የወላይታ ዘመን አቆጣጠር
ስለ ጊፋታ በዓል አከባበር አጭር ማብራሪያ [በደስታ ወጋሶ የጊፋታ በዓል ምንነት የወላይታ ብሔር የበርካታ የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ነው፡፡ ከእነዚህ ሀብቶች መካከል የብሔሩ ዘመን መለወጫ በዓል ጊፋታ አንዱ ነው፡፡ ጊፋታ የወላይታ ሕዝብ በኦሞ ወንዝ ተፋሰስ ቋሚ ኑሮ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሲተገብሩት የቆዬ ከማንኛውም ባህላዊ እምነትም ሆነ ዘመናዊ ኃይማኖትና የአምልኮ ሥርዓት ጋር ምንም ግኑኝነት የሌለው የዘመን መለወጫ ክብረ በዓል ነው፡፡ የጊፋታ በዓል ትርጉም
እንደ ብሔሩ የታሪክ አዋቂ ሽማግሌዎች ጊፋታ በብሄሩ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ታላቅ በዓል ሲሆን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ የብሔሩ ማንነት መገለጫ የሆነ የአሮጌው ዓመት ማብቅያና የአዲሱ ዓመት መጀመሪያ የመሸጋገሪያ በዓል ነው፡፡ ጊፋታ ማለት ባይራ(ታላቅ)፣ መጀመሪያ እንደ ማለት ሲሆን በሌላ በኩል ጊፋታ ማለት መሻገር ማለት ነው፡፡ ይህም ከአሮጌ ወደ አዲስ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሻገር የሚለውን ይገልጻል፡፡ ጊፋታ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ አእዋፋትና የቤት እንስሳትም ጭምር በጋራ የሚያከብሩት በዓል ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ የወላይታ ብሔር የራሱ የሆነ የዘመን መቁጠሪያ/ካሌንደር አለው፡፡ በወላይታ የዘመን አቆጣጠር ጊፋታ የዓመቱ የመጀመሪያ ወር ስያሜ ነው፡፡ በበዓሉ “Gifaata Gazzee Abuuna Gaylle” ተብሎ ይዘፈናል፡፡ ይህም የበዓሉን ታላቅነት ለመግለጽ ነው፡፡ የዘመን አቆጣጠር፡-
አሮጌው ዓመት እየተገባደ ሲሄድ በንጉሱ አማካሪዎች አማካይነት የዘመን ቆጠራ ባለሙያዎች ወደ ቤተመንግሥት ይጠራሉ፡፡ ከዚያም ሌሊት ሌሊት እየወጡ የጨረቃን ኡደት መነሻ ለማወቅ የጨረቃን አራት ክፍሎች ማለትም /ፖኡዋ፣ ጡማ፣ ጤሯ፣ ጎባና/ በየትኛው ክፍል እንደሚውል የዓመቱን የቆጠራ ምልክቶች ይዘው መጥተው የሙሉ ጨረቃዋን ኡደት ተመልክተው ለንጉሱና ለአማካሪዎቹ ያበስራሉ፡፡ ከዚያም ኮከብ ቆጣሪዎቹ በዓሉ የሚከበርበት ቀን በትክክል ለንጉሱ ከነገሩ በኋላ ሽልማት ይዘው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ ቀጥሎም ንጉሱ የበዓሉን መቃረብ ለህዝቡ “በጫላ ኦዱዋ” (አዋጇ) በየገበያውና የህዝብ መሰብሰቢያ እንዲነገር ያደርጋል፡፡ የጊፋታ በዓል ታሪካዊ አመጣጥ የጊፋታ በዓል ታሪካዊ አመጣጡን በተመለከተ በዘመናዊ ታሪክ አቆጣጠር ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ በአካባቢው ይከበር የነበረ በዓል እንደሆነ ይገመታል፡፡ ነገር ግን በዓሉ መቼና እንዴት ተጀምሮ እያደገ እንደመጣ ትክክለኛውን ጊዜ የሚጠቁም መረጃ በብዛት ባይኖርም ለበዓሉ ታሪካዊ አመጣጥ ሁለት ዋና ዋና አመለካከቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ የመጀመሪያው አመለካከት በወላይታ መንግሥት ተመስርቶ ግዛቱን ተቆጣጥሮ መኖር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ማለትም