ፍራንክ ኦ ኮናር

ከውክፔዲያ

ኤዲፐሳዊ ቅናቴ[1]

ብሩክ በየነ እንደተረጎመው

ፈላስፋው ፍሩድ ካብራራው በጣም የበለጠ አይርላንዳዊው ፋራንክ ኦ’ኮናር ቁልጭ አድርጎ ነገሩን ይገልጸዋል ...

አባቴ የጦርነቱን ዘመን በሙሉ ያሳለፈው ወታደር ሆኖ ነበር – ማለቴ በአንደኛው የዓለም ጦርነት በቤታችን ውስጥ አልነበረም – በመሆኑም ዕድሜዬ አምስት እስከሚሆን ድረስ ያን ያክል አባቴን ያን ያክል በደንብ አሳምሬ አላውቀውም ነበረ። በዚህም ምክንያት በዚያ የጦርነቱ ጊዜ ባጋጣሚ አግኝቼ ሳየው ምንም እኔን ሊያስጨንቀኝ የሚችል ባሕሪ አልነበረበትም። አንዳንድ ጊዜ ከእንቅልፌ ስነቃ፣ በቃ እሱ ማለት የሆነ በሻማ ብርሃን ቁልቁል አፍጦ የሚመለከተኝ፣ ካኪ የለበሰ ግዙፍ ሰው እንደሆነ ብቻ አድርጌ እቈጥረዋለሁ። አልፎ አልፎ ጠዋት በማለዳ የቤታችን የፊት በር በኃይል ተወርውሮ ጓ ብሎ ሲዘጋ እና በግቢያችን የእግረኛ መረማመጃ የተጠረበ ድንጋይ ላይ የቆዳ ቦቲ ጫማዎቹ ሶል ላይ የተለበዱት ብረቶች እየተንቋቁ ሲሄዱ ይሰማኛል። እነዚህ ድምፆች የአባቴን መምጣት እና መሄድ የሚጠቁሙኝ የድምፅ ምልክቶቼ ናቸው። ልክ እንደ አባት ድንገት ሳይታሰብ በምሥጢር ይመጣል፣ እንደገና ተመልሶ በድንገትና በምሥጢር ይሄዳል።

በርግጥ ምንም እንኳ በጠዋት ከእንቅልፌ ተነስቼ ትልቁ አልጋ ውስጥ ከመሃላቸው ስገባ ለእናቴ እና ለእሱ ምቾት የሚነሳ የመጣበብ ዓይነት ስሜት የሚፈጥርባቸው ቢሆንም የእሱ ወደ ቤታችን መምጣት እንዲያውም ደስ ይለኝ ነበር ማለት እችላለሁ። ሲጋራ ስለሚያጨስ እና ጺሙን ሲላጭ ሽቶ ነገሮችን ስለሚቀባባ የሲጋራው ሽታ እና ሽቶው አንድ ላይ ተደማምሮ የሆነ ደስ የሚል የሚጠነባ የሰውነት ጠረንን አጎናጽፎታል። ይህ ሁሉ ግን “እኔም ባደረግኩት” የሚያሰኝ የሆነ ለዓዋቂ ሰዎች ብቻ የተፈቀደ ድርጊት ነው። እንደ ሞዴል ታንኮች፣ እጀታቸው ከጥይት ቀለሃ የተሠሩ ጉርካ የሚባሉ ቢላዋዎች፣ የጀርመን ጦር ጥሩሮች (ሄልሜቶች) እና የወታደራዊ ቆብ የመለዮ ባጆችን እንዲሁም አጫጭር የጦር ሠራዊት ብትረ አዛዦችን ብሎም ሁሉንም ዓይነት ሌሎች የሚሊታሪ ቁሳቁሶችን የመሳሰሉ ነገሮችን እንደ ቅርስ በቤታችን ውስጥ እንዲቀመጡለት ትቶዋቸው ይሄዳል። ከቁም ሳጥኑ አናት ላይ በሚቀመጠው ረዥም ቀጭን ሳንዱቅ ውስጥ ልክ ለሆነ ነገር ድንገት ቢፈልጋቸው ወዲያው ሊያገኛቸው በሚችልበት አኳኻን በመልክ መልካቸው ለይቶ በጥንቃቄ አንድ ላይ ሸክፎ ያስቀምጣቸዋል። አባቴ ትንሽ የአራዳ ሌባ ዓይነት ባሕሪም ነበረበት፤ እንደርሱ አስተሳሰብ ሁሉም ነገር በሚፈለግበት ጊዜና በሚፈለገው ፍጥነት ወዲያው መገኘት መቻል አለበት። የሆነ ሌላ ነገር ለማድረግ ፊቱን ከእኛ ዞር ሲያደርግ፣ እናቴ ወንበር ላይ እኔ እንድወጣ እና እነዚህን ውድ ዕቃዎቹን ትንሽ እንዳተራምስለት ትፈቅድልኛለች። እሱ እንደሚያስበው እናቴ ያን ያክል ከእሱ ኮተቶች ዋጋ የምትሰጣቸው አይመስለኝም።

