የሾቶኩ ሕግጋት

ከውክፔዲያ

የሾቶኩ ሕግጋት ወይም 17 አንቀጽ ያለ ሕገ መንግሥት (ጃፓንኛ፦ 十七条憲法, /ጁሺቺጆ ከንፖ/) በ596 ዓ.ም. በጃፓን ልዑል ሾቶኩ የተጻፈ ሕገ መንግሥታዊ ሰነድ ነው።

እስከ 1883 ዓ.ም. ድረስ እንደ ጃፓን መንግስት ላዕላይ ሕግ ይቆጠር ነበር። በ1883 ዓ.ም. የጃፓን ንጉሥ አዲስ ዘመናዊ አይነት ሕገ መንግሥት አወጡ። ቢሆንም በግልጽ መቸም ስላልተሰረዘ፣ አንዳንድ የጃፓን ሕግ ጠባቂ የሾቶኩ ሕግጋት እስካሁን ሕጋዊ እንደሚሆኑ ይከራክራል። በ1939 ዓ.ም. የወጣ የአሁኑ ጃፓን ሕገ መንግሥት (አንቀጽ 98) ለእርሱ ተቃራኒ የሆነውን ሕግጋት ብቻ ሠረዘ።

የጃፓን ልዑል ሾቶኩ 17 አንቀጽ ያለ ሕገ መንግሥት (596 ዓ.ም.)[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