የመጀመሪያው የወላይታ ማላ ዘረ-ግንድ ቀዳሚ ንጉስ “ካዎ ቢቶ” ዘመነ መንግስት ጀምሮ ሲከበር እንደነበርና ይህንንም ከአያት ቅድመ-አያት “Mayzza ma”yaa” መሠረት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ነው ተብሎ በአፈ-ታሪክ ይነገራል፡፡ ሁለተኛው አመለካከት ደግሞ “በሞቼና ቦራጎ” ዋሻ እየተደረገ ካለው የአርኪዮሎጂ ጥናት ውጤት ጋር የተያያዘ ሲሆን መረዳት የሚቻለው ሴኖዞይክ ኤራ (የድንጋይ ወይም የበረዶ ዘመን) በመባል ስለሚታወቀው ዘመን በዓለም ላይ ምርምር ከሚካሔድባቸው ሰባት ታላላቅ የምርምር ቦታዎች አንዱ በሆነው በዚህ ዋሻ ከ58,000 እስከ 70,000 ዓመት በፊት የወላይታ ሕዝብ ሆነ ሌሎች የአካባቢው ህዝቦች በዚህ አካባቢ የተረጋጋ(ቋሚ) ሕይወት የጀመሩበት ጊዜ መሆኑን የፕሮፌሰር ስቴቨን 4ኛ ዙር ጥናት ግኝት ሪፖርት ያመለከታል፡፡ ይህ ጥናት ፍንጭ የሚሰጥ ምልክት የተገኘበት ለቀጣይ ጥናት ሁኔታ የሚመቻችበት ብለው መዝግበው አቆይተዋል፡፡ የበዓሉ አከባበር ጅማሮም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ እነዚህን ሁለት መላምቶችን መነሻ አድርገን በምናይበት ጊዜ የመጀመሪያው የጊፋታን በዓል አጀማመር ከወላይታ ቋሚ መንግስት መመሥረት ጋር ያገናኛል፡፡ ሆኖም ግን ሰዎች በአንድ አካባቢ ተሰባስበው በዓላትን ለማክበር የግድ መንግሥት በሚባል የአስተዳደር መሣሪያ ሥር መሆን ያለባቸው አይመስለንም፡፡ ምክንያቱም በቀደሙት ጊዜያት በአካባቢያችን የሚገኙ የተለያዩ ብሄሮችና ብሔረሰቦች ራሳቸውን የሚያስተዳሩበት የተደራጀ መንግሥታዊ መዋቅር ባይኖራቸውም የተለያዩ ሕዝባዊ በዓላትን ያከብሩ እንደነበር ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ በእኛ እምነት በአንድ አካባቢ ሰዎች ቋሚ ኑሮ መኖር ሲጀምሩ ማህበራዊ ግንኙነታቸው እየሰፋና እየተጠናከረ ይሄዳል፡፡ በዚህን ጊዜ የአምልኮ ሥርዓት፣ የሐዘንና የደስታ አገላለጽ፣ የበዓላት አከባበርም ጭምር በማህበር/በህብረት ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ስለሆነም የወላይታ ሕዝብ የዘመን መለወጫ በዓሉን ማክበር የጀመረው በንጉስ መተዳደር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሳይሆን በኦሞ ወንዝ ሸለቆ ቋሚ ኑሮ መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነው የሚለው መላምት የተሻለ ሳይንሳዊ አገላለጽ ያለው መሆኑን እናምናለን፡፡ የጊፋታ በዓል ቅድመ ዝግጅት፡- የጊፋታ በዓል ከሌሎች በዓላት በተለየ የረዥም ወቅት ዝግጅት ይደረግለታል፡፡ ሁሉም የማህበረሰቡ አባላት ማለትም አባቶች፣ እናቶች እንዲሁም ወጣት ወንዶችና ሴቶች ሕጻናትም ሳይቀሩ በጊፋታ በዓል ዝግጅት የየራሳቸው የሥራ ድርሻ አላቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቅድመ ዝግጅት ሥራው በማህበር ወይም በደቦ ሆኖ አንዱ ሌላውን በማገዝም ይከናወናል፡፡ በጊፋታ ሁሉም የቤተሰብ አባላት የየራሳቸው የሥራ ድርሻ አላቸው፡፡ የአባወራዎች ተግባር የጊፋታ በዓል ዝግጅት የሚጀምረው በቁጠባ/”ቆራጱዋ” ነው፡፡ ይህም በጊፋታ ዕለት ወንዶች በሬ ከታረደ በኋላ ከሁሉም የሥጋ ዓይነት ከየዓይነቱ ትንሽ ትንሽ ቆርጠው በባለተራው ቤት በተዘጋጀው ማባያ ማለትም