የጦርነቱ አብዛኛው ጊዜ ማለት ይቻላል፣ ሕይወቴ በጣም ሰላም የተሞላችበት የሚባል ዘመን ነበር። ከቤታችን ጣራ ላይ የተሠራችው የመኝታ ቤቴ መስኮት ፊቱን ወደ ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ ያደረገ ነው። እናቴ መስኮቱን በመጋረጃ ጋርዳዋለች፤ ቢሆንም መጋረጃው ውጭውን ዓለም እንዳላጣጥም በኔ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ጠዋት ጠዋት ከፀሐይ ብርሃን የመጀመሪያው ጨረር ጋር አብሬ ከእንቅልፌ እነቃለሁ፤ ባለፈው ቀን በኔ ላይ ተጥሎብኝ የነበረ ግዴታና ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ እንደ በረዶ ቀልጦ ወደ ኋላዬ ይቀራል። የንጋቷ ፀሐይን ስመለከት እኔው ራሴ ልክ እንደ ፀሐይዋ የሆንኩ ሆኖ ይሰማኛል፤ አለ አይደል በቃ ብርሃኔን ለመፈንጠቅ እና ለመደሰት ዝግጁ የሆንኩ ልዩ ዓይነት ፍጡር። ሕይወት እንደዚያ ዘመን ቀላልና ግልፅልፅ ያለች ብሎም በመልካም ነገሮች የተሞላች መስላ በጭራሽ ታይታኝ አታወቅም። እግሮቼን ከአንሶላዎቹ ቀስ ብዬ ሹልክ አድርጌ አወጣቸውና ወለሉን እረግጠዋለሁ – ለእግሮቼ “ወይዘሮ ግራ እግር” እና “ወይዘሮ ቀኝ እግር” በማለት ስም አውጥቼላቸዋለሁ። በእግሮቼ ወለሉን ከረገጥኩት በኋላ በዚያ ዕለት ከፊት ለፊታችን የተጋረጡትን ችግሮች እንዴት በቅድሚያ መፍትሔ እንደሚሰጡባቸው የሚወያዩባቸውን የውይይት መድረክ ለእግሮቼ እፈጥርላቸዋለሁ። ቢያንስ ወይዘሮ ቀኝ እግር ስሜቷን በአካላዊ እንቅስቃሴ ለማንፀባረቅ አትሰንፍም ነበር፤ ምክንያቱም የወይዘሮ ግራ እግርን ያክል ቅልጥፍና እና አንደበተ ርቱዕነት አልነበራትም። ስለዚህ ወይዘሮ ግራ እግር በውይይቶቹ ላይ በሚቀርበው ሐሳብ ላይ መስማማትዋን ጭንቅላቷን በመነቅነቅ ብቻ በውይይቱ ላይ በምታደርገው ተሳትፎ ደስተኛ ነበረች።

በዕለቱ እናቴ እና እኔ ምን ማድረግ እንዳለብን፣ ለእኔ ለልጅየው “አባባ እማማ” ምን ዓይነት የገና ስጦታ መስጠት እንዳለባቸው እና ቤቱን ለማድመቅ እንዲሁም በቤቱ ላይ ነፍስ ለመዝራት ምን ዓይነት እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው እግሮቼ ይነጋገራሉ። ለአብነት ከሚወያዩባቸው ችግሮች አንዱ ትንሽ ችግር ይኼ የማሙሽ ነገር ነው። እናቴ እና እኔ በዚህ ነጥብ ላይ በጭራሽ ልንግባባ አልቻልንም። በሰፈራችን ውስጥ የፎቁ በረንዳ ላይ ጠዋት ጠዋት ሕፃን ፀሐይ የማይሞቅበት ብቸኛ ቤት የእኛው የራሳችን ቤት ነው፤ እና እናቴ ማሙሾች እንዳይገዙ ዋጋቸው አሥራ ሰባት ፓውንድ ከስልሳ እንደሆነና አባባ ከጦርነቱ እስከሚመጣ ልጅ ለመግዛት አቅማችን እንደማይፈቅድልን አስረግጣ ደጋግማ ትነግረኛለች።

ይኼ አነጋገርዋ ምን ያክል ተራ ሴት እንደሆነች በተጨባጭ ያሳያል። ከኛ ቤት ማዶ ያሉ የጌኔይ ቤተሰቦች ማሙሽ ወደ ቤታቸው ገዝተው አምጥተዋል፤ እና ማንም በሰፈራችን ያለ ሰው ሁሉ እነርሱ አሥራ ሰባት ፓውንድ ከስልሳ ከየትም ሊያመጡ እንደማይችሉ አሳምሮ ያውቃል። ምናልባት የገዙት በጣም ርካሹን ማሙሽ ሊሆን ይችላል። እናቴ ምናልባት በጥሩ ዋጋ፣ ጥሩ የሆነ ማሙሽ መግዛት ነው የምትፈልገው፤ ቢሆንም በጣም ያበዛችው ሆኖ ይሰማኛል። እነ ጌኔይ ያመጡት ልጅ ለኛ ቢመጣ ምንም አይለንም፤ አሳምሮ ይበቃናል።

የቀኑን ዕቅዴን በሚገባ ከነደፍኩ በኋላ ከአልጋዬ እነሣና ከትንሿ መኝታ ቤት መስኮት ሥር የራሴን ወንበር አስቀምጣለሁ፤ ጭንቅላቴን ወደ ውጭ ለማውጣት የሚበቃኝን ያክል መስኮቱን ወደ ላይ እከፍተዋለሁ። መስኮቱ ከእኛ ቤት ጀርባ ያሉትን ቤቶች በረንዳ ከላይ ሆኖ ለመቃኘት ያስችላል፤ ከነዚህ ቤቶች ባሻገር ደግሞ ጭው ያለውን ገደል አልፎ ከወዲያ ማዶ ካለው ትንሽ ተራራ ላይ የተገነቡትን ረዣዥም፣ ባለ ቀይ ጡብ ቤቶች አንድ ላይ እጅብ ብለው አንድ ባንድ መንጥሮ ለማየት ያስችላል፤ በዚህ ጠዋት እንደ ወትሮው ሁሉ አሁንም ድረስ የፀሐይዋ ብርሃን አላገኛቸውም፣ ከእነርሱ ይልቅ ከገደሉ ወዲህ በእኛ ቤት በኩል ያሉት ቤቶች ግን በማለዳዋ ፀሐይ ፈክተዋል። ቢሆንም የሆነ እንግዳ ጥላ በላያቸው ላይ በቀጭኑ አጥልቶባቸው ደስ የማይሉ፣ ነፍስ የሌለባቸው የማይንቀሳቀሱ እና ከልክ በላይ በቀለም ያሸበረቁ የቤቶች ተራ መንጋ አድርጓቸዋል።

