Jump to content

የዞራስተር ፍካሬ ክፍል ፪

ከውክፔዲያ
"ዘሩን እንደዘራ ገበሬ ማደጉንም እንደሚጠባበቅ፣ ዞራስተር ከሰወች በማምለጥ ወደአምባው፣ ወደ የብቸኝነት ዋሻው ተመለሰ"

ዞራስተር በዚህ ወቅት ከተራራው ወርዶ ስላጋጠመው ሁኔታ ማንሰላሰል ጀመረ፣ በተለይ "ኃይልን መፈለግ" ("ኃይልን መፍቀድ") የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ተገነዘበ። በዞራስተር አስተያየት ኃይልን መፍቀድ ህይወት ያለው ነገርን ሁሉ የሚገፋፋ መሰረታዊ ጉልበት ነው። ይህ ሃይል፣ በዞራስተር አስተያየት፣ ለመኖር ከመፍቀድ ሁሉ በላይ የሆነ ኃይል ነው። ኃይልን መፍቀድ በብዙ መንገድ ይገለጻል፣ ለምሳሌ፡- ባህታዊወች በመብላት ፍላጎታቸው ላይ ያላቸው ሃይል፣ ግለሰቦች በህብረተሰብ ውስጥ የሚያሳዩት የእራስን ስልጣን የማረጋጥ ሁኔታ፣ አንድ የኪነ ጥበብ ሰው በስራው ላይ የሚያሳየው ሙሉ ክህሎት፣ ወዘተ..።

በሄድኩበት ቦታ ሁሉ ያገኘሁት ህይወት ያለው ነገር ሁሉ ኃይልን ይፈቅዳል፣ የሚታዘዙት እንኳ ሳይቀር ጌታ ለመሆን ይፈቅዳሉ! ደካሞች ለጠንካሮች ለመታዘዝ በሌላ ሳይሆን በራሳቸው ፈቃድ ይስማማሉ፣ ደካሞቹ ደግሞ በተራቸው ከነሱ የበለጠ ደካማ ለሆነው ጌትነት ይፈቅዳሉ፡ ይህ ጨርሰው ሊተውት የማይፈቅዱት ደስታቸው ነው!
ታናናሾቹ ከነሱ ያነሱት ላይ ኅይል እንዲኖራቸው ለበላዮቻቸው ፈቀቅ እንደሚሉ ሁሉ ከሁሉ የበላይ የሆነው ለአደጋና ከባድ ፈተና እንዲሁ ፈቀቅ ይላል፣ ለኅይል ሲልም ህይወቱን አደጋ ላይ ይጥላል። የሁሉ ታላቅ ፈቀቅ ማለት ለህይወት አስጊ ለሆነ አደጋና በሞትና በህይወት ቁማር ለመጫወት ነው።

በዚህ ክፍል ግማሽ አካባቢ ዞራስተር ብዙ ስራው የጭንቅላት ስራ እንደሆነ ተረዳ፣ ስለዚም ቶሎ ብሎ መዝፍንና መደነስ ተያያዘ። ደመነፍስ ኪነጥበብ የሆኑት ዘፈንና ዳንስ፣ የሰው ልጅ ኅልውና ዋና አካል መሆንቸውን በማስረገጥ ብዙ የጥበብና የብርሃን ተሸካሚ መሆን ጥሩ እንዳይደል አስረዳ። ይህ ሁኔታ ስለአጠቃላይ የህይወት ትርጉም ያለውን አስተያያእት ተፈታተነው፡ በፍልስፍናና በትምህርት የህይወት ትርጉም ራዕይ እንደማይገለጥለት ተረዳ። አስተማሪና አዋቂ ብቻ ከመሆን ይልቅ እንደ ዘፈንና ጭፈራ ያሉትን የህይወትን ደመነፍሳዊ ክፍሎች በመቋደስ የህይወት እውነታወች መረዳት እንዲቻል ተገነዘበ።

ከዘፈንና ዳንስ በኋላ ማስተማር ቀጠለ። በዚህ ትምህርቱ አጋጣሚ የሆነ አዋቂ ሰው አግኝቶት የዚህ አለምን የከንቱ ከንቱነት ሰማ። ይህ ጉዳይ በዞራስተር ላይ መወላወልን ፈጠረ። ዞራስተር የሰው በላይን መምጣት ቢሰብክም ይህ እራሱ ከንቱ እንዳልሆን ምንስ ምክንያት አለ? ዞራስትራስ የህይወትን ትርጉም እንዳወቀ ምንስ ማስረጃ አለ፣ የዞርስተር ፍልስፍናስ ካለፉት የስው ልጅ ባህሎችና አስተያየቶች ልዩ እንደሆነ ምንስ ማስረጃ አለ?

