Jump to content
አማርኛ ውክፔድያን አሁኑኑ ማዘጋጀት ትችላላችሁ - ተሳተፉበት!

ውይይት:የካቲት ፫

Page contents not supported in other languages.
ከውክፔዲያ

የዘመነ መሳፍንት የመጨረሻው ጦርነት 166ኛ ዓመት መታሰቢያ ደጃዝማች ካሣ ኃይሉ፣ ‹‹ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው ከመንገሳቸው በፊት የስሜንና የትግራይ ገዢ ከነበሩት ከደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም (የዳግማዊ ቴዎድሮስ ባለቤት የእቴጌ ጥሩወርቅ ውቤ አባት) ጋር የመጨረሻውን የዘመነ መሳፍንት ጦርነት ያደረጉት ከዛሬ 166 ዓመታት በፊት (የካቲት 3 ቀን 1847 ዓ.ም) ነበር፡፡ - - - ደጃዝማች ካሣ በኅዳር ወር 1845 ዓ.ም ደጃዝማች ጎሹ ዘውዴን ጉርአምባ ላይ፣ በሰኔ ወር 1845 ዓ.ም ደገሞ ራስ አሊ አሉላን (ዳግማዊ አሊን) አይሻል ላይ ካሸነፉ በኋላ ከወቅቱ የግዛት ኃያላን መሳፍንት መካከል ለደጃዝማች ካሣ ያልገበሩት የስሜንና የትግራይ ገዢ የነበሩት ደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም ብቻ ነበሩ፡፡ ደጃዝማች ካሣም ወደ ደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም ለመዝመት አቀዱ፡፡ ከዘመቻቸው በፊትም ደጃዝማች ውቤ በሰላም እንዲገቡላቸውና እምቢ የሚሉ ከሆነ እምቢታቸው እንደማይበጃቸው የማስጠንቀቂያ መልዕክት ላኩባቸው፡፡ - - - ደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም ከፊትም ጀምሮ ደጃዝማች ማሩ እና ራስ ይማም፤ ደጃዝማች ሰባጋዲስ እና ራስ ማርዬ በሚዋጉበት ጊዜ በብልጠትና በዘዴ አንዱን ከሌላው ጋር እያዋጉ፣ ከሚመቻቸው ጋር እየወገኑና በጋብቻ እየተዛመዱ፤ ሲሸነፉም እየገበሩ ራሳቸውን ከአደጋ ጠብቀው ይኖሩ ነበር፡፡ ደረስጌ ማርያምን አሰርተው ለመንገሥ ጊዜ ሲጠባበቁ የደጃዝማች ካሣ ተደጋጋሚ ድል ዓይኑን አፍጥጦ በላያቸው ላይ መጣባቸው፡፡ ይባስ ብሎም ለደጃዝማች ካሣ እንዲገብሩ የሚያሳስብ መልዕክት ደረሳቸው፡፡ - - - ደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም የደጃዝማች ካሣ መልዕክት ሲደርሳቸው … ‹‹ምን የጠገበ ነው?! ሳልዋጋ ይገባልኛል ብሎ ነው?!›› በማለት ከተናገሩ በኋላ ‹‹አልገባም!›› የሚል ምላሽ ሰጡ፡፡ ጳጳሱ አቡነ ሰላማም ለደጃዝማች ውቤ ‹‹ለካሳ ቢገብሩ ይሻላል›› ቢሏቸውም የስሜኑ ሰው ሃሳባቸውን ሳይቀይሩ ቀሩ፡፡ - - - ደጃዝማች ካሣም ጦራቸውን አስከትተው ‹‹… ከእኔ የተለየህ ለራስህ እወቅ! በምን ጠፋሁ እንዳትል! አይዞህ ወታደር፤ እኔ ደስ ከሚልህ አገር አገባሃለሁ›› የሚል አዋጅ አስነገሩ፡፡ ሕዝቡም ከራስ አሊ መሸነፍ በኋላ ‹‹ደጃች ካሣ መቼ ይነግሱ ይሆን? ስመ መንግሥታቸውስ ማን ይባል ይሆን?