ቆጮ፣ ቂጣ፣ ዳታ በርበሬ ጋር የ”አሙዋ” አባላት በጋራ ይቋደሳሉ፡፡ ይህም የአንድነትና የፍቅር ማብሰሪያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ከዚያም የተከፋፈሉትን ሥጋ ከመውሰዳቸው በፊት ለመጪው ዓመት በሬ መግዣ አሁን በታረደው በሬ ቆዳ ላይ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ይጀምራሉ፡፡ ይህንንም ስርዓት የጋዚያ ጨዋታ ሲጠናቀቅ በየሳምንቱ ገንዘቡን በታማኝ አባወራ ቤት ቁጠባውን ይቀጥላሉ፡፡ በመጨረሻም ዓመቱ ሲጠናቀቅ ተሰብስበው በሬ ከገዙ በኋላ የሚተርፈውን ገንዘብ ለቤት ውስጥ ወጪ ይጠቀማሉ፡፡ ለምግብነት የሚውሉ የምግብ ዓይነቶችን በዘር ወቅት መዝራት መሰብሰብና ለጊፋታ ወቅት ለይቶ ማስቀመጥ፤ ከበዓሉ ቀደም ብሎ ለማገዶ የሚሆኑ እንጨቶችን ሰብስቦ(ፈልጦ) ማከማቸት፤ በጊፋታ ወቅት ለከብቶች የሚሆን ሳር በበቂ ደረጃ አጭዶ መከመር፤ በዓሉ ሲቃረብ ለልጆች አዳዲስ ልብሶችን መግዛት፤ ለቅመማ ቅመም መግዣ የሚሆን ገንዘብ ለእናቶች መስጠት የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ ከአባዎራዎች ተግባር አንዱና ዋንኛው የበሬ ግዥ ነው፡፡ ለጊፋታ የሚታረድ በሬ ለመግዛት ሲፈለግ ከአሙዋ አባላት መካከል ሦስት ሰዎች ተመርጠው በገንዘብ ያዡ ቤት የጧት ቡና ከጠጡ በኋላ ገንዘብ ያዡን ይዘው ወደ ገበያ ይሄዳሉ፡፡ ገበያ እንደደረሱም ቢቀለብ በአጭር ጊዜ ሊሰባ የሚችል በሬ ዋጋ ተደራድረው ገዝተውና በአዲስ ገመድ አስረው በልጆች በማስጎተት ወደ “አሪያዋ” ቤት ያመጣሉ፡፡ “አሪያዋ“ ማለት በሬውን እስከ እርድ ዕሁድ ዕለት ድረስ በቤቱ አስሮ የሚንንከባከብ ተረኛ የ“አሙዋ “ አባል ማለት ነው፡፡ ለእርድ ቀን ከሁለት ወር በላይ የሚሆን ጊዜ ሲቀረው የተገዛው በሬ ለ”አርያዋ” ይሰጣል፡፡ ለበሬው ምቹ ቦታ ቀድሞ በዚህ ቤት እንዲዘጋጅ ይደረጋል፡፡ የጊፋታ በሬ እንደሙሽራ ስለሚታይ ሰው እንዳያየው የተለየ ጋጣ ተዘጋጅቶ ሁሉም ቀዳዳዎች በቆናሽያ (በደረቅ የኮባ ቅጠል) ከምግብ መስጫ ጠባብ በር ውጪ ሙሉ በሙሉ ይሸፈናል፡፡ ከዚያም የአሙዋ አባለት ስኳር ድንች፣ የበቆሎ አገዳ፣ በቆሎ… በልጆቻቸው እያሸከሙ ወይም በአህያ እየጫኑ በየተራ በማምጣጥ ይቀልባሉ፡፡ ቀጥሎም በየ15 ቀኑ ተሰብስበው በሬውን ወደ ውጪ በማውጣት ያለበትን ደረጃ በማየት በጣም እየወፈረ ከሆነ ተንከባካቢውን እያሞገሱ አስተያየት ይሰጣሉ፡፡ በዚህ ዓይነት የጊፋታ በሬ ይቀለባል፡፡ ሌላው በአባቶችና በወንድ ልጆቻቸው የሚከናወን የአካባቢ እድሳት ሥራ ነው፡፡ ይህም በወላይታ ብሔር አዲስ ዓመት የመታደስ ምልክት ስለሆነ ሰዎች በግላቸው የቤታቸውን የሳር ኪዳን በአዲስ ሳር መቀየር፣ በቤት ውስጥ ያረጁትን ነገሮች ማለትም ቃረጣ፣ ቁሩጧ፣ ሻኳ፣ ሴፋ፣ ጋጣታ፣ ዛዳሉዋ፣ ጎጵያ፣ ቱቂያ፣ ድዝግያ፣ ኮጫ፣ እንዳ … የመሳሰሉትን ከውጪ ደግሞ በቤቱ ዙሪያና በአካባቢው የሚገኙ ቆሻሻዎችን በማጽዳት በዓሉን ይቀበሉታል፡፡ እነዚህ ከአባወራ ተግባራት በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የእማወራዎች ተግባር እማዎራዎች ለጊፋታ በዓል ከሚያደርጉት ዝግጅቶች የመጀመሪያው ”ኦይሳ ቆራጱዋ” ወይም የቅቤ ዕቁብ ሲሆን ይህም ዋንኛው የእማወራ ተግባር ነው፡፡ በዚህም መሠረት ዓመቱን ሙሉ ለጊፋታ የቆጠቡትን ቅቤ በቦቦዳ አጥቢያ ሰብሳቢያዋ ቤት ተሰብስበው የቅቤ ቡና ከጠጡ በኋላ የየድርሻቸውን ተከፋፍለው ይወስዳሉ፡፡ ጊፋታ ካለፈ በኋላም ለቀጣይ ዓመት በየሳምንቱ ቁጠባውን ይቀጥላሉ፡፡ እናቶች ከሰኔ ወር መጨረሻ አካባቢ ለተለያዩ ባህላዊ ምግቦች ማለትም ለቆጮ፤ ለሙቹዋ፤ ለባጪራ፤ የሚሆኑ የደረሱ እንሰቶችን በመፋቅ ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡ እንሰት መፋቅ የእናቶች ተግባር ቢሆንም የሚፋቀውን እንሰት መርጦ ማዘጋጀት ግን የአባወራው ተግባር ነው፡፡ በአባወራው ተለይቶ የተሰጠውን እንሰት ጓደኞቿንና ሴት ልጆቿን በማስተባበር መፋቅና ማዘጋጀት የእማወራ ተግባር ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የወላይታ ዳታ በርበሬ ያዘጋጃሉ፤ በዓሉ ሲቃረብ የተለያዩ መጠጦችን ማለትም ቦርዴ፡ ጠላ እና ወተት በታላቅ እንስራ ይዘጋጃል፤ ለልጆች “ጋዚያ” ጨዋታ የሚሆን ሎሚ ገዝተው በቀዝቃዛ ቦታ ያስቀምጣሉ፤ የተለያዩ መዋቢያ ጌጣጌጦችን ይገዛሉ፤ ለምግብነት የሚውሉ የተለያዩ የእህል ዓይነቶችን ገዝተው ያጠራቅማሉ፡፡ በጊፋታ በዓል ዝግጅት የወጣት ወንድ ልጆችና ልጃገረዶች ዋና ተግባር ወንዱ የጉሊያ እንጨት ከመቁረጥ፣ ከማቆምና ከማቃጠል እንዲሁም የማገዶ እንጨት ከመፍለጥ፣ የከብቶችን ሳር አጭዶ ከመከመር ውጪ በአጠቃላይ አባቱ በሚያደርገው እንቅስቃሴ አባቱን የሚረዳ ሲሆን ልጃገረዶችም በመጨረሻው ቀን እንሶስላ ከመሞቅ ውጪ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ እናታቸውን ያግዛሉ፡፡
ዕዳ መክፈል ከጊፋታ በዓል ቅድመ ዝግጅቶች አንዱ ያደረ ዕዳ መክፈል ነው፡፡ በወላይታ ብሔር ሰዎች ከዕዳ ጋር አዲሱን ዓመት አይቀበሉም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብም ሆነ የመንግሥት ዕዳ ተሸክሞ አዲሱን ዓመት የሚቀበሉ ከሆነ ዓመቱን በሙሉ ቢያመርትም በረከት የለውም ተብሎ ይታመናል፡፡ ስለሆነም አንድ ገንዘብ ወይም እህል ያስፈለገው ሰው ከሌላ ሰው ሲበደር አበዳሪው ይህ ዕዳ እጅግ ቢዘገይ እስከ ጊፋታ በዓል ድረስ እንደሚመለስ በጣም እርግጠኛ ሆኖ ነው ብድሩን የሚሰጠው፡፡ በመሆኑ በብሄሩ ከጊፋታ በፊት ዕዳን አሟጦ መክፈል የቆየ ነባር ባህል ነው፡፡ በጊፋታ ሳይከፈሉ የዘገዩ ዕዳዎች ሁሉ አዲሱን ዓመት ከመቀበል አስቀድሞ ተሟጠው ይከፈላሉ፡፡ የጊፋታ በዓል ሲቃረብ የሚውሉ ገበያዎች ከእርድ ቀን ቀደም ብሎ የጊፋታ በዓል መቃረቡን የሚያበስሩ በብሔሩ አባላት የሚታወቁ ገበያዎች አሉ፡፡ እነሱም “ሃሬ ሀይቆ”፤ ”ቦቦዶ” እና “ጎሻ” በመባል የሚታወቁ ሲሆን ሌላው ደግሞ “ ቃኤ ጊያ “ ይባላል፡፡ 1. ሃሬ ሀይቆ ”Hare hayiqo”፡- ቀጥተኛ ትርጉሙ የአህያ መሞቻ እንደ ማለት ሲሆን ይህም በወቅቱ ለአህዮች ያለባቸውን ድካም ለማሳየት ነው፡፡ በዓሉ እየተቃረበ በመጣ ቁጥር ሁሉም ሰው ለበዓሉ ዝግጅት እህልና ሌሎችን ቁሳቁሶች በአህዮች እየጫነ ወደ ገበያ ያወጣል፡፡ ይህንን ጊዜ ከሌላዉ የሚለየዉ አንድ አህያ በቀን ከሦስት ጊዜ በላይ እየጫነ ወደ ገበያ ሊመላለስ ይችላል፡፡ በመሆኑም ይህ ወቅት በሕብረተሰቡ የጊፋታ በዓል ዝግጅት ሸመታና ሽያጭ የሚጀምሩበት ነው፡፡ በመሆኑም ከሌሎች ገበያዎች በጣም የተረጋጋ እንቅስቃሴ የሚታይበት ገበያ ነው፡፡ 2. ቦቦዳ“Bobooda”፡- ሁለተኛው በሃሬ ሀይቆ ሳምንት የሚውለው ገበያ ሲሆን ይህ ገበያ ከወትሮ ለየት ባለ መልኩ በአዳዲስ ነገሮች የተሞላ ገበያ ነው፡፡ በዚህ ገበያ ገበያተኛው በተለመደው ጊዜ ቀድሞ ወደ ገበያ የሚመጣበትና በአብዛኛው ሴቶች የሚበዙበት ነው፡፡ ሴቶች ለበዓሉ የሚያስፈልጋቸውን የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች የሚሸምቱበት ሆኖ በዚህ ገበያ የሸክላ ዕቃዎች ሽያጭና ግዥ በእጅጉ ይደራል፡፡ ከዚህም ሌላ በዓሉ እየተቃረበ ከመምጣት ጋር ተያይዞ ሰዎች ሆዳቸውን ባርባር(ፍርሃት ፍርሃት) የሚላቸው ጊዜ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ የፍርሃቱ ምንጭም ከበዓሉ ትልቅነትና ስፋት አንጻር ምን ይጎልብኝ ይሁን በማለት ቤተሰቡ በሙሉ በፍርሃትና በጭንቀት የሚያሳልፍበት ወቅት ነው፡፡ 3. ጎሻ “Gooshsha”፡- ሶስተኛው ሳምንት ገበያ ጎሻ የሚባል ሲሆን ጥሬ ትርጉሙ እብደት እንደ ማለት ነው፡፡ ሰዎች ከወትሮ በተለዬ ሁኔታ ከንጋቱ 11፡30 ሰዓት ጀምሮ ወደ ገበያ ይሰበሰባሉ፡፡ በገበያ ውስጥ እርስ በርስ የሚገፋፉበት፣የሚገጫጩበት፣እንደ እብድ የሚይዙትን የሚጨባጡትን የሚያጡበት ነገር ግን የማይቀያየሙበት የገበያ ውሎ ነው፡፡ ሴቶች የልጃገረዶችን አልባሳት ማለትም “ማሽኩዋ፣ ግጠቱዋ፣ ጥብቁዋ፣ ሻማጭያ፣ ጎማራ ሀዲያ፣ ዳንጩዋ፣ ሚግዱዋ፣ ሳጋዩዋ፣ ጎዝዳ፣ ዬሌሉዋ፣ ካሎስያ፣ ወሶሉዋ፣ ሎሚያ … ወዘተ” የሚገዙበት ሲሆን ወንዶች ደግሞ ወንድ ልጆቻቸውን አስከትለው ሄደው የወንዶች አልባሳትን ማለትም ቆሊያ፣ ሀዲያ፣ ማሄላንዱዋ፣ ሞጋ፣ ህርቦራ፣ ካላቻ፣ ሁካ፣ ጎፋሪያ ወዘተ የሚገዙበትና በአጠቃላይ ገበያተኛው የሚዋከብበት ገበያ ነው፡፡ ከጊፋታ የእርድ ቀን በኋላ ለሚቀጥሉት 15 ቀናት በየትኛውም አካባቢ ገበያ ስለማይኖር ለበዓሉና ለእነዚህ ጊዜያት የሚበቃ ቁሳቁስና እህል ተሟጦ የሚሸመትበት ነው፡፡ ስለሆነም ሁሉም ሰው በዚህ ሳምንት መረጋጋት የማይታይበት በጥድፊያና በችኮላ የተሞላበት ሳምንት በመሆኑ የዕብድ ገበያ ወይም የዕብደት ሳምንት ይባላል፡፡ ቃኤ ጊያ፡- ሌላው የመጨረሻው ማሳረጊያ ቃኤ ጊያ የሚባል ሲሆን ይህም በእርድ እሁድ ዕለት ማለትም ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ ከሌሊቱ 10፡00 እስከ ጧቱ 2፡00 ሰዓት የሚቆም ሲሆን በዚህም ለበዓሉ የሚያስፈልግ ሆኖ ድንገት የተረሳ ነገር ካለ የሚሸመትበት ነው፡፡ ለእርድ እሁድ 15 ቀናት ሲቀሩት ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ከበዓሉ ወቅትና ከበዓሉ በኋላ በሚኖሩት የመዝናኛ ሳምንታት ምንም ዓይነት ሥራ ስለማይሠራ ለከብቶች የሚበቃ ሳር በወንድ ልጆች ይታጨዳል፡፡ በአሞሌ ጨው ድርቆሽ ይዘጋጃል፡፡ ከዚህም ሌላ እንጨት በአባቶችና በታላላቅ ወንድ ልጆች ይፈለጣል፤ የቆጮ ቆረጣ በእናቶችና በሴት ልጆቻችው ይደረጋል፤ በድሮ ጊዜ ማሽላና በቆሎ በባህላዊ ወፍጮ ተፈጭቶ ዱቄቱ ይዘጋጃል፤ ዳታ በርበሬ የመለንቀጥ ሥራ በሴቶች ይሠራል፡፡ የጎሻ ሳምንት እየተገባደደ ሲመጣ የሚውለው ሀሙስ “ኮሰታ ሃሙሳ”(ሻጋ ጋላሳ) ይባላል፡፡ ትርጉሙ የእንኩሮ ሃሙስ ማለት ሲሆን ዓርብ ሱልኣ አርባ(ብዛ ጋላሳ) ይባላል፡፡ ይህም በየቤቱ ለቦርዴ የሚሆን እህል የሚዘጋጅበት ሲሆን ለሆድ ማሟሻ ጎዳሬ “Boynaa Cadhdhiyaa” እና ከቦዬ የሚዘጋጅ “Boyinaa Pichaata” የሚበላበት ዕለት ነው፡፡ ቅዳሜ የባጪራ ቅዳሜ “Baaccira qeeraa” የሚባል ሲሆን በዚሁ ዕለት ለእሁድ(የእርድ) ዕለት ሆድ ማለስለሻ ምግቦች ይበላሉ፡፡ በዚህ ዕለት በዋናነት የሚዘጋጁ ምግቦች ባጪራ፣ ሙቹዋ፣ ጉርዱዋ በመባል የሚታወቁ ናቸው፡፡ ሌላው ትልቁ ሥርዓት ደግሞ የእጥበት ሥርዓት ነው፡፡ በዚህ ዕለት ሌሊት ሁሉም ሰው ልብሳቸውን ያጥባሉ ገላቸውንም ይታጠባሉ፡፡ ይህም ከአሮጌው ዓመት እድፍና ቆሻሻ ጋር ወደ አዲሱ ዓመት መሻገር አያስፈልግም ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ እሁድ የአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ቀን ሲሆን ከሁለት ወር በፊት በቡድኑ”Amuwaa” አባላት የተገዛው የጊፋታ በሬ በተረኛ የአሙዋ(የቡድኑ) አባል ቤት እሼት በቆሎ፤ስኳር ድንች እንዲሁም ለምለም ሳር አባለቱ በየቀኑ እያዋጡ በደንብ የተቀለበዉ በሬ የሚታረድበት ዕለት ሲሆን የዝግጅት ምዕራፍ ተጠናቆ የመዝናኛ ሳምንት የሚጀመርበት ነው፡፡ የበዓሉ አከባበር የዕርድ ዕለት ጧት ወፍ እንደተንጫጫ በቤተመንግሥት 12 ጊዜ ነጋሪት ይጎሰማል፡፡ በዚህን ጊዜ ከሁሉም የወላይታ አካባቢዎች የአላና ኃላፊዎች ይሰበሰባሉ፡፡ የነጋሪቱን ድምጽ እንደሰሙ የበሬ አራጆች ሥራቸውን ይጀምራሉ፡፡ ከተለያየ ቦታ የመጡ የአላና ኃላፊዎች ወደ ግብር አዳራሽ ይገባሉ፡፡ ቀጥሎም ንጉሱ በክብር ወደ አዳራሹ ከገቡ በኋላ ለሰማይ አምላክ ምስጋና አቅርበው ለበዓሉ የተዘጋጀው ቦርዴ ንጉሱ ከቀመሱ በኋላ እርስ በርስ የፍቅር መግለጫ በሆነው የ”ዳጌታ“ ሥርዓት ይጠጣሉ፡፡ ለበዓሉ የታረደው ሥጋ በዳታ በርበሬ፣ በቂጣና በጎዴታ ቆጮ ይቀርባል፡፡ ሁሉም በልተውና ጠጥተው ወደ የአካባቢያቸው ይመለሳሉ፡፡ ይህም በብሔሩ የጊፋታ “ቃይዴታ” ሥርዓት የሚባል ሲሆን የተጣላ የሚታረቅበት ፍቅራቸውን ከአንድ ማዕድ በመቁረስ የሚያድሱበትና የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ ነው፡፡ በዕለቱ የበሬ ሥጋ በጋራ የሚያርዱ የ”አሙዋ” አባላት በየቤታቸው ጠዋት ሙቹዋ ወይም ባጭራ በቅቤ ቡና ይቀምሱና ብላዋና ቅርጫት አስይዘው ወንድ ልጆቻቸውን ወንድ ልጅ ከሌላቸው ሴት ልጆቻቸውን በሬ ወደሚታረድበት ደጃፍ ይሄዳሉ፡፡ የበሬውን ቆዳ ከገፈፉ በኋላ መጀመሪያ ፊኛው ወጥቶ ለልጆች ይሰጣል፡፡ ልጆች ሥጋው ታርዶ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ፊኛ በእግራቸው እየመቱ ይጫወታሉ፡፡ በሬ በሚታረድበት ቤት ደጃፍ የተሰበሰቡ ሰዎች “ባጭራ” ወይም “ሙቹዋ” ከቅቤ ቡና ጋር ይበላሉ፤ባህላዊ መጠጥም ይቀርባል፤ እነዚህ ሰዎች በሬውን በጋራ ያርዳሉ፤ በሬው እየታረደ እያለ ከሁሉም የሥጋው ብልት የተወሰነ ይቆረጥና የ”አሙዋ”አባላት የፍቅር መግለጫ ነው ተብሎ ስለሚታመን በጋራ ይቋደሳሉ፡፡ በመቀጠልም ዕጣ ጥለው ሥጋውን ከተከፋፈሉ በኋላ ለሚቀጥለው ዓመት ጊፋታ በዓል በሬ መግዣ ተቀማጭ በታረደው በሬ ቆዳ ላይ ይጀመራል፡፡ ይህ የቁጠባ ሥርዓት ከ”ጎሉዋ ኢጌታ” በኋላ በየሳምንቱ እስከ ዓመቱ መጨረሻ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ የአመጋገብ ሥርዓት የግፋታ ዕለት ከንጋት ጀምሮ ቤት ውስጥ የተለያዩ ዝግጅቶች ይደረጋሉ፡፡ እናቶች ከተዘጋጀው ዳታ ለዕለቱ የሚበቃውን ከፍለው ቅቤ በመጨመር በእሳት ያንተከትካሉ፣ ቂጣ፣ ቆጮ ያዘጋጃሉ፡፡ ከዚህም ሌላ “ኤርጊያ” የሚባላውን ያልተበሳሳ ኮባ ቅጠል ተቆርጦ ሳሎን ላይ በመሬት እንዲዘረጋ ይደረጋል፡፡ አባት ካመጣው ሥጋ መካካል