ከዚህ በኋላ ወደ እናቴ መኝታ ቤት እሄድና ትልቁ አልጋ ላይ እወጣለሁ። ከእንቅልፏ ትነቃለች። እኔም የዕለቱን ዕቅዶቼን አንድ በአንድ ለእሷ መንገር እጀምራለሁ። ሆኖም ምንም እንኳ ልብ ብዬ አስተውዬው የማውቅ ባይመስለኝም፣ ይህን ጊዜ የሆነ ፍርሃት ይወረኝ እና ቢጃማዬ በላብ ይጠመቃል። እንዲህም ሆኖ ግን የመጨረሻዋ ጤዛ እስክትቀልጥ ድረስ በፍርሃት ተውጬ ማውራቴን እንደቀጠልኩ፣ ሳላስበው ከእሷ አጠገብ ጋደም እንዳልኩ እንቅልፍ ጭልጥ አድርጎ መልሶ ይወስደኛል፤ ከዚያም እሷ ከምድር ቤት ቁርስ ልትሠራ ከታች ሸብ ረብ ስትል ደግሞ መልሼ ከእንቅልፌ እነቃለሁ።

ከቁርስ በኋላ ወደ ከተማ አብረን ከእናቴ ጋር እንወጣለን። በቅድስት አውጉስጢን ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ እንሰማለን፤ ለአባባ ጸሎት እናደርግለታለን እና በመቀጠል አንዳንድ የሚሸማመቱ ነገሮች ከገበያው እንገዛለን። ከቀትር በኋላ ያለው አየር ፀባይ ጥሩ ከሆነ ከመንደራችን ወጣ ብሎ ወደ የሚገኝው ገጠር በእግራችን ለመሸራሸር እንሄዳለን፤ ወይም በእመቤታችን ቅድስት ዶመኒክ ገዳም የሚኖሩትን የእማማን ምርጥ ወዳጅ ሄደን እንጠይቃቸዋለን። በገዳሙ ያሉትን ሁሉ ለአባባ እንዲጸልዩለት እማማ ታስደርጋቸዋለች፤ እና እኔም በየቀኑ ማታ ማታ ከመተኛቴ በፊት አባባን እግዚአብሔር በሰላም ወደ እኛ ከጦርነቱ እንዲመልስልን እለምነዋለሁ። በርግጥ ምን ብዬ እየጸለይኩ እንደሆነ በደንብ አልተገለጸልኝም ያኔ!

አንድ ቀን ጠዋት፣ በትልቅየው አልጋ ላይ ከእንቅልፌ ስነቃ አባቴ በተለመደ “የአባባ ገና” አስተኔው በርግጠኝነት በቦታው ተገትሮ ነበረ፤ ሆኖም ግን፣ ዛሬ የለበሰው በወታደራዊ መለዮ ምትክ ዝንጥ ያለውን ምርጡን ሰማያዊ ሙሉ ሱፍ ልብሱን ነበር። እማማ እንደዛን ቀን ተደስታ ዐይቼያት አላውቅም። በበኩሌ እንደዚያ የሚያስደስት ምንም ነገር አልታየኝም፤ ምክንያቱም አባቴ መለዮውን ሲያወልቅ ያን ያክል ደስ የሚል ዓይነት ሰው አይደለም። የሆነው ሆኖ ብቻ፣ እሷ በደስታ ብዛት ፈክታለች፤ ጸሎታችን መልስ እንዳገኘ ለእኔ ለማስረዳትም ሞከረች። በመቀጠል አባባን በሰላም ወደ ቤቱ ስለ መለሰው ለእግዚአብሔር ምስጋና ለማቅረብና ቅዳሴ ለመስማት ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ አለብን ተብሎ ሦስታችንም አብረን ሄድን።

ይህ ሁሉ ጸሎት ግን ከንቱ ነገር ነበር! ገና ከመምጣቱ በመጀመሪያው ቀን ምሳ ሰዓት ላይ ምሳውን ለመብላት ወደ ቤት ሲገባ የቆዳ ቡትስ ጫማውን አወለቀና ነጠላ ጫማውን ካደረገ በኋላ ከብርዱ እንዲያስጥለው በቤት ውስጥ የሚያደርገውን ቆሻሻ አሮጌ ቆብ ጭንቅላቱ ላይ አጠለቀ። እግሮቹን አጣምሮ ከተቀመጠ በኋላ እናቴን ክፉ ቃላት እየተጠቀመ ያናግራት ጀመረ። እናቴም የተጨነቀች መሰለችኝ። በደመ ነፍስ እናቴ እንዲህ ስትጨነቅ ሳያት በጭራሽ ደስ አይለኝም፣ ምክንያቱም ጭንቀት ደም ግባቷን ገፎ ያጠፋዋል፤ ስለዚህ ንግግሩን ጣልቃ ገብቼ አቋረጥኩበት።

"ላሪ አንድ ጊዜ ቆይ!" አለች ረጋ ብላ። እንዲህ ብላ የምታናገረኝ ደባሪ ሰዎች ቤታችን ሲመጡ ብቻ ስለሆነ ለንግግሯ ብዙም ቁብ ሳልሰጠው መናገሬን ቀጠልኩ።

"ላሪ ዝም በል እኮ አልኩህ!" ስትል ትዕግስቷን የጨረሰች መሰለች። "ከዳዲ ጋር እየተነጋገርኩ አይደለም እንዴ ያለሁት?"

እነዚህን “ከዳዲ ጋር እየተነጋገርኩ አይደለም እንዴ?” የሚሉ አስጨናቂና ግራ አጋቢ ቃላት ስሰማ ይኼ የመጀመሪያ ጊዜዬ ነበር፤ በመሆኑም እግዚአብሔር ሰዎች ለሚያቀርቡለት ጸሎቶች ምላሽ የሚሰጠው በዚህ መልኩ ከሆነ ጸሎቶቹ ምን እንደሚሉ ጆሮ ሰጥቶ ልብ ብሎ አይሰማቸውም ማለት ነው ብዬ እንዳላስብ የሚያደርግ ምንም አጥጋቢ ምክንያት ማግኘት አልቻልኩም።

"ለምን ዳዲን ታናግሪዋለሽ?" አልኩ በተቻለኝ መጠን ደንታ እንዳልሰጠኝ ለማስመሰል ያለኝን አቅም ሁሉ አሰባስቤ።

"ምክንያቱም ዳዲ እና እኔ የምንነጋገረው ቁም ነገር ጉዳይ አለን። በቃ፣ ከአሁን በኋላ ወሬያችንን እንዳታቋርጠን!"

