Jump to content

ውክፔዲያ:Today's featured article/ሓምሌ 9, 2010

ከውክፔዲያ

ማንኛውንም የሙቀት መጠን የሚቆጣጠሩ ረቂቅ መሣሪያዎች፣ በአኤሮፕላን ዋና አካል፣ በትንሹም ቢሆን፣ የመሰርጎድም ሆነ የመሰንጠቅ አደጋ ሲያጋጥም ወዲያው ወደ አንድ ማዕከላዊ የቁጥጥር ክፍል፣ የራዲዮ መልእክት ማስተላፍ የሚችል መሣሪያ፣ የጀርመኑ Fraunhofer የምርምር ተቋም ጠበብት ሠርተው በተሣካ ሁኔታ መሞከራቸውን፣ ከ ፍራይቡርግ አስታወቁ። አንዳች የኤሌክትሪክ ኅይል ማስተላለፊያ ሽቦም ሆነ ባትሪ የማያስፈልጋቸውና በአኤሮፕላን አካል የሚጣበቁት እጅግ የረቀቁ መሣሪያዎች፣ ጉልበት የሚያገኙት በአኤሮፕላኑ ውስጥና ውጭ ባለው የሙቀት ልዩነት ነው። በውጭ ከዜሮ በታች ከ 20 እስከ 50 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሲሆን ቅዝቃዜው፣ በአኤሮፕላን ውስጥ ተሣፋሪዎች በሚቀመጡበት ክፍል ደግሞ ሙቀቱ፣ 20 ዲግሪ መሆኑ የታወቀ ነው። የ ፍራውንሆፈር የምርምር ተቋም ባልደረባ የሆኑት ዲርክ ኤብሊንግ እንዳስረዱት፣ በአኤሮፕላን አካል የሚያጋጥም እንከንን የሚጠቁሙት መሣሪያዎች የሚገለገሉት «ማይክሮፔልት » ከተባለው ኩባንያ ጋር በመተባበር በተሠሩ በሙቀት ልዩነት ኃይል በሚያገኙ ጉልበት አመንጪዎች ነው። ሙከራው አመርቂ ቢሆንም፣ በሙቀት ልዩነት የማይቋረጥ ኃይል በማመንጨት በማጠራቀም ፣ እንዲሁም እንከን በመጠቆም፤ አገልግሎት የሚሰጥ የተሟላ ረቂቅ መሣሪያ በተጨባጭ ሁኔታ ጥቅም እንዲሰጥ ገበያ ላይ መዋል የሚችለው በ 3 ዓመታት ውስጥ እንደሚሆን ነው የተገለጠው። በተጠቀሰው ዘዴ የሚሠሩ ረቂቅ መሣሪያዎች፣ ለበረራ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን፣ ለህንጻዎች ግንባታ፣ እንዲሁም ለህክምና አገልግሎት ሰፊ ጠቀሜታ እንደሚኖራቸው ነው የሚታመንበት። ረቂቅ የሆነ፣ ይህን መሰል ተቆጣጣሪ መሣሪያ በአንድ አትሌት ሸሚዝም ተጣብቆ አትሌቱ ልምምድ ሲያደርግ የልብ ትርታውን እንደሚለካ፣ የመስማት ችግር ያለባቸውን ሰዎች የሚረዱ ረቂቅ መሣሪያዎችም ወደፊት ከተጠቃሚው ሰው አካል በሚያገኙት የሙቀት ኃይል ሊሠሩ እንደሚችሉ የሚያጠራጥር አልሆነም። ዚህን በተረፈ፣ ፣ ህዝብ አመላላሽ አኤሮፕላኖች፣ ሞተራቸው በሚቃጠል ቤንዚን መሆኑ ቀርቶ በኤልክትሪክ ኀይል እንዲንቀሳቀስ ማድረጉ ይበልጥ አስተማማኝነት እንዳለው ነው የሚነገረው። በዩናይትድ እስቴትስ የተደረገ ሙከራ እንደሚያረጋግጠው፣ የአኤሮፕላንን ቀዛፊ ሞተር (ፕሮፔለር) ያለሳንክ ለማንቀሳቀስ፣ በነዳጅ ከሚንቀሳቀስ ሞተር ይልቅ፣ የኤሌክትሪክ ሞተር ምናልባት 10 ፣ ብሎም 20 እጥፍ ያህል ይበልጥ አስተማማኝ ነው የተባለው። በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀስ ሞተር 95 ከመቶ ያህል እጅግ አስተማማኝ መሆኑ ሲነገርለት፣ ፣ በነዳጅ ኃይል የሚሠራው፣ አስተማማኝነቱ ፣ ከ 18 እስከ 23 ከመቶ መሆኑ ነው የተገለጠው። ከዚህም ሌላ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚበሩ አኤሮፕላኖች የድምፃቸው መጠን እጅግ ዝቅ ያለ በመሆኑ ፣ በአኤሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች አሠራር ረገድም ለውጥ ሊያስከትል እንደሚችል ነው የሚታሰበው።