Jump to content

የዞራስተር ፍካሬ ክፍል ፫

ከውክፔዲያ

ክፍል ፫[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

"ከትልቁ ተራራየ ፊት ቆምኩ፣ ከሩቁም መዋተቴ እንዲሁ። ለዛም ስል መጀመሪያ ወደ ጥልቁ ገደሌ፣ ወደ የሚያመኝ ስፍራ፣ ወደጥቁሩ ጎርፌ መውርድ አለብኝ"

በማለት ዞራስተር ከተከታዮቹ ተለይቶ ከባዱን ስራውን ለመፈጸም ባዘነ። ግቡም የ"በላይ ሰው"ን ማስተማር አቁሞ እራሱ የበላይ ሰው ለመሆን ነበር።

"መሰላል ከሌላችሁ በራሳችሁ ጭንቅላት ላይ መወጣጣትን ልመዱ፤ በሌላስ በምን መንገድ ወደላይ ለመውጣት ትሻላችሁ? በጭንቅላታችሁ፣ ከልባችሁ እርቃችሁ... ከዋክብቶቻችሁ ሳይቀሩ ከግራችሁ በታች እስኪሆኑ ወደ ላይ ተወጣጡ!"

ዞራስተር በከተሞችና በባህር ጠረፎች በሚዋትትበት ዘመን መንፈሱን ወደታች ስለሚጎትተው የስበት ሃይል ማውጣት ማውረድ ጀመረ። ይህ ሃሳቡን ወደታች የሚጎትተው መንፈስ ባለፈው ክፍል አዋቂው የነገርው የ«ሁሉ ነገር ከንቱነት ነበር። ሁሉም ወደ ላይ የተወረወረ ነገር ወደ መሬት መልሶ ይወድቃል፣ ስለሆነም ሁሉም የከንቱ ከንቱ ነው!»

ዞራስተር ይህን ወደታች የሚጎትት የስበት ሃይል ለማሸነፍ የሁሉ ነገር ዘላለማዊ መመላለስን ሃሳብ ማውጣት ማውረድ ጀመረ። በአለም ላይ ያለው የቁስ ብዛት የተወሰነ ሲሆን ጊዜ ግን የማያልቅ ጅረት ነው። ስለሆነም በቁስ ውስጥ ያሉት እያንዳንዱ አተሞች የሚደረደሩበት መንገድ ስፍር ቁጥር ባይኖርውም... ከጊዜ ወሰን የለሽ የትየለሌንት አንጻር እያንዳንዱ የአቶም አደራደር ዘዴ ተመልሶ ይመጣል። እያንዳንዱ ቁስ ያለፈበትን አደራደር በዘመናት ይደግማል። ሁሉም ነገር ተመልሶ ይመጣል። ሁሉም ኅልው ነገር ካሁን በፊት ኅልው ነበር ስለዚህ መጭው ዘመን እንደ በፊቱ ነው።

"ኦ! ዞራስተር" አሉ እንስሳቶቹ "ሁሉም ነገር ይሄዳል፣ ሁሉም ነገር ተመልሶ ይመጣል፣ ለዘላለም የህልውና ጎማ ይሽከረከራል። ሁሉም ይሞታል፣ ሁሉም እንደገና ያብባል፣ የህይወት ቀለበት በንዲህ መልኩ ለዘላለም ይቀጥላል። ሁሉም ይሰበራል፣ ሁሉም እንደገና ይጋጠማል፣ ላለም እስከ ዘላለም አንድ አይነት የኅልውና ቤት ይገነባል። ሁሉም ይለያያል፣ ሁሉም ከሁሉ ጋር እንደገና ይገናኛል፣ ለዘለዓለም የኅልውና ቀለበት በራሱ ላይ እንዲህ ይሽከረከራል።"

ጊዜ እንደ መስመር ቀጥ ብሎ የተሰመረ ሳይሆን፣ ላለም እስከ ዘላለም ክብ ሰርቶ በራሱ ላይ የሚሽከረከር እንጂ። "ቀጥ ያለ ሁሉ ውሸት ነው፣ ሁሉም እውነት የተንጋደደ ነው! ጊዜ ራሱ ክብ ነው!"