ጥሬ የሚበላውን በማዘጋጀት በቢላዋ እየቆረጠ በኮባው ቅጠል ላይ ዙሪያውን ያስቀምጣል፡፡ ቆጮና ቂጣም በተመሳሳይ ሁኔታ ይደረጋል፤ በመሃል በመሃሉ ዳታ በርበሬ በወጪት ተደርጎ ይቀመጣል፡፡ ማዕዱ ከቀረበ በኋላ ከዓመት ዓመት በሰላም ያሸጋገረውን አምላክ እንደዬ አምልኮ ስርዓታቸው ያመሠግናሉ፡፡ አባት ከሁሉም በፊት ከተዘጋጀው ማዕድ እናትን ያጎርሳል፡፡ በመቀጠል በማዕዱ ዙሪያ የተቀመጡትን ልጆች ሁሉ ያጎርሳቸዋል፡፡ ቀጥሎም የቤተሰቡ አባላት ለየራሳቸው መመገብ ይጀምራሉ፡፡ የጉሊያ አቀጣጠል ሥርዓት ፡- ጉሊያ የወላይታ ብሔር የጊፋታ በዓልን በእሳት ብርሃን የሚያከብረው ሥርዓት ሲሆን የሰኔ “ኩሻ” ወር ማብቂያ ሦስት ቀናት ሲቀሩት የሠፈር ወጣቶች ብዙ አገልግሎት የማይሰጡ እንጨቶችን ከጫካ ውስጥ ቆርጠው እየጎተቱ በአንድ ቦታ ይከምራሉ፡፡ የተከመረው እንጨት ለጊፋታ በዓል ሁለት ሳምንት ሲቀረው እንዲቆም ይደረጋል፡፡ የተከመረው እንጨት የጊፋታ ወር መጀመሪያ ጨረቃ በታየች አራት ቀናት መካከል በሚውለው እሁድ (ሹሃ ወጋ) እርድ ተከናውኖ ሥጋ ከተበላ በኋላ ማታ የሚከበር ታላቅ ሥነ-ሥርዓት ነው፡፡ በዚህ ዕለት ማታ አንድ ሰዓት አካባቢ የሠፈር ወጣት ወንዶችና አባቶች ከየቤታቸው ቺቦ(ጢፋ) በመያዝ በጉሊያው ዙሪያ ይሰበሰባሉ:: በአካባቢው ታዋቂና ታላቅ የሆነ ሰው ጉሊያውን በእሳት እንዲለኩስ ይጋበዛል፡፡ በዚህን ጊዜ ይህሰው(ሳሮ ላይታ ኦታ፣ ሲቆ ላይታ ኦታ፣ ካሎ ላይታ ኦታ) እያለ በእሳት የተቀጣጠለ ችቦ ይዞ ይዞርና ኡደቱን ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ ዞሮ ከገጠመ በኋላ ጉሊያውን ይለኩሳል፡፡ ከዚያም ከየቤታቸው ያመጡትን ችቦ ይጨምራሉ፣ የጉሊያው ምሶሶ እስኪወድቅ ድረስ ወጣቶች ዞሪያውን ከቦ “ሃያያ ሌኬ” የሚባለውን ባህላዊ ዘፈን ይዘፍናሉ፤ ይጨፍራሉ፡፡ ሥጋ ከተበላ በኋላ ልጃገረዶች በአካባቢው ጉሊያ ወደሚቀጣጠልበት ቦታ በመሄድ ክብ ይሠሩና የጊፋታን ጨዋታ እየተጫወቱ ያመሻሉ፤ በመጨረሻ በቀጥታ በአካባቢው አዲስ ሙሽራ ካለች ወደሷ ቤት በመሄድ እየዘፈኑና እየጨፈሩ ይቆያሉ፤ እኩለ ሌሊት ሲደርስ ቀን በዛ ቤት ተፍቆ አዘጋጅቶ ያስቀመጡትን እንሶስላ ይሞቃሉ፡፡
ከእርድ በኋላ ከፍ ብሎ እንደተጠቀሰው በእርድ ዕለት ማታ ጉሊያ የማቃጠል ሥርዓት የሚፈጸም ሲሆን የእርድ ዕሁድ ማግስት ሰኞ ታማ ሰይኖ ይባላል፡፡ ጥሬ ትርጉሙ የእሳት ሰኞ ማለት ነው፡፡ ይህም እሁድ ዕለት በሁሉም ሰው ቤት እስከ ሌሊት ድረስ እሳት ስለሚነድ በነጋታው ሰኞ ማንም ሰው ወደ ጎረቤቱ እሳት ለመጫር አይሄድም፡፡ ምክንያቱም የእሳቱ ፍም በነጋታውም ቢሆን በሁሉም ቤት አይጠፋም፡፡ በዚህ ቀን ከሚከናወኑ ተግባራት አንዱ የተረፈው ሥጋ ተዘልዝሎ እሳት በምድጃው ላይ በደንብ እንዲነድ ተደርጉ በምድጃው ግራና ቀኝ ባላ እንጨት ተተክሎ ተዘልዝሎ ይጠበስና ማባያ ተዘጋጅቶ ሁሉም ተሰብስበው ይበላሉ ይጠጣሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ቀን ቶሎ የሚበላሹ የሥጋ ዓይነቶችን በእሳት በማገንፈል ጨው አዘጋጅቶ በማከም ለረዥም ጊዜ እንዲቆይ ያደርጋሉ፡፡ ከግፋታ ቀጥሎ የሚመጣው ሁለተኛው ቀን ማክሰኞ “ጪሻ ማስቃይኖ” ይባላል፡፡ ይህም የመልካም ምኞት አበባ የሚለዋወጡበት ቀን ነው፡፡ በዚሁ ዕለት የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ “ኮርማ ጪሻ” ተብሎ የሚጠራው ነጭ አበባ ይህ ካልተገኘ ደግሞ የአደይ አበባ የተባለው የአበባ ዓይነት ተይዞ እንኳን አደረሳችሁ! ጊፋታ ዮዮ! እየተባለ አማች፣ አበልጅ ቤት እንዲሁም ደግሞ እንደየቅርበቱ ዘመድ አዝማድ ቤት እየተኬደ መልካም ምኞታቸውን የሚገልጹበት ዕለት ነዉ፡፡ አበባውን ይዘው ከሄዱ በኋላ ለቤቱ አባወራ የሚሰጥ ሲሆን እሱም በቀኝ እጁ ይቀበልና ከምሶሶ ጋር ያስራል፡፡ እነዚህ ሁለት ዓይነት አበቦች በጊፋታ ወቅት ብቻ የሚፈኩ አበቦች ስለሆኑ አባወራው አበባዉን ከተቀበለ በኋላ ጊፋታ እናንተን አይቁጠር እናንተ ጊፋታን ቁጠሩ “Gifaatay Inttena Qoodoppo Initte Gifaataa Qoodite” ከዓመተ ዓመት በሰላም ያድርሳችሁ በማለት ይመርቃሉ፡፡ ከዚያም የሚበላና የሚጠጣ ነገር ተጋብዘው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ በነጋታው ጋዜ ኦሩዋ ”Gazze Oruwaa” ሲሆን ይህም ሰዎች አጠቃላይ ሀሳባቸውን ወደ መዝናኛ የሚያደርጉበት ሆኖ ታላቁ የጊፋታ ጨዋታ ጋዚያ” Gazziyaa”መድመቅ የሚጀምርበት ዕለት ነዉ፡፡ በዚህ በተከታታይ ለሁለት ሳምንታት በሚቆየዉ ጨዋታ የመንደሩ ወጣት ወንዶችና ወጣት ሴቶች በአካባቢው ታዋቂ ሽማግሌ ደጃፍ ተሰብስበው ወንዶች ሃያያ ሌኬ እያሉ ትከሻ ለትከሻ ተቃቅፈው ሎሚ ከልጃገረዶች በመለመን ለትዳር የሚፈልጓትን የሚመርጡበትና የሚያባብሉበት ሴቶችም ደግሞ እንደ አስፈላጊነቱ ምላሽ እየሰጡ የሚጫወቱት የጨዋታ ዓይነት ነው፡፡ በጋዚያ ወጣቶች ይዘፍናሉ፤ ትግል ይገጥማሉ፤ ሩጫ ይወዳደራሉ፤ የፈረስ ጉግስ ይደረጋል፤ ሎሚ ከልጃገረዶች ላይ ይለምናሉ፡፡ ልጃገረዶች አንድ ላይ በመሆን በየቡድኑ ተከፋፍለው ተቀምጠው “ሀያ ወላሎሜ” እያሉ ለወንዶች ሎሚ በመወርወር ይመርጣሉ፡፡ አንዳቸው ለሌላው ልዩ ሚስጥረኛ ይሆናሉ፤ ከዚያን ዕለት ጀምረው በስማቸው ሳይሆን የሚጠራሩት “ሎሜ ሎሜ” በማለት እርስ በርስ ይጠራራሉ፡፡ ሌላው ደግሞ ልጃገረዶች እርስ በርስ ለሚዜነት ከሚመርጧት ጋር አንድ ሎሚ በጥርሳቸው በጋራ በመካፈል እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ እርስ በርስ ሚስጥር በመጠበቅ የልብ ጓደኛሞች ይሆናሉ፡፡ በጋዚያ ቦታ ወላጆች የልጆቻቸውን ጨዋታ ለማየት አልፎ አልፎ ይመጣሉ፡፡ እርስ በርስ እንዳይጣሉና ግጭት እንዳይፈጠር እንዲሁም ደግሞ ጠለፋ እንዳይፈጸም ይከታተላሉ፡፡ በዚያ ቦታ ከጓደኞቻቸው ጋር በመገናኘት ”Booray Molshsha! Miizziyaa Oysso!“ በመባባል እርስ በራሳቸው ይጫወታሉ፤ በመጨረሻም አንድ ላይ ተቃቅፈው ለዘለዓለም እንኖራለን ”Merinaayyo Daana” በማለት አንዱ ለሌላው መልካም ምኞቱን ይገልጻል፡፡ ከጋዜ ኦሩዋ ጀምሮ ተቆጥሮ የሚመጣው ሶስተኛ ረቡዕ ጎሏ ኦሩዋ ”Gooluwaa Oruwa” ይባላል፡፡ ይህም ከአንድ ወር በላይ ለሚሆን ጊዜ የቆየው የበዓል ዝግጅትና አጠቃላይ የጊፋታ በዓል ሥነ-ሥርዓት አብቅቶ የሚሸኝበት ቀን ሲሆን ከበዓሉ ጋር ተያይዞ በነበረው የመዝናኛ ወቅት ምክንያት በሕዝቡ ዘንድ ስንፍና እንዳይገባ በማለት ሁሉም ችቦ እያቀጣጠሉ ለሚመጣው በዓል አምላክ በሰላም እንዲያደርሳቸው በመመኛት ይሸኛሉ፡፡ ይህም የመዝናኛ የዕረፍት ወቅት አብቅቶ ወደ ሥራ የሚገባበት ወቅት በመሆኑ “Oruwaappe Hepinttay Ofintta” ይባላል፡፡ ይህም ከዕሮብ በኋላ ዕረፍትና መዝናናት የለም የሥራ ወቅት ተጀምሯል፤ ወደ ሥራ አንግባ እንደማለት ነው፡፡