እርዳታ ውይይት:የማዘጋጀት ዘዴ
እኛና የኛ ተራሮች(ክፍል ሁለት
[ኮድ አርም])
==ተራራ፤የከፍታ፣የበላይነት፣የክብር … ምልክት ነው። ነገሥታት፣ ያገር ሽማግሌዎች፣ ታላላቅ ሠዎች፣… በተራራ ይመሰላሉ። በዚህ መጣጥፍ ውስጥ መሪዎቻችን፣ ምሁራኖቻችን፣ የፖለቲካ መሪዎቻችንና ራሳቸውን አንቱ ያሉ ምናምንቴዎቹንም እንቃኛለን።
==የኛዎቹ ኩይሳዎች
==ኩይሳ፣ ምስጥ ወይንም ጉንዳን ወደ ውስጥ እየገባ የምድሩን አፈር ወደ ላይ እየገፋ፣የሚሰራው ጉብታ ነው። በአንዳንድ አካባቢ ኩይሳ በጣም ላጠሩ (ሚጅድስ)፣ ሰዎች የሚሰጥ ቅፅል ስም ነው። ኩይሳን ብትረግጡት ውስጡ ምንም የሌለው ባዶ ስለሆነ ባንዴ ይደረመሳል።የኛዎቹ ምሑራንንም በኩይሳ የሰየምኳቸው በተመሳሳይ ምክንያት ነው።
==ተራሮቻችን ለምን ዛፍ አልባ ሆኑ? ብለን የምንጠይቀውን ያህል ምሑራኖቻችንስ ለሀገራቸው ለምን አይሰሩም? ብለን መጠየቃችን አይቀሬ ነው።
==በዚህ ምድር ላይ ለተደረጉት፣ለሚደረጉትም ሆነ ላልተደረጉት ነገሮች በቂ ምክንያት አለ። ሒትለር ለሃያ ሚሊዮን ሕዝብ ሞት ምክንያት የሆነውን ጦርነት ሲቀሰቅስ የጀርመንንና የአካባቢዋን ሕዝብ ማሳመን ያስቻለ በቂ ምክንያት አቅርቧል።ንጉሰ ነገሥት ፂን ሺ ሁዋንግ 6352 ኪ.ሜ ርዝማኔ ያለውን ታላቁን የቻይና ግንብ ሲያስገነባ ሰሜናዊቷ ቻይናን ከጥቃት ለመከላከል የሚል ምክንያት ይዞ ነው።ታላቁ ሞንጎሊያዊው ጦረኛ ጀንጂስ ካሃን ተራራ ጫፍ ላይ ወጥቶ እኔ የዓለም ገዢ ነኝ ለማለት ያበቃው ምክንያት ከተራራው ባሻገር ያለው በረዶ ሰማይ መስሎት የዓለም መጨረሻ ደረስኩ በሚል ምክንያት ነው።የኛዎቹ ምሑራንስ ለሀገራቸው ላለመስራታቸው ምክንያታቸው ምንድነው?
==ላለፉት 34 ዓመታት ከምሑራኖቻችን ሲነገረን የነበረና እየተነገረን ያለው ነገር ቢኖር
“ ዲሞክራሲ በሌለበት ሀገር ልማት ሊሰራ አይቻልም።” የሚለው ነው።ኢትዮጲያ ውስጥ ዲሞክራሲ አለ? በዚህ ሁላችንም እንስማማለን፣ የለም። ኖሮም አያውቅም። ወደፊትስ ተስፋ አለ? አዎን ስልጣንን በመሳሪያ አሸንፎ መጣል ሲቀር ዲሞክራሲ ይኖራል። ስልጣንን በጨበጣ ከነጠቀ ዲሞክራሲ ተስፋ አይደረግም።ግን የዛሬ 34 ዓመት ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ምሁራን አጠገባችሁ አሉና ተመልከቷቸው ዛሬ ዕድሜያቸው ከ55 – 65 ደርሷል።አብዛኞቹ ለሀገራቸው ላልሰሩበት ምክንያት የሚሰጡት ዛሬ እናንተ የምትሰጡትን ምክንያት ነው። ይህ ምክንያት ዛሬ በ34 ዓመቱንኳ ገና እምቦቃቅላ ነው።እናንተ እስቲ ዛሬን 65ኛ አመታችሁ እንደሆነ አድርጋችሁ አስቡት አንድ ነገር ለሀገራችሁ ሰርታችሁ ቢሆን እንዴት ትኮሩ? እነዛ የ1966 ምሩቃን ዛሬ ባልሰሩበት ምክንያት ይኮሩ ይሆን?