በዚህ ውዥንብር ውስጥ ያለው ዞራስተር እንቅልፍ ወስዶት ህልም ተመለከተ፣ በህልሙ ከፍተኛ ነፋስ ተነስቶ የሬሳ ሳጥንን ሲገለብጥ፣ ከሬሳ ሳጥኑ "ህጻናት፣ መላዕክት፣ ጉጉት፣ ጅሎችና ግዙፍ ቢራቢሮወች" እያመለጡ ሲወጡ አየ። በድንጋጤ የነቃው ዞራስተር ስለህልሙ ለአንድ ተከታዩ ነገረው። ተከታዩም ንፋሱ የዞራስተር ትምህርት ምልክት ሲሆን አጠቃላይ ህልሙም የቀድሞውን የሞተ ባህል ማጥፋቱንና በምትኩ አዳዲስ እምቅ ሃይላትን ማውጣቱን ይሳያል አለው። ዞራስተር ግን ጥርጣሬው ሊበርድ አልቻለም። የወደፊት አለም ነጻ አውጪ ከመሆን ይልቅ የሞተው የኋለኛው ዘመን ባህል አካል እንዳልሆነ እራሱን ሊያሳምን አልቻለም።

ከዚህ በኋላ የነበረበትን ቦታ ለቆ ጉዞ ጀመረ። በጉዞው አንድ አዋቂ ጎባጣ ዞራስተር ለተከታዮቹና በራሱ ጭንቅላት ውስጥ ለራሱ የሚያስተምረው የተለያየና ግብዝ መሆኑን ነገረው። ዞራስተር በዚህ ጊዜ ትልቅ ስህተት በፍልስፍናው ውስጥ እንዳለ ተገነዘበ። ለተከታዮቹም ሆነ ለራሱ የማይነግረው፣ በተጨማሪ ለራሱ እንኳ የማያምነው ትልቅ ችግር እንዳለ ተገነዘብ። ይህ ነገር ምን እንደሆነ በግልጽ ሊረዳ አልቻለም ግን ጭላጭሉ ነበረው።

"ጭር ያለው ሰዓት" ባለው የመጨረሻው ክፍሉ ዞራስተር ድምጽ ከሌለው ድምጽ ጋር ሲከራከር እናነባለን። ድምጹ "የዞራስተር ፍራፍሬወች ቢጎመሩም፣ ዞራስተር ግን ለፍራፍሬወቹ እንዳልጎመራ" አስረዳው። ይህም በዞራስተር ስብዕናና በሚያስተምረው ትምህርት መካከል ልዩነት እንዳለና ዞራስተር ግብዝ እንደሆነ ስለሆነም ስብዕናውን በመቀየረ እራሱን ማሻሻል እንዳለበት ተረዳ።

ይህን በምሳሌ እነግራችዋለሁ። ትላንትና ፣ ጸጥታ በሰፈነበት ሰዓት፣ ድንገት ከእግሬ በታች ምድር ተንሸራታ ጠፋች፡ ህልሜም ጀመረ። የጊዜ እጅ ወደፊት በሚነጉድበት፣ የህይወቴ ሰዓት ትንፋሹን በዋጠበት የሰማሁት ጸጥታ ልቤን በፍርሃት ሞላው።
በድንገትም ያለምንም ድምፅ አለኝ "ታውቃለህ ዞራስተር?"
ሹክሹክታው ስላስፈራኝ ጮኽኩ፣ ፊቴም ገረጣ፣ ግን ካፌ ድምጽም አልወጣም!
ቀጠለም "ዞራስተር ታውቃለህ ግን አትናገርም!"
በመጨረሻ በሚገዳደር ቃል ተናገርኩ "አወ! አውቃለሁ ግን መናገር አልፈልግም!"
ድምጽ የሌለው ሹክሹክታ ግን ጠየቀ " አትፈልግም? ይሄ እውነት ነው? በመገዳደር ቃል እራስክን አትደብቅ!"
በዚህ ወቅት አለቀስኩ፣ እንደህጻንም ልጅ ተንቀጠቀጥኩ፣ መለስኩም፡ "ስለእውነትስ እፈልግ ነበር! ግን እንዴት አድርጌ? እባክህ ተወኝ! ይሄ ከኔ በላይ ነው!"
ድምጽ የሌለው ሹክሽክታም መለሰ፣ አለም "አንተ ማን ነህ ዞራስተር? ይልቁን የምትናገረውን ተናገርና ሙት!"

ከዚህ በኋላ ዞራስተር ተከታዮቹን ለሁለተኛ ጊዜ በመተው ወደ ብቸኝነቱ ዋሻ ተመለሰ።