የአፈር ሜካኒክስ

ከውክፔዲያ

የአፈር ሜካኒክስ የአፈር ፊዚክስ እና የምህንድስና ሜካኒክስ የሙያ ዘርፎች ጥምረት ሲሆን የአፈርን ፀባይን ከምንድህስና አንፃር የሚያጠና የሲቪል ምህንድስና ዘርፍ ነው።

የአፈር ሜካኒክስ ከፈሳሽ ሜካኒክስ (fluid mechanics፤ ስለ ፈሳሽ ነገሮች የሚያጠና ዘርፍ ነው) እና ጠጣር ሜካኒክስ (solid mechanics፤ ስለ ጠጣር ነገሮች የሚያጠና ዘርፍ ነው) የሚለየው አፈር የፈሳሽ ነገሮች (አብዛኛውን ጊዜ አየርና ውሃ) እና የቅንጣቶች (particles ትንንሽ ነገሮች፤ አብዛኛውን ጊዜ የሸክላ አፈር፣ ደለልማ አፈር፣ አሸዋ ወይም ጠጠር) ድብልቅ ስለሆነ ነው። ከዚህም ባለፈ የተፈጥሮ ብስባሾች እና ሌሎች ቁሶች በአፈር ውስጥ ሊገኙ ይችላሉ።

የአፈር ሜካኒክስ ከድንጋይ ሜካኒክስ (rock mechanics) ጋር በመሆን የጂኦቴክኒክ ምህንድስና (geotechnical engineering) ፅንሰ ሀሳብ መሰረት ነው።

የጂኦቴክኒክ ምህንድስና (geotechnical engineering) ስለ ህንፃ መሰረት (foundations)፤ ተዳፋት (slopes)፤ መጠበቂያ ግድግዳዎች (retaining walls)፤ የአፈር ድልድሎች (ቁልል፤ embankments)፤ የመንገድ ንጣፎች፤ ዋሻዎች፤ የማእድን ማውጫ ቁፋሮዎች፤ የአፈር ሙሌቶች (landfills) እንዲሁም ሌሎች በአፈር ወይም በድንጋይ የተሰሩ ወይም የተደገፉ የግንባታ አካላትን ጥናት፣ ንድፍ እና ግንባታ የምናከናውንበት የሙያ ዘርፍ ነው። የጂኦቴክኒክ ምህንድስና የከርስ ምድር ምህንድስና (geological engineering) ዘርፍንም ያካተተ ነው።

የአፈር ሜካኒክስ በአፈር ላይ፣ በአፈር ውስጥ ወይም በአፈር የተሰሩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ የግንባታ አካላት ላይ የሚከሰተውን የቅርፅ ለውጥ (deformation) እንዲሁም በአፈር ውስጥ የሚኖርን ፈሳሽ ፍሰት (በአብዛኛው ጊዜ ውሃ) የሚመረመርበትና የሚጠናበት የሙያ ዘርፍ ነው። ለምሳሌ ለመጥቀስ ያህል፤ የህንፃና የድልድይ መሰረቶች፣ የመደገፊያ ግድግዳዎች (retaining walls)፣ ግድቦች፣ ከመሬት ውስጥ የሚቀበሩ የመተላለፊያ ትቦዎች፣ ዋሻዎች፣ የመንገድ ንጣፎች ይገኙበታል።

የአፈር ሜካኒክስ ፅንሰ ሀሳቦች እንደ የከርስ ምድር ምህንድስና (geological engineering)፣ የባህር ዳርቻ ምህንድስና (coastal engineering)፣ የእርሻ ምህንድስና (agricultural engineering)፣ የውሃ ምህንስና (hydrology) እና የአፈር ፊዚክስ (soil physics) በመሰሉ መያ ዘርፎች ውስጥም ጥቅም ላይ ይውላል።