የሳይንስ ፍልስፍና

ከውክፔዲያ

የሳይንስ ፡ ፍልስፍናሳይንስ መሠረቶችን ፣ ዘዴዎችን እና መዘዞችን በጥልቀት የሚያጠና የፍልስፍና ዘርፍ ነው። ሳይንስን ከሌሎች የ ዕውቀት ዓይነቶች የሚለየው ምንድን ነው? ምን ዓይነት ዕውቀት ሳይንስ ሊባል ይችላል? ምን ዓይነትስ አይባልም? የሳይንስ ጽንሰ ሓሳቦች የቱን ያክል አስተማማኝ ናቸው? የዚህ ሁሉ የሳይንስ ዕውቀት የመስተጨረሻ ግብ ምንድን ነው? የሰውን ህይወት ማሻሻል ነው? ወይንስ ስለከባቢ ዓለም ዕውነትን ለማዎቅ ነው? እነዚህ ጥያቄዎች የዚህ ፍልስፍና ዋና ትኩረት ናቸው።

ተጨባጩን ዓለም ለመገንዘብ በተደረጉ ጥረቶች፣ ከጥንት ጀምሮ ብዙ ዓይነት ሐሳቦች ፈልቀዋል። እነዚህ ጥረቶች፣ በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ምናባዊን አለም፣ መናፍስትንና እና ሌሎች ተጨባጭ ያልሆኑ ነገሮችን ያሳተፉ ነበሩ። ሆኖም ቀስ በቀስ፣ አንዳንድ ፈላስፋዎች እነዚህ ለሽህ ዓመታት የተሰራባቸው ሐሳቦች ከባድ ስህተት እንዳለባቸው ፤ ይባስ ብሎም ለቀጣይ የመሻሻል እርምጃ እንቅፋት እንደሆኑ ማሳዎቅ ጀመሩ።

ይህ የተጠራቀመ ትችትና ቅሬታ በአውሮጳ የሳይንስ አብዮትን አስከተለ። የዛሬ አራት መቶ ዓመት አካባቢ የነበሩ ፈላስፎች በውርስ ባገኙት የጥንታዊት ግሪክ ፍልስፍናዎች ላይ አመጽ በማድረግ የዘመናዊውን ሳይንስ መሰረት ጣሉ። የተጨባጩን አለም ለመረዳት ተጨባጩ ዓለም በቂ ነው። ተጨባጩን ዓለም ለመረዳት፣ ከተጨባጩ ዓለም ውጭ መንስዔ መፈለግ አላስፈላጊ መሆኑን በማስረገጥ አዲሱን ሳይንስ መገንባት ጀመሩ።

ይህም እጅግ በጣም የተሳካ ፍልስፍና ስለነበር ሰዎች ስለተፈጥሮ ያላቸው ግንዛቤ በከፍተኛ ፍጥነት እንዲያድግ አድርጓል። ባሁኑ ዘመን ላለው የምዕራባዊው ዓለም የህክምና፣ እርሻ እና ቴክኖሎጂ ውጤቶች መትረፍረፍ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ክስተት ነው።