ውክፔዲያ:ታሪካዊ ማስታወሻዎች/ሐምሌ 26

ከውክፔዲያ
ከሰባት አመታት በፊት ሳሲት* ከተማ አቅራቢያ ታሪክ ራሱን ደገመ፡፡ ዛሬ ላይ ሆኖ ሲያስቡት ይደንቃል፡፡ ድርጊቴንና ወኔዬን ከዳኛቸው ወርቁ ልቦለድ ገጸባህሪ ከአደፍርስ እንግዳ ተግባራት ጋር እንዳወዳድር ይዳዳኛል - ከቋንቋ ተማሪነት ወደ አማተር ጂኦሎጂስት ወይም አርኪኦሎጂስትነት ተለውጬ ነበርና፡፡ ሳሲትና አካባቢዋም ከ70 አመታት በኋላ ባለውለታዋን አስታወሰች፡፡ በሳሲትና አካባቢዋ ነዋሪዎችና በዋሻዎች መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ቁርኝት ሊያሳይ የሚችለው ቀላሉ ነገር የተለያዩ ስፍራዎች የተሰየሙበት ከዋሻ ጋር የተያያዘ ስማቸው ይመስላል - ቀለም ዋሻ፣ ጠጠር ዋሻ፣ ጅብ ዋሻ፣ እንግድዋሻ፣ ልሳንዋሻ፣ ምግልዋሻ፣ አምባዋሻ፣ እምብስ ዋሻ፣ ጽድ ዋሻ፣ ንብ ዋሻ፣ ድል ዋሻ፣ ወርቅ ዋሻ፣ ላም ዋሻ፣ ጨለማ ዋሻ፣ ዋርካ ዋሻ፣ ሾላ ዋሻ …

በታሪካዊ ልቦለዱ በአዳባይ ላይ እንደተገለጸው ‹‹በ1931 ዓ.ም. በአንቀላፊኝ የራስ አበበ የጦር አዝማቾች ከምሁራን ባልደረቦቻቸው ጋር ባደረጉት ውይይት ‹የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖቸ አርበኞች ማህበርን› አቋቁመው ፈረሙ፡፡›› (ገጽ 166-7)፡፡ አንቀላፊኝ ሜዳ እና ሌሎችም ታሪካዊ ስፍራዎች በትውልድ አካባቢዬ ቢገኙም በቅድሚያ የመጎብኘት ትኩረቴን የሳበው ከሳሲት እስከ ሰላድንጋይ በምድር ውስጥ ያስኬዳል ተብሎ የሚታመንበት ዋሻ ነበር፡፡ 20 ኪሎሜትር ገደማ ‹‹ይረዝማል›› ይባላል፡፡ ዋሻ መሸሸጊያ መሆኑ በታሪክ የታየበት ጊዜ አለ በሞጃ እና ወደራ ወረዳ፡፡ በጣሊያን ወረራ ወቅት ልጅ ሆነው ተሸሽገውበት እደነበረ ያጫወቱኝ አቶ ማሞ ገብሬ፣ ካሳዬ ወንዳፈረው የተባለ የአካባቢው ተወላጅ አርበኛ ከጣሊያን ወራሪ ወታደሮች ጋር እየተታኮሰ የአካባቢውን ህዝብና ከብት ይዞ ወደ ዋሻው እንደገባ፣ ከብቱን የፋሽስት ወታደሮች ከዋሻው አውጥተው ሲያርዱና ሲጥሉት ህዝቡ ግን ራሱን ተከላክሎ ወደ ውስጥ ገብቶ እንደዳነና በማግስቱም የአምስት አመት የስደት ጊዜ ለማሳለፍ ወደ ይፋት እንደወረደ ዋሻውም መጨረሻው እንደማይታወቅና ሰላድንጋይ ይደርሳል ሲባል እንደሰሙም ነግረውኛል፡፡ አቶ አስፋውና አቶ ተክለወልድ ደግሞ ከደጋው ህዝቡ ሲያባርረው የመጣን ጅብ ዋሻው ውስጥ ሊገባ ሲል እንደገደሉት አጫውተውኛል፡፡ ከአብዛኛዎቹ ተጠያቂዎቼ እንደሰማሁት ግን በአንድ ወቅት አንዲት ውሻ በዋናው በር ስትገባ ታይታ ሰላድንጋይ ለጉዳያቸው የወጡ ስትገባ ያዩዋት ሰዎች እዚያም ባለው በር ስትወጣ አይተዋታል እየተባለ እንደሚተረት ነው፡፡ እንዲያውም የዋሻው የሰላድንጋዩ መውጫ በሩ ቁሮ ገደል በተባለ ስፍራ እንደሚገኝ ነግረውኛል፡፡ ለተጠያቂዎቼ ግን ‹‹ይህን ያህል ርዝመት እንዳለው አይታችኋል›› ስላቸው ‹‹እሱ ተብሎ ያለቀ ነው›› ይሉ ነበር፡፡ በህዝቡ ዘንድ የሚወራውን ለማረጋገጥ ዘመቻ ግድ ይል ነበር፡፡

ለ15 ቀናት ያህል ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ስለዚሁ ጉዳይ እንመክራን፤ ስለ ዋሻው የሰሙ ሰዎች መጥተው የሚነግሩኝንና ለዝግጅት የሚያስፈልጉትን ቁሳቁስም እጽፋለሁ፡፡ እንደነፍሰጡር ቀናችንን መቁጠሩ የባሰ ጉጉት አሳደረብን፡፡ ከመካከላችን አንዳንዶቹ የሚያነሷቸው ሃሳቦች የሚከተሉትን ይመሳስሉ ነበር - ‹‹ወደ ዋሻው ገብተን ብንጠፋፋና የዋሻው በር ቢጠፋብን የት እናገኘዋለን?›› እና ሌሎች ደግሞ ‹‹ስንሄድ ባህር ወይም ጎድጓዳ ስፍራ ቢገጥመን ተቀርቅረን መቅረታችን አይደለምወይ?›› ይላሉ፡፡ አስጊ ሁኔታ ነበር፡፡ ከአዛውንቶች በሰበሰብኩት መረጃ መሰረት ዋሻው ወደተለያየ አቅጣጫ የሚወስዱ መንገዶች ስላሉት አንዱን ተከትለን ሰው ወደ ጎን እንዳይሄድ እየተቆጣጠርን መሄድ ፣ ሰላድንጋይ ከተማ የሚያደርስ ከሆነ መንገዱ እንደ መሬት ላይ መንገድ ስለማይቀና ስንቅ ቋጥረን የፈጀውን ያህል ጊዜ ይፍጅ እንጂ የዋሻውን መጨረሻ ማየት አለብን አልን፡፡ በጉዟችን ወቅት ድቅድቅ ጨለማውን ለማብራት ችቦ፣ ጧፍ፣ ማሾ፣ ባትሪ እና ሻማ እንያዝ የሚሉ ሃሳቦች መጡ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ችቦ ጭሱ ያፍነናል ባትሪም ዋሻው ውስጥ አይበራም በማለታቸው ማሾ እና ጧፍ ለመያዝ ተስማማን፡፡ መሽቶ ሲነጋ ሁለት ሳምንት ቀኑን ሙሉ ስለዚሁ ዋሻ ስናወራ እንውላለን፡፡ገብተን ሰይጣን ልናገኝ፣ ለደህንነታችን የሚያሰጋ ተአምራዊ ሁኔታ ሊገጥመን ይችላል የሚሉ ሰዎችን ስጋት ወደኋላ እየተውን ለመግባት የሚያስፈልገውን የቁሳቁስም ሆነ የስነልቦና ዝግጅት