ነገር ግን የዘላለም መመላስ ዞራስተርን ከማስደስተ ይልቅ በጣም በጠበጠው። በዚህ ፍልስፍና መሰረት ሁሉ የሰው ልጅ የበላይ-ሰው ለመሆን የሚያደርገው ጥረት መና ሆነ እንደገና ወደ ነበረበት ዝቅተኛ ስብእና ጊዜውን ጠብቆ ይመለሳል። የበላይ ሰው ማለት የሰው ልጅ በትግል የወጣው ተራራና ከዚህም ተራራ ተነስቶ ወደ የበለጠ ከፍታ የሚወጣጣበት ሳይሆን በአዙሪት ውስጥ ያለ አንድ አልባሌ ነጥብ ሆነ። ሃሳቡ ዞራስትራን ክፉኛ አውኮት ሲቆዝም የአንድ ወጣት እረኛ ታሪክ በራዕይ መልኩ ታየው። እረኛው ጉሮሮ ውስጥ ጥቁር እባብ ተሰንቅሮ መተንፈሻ አሳጣው። እባቡንም ከጉሮሮው መንግሎ ለማውጣት የማይቻል ሆነ። በዚህ ጊዜ ዞራስተር ድምጹን ከፍ አድርጎ "እራሱን ግመጠው!" ብሎ ለዕረኛው ጮኽ። ዕረኛውም የተባለውን በማድረግ የእባቡን እራስ ቱፍ ሲል የነጻነትን ሳቅ ያቀልጠው ጀመር። ከዚህ ጀምሮ ዞራስተር አንድና አንድ አላማ ብቻ ህይወቱን ገዛ፣ እርሱም ወደታች የሚጎትተውን መንፈስ በማሸነፍ ልክ እንደ እረኛው የነጻነቱን ሳቅ መሳቅ።

ዞራስተር ከብዙ ጉዞ በኋላ ከተራራው ዋሻ ደረስ። በዚህ ክፍል መጨረሻ ዞራስተር ያወከውን ወደታች የሚጎትተውን መንፈስ ሲያሸንፍ እናነባለን። የዘላለም መመላስን ተስፋ አስቆራጭ ሃሳብ ያሸነፈው እንዲህ ነበር፡ ጊዜ ክብ ከሆነ፣ እክቡ የትኛው ላይ ኅልው እንደሆን (የት ላይ እንደምንኖር) ምንም ለውጥ አያመጣም፣ በየትኛው የዕድገት ደረጃ ላይ ኅልው መሆናችንም ምንም ለውጥ አያመጣም፣ "ሁሉም ቅጽበት ላይ ኅልውና ይጀመራል... መካከሉ ሁሉም ቦታ ነው።" ብዙ ሰወች ባለፈው ዘመን ይኖራሉ (ማለት በትውፊት፣ ባህል፣ ካለፉት ዘመናት በተወረሱ የግብረገብ ህግጋት፣ ወዘተ...ስር)። ዞራስተር ደግሞ ወደፊት በሚመጣው፣ ባልተፈጠረው አለም ባህል ይኖር ነበር። ሆኖም ግን ዞራስተር እንደተገነዘበ ያለፈውና መጭው ዘመን ምንም ዋጋ የላቸውም፣ ህይወትን መኖር በአሁኗ ቅጽበት ነው። የህይወት ትግል የሚካሄደው በዚች ቅጽበት ሲሆን ህይወትም የሚገለጸው ኗሪው በትግሉ ውስጥ በሚያሳየው ብርታት ነው። ከዚህ አንጻር የዘላለም ምልልስ ተስፋ የሚያስቆርጥ ጽንሰ ሃሳብ ሳይሆን ከሃይማኖት ውጭ የሆነ አዲስ አይነት የሚያሰደስት ዘላለማዊነት ሆነ።