ከቀትር በኋላ በእናቴ ጥያቄ አባቴ በእግር ሊያሸራሽረኝ ወደ ውጭ ወሰደኝ። እንደሌላው ጊዜ ከእናቴ ጋር እንደምንሄደው ወደ ገጠር ሳይሆን የሄድነው ወደ ከተማው እምብርት ነበር። በመጀመሪያ እንደ ወትሮው ቀና ቀናውን የማሰብ ልማዴ መሠረት ከዚህ በፊት የነበረው በእኔ እና በእሱ መካከል ያለው ደስ የማይል ሁኔታ እየተሻሻለ ነው ብዬ አስቤ ነበረ። ሆኖም ግን አብረን ያሳለፍነው ጊዜ ምንም የዚህ ዓይነቱ ምልክት በላዩ ላይ አልነበረበትም። አባቴ እና እኔ በከተማው ውስጥ በእግራችን ስንዟዟር ሁለታችንም ስለ ሽርሽሩ ትርጉም የየራሳችን የተለያየ ግንዛቤ ነበረን። አባባ እንደ የከተማ ባቡር፣ ጀልባዎች እና የፈረስ ጋሪዎች በመሳሰሉ ነገሮች ላይ ምንም ዓይነት የጨዋ ሰው አመለካከት ወይም እነዚህን ነገሮች የማድነቅ ስሜት በላዩ ላይ አልነበረበትም። ቀልቡን የሚስበው ነገር ቢኖር ዕድሜያቸው እንደሱ ከሆኑ ቢጤዎቹ ጋር ማውራት ብቻ ነው። እኔ ቆም ማለት ስፈልግ፣ የእኔን ስሜት ከምንም ሳይቆጥር እኔን በእጄ በግድ ከኋላ ከኋላው እየጎተተ ወደፊት መራመዱን ይቀጥላል፤ እሱ ቆም ማለት ሲፈልግ ግን እኔ ሌላ ምንም አማራጭ አልነበረኝም፣ ያው በግድ ሲቆም እቆማለሁ። ግድግዳ በተደገፈ ቊጥር ለረዥም ጊዜ ሊቆም እንደፈለገ ምልክት ሊሆን እንደሚችል አስተውያለሁ። ለሁለተኛ ጊዜ ሲደግመው ስመለከተው ራሴን መቆጣጠር እስኪያቅተኝ ድረስ አናደደኝ። ልክ ለዘላለም እዛው ግድግዳውን ተደግፎ ተገትሮ የሚቀር ይመስላል። በኮቱ እና በሱሪው ይዤ ጎተትኩት፣ ግን እንደ እናቴ በቀላሉ እጅ የሚሰጥ ዓይነት ሰው አልነበረም። “እንሂድ” ብለህ ከጨቀጨቅከውና አልቀህም ካልከው ጭራሽ “ላሪ፣ አደብ የማትይዝ ከሆነ በጥፊ አጮልሃለሁ” ይልሃል። አባቴ ፍቅር የተሞላ ቀልብ የመንሳት ድርጊትን የሚያስተናግድበት የራሱ የሆነ የተለየ ተሰጥዖ ነበረው። ከሱ በልጬ ተገኘሁ ብዬ በለቅሶ ላጨናንቀው ሞከርኩ። ግን እሱ እቴ! ደንቆት ነው! የፈለገውን እሪ ብልም ጭራሽ ደንታ አልሰጠውም። እውነት ለመናገር ከሆነ ተራራ ነገር ጋር በእግር ሽርሽር የመሄድ ያክል ነበር። አይሞቀው፣ አይበርደው! ልብሱን መጎተቴን እና ውትወታዬን ከመጤፍ አይቆጥረውም ወይም ከላይ ወደ ታች የግርምት ፈገግታ እያሳየ በመገልፈጥ ይመለከተኛል። እንደ እርሱ የመሰለ በራሱ ስሜት ብቻ የሚመራ ሰው በሕይወቴ አጋጥሞኝ አያውቅም።

ከሰዓት በሻይ ሰዓት ጊዜ “ከዳዲ ጋር እየተነጋገርኩ አይደለም እንዴ?” የምትለው አነጋገር እንደገና ተጀመረች። እሱ ማታ ማታ ታትሞ የሚወጣውን ጋዜጣ እያነበበ ነበረ። በየጥቂት ደቂቃ ልዩነት ጋዜጣውን ቁጭ ያደርገውና ስላነበበው የሆነ አዲስ ነገር ለእማማ ይነግራታል። በዚህ የተነሳ ያቺ አነጋገር ከቅድሙ እንዲያውም ይበልጥ እየከረረች ሄደች። ይሄ ሙሉ በሙሉ ፋውል የተሞላ ጨዋታ እንደሆነ ሆኖ ተሰማኝ። ልክ ወንድ ከወንድ ጋር እንደሚፋለመው፣ የእማማን ቀልብ ለማግኘት በሞከረ ቁጥር ከእርሱ ጋር ለመፎካከር ተዘጋጀሁ። ዕድሉ ሲሰጠው የእሱ ወሬ ሌሎችን ሰዎች በወሬው ውስጥ ገብተው ስለሚያደርገው የእሷን ጆሮ ከእኔ ይልቅ ይበልጥ ለመያዝ ተመቻችቶለታል። ለእኔ ምንም የሚተርፈኝ የእናቴ ጆሮ አልነበረም። የሚያወሩትን ነገር ርእሰ ጉዳይ ለመቀየር ደጋግሜ ብሞክርም ምንም ሊሳካልኝ አልቻለም።

"ላሪ፣ ዳዲ ሲያነብ ዝም ማለት አለብህ!” ትዕግስቷ አልቆ እማማ ጮኸችብኝ።

እኔን ከማናገር ይልቅ ከአባባ ጋር ማውራት እንዲሁ በቀናነት ይበልጥ ደስ ይላታል ወይም እውነቱን አውጥታ እንዳትናገር የሚያስፈራት የሆነ እሷን ጨቆኖ የያዘበት ምሥጢር እንዳለው ግልጽ ነው።

"ማሚ፣" አልኳት ልክ እኔን አፌን ለማስዘጋት ስትጮኽብኝ፣ “በደንብ ጠንክሬ ብጸልይ እግዚአብሔር ዳዲን እዛው ወደ የነበረበት ወደ ጦር ሜዳው ሊመልሰው የሚችል ይመስልሻል?" ስል ጠየቅኳት።

በዚህ ነጥብ ላይ ትንሽ ስታስብበት የቆየች መሰለች።

"አይመስለኝም፣ ውዴ" ፈገግ ብላ መልስ ሰጠችኝ። "የሚመለስ አይመስለኝም።"

"ለምን አይመለስም፣ ማሚ?"