አንድ ሺህ ችግር ባለበት ሀገር አንዱ ችግር ካልተፈታ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ዘጠኙ እንዳለ ይቀመጥ? ? አስተዳደሩን ለማስተካከል ካልቻላችሁ፣ ምክንያታችሁን አሸንፋችሁ ሀገራችንን ከድህነት መታደግ አለባችሁ።
እስቲ የምትኮሩባቸው አባቶቻችሁ በዓድዋ ያደረጉትን ተጋድሎ በዐይነ-ኅሊናችሁ ተመልከቱት “ኑ ጣሊያንን እናሸንፍ…” ብለው ተጠራርተው አሸንፈው በድል ተመለሱ! በቃ! ምንም ችግር አልገጠማቸውም? ጋሻና ጎራዴ ታጥቆ ጦር ወድረው፤ በአውሮፕላን፣ በመድፍ፣ በታንክ የተደራጀን ጠላት መመከትና ማጥቃት ቀላል ፈተና ነበር?እስቲ መቀሌ የመሸገው የጣሊያን ጦር እንዴት እንደነበረ በቃላት ላሳያችሁ።
የመቀሌው ምሽግ በደቡብ በኩል 3ሜትር ስፋት ያለው ሆኖ በግንብ ተ ገነባ። ከግንቡ ውጭ 30 ሜትር ራቅ ብሎ በጣም የሾሉ እንጨቶች በግንቡ ዙሪያ ተተከሉ። ከአንዱእንጨት ወደ አንዱ ያለው ርቀት 20 ቁመታቸው ደግሞ 30 ሳንቲ ሜትር ነበር። በነዚህ እንጨቶች መሀል ማለፍ የሚቻለው ቀስ ተብሎ እግርን እያሰሉ በዘዴ ለሚራመድ ሰው ብቻ ነው።እንዲህ ተደርጎ እንዳይታለፍ ደግሞ ጣሊያኖቹ ጥይቱን እንደ ውኃ ይረጩት ነበር።አደናቅፎት የወደቀ ሰው መነሳት አይችልም።
ከሹል እንጨቶቹ አልፎ ደግሞ እሾሀማ ሽቦ እየተድቦለቦለ በምሽጉ ዙሪያ ተከምሯል። ሽቦውን እንኳን ሰው ወፍ አትሾልከውም።ኢትዮጲያውያን ጫማ ስለማያውቁ ከሽቦው ውጭ የተሰባበረ ጠርሙስ መሬት ላይ ተነስንሷል።ይህ ሁሉ ሆኖ ኢትዮጲያውያን የምሽጉን አጥር አልፈው ምሽጉ ውስጥ ይዋጉ ነበር?እንዴት? እሾሁላይ ጋሻቸውን አንጥፈው እየተራመዱ፣ ሹል እንጨቶቹን ጦራቸውን ምርኩዝ እያደረጉ እየዘለሉ፣ ከምሽጉ ውስጥ የሚተኮሰው ጥይት ሳይበግራቸው እንደ ጆቢራ እየበረሩ ምሽግ ውስጥ ይገቡ ነበር።
እነዛ የዓድዋ ባለሟሎች ገለው ሳይሆን ሞተው ከጠላት ቅኝ ግዛት ጠብቀውናል። ዛሬ ያላችሁት ምሁራን በኢሕአዴግ አመካኝታችሁ እጃችሁን አጣጥፋችሁ መቀመጥ የለባችሁም።ሀገራችንን ከኋላቀርነት ላለማውጣት ስበብ ወይንም ምክንያት አትንገሩን። ምክንያታችሁን ለማሸነፍ የመቀሌን ምሽግ የሰበሩትን እኒያ ማንበብና መፃፍ የማይችሉትን አበውና እመው አስቧቸው።መቻልን ቻሉት።
ሳይማር ያሰማራችሁ ኢትዮጲያዊው ገበሬ የሚያርሰው እሾህ ነቅሎ፣ድንጋይ ፈንቅሎ፤ ቆንጥር ጥሶ፣ እዳሪ መሬት ከስክሶ፤ አሜኬላ ጠርጎ፣ በኋላ ቀር የእርሻ መሳሪያ፣ በባዶ እግሩ ዝናብና ፀሐይ እየተፈራረቀበት፣ ሰብሉን አንበጣ እየበላበት፣ተምች እያጠፋበት፤ጎተራ አስገብቶም እህሉን ነቀዝ እያጠፋበት ነው። ይህን ሁሉ አልፎ ሰብል ለቤተሰቡና ለገበያ ያቀርባል።የዚህ ገበሬ አቅም ታጥጧል። ተስፋው በተማረው ልጁ ላይ ነው።እናንተ ይህንን ገበሬ ላለመታደግ በቂ ምክንያት ካላችሁ ያ ደሀ ገበሬ እናንተን ከሚያስተምር እንደ ጥንቱ ዝናብ አዝንብልኝ እያለ ሰማይን ተስፋ ቢያደርግ ይሻለው ነበር ማለት ነው።