ቀጠልን፡፡ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ከመሬት በታች መላዕክት እንደሚኖሩ፣ ሰዎች የሚኖሩበት ሌላ ሃገር እንዳለ፣ በዶሮ የሚታረስበት ግዛትም እንደማይጠፋ ስንሰማ አድገናል፡፡ ምናልባት ይህን የምናይበት ሌላ አለም ሊገኝ ይችላል ብዬ እኔም አስብ ሌሎችም በአዕምሯቸው ያወጡና ያወርዱ ነበር፡፡ሰው ባገኘኝ ቁጥር አስረዳለሁ፤ ጥያቄዎቻቸውንም እመልሳለሁ፤ በሰዎቹ ፍላጎት ደስታና እርካታ ይሰማኛል፤ እጓጓለሁ፤ እገረማለሁ፡፡ በአካባቢያችን ሌሎች መሰል ዋሻዎች አሉ ቢባልና እኛም ብናውቅ መጀመሪያ ያደረግንውን ይህን ዋሻ ለመጎብኘት አንድ ቀን ቀረን - ቅዳሜ መስከረም 6 ቀን 1999 ዓ.ም. ፡፡ በትውስት ማሾዎች ጋዝ ሞላን፤ ጧፎቻችንን ገዛን፤ ሻማና ሌሎችንም እንዲሁ አሟላን፡፡ ሰዉ በማቴሪያል፣ በገንዘብ እንዲሁም በጉልበት ከጎናችን ስለነበረ ነው ዓላማችንን በመጠኑ ለማሳካትና ይህን ለእናንተ ለመንገር የበቃንው፡፡ በማግስቱ በዋሻው አቅራቢያ ያሉና ሊገቡ የተስማሙ ገበሬዎች በጠዋት እንድትመጡ ስላሉን ሕዝቡንም ለመቀስቀስ ከሌሊቱ 11 ሰአት ላይ ከእንቅልፌ ተነሳሁ፡፡ ጓደኞቼን ቀስቅሼ ሌሎችንም እንዲቀሰቅሱ አሳሰብኩ፡፡ ከነጋ በኋላ ወደ 12፡30 ሰአት ላይ ተጠቃለን ጉዟችንን ለማድረግ ከከተማዋ እምብርት ተነሳን፡፡ ያሰብንውን ያህል ባይሆንም ወደ ሃያ አምስት ያህል ሰዎች ተሰባስበናል፡፡ በየቤቱ እየሄድን ስንቀሰቅሳቸው በሰበብ ባስባቡ እንደማይሄዱ አስተዛዝነው ይነግሩናል፡፡ እኛም ‹‹አላስገደድናቸው ከመጀመሪያው ለምን እሺ አሉ? ሰው ሂድ ብሎ ሳያስገድዱት እሄዳለሁ ይላል እንዴ?›› ብለን ታዘብናቸው፡፡ ለማንኛውም እኛው እንበቃለን ብለን ዝግ ባለ አረማመድ ከተማዋን ለቀን ወደ ምዕራብ ስንጓዝ ሰው ሁሉ ያየናል፡፡ ‹‹አረ የነብር ቁርስ እንዳትሆኑ!›› ሳይል አይቀርም ተመልካቹ - ካይኑ ያስታውቅበታል፡፡ ከተማዋን ለቀን ወደገጠሩ ስንገባ ሰዎች ከዚህም ከዚያም እየሮጡ ከከተማዋም ጭምር ተከተሉን፡፡ በርከትከት እያልን መጣን፡፡ በየቤቱ እንዲሰማ አድርገን የምናውቃቸውን ሰዎች ተጣርተን ብዙ ሰዎች ለመሰብሰብም ቻልን::

