ ስለሚገኝ ብሄር አይደለም የሚለዉ ክርክር ወንዝ የሚያሻግር ሆኖ ይገኝም።

ይሄም አማራ የሚለዉ ብሄር በዉስጡ ልዩ ልዩ ሀይማኖቶችን /ክርሰትና፣ እስልምና፣አይሁድነት፣ ኢአማኝነትና ወዘተ/ የያዘና ሰፊ የማንነት መሰረት ያለዉ ህዝብ ሆኖ ይገኛል። ወደፊትም ይሄ የማንነት መሰረት እየሰፋ እነደሚሄድ ይጠበቃል። ምክንያቱም አንድ ህዝብ/ብሄር/ ከሌላዉ ህዝብና ብሄር ጋር መስተጋብር እያደረገ በሚመጣበት ጊዜ ሰፊ የሁለተዮሽ የማንነት ቅብብሎሽ እና ዉህደት እንደሚያደርግ ሳይታለም የተፈታ ነዉ። ይህም ማለት ከሌሎች ይወስዳል እሱም ለሌሎች ማነነቱን ያጋራል። በዚህ ሂደት ዉስጥም ቀድሞ የነበረዉ የስምም ሆነ የማንነት ትርጉም እየሰፋና ሌሎች ጽንሰሀሳቦችን አካታች እየሆነ ይሄዳል።

ስለሆነም  ቀድሞ አምሐራ  ማለት በክርስቶስ ነጻ የወጣዉን ወገን ብቻ የሚወክል ትርጉም አሁንም ላለዉ ሁኔታ ይሰራል የሚለዉም አስተሳሰብ የትም የማያደርስ ህሳቤ ነዉ። ይህ አይነት አስተሳሰብ የታሪክን ፍሰት፣ 

የማህበረሰብን የመስተጋብራዊ ዉህደትና ጥምረት ያላገናዘበ ትንታኔ ነዉ የሚሆነዉ። ስለሆነም በአሁኑ ሰአት ያለዉ አማራ የሚለዉ ጽንሰ ሀሳብ ከክርስትና ምነት በዘለለ በርካታ እምነቶችን (ክርስትና፣እስልምና፣ አይሁድነት እና ሌላም የእምነት አመለካከቶችን የሚያካትት)፣ በርካታ ማንነቶችን፣በርካታ ባህሎችን እና በርካታ የታሪክ ሂደትና ዉጤቶችን የሚያካትት ሆኖ ይገኛል። ማህበረሰብ የታሪክ ዉጤት እንደመሆኑ መጠን በታሪክ ሂደት ዉስጥ በርካታ ለዉጦችና ክስተቶች እዉን በሚሆኑበት ሂደት ዉስጥ የማህበረሰቡም እድገት በዚያዉ ልክ እየሰፋ ፣ ይበልጥ አካታችና ሁል አቀፍ እየሆነ እንደሚመጣ በርካታ ምሳሌዎችን መጥቀስና ማቅረብ ይቻላል።