"ምክንያቱም ከእንግዲህ ምንም ዓይነት ጦርነት የለማ፣ ውዴ።"

"ግን ማሚ እግዚአብሔር ከፈለገ ሌላ ጦርነት ማስነሳት አይችልም?"

"እግዜር ጦርነት አይፈልግም ውዴ። ጦርነት የሚያስነሱት መጥፎ ሰዎች እንጂ እግዚአብሔር አይደለም።”

"ኤጭ!" አልኩ። በዚህ በጣም ነው የተከፋሁት። ለካስ እግዚአብሔር እንደሚባለው ዓይነት ሁሉን ነገር ማድረግ አይችልም ኖሯል ብዬ ለራሴ ማሰብ ጀመርኩ።

በማግስቱ ጠዋት ላይ በተለመደው ሰዓቴ ከእንቅልፌ ስነቃ ልክ የሻምፓኝ ጠርሙስ የሆንኩ ይመስል ልፈነዳ በነገር ተወጥሬ ነበረ። እግሬን ወለሉ ላይ አደረግኩና ረዥም ውይይት በእግሮቼ መካከል ፈጠርኩ። በውይይቱ ላይ ወይዘሮ ቀኝ እግር አባትዋን ወደ መኖሪያ ቤቷ ከማስገባቷ በፊት ከአባቷ ጋር ስለነበረባት ችግር አወራች። መኖሪያ ቤት ማለት በትክክል ምን እንደሆነ እስከዚያ ጊዜ ድረስ በደንብ አይገባኝም ነበረ። ሆኖም ትርጉሙ ለአባት ምቹ የሆነ ቦታ እንደ ማለት ይመስላል። ከዚያ ወንበሬን በቦታው አስቀመጥኩ እና በትንሿ መኝታ ቤት መስኮት በኩል አንገቴን አስግጌ አወጣሁ። ገና እየነጋ ነበር፣ እያደረግኩ ባለሁት ያልተፈቀደ ድርጊት እጅ ከፍንጅ የተያዝኩ ያክል የሚመስል የጸጸት ስሜትን ያዘለ አየር በሰፈራችን ይነፍስ ነበር። ጭንቅላቴ በተለያዩ ታሪኮች እና ዕቅዶች ተወጥሮ ሊፈነዳ እንደደረሰ በቤቱ ውስጥ ወዳለው ሌላኛው በር እየተንገዳገድኩ ደረስኩ። እናም ግማሽ በግማሽ ጨለማ በተሞላው ክፍል ውስጥ እንደምንም ተፍጨርጭሬ ትልቁ አልጋ ውስጥ ገባሁ። በእማማ በኩል ምንም ክፍት ቦታ አልነበረም ስለዚህ በእሷ እና በአባባ መካከል ባለው ቦታ ላይ መግባት ነበረብኝ። ለጊዜው ስለ እሱ ማሰቤን እርግፍ አድርጌ ተውኩት። እና ለበርካታ ደቂቃዎች እግሬን እንዳጠፍኩ ቀጥ ብዬ በመሃላቸው ቁጭ አልኩና ከእሱ ጋር ምን ማድረግ እንዳለብኝ በማሰብ አንጎሌን ውስጥ ለውስጥ እየነቀነቅኩ በሐሳብ አወዛወዝኩት። አልጋውን ለእሱ ከሚገባው በላይ ቦታ ይዞ ተንደላቆ በማን አለብኝነት ተቆጣጥሮታል። ስለዚህ ምንም ሊመቸኝ አልቻለም። ደጋግሜ በእግሬ ጎሸም ጎሸም ሳደርገው እያጉረመረመ ሰውነቱን ዘረጋጋው። አሁን እንደ ምንም የተወሰነ ቦታ ለቆልኛል፣ ጥሩ ነው። እማማ ነቃችና እቅፍ አደረገችኝ። ጣቴን አፌ ውስጥ ከትቼ በአልጋው ሙቀት ተደላድዬ ዘና ብዬ ጋደም አልኩ።

"ማሚ!" አልኩ ጮኽ ብዬ በደስታ።

"እሽሽሽ! ውዴ፣" አንሾካሾከችልኝ። "ዳዲን እንዳትቀሰቅሰው!"

ይህ ““ከዳዲ ጋር እየተነጋገርኩ አይደለም እንዴ?” ከሚለው አነጋገር ይልቅ እጅግ የከፋ አስፈሪ የሆነ አዲስ ነገር ነበር። ጠዋት በማለዳ ከእናቴ ጋር ከማደርገው ውይይት ውጭ ሕይወትን መኖር በጭራሽ ሊታሰብ አይችልም።

"ለምን?" ምርር ብሎኝ ጠየቅኩዋት።

"ምክንያቱም ምስኪኑ ዳዲ ደክሞታል።" ይህ ሙሉ በሙሉ ለእኔ አጥጋቢ ምክንያት ሆኖ ሊገኝ አልቻለም። እንዲያውም ይኼ የእሷ “ምስኪኑ ዳዲ” የሚለው አነጋገሯ ጭራሽ ሊያስታውከኝ ወደ ላይ አለኝ። እንዲህ ያለው እንዲያው ድንገት ደርሶ ልፍስፍስ ማለት በጭራሽ እኔ አልወደውም፤ ሁልጊዜም የሆነ ሽንገላ ነገር፣ የማስመስል ዓይነትና እምነትን የማጉደል ድርጊት ሆኖ ይታየኝ ነበር።

"ኤጭ!" አልኩ ቀስ ብዬ። በመቀጠል አንጀትዋን ሊበላ በሚችል ምርጥ የመጨረሻ ቅላጼዬ ተጠቅሜ፦ "ዛሬ ከአንቺ ጋር የት መሄድ እንደምፈልግ ታውቂያለሽ ማሚ?"

"አላውቅም፣ ውዴ" ተንፈስ አለች።

"ወደ “ግሌን” ወንዝ እንድንሄድ እና በአዲሱ የዓሣ ማስገሪያ መረቤ ዓሣዎችን ማጥመድ እፈልጋለሁ። ከዚያ ወደ ፎክስ እና ሃውንድስ መጫወቻ ቦታ መሄድ እፈልጋለሁ፣ ከዚያ –"

እጇን አፌ ላይ እየደፈነች "ዳዲን እንዳትቀሰቅሰው!" በማለት በስጨት ብላ በለሆሳስ ተናገረች።

ግን ዘግይታለች። ነቅቶ ነበር ወይም ሊነቃ ተቃርቦ ነበር። አጉረመረመ እና ክብሪቱን በእጆቹ መፈለግ ጀመረ። ከዚያም ዓይኑን ማመን ያቀተው ይመስል የእጅ ሰዓቱ ላይ አፈጠጠ።

ከዚህ በፊት ስትጠቀምበት ሰምቼያት በማላውቀው ፍጹም ትህትናና ጨዋነት በተሞላ ለስላሳ ድምፅ "ሻይ ትፈልጋለህ፣ የኔ ጌታ?" ስትል ጠየቀችው እናቴ። እንዲያውም ልክ በጣም የፈራች ዓይነት ነው የሚመስለው።

"ምን? ሻይ ነው ያልሽው" በቁጣ ጮኸ። "ስንት ሰዓት እንደሆነ ታውቂያለሽ?"

"እና ከዚያ በኋላ ደግሞ በራዝኩኒ ጎዳና ላይ ሽቅብ በእግሬ መሄድ እፈልጋለሁ" ጮኽ ብዬ ተናገርኩ፣ እንዲህ ባሉት ሁኔታዎች ሐሳቤ እየተበታተነ የሆነ ነገር እንዳልረሳ ጭንቅ ይዞኛል።

"ላሪ አርፈህ ተኛ፣ በቃ!" አንባረቀች።

እየተነፋነፍኩ ማልቀስ ጀመርኩ። ቀልቤን ሰብስቤ ምንም ነገር ማሰብ አልቻልኩም። እነዚህ ጥንዶች እያደረጉ ያሉት ነገር አስቸጋሪ ነው፤ የእኔን የማለዳ ጠዋት ዕቅዶች እንዲህ ፋይዳ ቢስ ማድረጋቸው አንድን ጨቅላ ሕፃን ከነጨቅላ መኝታ አልጋው ከነነብሱ የመቅበር ያህል አስነዋሪ ድርጊት ነው። አባቴ ምንም ነገር አላለም፣ ግን በአጠገቡ እማማ ሆነ እኔ መኖራችንን የረሳ ያህል በቤቱ ውስጥ ያሉትን ጥላዎች ትኩር ብሎ እያየ ፒፓውን ለኮሰ። በጣም እንደተናደደ ገብቶኛል። የሆነች ነገር ትንፍሽ ስል እማማ በስጨት ብላ አፌን ታስይዘኛለች። ይኼ በጭራሽ ፍትሐዊነት የጎደለው አካሄድ ነው ብዬ ተሰማኝ፤ እንዲያውም በዚህ ጉዳይ ላይ የሆነ የተደባበቀ ተንኮል ነገር እንዳለ አሰብኩ። በፊት በፊት አንድ አልጋ ላይ ሁለታችን መተኛት እየቻልን በተለያየ ሁለት አልጋ ላይ እኔና እሷ መተኛታችን ዝምብሎ ኪሳራ እንደሆነ ጠቆም ባደረግኩላት ቊጥር ለጤናችን የተሻለው እንደዚያ ተለያይቶ መተኛቱ እንደሆነ ትነግረኝ ነበር። እና አሁን ደግሞ ይኼ እንግዳ ሰውዬ ቤታችን መጥቶ ስለ የእሷ ጤና ቅንጣት ያክል እንኳ ሳያስብ ይኸው አብሯት እየተኛ ነው! ቀደም ብሎ ከአልጋ ተነሣ እና ራሱ ሻይ አፈላ፤ ምንም እንኳ ለእማማ ሻይ ቢያመጣላትም እኔ ግን ጭራሽ ትዝም አላልኩትም።

"ማሚ፣" ጩኸቴን ለቀቅኩት፣ "እኔም ሻይ እፈልጋለሁ።"

"እሺ የኔ ውድ፣" አለች በትዕግስት። "ከእናትህ ስኒ ላይ መጠጣት ትችላለህ።"

ለችግሩ መፍትሔ ሰጥታ ሞታለች! አባቴ ወይም እኔ ቤቱን ለቀን መውጣት አለብን። ከእናቴ የሻይ ስኒ በጭራሽ መጠጣት አልፈልግም፤ በገዛ ቤቴ እንደ ማንኛውም ሰው እኩል እንድታይ እፈልጋለሁ፣ ስለዚህ ዋጋዋን ለመስጠት ያክል በስኒው ውስጥ የነበረውን ሻይ በሙሉ ሙልጭ አድርጌ ጠጣሁትና ለእሷ ምንም ሳልተውላት መልሼ ሰጠኋት። ይኼንንም በፀጥታ ምንም ሳትል አለፈችው። ግን የዚያን ቀን ማታ አልጋዬ ላይ ስታስተኛኝ ቀስ ብላ እንዲህ አለችኝ፦

"ላሪ፣ የሆነ ነገር ቃል እንድትገባልኝ እፈልጋለሁ።"

"ምንድን ነው ቃል የምገባልሽ?"