ወደ ሰሜን ታጥፈን ቁልቁል ከወረድን በኋላ አፋፉ ላይ ስንደርስ መንዝን ካድማስ ወዲያ ማዶ እያየንና የቆላማውንም ስፍራ ልምላሜ እያደነቅን ለደቂቃዎች እንኳን ሳንቆይ፣ አያቴ ‹ያ ማዶው ሰላሌ ነው› የሚለኝን ጨለማ አገር ቃኝተን ሳንጠግብ አትኩሮታችንን ወደ ተጉለቱ ድንቅ ዋሻ መለስን፡፡ የአካባቢው ገበሬም ቀድሞን ዋሻውንና አካባቢውን ወሮታል፡፡ በዙሪያው ከሩቁ የሚታዩትና ነጫጭ የለበሱት እነዚህ ሰዎች የጥንት አርበኞችን ያስታውሷችኋል፡፡ ደምቃ ፍም መስላ ከወጣችው የጠዋት ፀሀይ ግርጌ ከግራና ከቀኝ ትልልቅ ተራሮችን የተሸከመውና በመሃልም ሸለቆ የሚንፈላሰስበት ባለረጅም አፉ ዋሻ በአረንጓዴ ቅጠላ ቅጠል ተከቦ፣ በሸለቆው ውስጥ የሚመጣው ወንዝና በዋሻው መግቢያ ፊት ለፊት የሚወርደው ፏፏቴ አንድ ላይ ሆነው ሌላ ተፈጥሯዊ ገጸ በረከት እነሆ አሉን፡፡ አንዲት አጎንብሳ ጸጉሯን በሳሙና የምታሽና ጸጉሯም በመታጠቢያው ሳፋ ላይ ለሽ ያለን ኮረዳ ያስመስለዋል፡፡ ጸጉሯን በፏፏቴው፣ ከንፈሯን በዋሻው አፍ ፣ ሁለቱን ትከሻዎቿን በተራሮቹ እንዲሁም ሳፋውን እታች ፏፏቴው በሚያርፍበት ባህር መመሰል ይቻላል፡፡ ይህን ሁሉ በማየቴ ተደነቅሁ፡፡ ከባልንጀሮቼ ጋር ወደዋሻው ተጠጋሁ፡፡ የሀገር ሽማግሌዎች በዋሻው በር ላይ ተቀምጠው ታሪክ ያወራሉ፣ ይመክራሉ፡፡ ዋሻው በጎንና በጎኑ መግቢያ መንገድ ስላለው ሸረር ብለን ገባን፡፡ አቤት የነበረ ጥድፊያ! አቤት ያን ዋሻ ተጠግቶ ሲያዩት ያለው ግርማ ሞገስ፡፡ ውስጥ ስንገባ አናቱ ደማቅ ጥቁር ፣ መሬቱ ደግሞ ቀይ ደረቅ ለስላሳ አፈር ሲሆን ጣራው የጠቆረው አባቶቻችን በጣሊያን የግፍ ወረራ ጊዜ በችቦ ለብልበውት ነው ተባልን፡፡ ምክንያቱም ማዕድን ሊሆን ስለሚችል በጣሊያኖች አይን እንዳይገባ ተብሎ ነበር፡፡ ሲፈረፍሩት የሚያብረቀርቅ ልዩ አለት እየተፈረፈረ ይወርዳል፡፡ የወንዙ/የፏፏቴው ውሃ በፊታችን ወርዶ መሬት ላይ ሲያርፍ የሚያሰማው ልዩ ድምጽ ልብን ያሸብራል፣ አዕምሮን በአንዳች ፍርሃታዊ ምትሃት ያርዳል፤ ሁለመናን ይቀሰቅስማል፡፡ ሽሽሽ… ቻቻቻ… ይላል፡፡ ይህም በአቅራቢያው ካለው አያልፉሽ ከተባለው የጸበል ቦታ፣ ከአጃና ሚካኤልም በላይ ምጡቅ ነበር፡፡ ባሕታዊነትን ያስመኝማል፡፡ በዋሻው አቅራቢያ ያለው ስነ-ሕይወታዊ መስተጋብር ለዘርፉ ምሁራን ለም የምርምር ቦታ ሊሆን ይችላል፡፡ አይደርሱ የለ ደረስን፣ አየንው የንን የጓጓን የቋመጥንለትን ዋሻ! ታዲያ አፉን እንጂ ሆድ እቃውን ለማየት ገና በዝግጅት ላይ ነበርን፡፡ ማሾዎች ተለኮሱ፤ ጧፉንም