የሆኖ ሆኖ አማራ የሚለዉ ጽንሰ ሀሳብ ብሄርን የሚወክል ነዉ ወይም ብሄርን አይወክልም ብለዉ ለሚከራከሩ ወገኖች አንድ የሚያስታርቃቸዉ ነጥብ መኖሩን ግን ሁሉም በልቡ የተቀበለዉ ይመስላል። ይሄም አሁን ላለዉ ብዙሃኑ የአማራ ህዝብ በብሄርህ አማራ ነህ እያለ ለሚወተዉተዉ ወገን የቀዘቀዘ ስሜት በመስጠት ለኢትዮጵያዊ ማንነት የገነነ ትኩረት የሚሰጥበት ሁኔታ መኖሩ ነዉ። አማራ የዚህ አይነቱ የስነልቦና ጭብጥ ለምን ሊኖረዉ ቻለ ብሎ ለሚጠይቅ ሰዉ በርካታ ምክንያቶችን ሊቆጥር ይችላል። ከእነዚህ ምክንያቶች ዉሰጥም፤ 1. አማራ እራሱ እንደማህበረሰብ በሰፊ ልዩነቶች ላይ የቆመና በሂደት እየሰፋ የመጣ ማንነት እንጅ አንድ ጊዜ የተቀመረ ማንነት ስላልሆነ በአንድ አረፍተ ነገር አማራ ማለት አንዲህ ነዉ ብሎ የሚያሰማማ ትርጉም ሊፈጠርለት የሚችል ጉዳይ አለመሆኑ አንዱ ነዉ። ለዚህ ማረጋገጫዉም በንቡረዕድ እይታ አማራ የሚለዉን ጽንሰ ሀሳብ ወደ ቀደመዉ ዘመን በመጎተት ከክርሰትና ጋር ሲያገናኙትና አሁንም ይሄ አስተሳሰብ እንደሚሰራ ሲያስቀምጡት፤ ፕሮፌሰር አስራት ደግሞ አማራ ማን ነዉ የሚለዉን ጽንሰሀሳብ አማርኛ ቋንቋዉ ሁሉ አፍ መፍቻዉ የሆነ ነዉ ሲሉ ያስቀምጡታል። ብሄር የሚለዉን ጽንሰሃሳብ ለመፍታት የሶሺዎሎጅስቶችን ትርጉም በመዉሰድ የጋራ ስነልቦና ፣ ኩታ ገጠም መልከአምድር ፣ የጋራ ቋንቋ፣ የጋራ ባህል/ባህለ ማህበራዊ ተቋማትን ጨምሮ/፣ የጋራ ታሪክ ፣ተደጋጋፊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ያለዉ ህዝብ ስለሆነ እራሱን ያቻለ ብሄር ስለሆነ እንደሌሎች ብሄረተኛ ስሜትን በአማራዉ መሃል ማምጣት አይከብድም ብለዉ የሚከራከሩ ወገኖችም አሉ። ሆኖም የንቡረዕድ ትርጓሜ በአሁኑ ዘመን ላለዉ የአማራ ህዝብ እንደማይሰራ ግልጽ ነዉ።

በርግጥ ንቡረዕድ ኤርምያስ የአማራን ታሪካዊ ስሩን በመተንተን የተዋጣለት ስራ ሰርተዋል። ወደዚህኛዉ ዘመን አገናኝተዉ ሲተረጉሙት ግን አማራ የሚለዉን ጽንሰ ሃሳበ በክርስትና ዙሪያ ማጠራቸዉ አግባብ ሆኖ አይታይም። ለምን ቢባል? አሁን የአማራ ህዝብ በታሪክ ሂደት ሁሉም እምነቶች ያለዉ ህዝብ ሆኖአልና። ክርስትና፣እስልምና፣አይሁደነት፣ኢአማኝነት ምናልባትም ወደፊት በርካታ በአሁኑ ሰአት ወደ ሀገሪቱ ያልገቡ እምነቶችን የሚቀበሉ የተለያዩ የአማራ ወገኖች ሊኖሩ ይችላሉ።

