ዳንግላ ወረዳ
የጎጃሟ ዳንግላ ከተማ ታሪክ ባጭሩ
ዳንግላ ከተማ ከአዲስ አበባ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ 485 ኪ.ሜ ፣ ከክልሉ ባህር ዳር ከተማ በ78ኪ.ሜ እና ከዞኑ ርዕሰ ከተማ እንጅባራ በ36 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ናት፡፡
ከተማዋ በ 11° 18N ላቲቲዩድ እና በ36° 57E ሎንግቲዩድ ላይ ከበሀር ጠለል በላይ በ 2190 ሜትር ከፍታ ላይ ትገኛለች፡፡
የዚች ከተማ የቆዳ ስፋት 9486.4 ሔክታር ሲሆን የአየር ንብረቷ ወይና ደጋ የሆነ እና በአመካኝ 18℃ የሙቀት መጠን እና 1481.25 ሚ.ሜ የዝናብ መጠን አላት፡፡
የዳንግላ ከተማ ስያሜን በተመለከተ የሚነገረው አፈታሪክ እንደሚያስረዳው፣ ከሰባቱ የአገውአዊ መስራች ወንድማማቾች 3 አንዱ የሆነው ዳንግሊ ይኖር የነበረው በዚች ከተማ ከመሆኑጋር ተያይዞ የሚነገረው ነው፡፡
ይህ አፈታሪክ የከተማዋን አሰያየም ሲያስረዳ የ“ዳንግሊ” ወንድሞች ወደዚች ከተማ በመምጣት “ዳንግሊ አለ” ብለው ሲጠይቁ “ዳንግሊ ላ” (ዳንግሊየለም) የሚል ምላሽ ያገኛሉ፡፡ ከዚህም ምላሽ ተነስተው “ዳንግሊ ዕላ” (ዳንግሊ የለም) የሚለው በሒደት ወደ “ # ዳንግላ ” እንደተቀየረ የአካባቢው የእድሜ ባለፀጋዎች ይናገራሉ።
በመሆኑም የዳንግላ ከተማ ስያሜዋን ያገኘችው ከሰባቱ የአገው መስራች ወንድማማቾች አንዱ በሆነው “ዳንግሊ” ስያሜ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
የዳንግላ ከተማ አመሰራረትን በተመለከተ በ2001 ዓ.ም የታተመው “ገጽታ” መጽሔት በመረጃ ላይ ያልተመሰረቱ አፈታሪኮች እንደሚያስረዱት የዳንግላ አመሰራረት ከንግድ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ መሆኑን ይገልጻል፡፡
በዚህ ገለጻ መሰረትም ዳንግላ በሚባል ገበያ ዚጉዳ ኪዳነ ምህረት አካባቢ በአዳምሰገድ እያሱ (በአፄ እያሱ ዘመነ መንግስት) 1676-1696 ዓ.ም በወቅቱ የዳንግላና አቸፈር ገዥ በነበሩት በኪዳኑ ዲቁ እንደተቋቋመ ይነገራል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ለአገው ምድር እና የአቸፈር ነጋዴዎች መቀመጫ ከመሆኗም በተጨማሪ ለረጅም ጊዜ የቀረጥ ማስከፈያ ኬላ እንደነበረች ይነገራል፡፡
“ገጽታ” መጽሔት የታዋቂው ስኮትላንዳዊ አሳሽ ጀምስ ብሩስን (1761-1763) የጉዞ ማስታወሻ መሰረት አድርጎ እንዳቀረበው፣ “ወደ ዳንግላ ገበያ ልዩ የሆነ በግ ይመጣል ስሙንም ሙክት ይሉታል፡፡”
በሚል ያሰፈረውን በማጣቀስ የአሁኗ ዳንግላ ከተማ ከተቆረቆረች ቢያንስ ከ240 አመት በላይ ማስቆጠሯን ይገልጻል፡፡ አንዷ በመሆን የአገውምድር የባህርዳር እና የመተከል ዋና ርዕሰ ከተማ ሁና እንድታገለግል አድርጓታል፡፡
በ1948 ዓ/ም መተከል እንዲሁም በ1949 ዓ/ም ባህር ዳር እራሳቸውን ችለው አውራጃ ከሆኑ በኋላ ሦስት ወረዳዎችን (አንከሻ ፣ባንጃ እና ዳንግላ) በመያዝ እስከ 1983 ዓ/ም የአገው ምድር አውራጃ ዋና ከተማ በመሆን ቆይተታለች።