ያዝንና ታጥቀን ተመራርጠን ተነሳን፡፡ የዋሻውን አፍ ርዝመት ለክተን 105 ሜትር መሆኑን አረጋገጥን፡፡ ከፍታውም በመግቢያው በር አካባቢ ከ3 ሜትር ቢበልጥ እንጅ አያንስም፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ በጉንብስ አለያም በጣም ዝቅ ሲል በደረት መሄድ ግድ ይላል፡፡ በውስጠኛው የዋሻው ክፍል አለትና ቋጥኝ፣ የጅብ ጽዳጅ፣ የእንስሳት ብሎም የሰው አጽም አግኝተናል፡፡ ዙሪያውን አሰስንው፤ ጎበኘንው፡፡ ሆኖም ግን በዚያ በሰፊው የዋሻው ክፍል ውስጥ ወደ ውስጥ መፈናፈኛ ጠፋ፡፡ ‹‹በምን ተገብቶ ነው ሰላድንጋይ የሚደረሰው?›› ብዬ ላቀረብኩላቸው ጥያቄ አብዛኛዎቹ ተጠያቂዎቼ ‹‹በግለሰቦች ተደፍኖ ነው እንጅ በር ነበረው ፤ የቱጋ እንደሆነ ለማግኘት ከቋጥኙ መብዛት የተነሳ አልቻልንም›› አሉኝ፡፡ ቋጥኞቹን አልፎ ሄድ ሲሉ በዋሻው የቀኝ ክፍል ወደ መሬት የሚያሰገባ መንገድ አግኝተው የተወሰኑት ጓደኞቻችን ገቡ፡፡ አንዲት ሽንቁር ማሰሮና ሁለት የሰው የራስ ቅል ይዘውም ተመለሱ፡፡ ደረጀ አስራተ የተባለው ሌላኛው ዘማች ደግሞ በዋሻው መግቢያ ትይዩ ባለው አቅጣጫ ‹‹ጎራዴ ና ባትሪ ብቻ ስጡኝ›› ብሎ በአንዲት ሰው ሁሉ በፈራት ጠባብ ጎሬ አልፎ ሄዶ ቀረብን፡፡ ግማሹ ሰው ፈራ ተባ እያለ ‹‹ወደ ኋላ ልመለስ ወይንስ ልጠብቀው፣ ጅብ በልቶት ይሆን ነብር?›› ሲል፣ ደምሰው ታችበሌ በልበሙሉነት ሲጋራውን ሲያጨስ በመጨረሻ የደረጀ ድምጽ ሲሰማ ህዝቡ እፎይ አለ፡፡ እኔም ደስ አለኝ፡፡ ‹‹ምን አለ›› ስንለው ‹‹የሆነ ወደላይ የሚያስወጣ መንገድ አለ ወጥቼ ልምጣ›› ሲለን እንደገና ደንገጥ አልንና ጠበቅንው፡፡ ‹‹አይይይ ምንም የለ›› ሲል አንድ ሆነ፡፡ ወደ አስር የሚሆኑ በዋሻው የግራ አቅጣጫ የሄዱ ሰዎች ደግሞ ትንሽ ሄደው ሰማይ ሲያዩ ‹‹ሌላ አገር የደረስን መሰለን›› ብለው ጮሁ፤ ግን ሌላ የዋሻው መግቢያ በር ነበር፡፡ ስለዚህኛው መግቢያ በር፣ ከዋናው በር ሌላ መሆኑ ነው፣ በዚያኛው ቡድን በኩል ባለመሆኔ ማየት ባልችልም ከሰማሁት ለመናገር ግን እችላለሁ፡፡ እኔ የነበርኩት በበሩ ትይዩ በነበረው አቅጣጫ ነበር፡፡ አቶ ታደሰ ዘነበ እንደነገሩኝ ደግሞ በዚሁ በቀኙ አቅጣጫ ወደታች አይቼ ልምጣ ብለው ገብተው ጓደኞቻቸው ጥለዋቸው/ረስተዋቸው ሄደው መውጫው ጠፍቷቸው ለደቂቃዎች ተቸግረውና ቢጣሩ የሚሰማቸው አጥተው በስንት ፍለጋ የገቡባትን ከሰው ትከሻ የማትሰፋ በር አግኝተው ወጥተዋል፡፡ ‹‹እኔ ተቻኩዬ ተመለስኩ እንጂ ያችማ ያች የተባለችው ከጎተራ አፍ ትጠባለች ያሏት ወደሰላድንጋይ የምታወጣው የጠፋችብን ዋናዋ በር ሳትሆን አትቀርም፤ ስንትና ስንት መንገድ እኮ ሄጃለሁ፤ በደንብማ ቢፈለግ ይህ ዋሻ አንድ ነገር አይጠፋውም ›› ብለዋል በእለቱ ከሰዓት በኋላ ጉዟችንን ስንገመግም፡፡

በሁሉም አቅጣጫዎች የአለቱን ብዛት አንድ መሃንዲስ ቢኖር በቢያጆ ይገምትልን ነበር፡፡ አንድ ትምህርት ቤት ይሰራል፡፡ ወደፊት በዚያ ዋሻ ሄደን ምናልባት ሰዎች ካገኘን ለልጆቻቸው ትምህርት ቤት መስሪያ ስሚንቶ ብቻ ከገዙ ይበቃቸዋል፡፡ ዋሻችን ከላይ የሚያዥ ነገር እና መሬትም ላይ የዚያው ክምችት (stalactites and stalagmites) ብዙ ቦታዎቹ ላይ አለው፡፡ ወለሉ ጫር ጫር ሲያደርጉት አፈሩ ልስልስና በእጅም ቢዝቁት የሚዛቅ ነው - ልክ አሸዋ በሉት፡፡ አንዳንዴ በቡድን በቡድን ሆነን ስንድህ ልጅነታችንን ያስታውሰናል፡፡ ከዚያ ደግሞ ሄደን የሚያስቆምና የሚያስፎክር ቦታም እናገኛለን፡፡ በእንደዚህ አይነት ጉዞ ታዲያ መደራጀትን የመሸሽ ችግር አይቀረፍምና ‹‹በቃ እንሂድ፤ በቃ አገራችን እንውጣ!›› እያሉ ካስቸገሩትና ባጭሩ ተስፋ ከቆረጡት በላይ አንዳንዶቹ ከዋሻው እየወጡ ወደ ሳሲት ይመለሱ ጀምረው ነበር፡፡ አንድ ሽማግሌ ደግሞ ከዋሻው በር ላይ ካለው ካብ ላይ ትልልቅ ድንጋይ እያነሱ ታች ቆላ ወዳለው ባህር ሲወረውሩ ረበሹኝ፡፡ ‹‹አረ ተው አብዬ ምነው?›› ሲሏቸው መች ይሰማሉ፡፡ ብቻ ይስቃሉ ደስ ብሏቸዋል መሰለኝ ቦታው፡፡ ይህ በዋሻው በር ላይ የተካበው ካብ አርበኞች ምሽግ አድርገው ይጠቀሙበት የነበረ ይመስለኛል፡፡ በጎብኝዎቹ መጣደፍ ምክንየት ብቻ ከሰአታት መጠነኛ አሰሳ በኋላ ወደ ሳሲት ከተማ በዋሻው በር በሌላኛው አቅጣጫ ወጥተን ትንሽ ዳገትም (ልዩ ስሙ ትልቅ አረህ) ፈትኖን የመልስ ጉዟችንን ያልተመለሱ ጥያቄዎች ይዘን ጀመርንው፡፡ የወረድንው በጭጨት ነበር፡፡ ብዙም ተጉዘን እረፍት ተደረገና ወደ ከተማችን ደርሰን አንድ ቤት ገብተን ውይይትና ጨዋታው ቀለጠ፡፡ ከጉዟችን በኋላ ገበሬው ማዕድን አለበት እያለ የዋሻውን አናት ያገልሰው እንደያዘ ሰማን፡፡ በጣሊያን ወረራ ወቅት