የሀገራችንን ችግር ለማጥፋት ከሰይጣን ጋር መተባበር ግድ ከሆነ ተባበሩ፣ ሀገራችንን ለማበልፀግ አንድ መንገድ ቢኖርና ያም ስህተት ቢሆን ለሀገራችሁ ስትሉ ተሳሳቱ።የእንግሊዙ ጠ/ሚኒስትር ዊኒስተን ቸርችል “ለሀገራችን ብለን ብዙ ሀገራችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ ስሕተቶችን ሰርተናል።ይህን ሁሉ ያደረግነው ለሀገራችን ዘላቂ ጥቅም ስንል ነው።” ብለዋል። እናንተም ተሳሳቱ። ብቻ ስሩ። መሳሳት አትፍሩ።ትልቁ ስሕተት አለመስራት ነው።
ለመሆኑ የተሻለ አሰዳደር እስኪመጣ ድረስ ኢትዮጲያ ውስጥ የሚኖሩ በተሰቦቻችሁን አትረዱም? ኢሕአዴግ እስኪወርድ ቤተሰቦቻችሁን ትቀጣላችሁ? በቤተሰቦቻችሁ ላይ የማትፈርዱ ከሆነ በዛ ደሀ ገበሬ ላይ እናንተን ማን ፈራጅ አደረጋችሁ?ቤተሰቦቻችሁ ውጭ ሀገር ልጅ ስላላቸው የተሻለ የሚኖሩ ከሆነ ልጁን ውጭ ሀገር መላክ የማይችለው ብዙሀኑ ኢትዮጲያዊስ?ዲሞክራሲ በሌለበት ሀገር ቤተሰባችሁን እንደምትረዱ ሁሉ የዛን ደሀ ገበሬ ችግር ለማስወገድ የአስተዳደር ብልሽት ምክንያት ሊሆን አይገባም።
እላንት የሀገሬ ምሑራን፣ሰው ተመጣጣኝ ምግብ ቢመገብና ጥሩ ቢኖር ላዩ ላይ ያለው ተባይ ለመራባትና ለመወፈር ይመቻቹለታልና ሰውየው ተመጣጣኝ ምግብ መመገብና ጥሩ መኖር የለበትም ነው የምትሉት? ሰውየው ተባዩ የሚያመጣበትን በሽታ መቋቋም የሚችለው ተመጣጣኝ ምግብ ሲመገብና ጥሩ ሲኖር አይደለምን?
ግልፁን ልንገራችሁ? ድህነት ባለበት ተባይ አለ።አንዱን ተባይ ብታጠፉት ሌላ ተባይ ይተካል።ይህ ደሞ የኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን የመላው 3ኛ አለም ችግር ነው።የሀገሬን ችግር አጥፉ፣ ተባዩን ሕዝቡ ያጠፋል።አንድ መንገድ ብቻ የሀገሬን ችግር አያጠፋም። “ፕላን ኤ፣ ፕላን ቢ፣ ሲ ዲ፣ …ዜድ” ድረስ እቅድ ሊኖራችሁ ይገባል።ፕላን “ኤ” ስላልተሳካ እጃችሁን አጣጥፋችሁ ቁጭ ካላችሁማ ዝናል አልዘነበም ብሎ በረሀብ ከሚታመሰው ምኑን ተሻላችሁት?
ኢሕአዴግ ዘላለማዊ መንግስት እንዳልሆነ እኔም እናንተም እናውቃለን።ኢሕአዴግ ሲወድቅ ድህነትን የምታጠፉት እንዴት ነው? ሕዝባችንን ከረሀብ የምትታደጉት በምን ዘዴ ነው? በሙያችሁ ለሀገራችን ብልፅግና የምታደርጉት አስተዋፆ ምንድነው?በሽታ ከሀገራችን እንዲጠፋ፣ የሕፃናት ሞት እንዲቀር እንዳታደርጉ ዛሬ ኢሕአዴግ ማጅራታችሁ ላይ ቆሟል። ኢሕአዴግ ሲወድቅ የምትተገብሩት የተፃፈ ነገር የታለ?