 • አንቀጽ 1፦ መስማማት ሊከብር ይገባልና ከጠብ መንገሻገሽ ይገባል። ሰው ሁሉ ዝንባሌውን አለው፤ ጥቂት ሰዎች ሩቅ ዕይታ አላቸው። ስለዚህ አንዳንድ ሰዎች ጌቶቻቸውን አባቶቻቸውንም እምቢ ይላሉ፣ ከጎረቤቶቻቸውም ጋር ይበባቃላሉ። ነገር ግን አለቆቹ ሲስማሙ፣ ተገዦቹም ወዳጅ ሲሆኑ፣ ያንጊዜ ጉዳዮች በጸጥታ ይወየያሉና ትክክለኛው አስተሳሰብ ያሸንፋል።
 • አንቀጽ 2፦ ሦስቱ መዝገቦች - እነርሱም ቡዳ፣ የቡዳ ሕግ፣ እና የቡዳ ቄሳውንት - በቅንነት ሊከብሩ ይገባል፤ እነርሱ የሁሉ ኗሪዎች መጨረሻ መሸሸጊያ ናቸውና። ከሰው ልጆች መካከል፣ ጥቂት ብቻ ዕውነታቸውን ለመማር የማይችሉ መጥፎዎች ናቸው።
 • አንቀጽ 3፦ ለንጉሳችሁ ትዕዛዛት ከመገዛት እንዳትቀሩ። እርሳቸው ከምድር በላይ እንዳለው ሰማይ ናቸው፤ ተገዡም ስማይን እንደምትዳግፈው ምድር ነው። ሰማይና ምድር በሚገባቸው ስፍራቸው ሲኖሩ፣ የአመቱ ወቅቶች መንገዳቸውን ይከተላሉና በሥነ ፍጥረት ሁሉ መልካም ነው። ምድር ግን የሰማይን ቦታ ለመውሰድ ብትሞክር ኖሮ፣ ሰማይ በፍርስራሽ ይወድቅ ነበር። ከዚህ የተነሣ፣ ጌታው ሲናገር ተገዢው ያዳምጣል፤ አለቃውም ሲንቀሳቀስ፣ ተገዢው ይታዘዛል። ስለዚህ የንጉሳችሁን ትዕዛዝ ስትቀበሉ፣ እሱን ከመፈጽም አትቀሩ፤ አለዚያ መበላሸት ተፈጥሮአዊ ውጤቱ ይሆናል።
 • አንቀጽ 4፦ ሚኒስቴሮችና የመንግሥት ባለሥልጣናት መጀመርያ መርኃቸው ግብረ ገብ እንዲያድርጉት ይገባል። አለቆቹ በደንብ ካልሠሩ፣ ተገዦቹ ቅጥ ያጡ ይሆናሉና፤ ተገዦቹም አላግባብ ከሠሩ፣ ጥፋቶች በተፈጥሮ ይነሣሉ። ስለዚህ ጌታውና ተገዢው በግብረ ገብ ሲሠሩ፣ የማዕረግ ልዩነቶች አይዛቡም፤ ሕዝብም በሚገባ ሲሠራ፣ መንግሥት በመልካም ይተዳደራል።
 • አንቀጽ 5፦ የሚቀርቡልህን አቤቱታዎች ያለ አድልዎ ፍረድ። ክስ የሚሰማው በያኝ መነሻው መቀዳጀት ከሆነ፣ ክሱንም የሚሰማው ጉቦ ለማግኘት በማሰቡ ከሆነ፣ እንግዲህ የሀብታሙ ክስ ወደ ውሃ እንደሚወረውረው ድንጊያ ምንም መቃወም የማይገኘው ይሆናል፤ የድኆቹ አቤቱታ ግን በድንጊያ ላይ እንደሚውረወር ውሃ ይሆናል። በዚያ ሁኔታ፣ ድኃ ወዴት እንደሚዞር አያውቅም፣ በደንብም አይሠራም።
 • አንቀጽ 6፦ ክፉውን ቅጣ፣ መልካሙን ደግፍ። ይህ የጥንቱ አንጋፋ ደንብ ነበረ። ስለዚህ የሌሎችን መልካም ጸባይ አትሸሽግ፣ ወይም ስታየው የተሳተውን ከማረም አትቀር። ሸንጋዮችና አታላዮች መንግሥትን ለመገልበጥ ስለታም መሳሪያ ናቸው፣ ለሕዝብም ጥፋት የተሳለ ሠይፍ ናቸው። እንዲህ አይነት ሰዎች ለጌታቸውም ሆነ ለሕዝቡ ከቶ ታማኝ አይሆኑም። ይህ ሁሉ የብርቱ ብሔራዊ ሁከት ምንጭ ነው።
 • አንቀጽ 7፦ ሰው ሁሉ የራሱን ሥራ አለው። የተግባር ክፍፍሎች አይዛቡ። ጥበበኞች ለሹመት ሲታመኑ፣ የምስጋና ድምጽ ይነሣል። ብልሹ ሰዎች ቢሾሙ፣ ጥፋትና ሁከት ይበዛሉ። በነገሮች ሁሉ - በትልቁም በትንሹም - የሚገባውን ሰው አግኝና በትክክል ይተዳደራሉ። ስለዚህ የጥንቱ ጥበበኞች ነገሥታት የፈለጉት ማዕረጉን የሚሞላውን ሰው እንጂ ሰውዬውን የሚሞላውን ማዕረግ ለማግኘት አልነበረም። እንዲህ ከሆነ፣ መንግሥቱ ዘላቂ ይሆናል፣ ግዛቱም ከአደጋ ነጻ ይሆናል።
 • አንቀጽ 8፦ ሚኒስቴሮችና ባለሥልጣናት በማለዳ በችሎት እንዲቀመጡ፣ እስከ ምሽትም ድረስ እንዲሠሩ ይገባቸዋል፤ ቀኑ ሙሉ የመንግሥቱን ጉዳይ ለመፈጽም አይበቃምና። ሰው ለችሎት ቢረፍድ እንደ ሆነ፣ አደጋዎች ሊፈቱ አይችሉም፣ ሹሞቹም ቶሎ ቢትዉት፣ ሥራው ሊጨረስ አይችልም።