›› እያለ ይጠይቅ ስለነበር ‹‹እኔ በመራሁህ ተጓዝ፤ ስሜን በስሜን እነግርሃለሁ›› ብለው ከአምባጫራ አልፈው በወገራ በኩል አድርገው ስሜን ገቡና ደረስጌ ላይ ‹‹እንጨት ካብ›› በተባለ ቦታ ሰፈሩ፡፡ የደጃዝማች ውቤ ጦርም በአካባቢው (‹‹መከሁ›› በተባለች ቦታ) ሰፍሮ ነበር፡፡ - - - ደጃዝማች ካሣም አብሯቸው የነበረውንና ዮሐንስ ቤል (ጆን ቤል) የተባለውን እንግሊዛዊ የደጃዝማች ውቤን ጦር አሰፋፈር በመነፅር ዓይቶ እንዲነግራቸው ጠይቀውት ነበርና የደጃዝማች ውቤን ጦር አሰፋፈርና ድንኳን ዐይቶ በነገራቸው ጊዜ ‹‹አያሳድረኝ አላሳድረውም! … እንኳን ይህን ቁርጥማታም ሽማግሌ ይቅርና ወሎን መትቼ የሸዋውን ንጉሥ እይዘዋለሁ፤ ወታደር ሆይ ‹የውቤ ነፍጥ የውቤ ነፍጥ› ቢሉህ የተለጎመው ጨርቅና ባሩድ ነው፤ አይነካህም፤እኔ የክርስቶስ ባርያ ሁሉንም ዐሳይሃለሁ! … ‹ስሜን በስሜን እነግርሃለሁ› ያልኩህ ወታደር ሁሉ ስሜ ቴዎድሮስ ነው›› ብለው ፎክረው ተነሱና ጦርነቱ የካቲት 3 ቀን 1847 ዓ.ም ‹‹ቧሂት›› በተባለ ቦታ ላይ ተጀመረ፡፡ - - - ጦርነቱ ተፋፋመና ደጃዝማች እሸቴ የተባሉት የደጃዝማች ውቤ ልጅ ተመትተው ሲወድቁ የደጃዝማች ውቤ ጦር ሽሽት ጀመረ፡፡ ብላታ ኮከቤ የተባለው የደጃዝማች ውቤ የጦር አዝማችም አለቃውን ከድቶ ከነጭፍራው ወደ ደጃዝማች ካሣ ዞረ፡፡ ደጃዝማች ውቤም ቆስለው ተማረኩና ድሉ የደጃዝማች ካሣ ኃይሉ ሆነ፡፡ ደጃዝማች ካሣም ተሸናፊውን ደጃዝማች ውቤን ‹‹እኔ እሳቱ የመይሳው ልጅ! … አንተ ቆፍጣጣ (ጎባጣ) ቁርጥማታም ሽማግሌ አክብሬህ ‹ገብር› ብዬ ብልክብህ ምነው ሰደብከኝ? አሁንም ነፍጤንና ገንዘቤን አግባ!›› አሏቸው፡፡ ደጃዝማች ውቤም ‹‹እግዜር ያሳይዎ የነበረኝ ነፍጥና ገንዘብ ሁሉ አንድም ሳያመልጥ ከእጅዎ ገባ፤ ሌላ ምን አለኝ?›› ብለው መለሱላቸው፡፡ - - - ደጃዝማች ውቤ ቤቴል (አምባ ጠዘን) በሚባለው ቦታ ያከማቹት እጅግ በጣም ብዙ ወርቅ፣ ብር (40ሺ ማርትሬዛ)፣ ጥይት፣ ጠመንጃ (ሰባት ሺ)፣ አህያ፣ ፈረስ፣ ግመል፣ ላም፣ በግ፣ ፍየል፣ በወርቅ የተለበጡ አልባሳት፣ የከበሩ ጌጣጌጦችና፣ ውድ ምንጣፎችና ሌሎች እቃዎች ተገኙ፡፡ በዚህ ጊዜም ደጃዝማች ካሣ የታሰሩትን ደጃዝማች ውቤን አስጠርተው ‹‹ይኸን ሁሉ ሀብት የሰበሰብከው ምን ሊሰራልህ ነው?›› ሲሉ ጠየቋቸው፡፡ ደጃዝማች ውቤም ‹‹ለክፉ ቀኔ እንዲሆነኝ ብዬ ነው›› አሏቸው፡፡ ደጃዝማች ካሣም ‹‹ሰው ያለውን ሀብት ከተጠቀመ ምን ክፉ ቀን አለ?›› በማለት መለሱና ወደ እስር ቤቱ እንዲመለሱ አዘዙ፡፡ ደጃዝማች ውቤም ከዓመታት በኋላ እስር ቤት ውስጥ ሞቱ፡፡ - - - በመጨረሻም … ‹‹የኮሶ ሻጭ ልጅ›› ተብለው የተናቁት… ‹‹… ደግሞ ለቆለኛ አንድ ወርች ስጋ ምን አነሰው?›› ተብለው በአማቶቻቸው የተቀለደባቸው … ካሣ ኃይሉ … ደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም ሊነግሱባት አስጊጠው ባሰሯት ደረስጌ ማርያም ቤተ-ክርስቲያን የካቲት 5 ቀን 1847 ዓ.ም በጳጳሱ በአቡነ ሰላማ እጅ ተቀብተው፣ ‹‹ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው የኢትዮጵያ ንጉሥ ሆኑ!

Start a discussion about የካቲት ፫

Start a discussion