ከተደረገው ቀጥሎ (ከሰባ አመታት በኋላ) ህዝብ ተነሳስቶ የገባበት ትልቁ ዘመቻ በዚህ መልኩ ተጠናቋል፡፡ ሌላ ጉብኝትና ጥናት ለማድረግ ሰባ አመታት እንጠብቅ ይሆን? ስለተነሳሽነቱ ህዝቡን ባያሌው አመሰግናለሁ፡፡ ህዝቡ ያለው ‹‹ዱሮስ እሱን አምነን›› ሳይሆን ‹‹ይህ ዋሻ ቀን ይወጣለታል›› ነው፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዶ/ር ሲቪል መሃንዲስ ሀይለጊዮርጊስ ወርቅነህ የህይወት ታሪክ ላይ እንደተመለከተው ከሶስት መቶ በላይ የአርበኛ ጦር ከነቤተሰቡ በሳሲት አቅራቢያ ባለ አንድ ዋሻ መሽጎ ነበር፡፡ በተጉለት ሌሎች አርበኞችን ፍለጋ የሚዘዋወረው ይህ ጦር ዋሻ ውስጥ እንደመሸገ በአካባቢው ነዋሪዎች ይጠቆምበትና በአንድ ሺህ የጣሊያን ጦር ይከበባል፡፡ አስራ አራት ቀን ሙሉ በረሃብ ተሰቃይተውና ከዋሻው የላይኛው ክፍል የሚያዠውን ውሃ እየመጠጡ፣ ኮርቻ ፈልጠው እያነደዱ የጤፍ ቆሎ እየቆሉ እየበሉ፣ የጣሊያን ጦር እየተኮሰባቸው ከቆዩ በኋላ በአስራ አራተኛው ሌሊት ወንዶቹ ጥሰው ሲወጡ ተጨፈጨፉ፤ አስራ ሁለት አመት ገደማ ያሉ ወንድ ልጆችም ተረሸኑ፤ ሴቶቹና ህጻናት መጀመሪያ ወደ መንዝ ከዚያም ወደ ደብረ ብርሃን እስርቤቶች ተወሰዱ፡፡ ከላይ የተጠቀሱትም ዶ/ር በዚያን ወቅት አስር አመታቸው ሲሆን በኋላ አድገው ተምረው አለምአቀፍ ምርምሮችን አቅርበው ተሸልመዋል፡፡ በሳይንስ መዛግብት ላይ ስማቸውን ያሰፈረላቸው እስከ 150 ኪሎሜትር ርቀት ጠጣር ነገርን የሚያስተላልፈው ቧንቧቸው ያስመሰግናቸዋል፡፡ (አልፈዋል)! ከመጽሀፋቸው የሚከተለውን እንመልከት ፡- ‹‹በዋሻው ውስጥ አባቴ፣ አጎቴ፣ እናቴና ያጎቴ ባለቤት እና ከዘጠኝ የሚበልጡ የቅርብ ዘመዶቻችን፣ እና ሌሎች ቤተሰቦች እንዲሁም ከ300 የሚበልጥ መሳሪያ ያለው ሰው ነበር፡፡ በዚያም ላይ የቀንድና የጋማ ከብቶችና የቤት እንስሳዎችን የመሳሰሉ ሁሉ ከዋሻው ውስጥ ነበሩ፡፡ ለጥቂት ቀናት የሚበቃ ምግብ፣ ውሃና ማገዶም ተይዞ ተገብቶ ነበር፡፡ ነገር ግን፣ ለ14 ቀናት ያህል በመከበባችን፣ ያ ይዘን የገባንው ምግብና ማገዶ አለቀ፡፡ ዋሻው ፊት ለፊት ከሚፈሰው ውሃ ለመቅዳት እንዳንችል፣ ጠላት ፊት ለፊት መሽጎ ይጠባበቅ ስለነበረ፣ በጣም አስቸጋሪ ሆነ፡፡›› የህይወቴ ታሪክ (10) ይህን ታሪክ እኔና ሳሲቶች የገባንበት እንግድዋሻ አለያም በሱው አቅራቢያ የሚገኘው ልሳን ዋሻ ሊጋሩት ይችላሉ፡፡ ልሳን ዋሻ በአንድ ቀን ብቻ ከ600 በላይ ሰው እንደተረሸነ አዛውንቶቹ አጫውተውኛል፡፡ ይህ ከላይ የተጠቀሰው ግድያ ሊሆንም ይችላል፡፡ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲም የታሪክ፣ የጂኦሎጂና የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎቹን አስተባብሮ ይህን ዋሻ፣ ሌሎችን ዋሻዎችና ታሪካዊ እንዲሁም ተፈጥሯዊ ስፍራዎችን ቢያስጠና ለአካባቢው ህዝብ ባለውለታ ያደርገዋልና ቢያስብበት እላለሁ፡፡ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ የፌደራሉ መንግስት፣ የአርበኞች ማህበር እንዲሁም ሌሎች ድርጅቶችም የተጉለት ቅርሶች ላይ የተቻላቸውን ሁሉ ቢሰሩ በማለትም አሳስባለሁ፡፡ ጣሊያን ቤቱን ሲያቃጥልበት ህዝቡ ዋሻዎች ውስጥ ነበር የኖረው፡፡ አሁንም ዋሻ እንደሚፈለግ ያሳየኝ ክስተት ቢኖር አንድ አዛውንት በ1999 ዓ.ም. ‹‹አንተ ልጅ ጓዳችንን ለምን ለሰው ታሳያለህ?›› ያሉኝ ነው፡፡ የእርሳቸውን ሃሳብ እያከበርኩ አሁን የአለም ሁኔታ እየተቀየረ መሄዱንና ዋሻ ውስጥ እስክንገባ የሚያሳድደን ነገር እንደማይኖር ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ዋሻውን ለአገር ጎብኝ እያሳየን የገቢ ምንጭ እንድናደርገው እና እኛም እንጎበኘው ዘንድ የሁላችሁንም ትብብር በሁሉም ዘማቾች ስም እጠይቃለሁ፡፡ በመጨረሻም ለጭቁን ህዝቦች አርዓያና መጽናኛ በሆኑት በኢትዮጵያ በአርበኞች መዝሙር ልሰናበት፡- ጥንታዊት ኢትዮጵያ እናታችን ሆይ አርበኛሽ ጽኑ ነው ቆራጥ ተጋዳይ የደሙ ምልክት ያው በልብሱ ላይ ጥንታዊት ኢትዮጵያ አትደፈሪቱ ጠላትሽ ግፈኛ አረመኔ ከንቱ፡፡ ጥንታዊት ኢትዮጵያ የጀግኖች ማህበር ጠላትሽ ተዋርዶ ስምሽ እንዲከበር እንሸከማለን የመከራ ቀንበር፡፡

አዳባይ (243)


  • ሳሲት ከተማ ከደብረ ብርሃን ከተማ በስተሰሜን 92 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የምትገኝ ተጉለቴ ነች፡፡ ከሞጃና ወደራ ወረዳ መዲናዋ ከሰላድንጋይ ደግሞ 20 ኪ.ሜ ትርቃለች፡፡ ሰላድንጋይን ብዙ ሰው በጻድቃኔ ማርያም ገዳም ያውቃታል፡፡