የፕሮፌሰር አስራት አማራ ማለት አማርኛን አፍ መፍቻዉ ያደረገ ሁሉ ነዉ የሚለዉም አከራካሪ ነዉ። በርግጥ ፕሮፌሰር አስራት እድሜ ዘመናቸዉን ሙሉ ስለአማራነትም ወይም ስለኢትዮጵያ ፖለቲካ አስበዉ የሚያዉቁ ሰዉ አለነበሩም። ወደ ፖለቲካዉ ድንገት የታሪክ እዳ አምጥቶ የጣለባቸዉን ቀንበር ተሸክመዉ ዘዉ ያሉ የቀዶ ህክምና ምሁር ስለሆኑ እሳቸዉ ስለ ቃላት ትርጉም ሳይሆን ስለ ተገባራዊ ስራ ብቻ የሚጨነቁ ኮስታራ ክርስቲያን ሰዉ ነበሩና በዬቦታዉ የክርስቲያኖች መታረድና የቤተክርስቲያኖች መቃጠል አንገብግቧቸዉም ሊሆን ይችላል ወደ ማያዉቁት የፖለቲካ ስራ የገቡት። ስለሆነም የእሳቸዉን የቃል ፍች አጥልቀን ልንሄድበት የሚገባ ላይሆን ይችላል። በአንድ ንግግራቸዉ ላይ በስፋት ሲያብራሩ እንደሰማሁት ፐሮፌሰር አስራት አጥልቀዉ ሲተነትኑ የነበረዉ በደል ስለደረሰባቸዉ ክርስቲያኖች በሙሉ ነዉና ምናልባትም የአስራት መንፈስ ዉጊያዉ የቀደመዉን የክርስትና/አማራነት/ ህሳቤ ከሚዋጉ ወገኖች ጋር ሁሉ ሊሆን ይችላል ብዬ ጠረጠርሁ። ሆኖም በበቂ መረጃ ያልተደገፈ የራሴ የግል ጥርጣሬ እንጅ ርግጠኛ አይደለሁም። ይሄን ጉዳይ ወደፊት በስፋት ለማጥናትና ለማቅረብ እሞክራለሁ።

የሶሽዎሎጂስቶችን የብሄር ትርጉም ብቻዉን ወስደን በአማራ ብሄር ሁኔታ ስራ ላይ እናዉለዉ ያል እንደሆነም በርካታ ያላገናዘብናቸዉ ተያያዥ ጉዳዮች ከየስርቻዉ ብቅ ብቅ እያሉ ከተግባራዊ እዉነታዉ ጋር የሚጣረሱ ሆነዉ እናገኛቸዋለን። እነዚህ ያላገናዘብናቸዉ ተያያዥ ጉዳዮች ከየስርቻዉ ብቅ ብቅ እንደሚሉ የምንገነዘበዉም ከዚህ ቀጥሎ ከ2-7 የተዘረዘሩትን ነጥቦች አንድ በአንድ ማስተዋል ከቻልን ነዉ።


2. በጦርነት ምክንያት ይሁን በሰላማዊ መስተጋብር አማራ በኢትዮጵያ ምድር ያልተቀዬጠዉ፣ያልተዋለደዉና በደም ያልተወራረሰዉ ህዝብ ስለሌለ ሰፊ የሆነ ዉህደትን ከበዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ያደረገ ህዝብ ሆኖ ይገኛል። በዚህም በብዙሃኑ የአማራ ብሄር ዉስጥ የብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ደም ተዋሀዶ ይገኛል። የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያዊነት የመጽናት ምንጩም ከብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ጋር የተሳሰረበት የደም : የባህል: የታሪክ: የስነልቦና ወፍራም ቀለበት እና በት/ኤርምያስ 13: 23 የተነገረዉ በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? የሚለዉ የተራቀቀ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ነው::

3. በስነልቦና፣ በባህል፣በእምነት /በክርስትናዉም ሆነ በእስልምናዉ/ ከአበዛኛዉ ኢትዮጵያዊ ጋር የጠለቀና የሰፋ መተሳሰርን/መዋሃድን ስለፈጠረና በመላዉ ኢትዮጵያዊ ማንነት ዉሰጥ ገብቶ ስለተወራረሰ የተነጠለ ማንነት ያለኝ ህዝብ ነኝ ብሎ ማመን አይፈልግም። ስለ ብሄሩ ማንነት ላሳምንህም ለሚሉት ወገኖችም ጆሮ መሰጠት አይፈልግም። በአሁኑ ሰአት ጥናቶች እንደማያረጋግጡትም አማርኛ ቋንቋ እስከ 40% የሚሆን ቃላት ከተለያዩ የኩሽና ልዩ ልዩ የሀገሪቱ ቋንቋዎች በዉርርስ መዉሰዱን ይጠቁማሉ። ይሄም የሚያሳዬዉ የአማራ ህዝብ ከነቋንቋዉ ምን ያህል በብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ማንነት ዉስጥ ገብቶ እንደተሸመነ ብሎም ድርና ማግ እንደ ሆነ ነዉ። ይህን ጉዳይ ለማረጋገጥ የዶ/ር አሰፋ እንዳሻዉ መጽሀፍን ማንበብ በቂ ነዉ:: የዶ/ር አሰፋ እንዳሻዉ መጽሀፍን (ኢትዮጵያ:- የህዝቦች ስብጥርና የአገዛዞች አወቃቀር አጨር ታሪክ) ማንበብ ለማገናዘቢያነት ማንበቡ መልካም ግንዛቤ ያስጨብጣል::