መቼም ተምራችሁ ተመራምራችሁ ዲግሪ ጭናችሁ በማዕረግ (ፕሮፌሶር፣ዶፍቶር፣ ኢንጂነር፣…) በሚል ማዕረግ ተንቆጥቁጣችሁ የተፃፈ የሥራ አፈፃፀም ዕቅድ (“ፕሮጀክት ፕላን”) የለንም አትሉኝም። መሐይም የምትሏቸው ምንዥላቶቻችንና የምንዥላቶቻችን ምንዥላቶች በብራናና በትክል ድንጋይ ፅፈው ሺህ ዓመታት አስቀምጠው እናንተ በኮምቡጠር (ኮምፒውተር) ስልጡን ዘመን ምነው እጃችሁ ተያዘ?
እውነት ነው ጥቂት ምሑራን በገዢው መደብ መብታቸው ተረግጧል፣አንደበታቸው ተይዟል፣ እንዳይፅፉም እጃቸው ታብቷል። ግን ደሞ ምሑር ሁሉ በነሱ ጀርባ መሸሸግ አይችልም።ቢያንስ ዕቅዳችሁን እናንብብ፣ ራዕያችሁን እናጥናው።እኔ ዕቅዳችሁን አንብቤ የሀገሬን ረሀብና ችግር እንዳላጠፋ ለኮፒ ራይታችሁ ትሰጉ ይሆን?
የፖለቲካ መፅሔት፣መፅሐፍና ጋዜጣ እንደ አሸን ሲፈላ ምነው ስለ አባይ ወንዝ ታሪክ የፃፈ ሀበሻ ምሑር አላየን? ነጮቹ ደጀንን ዳሸን ብለው ታሪኩን ሲፅፉ ስለ ደጀን ተራራ ግድ የሚለው ምሑር ጠፋ? እኔ የምኖርበት ከተማ 80 ኪ.ሜ ርዝመት ስላለው ዶን ስለተባለው ወንዝ እያንዷንዷ ሜትር ታሪኩ ሲፃፍ የኛ አዋሽን የሚያስታውስ ምሑር ምነው ጠፋ?።እኔ ሳላነበው ቀርቼ ይሆን? እስቲ ይኸው ብላችሁ አሳፍሩኝ።
ስለ ዮርክ ሲቲ( ያዛሬዋ ቶሮንቶ) በሺህ የሚቆጠሩ መፅሀፍት ሲፃፉ ላኮመልዛ (የዛሬዋ ደሴ) የአንድ ምሑርን እንኳ ቀልብ አልስብ አለች። አንትሮፖሎጂስቶቻችን መድረክ ላይ ስለ ብሔረሰቦቻችን ሲደሰክሩ አንዲትም መፅሐፍ ሳይፅፉ ከዚህች ምድር እስከመጨረሻው ኮበለሉ።
ኢትዮክሎፔዲያ (ኢትዮፒያዊ ኢንሳይክሎፔዲያ)ን የፃፈው፣ አባይን ከመነሻው እስከ ሱዳን ጠረፍ በግሩ ተጉዞ ያስነበበን የአራተኛ ክፍል ግራጁዌት ነው።ለነገሩ እስካሁን የሀገራችንን ቅርፅ ለመለወጥ የጣሩት ምሑራን አይደሉም።ምን ያርጉ ዋርካ በሌለበት ብሳና አድባር ይሆን የለ?
አንድ በከተማችን የሚኖር ቀንደኛ የኢሓዴግ ደጋፊ በአንድ መጠነኛ ስብሰባ ላይ እናንተ ኢትዮጲያ ውስጥ ዲሞክራሲ የለም፣ ኢሕአዴግ አያሠራም ትላላችሁ። እኔ ላለፉት ሁለት ዓመታት ወደ አዲስ አበባ ጠቅልዬ ገብቼ እየኖርኩ ነው። እናንተ የምትሉትን ነገር አላይም። እያለ ሲናገር “ክራር የቅኝቱን ይጫወታል ብዬ የተረትኩት እኔ ነበርኩ። ይህ ሰው ግን አንድ ቁምነገር ተናሯል። ዶክተር ብርሀኑ ነጋ እስር ቤት ሆኖ 615 ገፅ ሙሉ ኢሓዴግን እየተሳደበ ፅፎ እንዴት ነው ዲሞክራሲ የለም የምትሉት…?”