"ጠዋት ላይ ሁለተኛ ወደ መኝታ ቤት እንዳትመጣ። ምስኪኑን ዳዲን ከእንቅልፉ እንዳትረብሸው እሺ? ቃል ትገባልኛለህ?"

እንዲህ ነችና አሁንም እንደገና "ምስኪኑ ዳዲ"! ያ በምንም ታግዬ ላሸንፈው ያልቻልኩት ሰውዬ በሚያደረገው ነገር ሁሉ በጣም መጠራጠር ጀመርኩ።

"እንዴ ለምን?"

"ምክንያቱም ምስኪኑ አባባ ጭንቀት ላይ ነው። በዚህ ላይ ደክሞታል። ስለዚህ በደንብ እንቅልፍ አይተኛም።"

"ለምንድን ነው የማይተኛው፣ ማሚ?"

"አየህ ምን መሰለህ፣ ትዝ ይልህ እንደሆነ እሱ ጦር ሜዳ እያለ ማሚ ከፖስታ ቤቱ እየሄደች ሳንቲሞች ስትቀበል ትዝ ይልሃል?"

"ከወይዘሪት ማክካርቲ አይደል?"

"ትክክል ብለሃል። ግን አሁን እንደምታውቀው ወይዘሪት ማክካርቲ ምንም የቀራት ሳንቲም የለም። ስለዚህ ዳዲ ወደ ውጭ ሄዶ የተወሰነ ሳንቲም ለእኛ ማግኘት አለበት። ሳንቲሙን ሳያገኝ ቢቀር በእኛ ላይ ምን ችግር እንደሚፈጠርብን ታውቃለህ አይደል የኔ ልጅ?"

"አላውቅም" አልኳት ወዲያውኑ፣ "ምን እንደሚፈጠር ንገሪና።"

"እሺ ግድየለም፣ እነግርሃለሁ። ልክ ዓርብ ዓርብ እንደምታያቸው እኒያ አሮጊት ሴትዬ ከቤት ወጥተን ሳንቲሞቹን ለማግኘት ሰዎችን መለመን ይኖርብናል። እንደዛ እንድናደርግ አንፈልግም አይደል ልጄ?"

"አንፈልግም" ተስማማሁ። "በጭራሽ አንፈልግም።"

"ስለዚህ ወደ መኝታ ቤቱ እየመጣህ እንደማትቀሰቅሰው ቃል ትገባልኛለህ?"

"እሺ በቃ፣ ቃል ገብቼያለሁ።"

ልብ አድርጉ እንግዲህ፣ ቃል የገባሁት ከልቤ ነበረ። ሳንቲሞች በጣም አሳሳቢ ነገሮች እንደሆኑ አሳምሬ ዐውቃለሁ እና ከቤት ወጥቶ ልክ እንደዛች ዓርብ ዓርብ የምናያት አሮጊት ወደ ልመና ሊያስገባን የሚችልን ማናቸውንም ነገር ሁሉ አምርሬ እቃወማለሁ። ከአልጋዬ በየትኛውም ጎን በኩል ብነሳ አንዳቸው ላይ እንድወድቅ አድርጋ እናቴ መጫወቻዎቼን በሙሉ ሰብስባ በአልጋዬ ዙሪያ ደረደረቻቸው። በዚህ መንገድ ከእንቅልፌ ስነሳ ወዲያው የገባሁትን ቃል ማስታወስ እችላለሁ ማለት ነው። ከእንቅልፌ ተነሣሁ እና ወለሉ ላይ ቁጭ ብዬ ለእኔ ለሰዓታት – ለሚመስል ጊዜ ብቻዬን ተጫወትኩ። ቀጥዬ ወንበሬን ሳብኩ እና ለተጨማሪ ሌሎች ሰዓታት በትንሿ መኝታ ቤት መስኮት አንገቴን አውጥቼ ወደ ውጭ ስመለከት ቆየሁ። አባቴ ከእንቅልፉ የሚነሣበት ጊዜ በደረሰ ብዬ በጣም ተመኘሁ፤ የሆነ ሌላ ሰው ለእኔ ሻይ ባፈላልኝ ብዬም ተመኘሁ። እንደ ፀሐይ የሆንኩ መስሎ ይሰማኝ የነበረው ስሜት ምንም አልተሰማኝም፤ በዚህ ፈንታ በጣም ተደብሬ እና በጣምም በርዶኝ ነበር! የሚያሞቀኝ ነገር ባገኘሁ እና ትልቁን ከወፍ ላባ የተሠራው አልጋ ውስጥ በገባሁ ብዬ ብቻ ስመኝ ነበር። ወደ የሚቀጥለው ክፍል ሄድኩ። በእማማ በኩል ምንም ክፍት ቦታ ሳላልነበረ በእሷ ላይ ወጣሁ። ገና መውጣት ከመጀመሬ ብን ብላ ነቃች። “ላሪ፣” እጄን አጥብቃ ይዛ፣ አንሾካሾኸች፣ "ምን ብለህ ነበር ቃል የገባኸው?"

"እንዴ የገባሁትን ቃል አክብሬያለሁ፣ ማሚ" ያው እጅ ከፍንጅ እንደመያዜ እንደ መነፋነፍ አደረገኝ። "እስካሁን እኮ ለረዥም ጊዜ ጭጭ ብዬ ተቀምጬ ነበረ።"

"ኦ የኔ ልጅ፣ በጣም ተቅዘቅዛለህ!" አዘነችልኝ፣ እና እቅፍ አደረገችኝ። "አሁን፣ እዚህ እንድትሆን ከፈቀድኩልህ ምንም ነገር ላለማውራት ቃል ትገባለህ?"

"ግን ማውራት እኮ እፈልጋለሁ ማሚ፣" አሁንም ተነፋነፍኩ።

"ያ ከምልህ ነገር ጋር ምንም አያገናኘውም፣" ለእኔ አዲስ በሆነ ቆራጥ አነጋገር ተናገረችኝ። "ዳዲ መተኛት ይፈልጋል። አሁን የምለው ይገባሃል? አይገባህም?"

ከሚገባው በላይ ገብቶኛል እንጂ። እኔ ማውራት እፈልጋለሁ፣ እሱ መተኛት ይፈልጋል – ግን ለመሆኑ ቤቱ የማን ነው?

