Jump to content

ኪቼፓ

ከውክፔዲያ

የኪቶላ ብሔረሰብ በጥታዊት ኢትዮጵያ ታሪክ በጋርዱላ ሰንሰለትማ ተራራ ዙሪያና አካባቢ እንዲሁም በጋንጁሊ ስምጥ ምስራቃዊ ተራራና አካባቢ የሚኖር የጋሞ ጎፋ ክፍለ ሀገር በጋርዱላ አውራጃ ሥር ይተዳደሩ ከነበሩ ከአምስቱ ወረዳዎች አንዷ የጋርዱላ ዙሪያ ወረዳ ሕዝብ ናቸው። የብሔረሰቡ መጠሪያ ስያሜውን ትርጓሜውም «ሕዝባችን» ማለት እንደሆነ መረጃዎች ያስረዳሉ። ጊዶሌ የሚለው የከተማዉ ስያሜ የመጣው በዚሁ ታሪካዊ ሥፍራ ከሚኖሩ ብሔረሰብ “ኪቶላ” ከሚለው ስም ነው። ይህ ብሔር ሰፊና በውስጡ አምስት የመጀመሪያዎቹ ማህበረሰብ ወይም በአካባቢዉ እሳቤ “ቃንዻ ሁሳት” የያዘ(ኩሱሜ፣ ማሾሌ፣ ሞስዬ፣ ዺራሼ እና ዾባሴ ማህበረሰብ) እንዲሁም በአካባቢው የሚኖሩ የተለያየ ታሪካዊ ዳራ ያላቸው መጤ ሕብረሰብን በአንድነት ያቀፈ ታላቅ ሕዝብ ነው።

በ1999 ዓ.ም በተደረገ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤት መሠረት የብሔረሰቡ ሕዝብ ብዛት 174,532 ነው፡፡

መልክዓ ምድር

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የኪቶላ ወይም ጋርዱላ ምድር ሦስቱን የአየር ንብረት ወይም ጸባይ የታደለች በመሆኗ እንደየአየር ጸባዩ የተለያየ የማሽላ ዓይነት፣ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ገብስ፣ ስንዴ፣ አደንጓሬ፣ ባቄላ፣ አተር፣ እንሰት፣ እና ሌሎች በርካታ አዝርዕት በከፍተኛ ምርትና ምርታማነት የሚመረትባት፤ ህዝቦቿ ስራን እንደስራ ብቻ ሳይሆን እንደባህል አድርጎ በመውሰድ(ወንድና ሴት እኩል ይሰራሉ) ገና ሳይነጋጋ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ማልደው በመነሳት በ‹‹ሎላት›› እርስ በርስ በመቀሳቀስ ወደ በረሃ ወይም ማሳ የተመመው ከምሽቱ ሁለት ሰዓትና ከዚያ በኋላ ወደ ቤት ይመለሳሉ። ገና ከጥንት ከጥዋቱ በሚታወቅ ምክንያት ኩታ ገጠም አስተራርስን ባህሉ ያደረገው፣ የ‹‹ታርጋ›› ባለቤት የሆነው፣ ዓመቱን ሙሉ፣ ወሩን ሙሉ፣ ሳምንቱን ሙሉ፣ አስራ ሰባት ሰዓት በቀን የሚሰራ ማህበረሰብ፤ የቁጠባ ባህልን በእህል ጉድጓድ ወይም በ‹‹ፖሎት›› ያስረገጠ፣ ራብተኛንና ችግርተኛን በ‹‹ኩር›› የረዳ፣ ባህላዊ መጠጥ ‹‹ፓርሾት›› በማዘጋጀት ያለውን በጋራ የሚበላ፣ እንደ እነ ‘Kala’, ‘Dha’et’ እና ‘Dhingam’ በመሳሰሉት ህብረት የሚሰራ ድንቅ ሕዝብ ነው። ስለሆነም ሕዝቡ “ከእጅ ወዳፍ ወደ ስንቅ” በሚል መሪ ቃል እየሠራ ከራስ አልፎ ለሌላዉም የሚተርፍ ታሪካዊ ሕዝብ ነው። ማህበረሰቡ ከእርሻ ሥራ በተጓዳኝ የከብት እርባታ እና የንብ ማነብ ሥራንም ያከናውናል።

“የኪቶላ” ብሔረሰብ በአብዛኛው በጎሳ ሥርዓት የሚተዳደር(ዘጠኝ ጎሳዎች ያሉአቸው)፤ እያንዳንዱ ጎሳ እኩል ዋጋ፣ ቦታና ክብር ያለው፤ በአንድ ጎሳ ውስጥ ያሉ በሙሉ እንደ አንድ ቤተሰብ(እህትና ወንድም፣ አባትና ልጅ፣ አክስትና ልጅ) የሚታሰብ ሲሆን፤ አምስቱም ማህበረሰብ የሚያመሳስላቸው የጋራ የሆነ ባህል፣ የቋንቋ ዘይቤ፣ አምልኮት፣ የዘር ግንድ እሳቤ፣ ብሔራዊ አመለካከት፣ ወዘተ አላቸው። ኪቶላ ሕዝብ በጋርዱላ ምድር ላይ ከዝንታዓለም ጀምሮ የሚኖሩ፣ የራሳቸው የሆኑ የማንነት መገልጫ እሴቶች ያላቸው፣ በጥንት ኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የራሳቸው የሆነ ጉልህ አስተዋጽዖና አሻራ ያላቸው አሁንም በኢትዮጵያ ግንባታ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ እያበረከቱ ያሉ፣ በአብዛኛው በግብርና ሥራ(በተጓዳኝ የከብት ማርባትና የንብ ማነብን ሥራ በከፊሉ የሚሠሩ) የሚተዳደሩ፣ ከአጎራባች ወንድም ብሔረሰቦች ጋራ በሰላምና በመከባበር የሚኖር ሕዝብ ነው። ሕዝቡ በመሠረታዊነት የኩሽ ቤተሰብ ቋንቋ የሆነውን ኪዶ’ሊያ ከመናገር ባሻገር፤ አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ጋሙኛ፣ ወላይትኛ፣ እና ሌሎች ቋንቋዎችን የሚናገሩ ትንሿ ኢትዮጵያ ናቸው።

ኪቶላ የኢትዮጵያ ብሔር ነው።