4. በመልከኣምድራዊ አቀማመጡ ከብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ጋር ከፍተኛ የሆነ ቁርኝት ስላለዉ በዚህም የኢኮኖሚያዊ ትስስሩ በጥብቅ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ህዝብ ጋር የተሳሰረ ስለሆነና በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ህዝብ መሃል ገብቶና ተሰግስጎ የሚኖር ስለሆነ የተነጠለ ማንነት ላይ ከማተኮር በህብር የሚፈጠረዉ ኢትዮጵያዊ ማንነት ያማልለዋል

5. አማራ የሚለዉን ስምና ማንነት ለብዙ ጊዜ ነጥሎ ሲጠቀምበት የነበረዉ ከእምነት ጋር በማያያዝ ስለነበረ አማራ ብሎ ሲያስብ በደም የተሳሰረ የብሄር ማንነት ወደ አዕምሮዉ ስለማይመጣለት አማራ ነኝ ብሎ ለራሱ ይሄን ማንነት ለማልበስ ስለሚከብደዉ ይቸገራል


6. ከቀድሞ ዘመን ክርስቲያኖች በወረሰዉ ትዉፊት ኢትዮጵያ የሚለዉን ቃል ከሀገር ስምነትና ከማንነት በዘለለ ከቅድስና ጋር በማያያዝ ስለሚያስበዉና ስለሚመካበትም ብሎም ስለሚኮራበት ይህን የተቀደሰ ስም ትቶ ወደ ሌላ ስም መሄድ በማንነቱ ዝቅ የማለት ስሜት ስለሚሰማዉ ከኢትዮጵያዊነት መላቀቅ አይፈልግም። ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች (መዝ.ዳ 68፥31)። በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ፥ ጠላቶቹም አፈር ይልሳሉ (መዝ.ዳ 72፥9 ):: የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን? ይላል እግዚአብሔር፦ እስራኤልን ከግብጽ ምድር፥ ፍልስጥኤማውያንንም ከከፍቶር፥ ሶርያውያንንም ከቂር አላወጣሁምን? (ት. አሞጽ 9፥7):: አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው (መዝ.ዳ 74፥14):: እነዚህን እና ሌሎች ጥቅሶችን በማንሳት በተለይም ህዝቤ የተባለ : ወደ እግዚአብሄር እጁን እንዲያነሳ መመሪያ የተሰጠዉ: ማንነቱና ምግቡ እንኩዋን በእግዚአብሄር በግልጽ የተቀመጠለት ህዝብ እግዚአብሄር ጽዋዬ ነው ብሎ መናገር ብቻ ሳይሆን ስራዉን ሁሉ ከእግዚአብሄር ቅዱስ መንፈስ ጋር በማስተሳሰር መከወን አለበት የሚለዉ የኢትዮጵያ ክርስትና አስተምሮትም ሌላዉ የዚሁ ኢትዮጵያዊነት ማጠናከሪያ ምንጭ እንደሆነ የሚያስረዱም አሉ:: ይህ የአማራ አመለካከትና እይታም አንዳንድ ጽንፈኛ የብሄር አስተሳሰብ ያላቸዉ ኢትዮጵያዊ ወገኖቹን ስለሚያበሳጫቸዉ አማራ እኔ ብቻ ኢትዮጵያዊ ነኝ የማለት ትምክህት አለበት የሚል ወቀሳን እና ትችትን ሲያስከትልለት ይስተዋላል። ነገሩ ግን ያዉ የሀበሻ ባህል ሆኖ በእያንዳንዱ ወገን ያለዉን የአስተሳሰብ ጭብጥ በግልጽ ካለመወያዬትና ካለመነጋገረ የሚመጣ ነዉ እንጅ ይህ አማራ ዉስጥ ያለ የገነነ የኢትዮጵያዊነት ማንነት ስሜት በበርካታ ኢትዮጵያዊያን ብሄረሰቦች ዉስጥ ያለ አስተሳሰብ ሆኖ ይገኛል።ከዚሁ ጉዳይ ጋር በማያያዝም በሌሎች ኢትዮጵያዉያን ብሄረስቦች ላይ የሚያተኩር አንድ ጥናታዊ ጽሁፍ ወደፊት ለማቅረብ እሞክራለሁ::