ከዚህ አንድ ነገር አስተዋልኩ። ለሀገራችን ለመስራት ጭላንጭል አለ። እንጠቀምበት።
ከሰሜን አሜሪካ ሐደው የመጓጓዣ ወጪያቸውን ራሳቸው ሸፍነው፣በራሳቸው የሕክምና መሣሪያዎች፣በሺህ የሚቆጠሩ የልብ ሕሙማንን ያለምንም ክፍያ እንዴት ተሳካላቸው? WWW.ENAHPA.ORG ይመለከቷል።
ከካናዳ ሔደው ሀምሳ ሺህ ዛፍ ተክለው የተመለሱትን እስቲ ንገሩን በኢሃዴግ ላይ ምን አፍዝ አደንግዝ ሰርታችሁ ነው ውጤጣማ የሆናችሁት? WWW.ETHIORAINMAKER.COM ይመለከቷል።
አንድ ግለሠብ (አቶ ሳህሌ ወንዳፍራው) ብቻውን አሠበ ተፈሪ ከተማ ገብቶ ሲያለማ የተጠቀመበት ዘዴ ምንድነው? ኢህአዴግን እንዴት አቸነፈው?ጋሽ አበራ ሞላ አዲስ አበባ ላይ ለውጥ ሲያመጣ በኢሃዴግ ላይ ያደረገው ድግምት ምንነበር? http://www.ethioselfhelp.org/actions.html ይመለከቷል። እነዚህን ወያኔዎች ናቸው? እንግዲያውድስ እነሆኝ ወያኔው። መወየን ማመፅ፣ መሸፈት፣ነው፣ ብያችሁ የለ? እኔም በናንተ ላይ ወየንኩ።
ላለፉት ሶስት ዓመታት የኢትዮጲያን ረሐብ ለማጥፋት ዘመቻ የጀመረ ኢትዮጲያዊ “ኢህ አዴግ ችግር አልፈጠረብህም ወይ? ሲባል ለጋዜጣ የሰጠውን መልስ ላጋራችሁ
“…ብዙዎቻችን፣በውጪ ያለነው ማለቴ ነው፤ ስራችንን፣ የስራ ባልደረቦቻቸንን፣ እንዲሁም አለቆቻችንን ወደናቸው አይደለም ስራ የምንሄደው ከስራ የምናገኘውን ጥቅም ፈልገን ነው።
የኢትዮጲያን ረሃብ ለማጥፋት ከጠላቶቻችንም ጋር ቢሆን መስራት መቻል አለብን። የሃገራችንን ረሃብ ለማጥፋት ተራራውን ደልድላችሁ ሜዳ አድርጉልን አሊያ አንሰራም አንልም፤ወይንም የተመቻቸ መንገድ ብቻ አንመርጥም እሾሁንም ቆንጥሩንም ጋራውንም ተራራውንም አልፈንም ቢሆን ሃገራችንን ከረሃብ ነጻ ማውጣት አለብን።…”
በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን ላይ ሰርተው ውጤት ያመጡትን ምሁራንንና ቀናኤ ኢትዮጲያውያንን በታላቅ አክብሮት እጅ መንሳት እፈልጋለሁ።
ማጠቃለያ
ጎፈር የሚባል የ ኤሊ ዝርያ አለ። ይህ ዔሊ እስከ 120 ሜትር ውስጥ ለውስጥ መንገድ ይቆፍራል።ይህ ዔሊ የቆፈረውን 400 የሚሆኑ እንሰሳት ለመጠለያነት ይጠቀሙበታል።ይህ ዝርያ ከምድረ-ገፅ ቢጠፋ ወይንም መቆፈር ቢተው፣ 37 ዝርያ ያላቸው እንሰሳት በመጠለያ ዕጦት ይጠፋሉ። እናንተ ለኢትዮጲያ ጎፈር ዔሊ፣ ያ ደሀ ገበሬ ደግሞ በናንተ ተማምኖ የሚኖር ነው። እናንተ እጃችሁን አጣጥፋችሁ ስለተቀመጣችሁ እሱም እስከዛሬ በወገልና በድግር ያርሳል፤በጥማድ በሬ ሞፈር ይጎትታል፤ ስሩ፣ ከተቀመጠበት አንስታችሁ አሰሩት። አሊያ መማራችሁ ካልጠቀመው አልተማራችሁም። እኔም እንደናንተው ብዙ አወራሁ መሰለኝ።ለዛሬ ይብቃኝ በሚቀጥለው ስላልታወቁት ተራሮች ይዤ እቀርባለሁ ውድ ኢትዮጲያውያን ውለታ ዋሉልኝ። (ምሑራንን አይመለከትም) ምሑር ሲያጋጥማችሁ ለሀገርህ ምን ሰራህ? ብላችሁ ጠይቁልኝ።
ጠመኔ ነኝ
ቶሮንቶ ካናዳ temenew@yahoo.ca