 • አንቀጽ 9፦ መልካም እምነት የመተካከል መሰረት ነው። በነገሮች ሁሉ መልካም እምነት ይኖር፤ አለቃውና ተገዢው ቢተማመኑ፣ ምን የማይቻል ነገር አለና? አለቃውና ተገዢው ባይተማመኑ፣ ሁሉ በውድቀት ይጨረሳል።
 • አንቀጽ 10፦ ራሳችንን እንቆጣጥር፤ ሰዎችም ሲውዛግቡን አንቀየም፤ ሰው ሁሉ ልቡና አለውና፣ እያንዳንዱም ልቡና የገዛ ስሜቱን አለውና። ለሰው ትክክለኛ የሆነው ለኛ ስኅተት ነው፤ ለኛም ትክክል የሆነው ለነርሱ ስኅተት ነው። እኛ ያለ ጥያቄ ጠቢቦች አይደለንም፣ እነርሱም ያለ ጥያቄ ሞኞች አይደሉም። ሁለታችን በቀላሉ ተራ ሰዎች ነን። ማንም ሰው መልካሙን ከስህተቱ የሚለይበት ደንብ ለማዋጅ እንዴት ይችላል? ሁላችን አንዴ ጥበበኛ፣ አንዴም ሞኝ ነን። ስለዚህ፣ ሌሎች ለቊጣ ፈቀቅ ቢሉም፣ እኛ ግን የራሳችንን በደል እንፍራ፤ እኛም ብቻ ትክክለኛ እንድንሆን ቢመስለንም፣ አብዛኞቹን እንከተልና እንደነርሱ እናደርግ።
 • አንቀጽ 11፦ ከዋጋና ከቅጣት መካከል ያለውን ልዩነት ዕወቅ፤ ለያንዳንዱም ዋጋውንና ቅጣቱን ስጠው። በአሁኑ ወቅት፣ ዋጋ ከጉብዝና ወይም ቅጣት ከወንጀል ሁልጊዜ አይከተልም። በሕዝቡ ጉዳዮች ላይ ኅላፊነትን ያላችሁ እናንተ ባለሥላጣናት ሆይ፣ ዋጋና ቅጣትን በንጹሕ መስጠት አደራረጋችሁ ይሁን።
 • አንቀጽ 12፦ የክልሉ መሳፍንት በሕዝብ ላይ እንዳይገብሩ። በሀገር ውስጥ ሁለት ጌቶች ሊኖሩ አይቻልም፤ ሰዎችም ሁለት ገዢዎች ሊኖሯቸው አይችሉም። ንጉሡ የመላውን ግዛት ሕዝብ አንድያ ጌታ ናቸው፤ የሚሾሟቸውም ሹሞች ሁሉ የሳቸው ተገዦች ናቸው። እነርሱ በሕዝቡ ላይ ግብርን ለመጣል እንዴት ይደፍራሉ?
 • አንቀጽ 13፦ በሹመት የታመኑት ሰዎች ሁሉ ተግባራቸውን በእኩልነት ይጠብቁ። ምናልባት አንዳንዴ ሥራቸው በኅመም ወይም በተልእኮ ሊቋረጥ ይቻላል። ሆኖም ተግባራቸውን ለመጠብቅ በሚቻላቸው ሰዓት ሁሉ፣ እንደሚያውቁት አድርገው ይፈጽሙት፤ አላውቅበትም ብለው በሕዝቡ ጉዳይ መሰናከል አይሆኑ።
 • አንቀጽ 14፦ ቅናተኞች አትሁኑ! ሰዎችን በምቀኝነት ብንይ፣ እነርሱም በፈንታቸው እኛን በምቀኝነት ያዩናልና። የቅናት ክፋት ወሰን የማያውቅ ነው። ሰው በብልሃቱ ቢበልጠን፣ ደስ አይለንም፤ ችሎታው ቢበልጥ፣ ቀናተኞች ነን። ነገር ግን ጥበበኞችንና ጠቢቦችን ካላገኝን፣ ግዛቱ እንዴት ይገዛል?
 • አንቀጽ 15፦ የግሉን ጥቅም ከጋራው ጥቅም በታች ማድረግ - ያው የተገዢው መንገድ ነው። አሁን የሰው ተጽእኖ የግል መነሻው ከሆነ፣ ቅሬታ ይኖረዋል፤ ቅሬታውም ተጽእኖው ከሆነ፣ ከሰዎች ጋር በስምምነት መስራቱ ይቀረዋል። ቅሬታ ለሥርአት እንቅፋት ነውና ሕግን መጣስ ነው።
 • አንቀጽ 16፦ ሕዝቡን በወቅታዊ ወራት በሥራ አስገድዳቸው። ይህ ጥንታዊና አንጋፋ ደንብ ነው። በበጋ በመዝናናታቸው ጊዜ ቀጥራቸው፣ ነገር ግን በልግና ክረምት የእርሻ ስራ ሲይዛቸው ወይም ቅጠል ለሐር ትል የመመግብ ሥራ ሲይዛቸው አትቀጥራቸው። ሰዎች እርሻን ባይጠብቁ፣ ምን የሚበላ ይኖራልና? ቅጠሉንም ለሐር ትል ባይመግቡ፣ ምን የሚለበስ ይኖራልና?
 • አንቀጽ 17፦ ቁም ነገር በሆነው ጉዳይ ላይ ያለው ብያኔ በአንድ ሰው ብቻ ሊደረግ አይገባም። ከብዙ ሰዎች ጋር ሊወያዩ ይገባል። ጥቃቅን ነገሮች እንዲህ ከባድ አይደሉምና ብዙ ሰዎችን ማማከር አያስፈልግም። ቁም ነገር በሆኑት ጉዳዮች ብቻ፣ ሊዛቡ እንደሚቻል ሲጠራጠር፣ ትክክለኛውን ድምዳሜ ለመድረስ ከሌሎች ጋር ማማከር ይገባል።

የውጭ መያያዣ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]