7. በኢትዮጵያ ምድር የገዙ ነገስታቶች በዋናነት ሲያካሂዱት የነበረዉ የማዋሃድ፣ሁሉን ህዝብ እንደግል ንብረታቸዉ በመያዝና በመቁጠር የጋራ ማንነት ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲያተኩር እድርገዉት ስነበረ አማራ የሚባል የብሄር ማንነት በተለዬና እራሱን በቻለ ሁኔታ ለመፍጠር የተደረገ ምንም አይነት ሙከራ አልነበረም። ለዚህ ነጥብ ማረጋገጫችንም በ1923 ዓም የወጣዉ የኢትዮጵያ ህገመንግስት “የኢትዮጵያ መሬትም ፣ህዝቡም ፣ህጉም የንጉሰ ነገስቱ ነዉ” ይላል።/ምዕራፍ አንድ አንቀጽ ሁለትን ተመልከት/። ይህም ማለት በሀገሪቱ አይደለም የተለያዬ የብሄር ማንነት ሊኖር ይቅርና አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የንጉሰ ነገስቱ ንብረት ነበር ማለት ነዉ። አንድ ሰዉ ደግሞ ለንብረቶቹ እራሱ ማንነት ይሰጣቸዋል እንጅ ንብረቶች እየተነሱ የራሳችን ማንነት አለን እያሉ ማወጅ አይችሉም። ንጉሰ ነገስቱም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንብረቱ ስለሆነ የሚፈልገዉ አንድ አይነት ኢትዮጵያዊ ማንነት እንዲኖራቸዉ ነዉ። ይህ አስተሳሰብ በሀይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት ተጽፎ ይታወጅ እንጅ በቀድሞ ዘመን ነገስታትም ህሳቤ ዉስጥ የነበረ አመለካከት መሆኑ ግልጽ ነዉ።

በእነዚህና በሌሎችም ሁኔታዎች አማራ ለብሄር ማንነቱ ትኩረት መስጠት አይፈልግም ። በርግጥ ይህ አመለካከት በተለያዩ ወገኖች የተለያዬ ስያሜ ያሰጠዋል። ዋናዉ ነጥብ ግን ኢትዮጵያዉያኖች የጋራ ማንነታቸዉን በአግባቡ ከፈተሹት በርካታ የሚያስተሳስሩዋቸዉ ታሪካዊ፤ ትዉልዳዊ፤ስነልቦናዊ፡ ሀይማኖታዊ፡ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጭብጦች ስላሉ ነገሩን እዚህ ከቀረበዉ ጽሁፍ በሰፋና በጠለቀ መልክ ሁሉንም ነገር በገንቢና አዎንታዊ መንፈስ መመርመር የሚበጅ መሆኑን መገንዘብ ወሳኝ መሆኑ ነው።

                                                  ዋናዉን /ኦርጅናል/ ሰነድ ለማንበብ የሚከተለውን ዌብሳይት ይጫኑ 
                     http://www.iwooket.com/wp-content/uploads/2012/09/The-Concept-of-Amhara-from-religious-name-to-ethinic-name.pdf