ስለሆነም ዞራስተር ከነበረበት ተውከት ዳነ። ለዚህም ሲል መዝፈንና መደነስ ጀመረ። መዝፈንና መደነስ ከመናገር አንጻር የበለጠ ሃይል አላቸው፡ መናገር ከሰውነታችን የተቆረጠ፣ የንቃተ ኅሊና ስራ ሲሆን መዝፈንና መደንስ ግን ከሰውነታችን ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴወች ስለሆኑ ንቃተ-ኅሊናንና አካላታችንን አንድ ላይ የሚያሳትፉ ስራወች ናቸው። መዝፈንና መደነስ የሚችል ሰው ሙሉ ስለሆነ ህይወቱም ከአዋቂ አስተማሪወች ይልቅ በአሁኗ ቅጽበት የሚካሄድ ነው። ዞራስተር አስተማሪ በነበረበት ጊዜ የተሰማው ጎደሎነት ከዚህ አንጻር ነው። መዝፈንና መደነስ ባለመቻሉ ጎድሎ ነበር።

ለማጠቃለል ያክል፣ የመጽሃፉ የመጀመሪያ ክፍል የ"በላይ ሰውን" መምጣት የሚሰብክ ሲሆን፣ እጅግ በለመለሙና ጣፋጭ በሆኑ እይታወች የታጀበ ነበር። ክፍሉ ከተዘበራረቀው የባህል ፍርክስካሽ የተስተካከለ ስልጣኔን ለመገንባት የሚጥር ነው። ሆኖም ሁሉም የተስተካከለ ነገር የተሸሸገ ዝብርቅርቅ አስከፊ ነገር ስላለው፣ ይህም አስከፊ ነገር ዞሮ ዞሮ እራሱን የበላይ ስለሚያደርግ፣ ይህን መጋፈጥ ግድ ይላል። የአፖሎ ቀን ያለ ዳዮኒስ ጭለማ ኅልው አይሆንም። ማታው እንዳውም ከቀኑ በጣም ሃይለኛ ነው። እኒህ ጭለማ የሆኑ የህይወት ኃይሎች እጅግ ሃይለኛ ስለሆኑ ሰወች ብዙ ጊዜ ከህይወት መራቅ ይመርጣሉ፣ ስለዚህም በብዙወች አስተያየት ህይወት እጅግ ስቃይ የበዛበትና መጥፎ ሲሆን፣ ኑሮ መሸነፍ ያለበት ነገር ነው ብለው ያምናሉ። የዞራስተር አላማ እንግዲህ ምንም እንኳ ህይወት ብዙ ጊዜ ሽብር ቢኖረውም፣ መጥፎውም ቢበዛም ህይወት መኖር ያለበትና መደገፍ ያለበት እንደሆነ ማሳየት ነው። የመጽሃፉ የመጨረሻ ክፍል የዋናወቹ ገጸ ባህርያት ወደ ህይወትን ከነሽብሩና ጭለማው መውደድን ሽግግር ይተርካል። ከብዙ ማሰብና ማስተማር በኋላ - ህይወትን መኖር፣ ህይወትን ማፍቀር። የሚያይ፣ የሚሰማው፣ የሚያውቅ ፍቅር።


ከዘላለም መመላለስ በተጨማሪ ኒሼ ስለ አዳዲስ ህግጋት/ዋጋወች ማውጣት በዚሁ ክፍል አጥብቆ አስተምሯል።

"በተሰባበሩና ግማሽ ድረስ በተጻፈባቸው ጽላቶች ተከብቤ ተቀምጨ እጠባበቃለሁ። ከቶ መቼ ይሆን የኔስ ጊዜ?"