"ማሚ፣" እኔም ከሷ ባልተናነሰ ቆራጥነት የተሞላ አነጋገር መናገር ጀመርኩ፣ "ዳዲ በራሱ አልጋ ላይ ቢተኛ እኮ ለጤናው የሚሻል ይመስለኛል።"

ያ አነጋገር የሆነ ነገሩዋን ውስጥ ገብቶ የጎረበጣት መሰለኝ፣ ምክንያቱም ለትንሽ ጊዜ ምንም መናገር አልቻለችም።

"አሁን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ" ማስፈራራትዋን ቀጠለች፣ "አንዳች ነገር ትንፍሽ ሳትል ዝም ትላለህ ወይስ ወደራስህ መኝታ ተመልሰህ ትሄዳለህ? የትኛው ይሻልሃል?"

የፍትሕ መዛባቱ ክፉኛ ስሜቴን ጎዳው። በገዛ ምላሷ ራሷ የተናገረችውን ስታፈርሰው በማየት የምትደረድራቸው ምክንያቶች እርስ በርስ እንደሚጋጩ በማሳየት ጥፋተኛ መሆንዋን አሳያቼያታለሁ። ይህን ሳደረግ ምንም ማስተባበያ መልስ እንኳ መስጠት አልቻለችም ነበር። ውስጤን ቂም እንደተሞላሁ አባባን በእርግጫ አቀመስኩት። ይህን ሳደርግ እሷ አላየችኝም እሱ ግን አጉረመረመ እና በድንጋጤ ዓይኖቹን በልቅጦ በረገዳቸው።

"ስንት ሰዓት ነው?" ድንጋጤ በወረረው ድምፅ ጠየቀ፣ እናቴን ሳይሆን በር በሩን እየተመለከተ፤ ልክ የሆነ ሰው በሩ ላይ ቆሞ የሚታየው ያለ ይመስል።

"ገና ነው፣" ቀስ ብላ አለሳልሳ መልስ ሰጠችው። "ምንም ነገር የለም፣ ልጃችን ብቻ ነው። መልሰህ ተኛ.... ስማ ላሪ አሁን!" ከአልጋው ላይ እየተነሳች፣ "ዳዲን ከእንቅልፉ ቀሰቅሰኸዋል ወደ መኝታ ቤትህ መመለስ አለብህ።"

ይኼን ጊዜ እንዲህ በተረጋጋ ሁኔታዋ፣ የተናገረችው ከልቧ እንደሆነ ዐውቄያለሁ። እና የእኔን ዋንኛ መብቶች እና ጥቅማ ጥቅሞቼን አሁኑኑ ማስከበር ካልቻልኩ እስከ ወዲያኛው ተመልሰው ላይገኙና እልም ብለው እንደሚጠፉም አሳምሬ ተረድቼያለሁ። ከአልጋው ላይ ስታነሣኝ፣የተኛውን አባቴን አይደለም ሙታንን እንኳ ሊቀሰቅስ የሚችል እሪታዬን አስነካሁት።

አጉረመረመ። "ይኼ የተረገመ ልጅ! እንዴ እንቅልፍ የሚባል ነገር አያውቅም እንዴ? ለመሆኑ መቼ ነው የሚተኛው?"

ምንም እንኳ አነጋገሩ እንዳስቀየማት እኔ ማየት ብችልም "ዝምብሎ መጥፎ ልማድ ሆኖበት ነው የኔ ጌታ" ስትል ተለሳልሳ በትህትና መልስ ሰጠችው።

"ይሁና፣ ከዚህ መጥፎ ልማዱ መታረም ያለበት ጊዜ አሁን ነው፣" አባቴ አንባረቀ፣ አልጋው ውስጥ መንደፋደፍ ጀመረ። የአልጋ ልብሱንና አንሶላውን በሙሉ ወደ ራሱ ሰበሰበና ፊቱን ወደ ግድግዳው አዞረ። ቀጥሎ አንገቱን ዞር አድርጎ ሌላ ምንም ነገር ሳይሆን ሁለት ጥላቻ የተሞሉ የሞጨሞጩ ዓይኖቹን አሳየኝ። ሰውዬው በጣም ተንኮለኛ ይመስላል። የመኝታ ቤቱን በር ለመክፈት፣ እናቴ እኔን ወደ መሬት ማውረድ ነበረባት። ያኔ ነጻነቴን መልሼ አገኘሁ። በተቻለኝ ፍጥነት ወደ አንዱ ጥግ ቱር ብዬ ሄጄ ጥጌን ይዤ እሪታዬን ለቀቅኩት።

አባቴ ደንግጦ አልጋው ላይ በረገግ ብሎ ቁጭ አለ። "ዝም በል አንተ ትንሽ ቡችላ" አለ በታነቀ ድምፅ።

እሪታዬን መልቀቄን በማቆሜ ለራሴ በጣም ገርሞኛል። ከዚህ በፊት ማንም እንዲህ ባለ ድምፀትና ቃና በጭራሽ፣ በጭራሽ ተናግሮኝ አያውቅም። ባለማመን ስሜት ትኩር ብዬ አየሁት። ፊቱ በቁጣ ግሎ እየተንቦገቦገ እንደሆነ አስተዋልኩ። እግዚአብሔር ይኼ ጭራቅ ወደ እኛ ቤት በሰላም እንዲመጣ ለጸለይኩት ጸሎት ምንኛ ዋጋዬን እንደሰጠኝ ገና ያን ጊዜ ነበረ በደንብ ፍንትው ብሎ የታየኝ።

"አንተ ራስህ ዝም በል!" አቅሜ የፈቀደውን ያክል እኔም አንባረቅኩ።

"ምንድነው ያልከው አንተ?" አባቴ ጮኸና እየተንገዳገደ ከአልጋው ዘሎ ወረደ።

"ማይክ፣ ማይክ!" እማማ ጮኸች። "ይኼ ልጅ ገና በደንብ እንዳልለመደህ አይገባህም እንዴ?"

"አዎ፣ ዝም ብሎ ደህና እንደተቀለበ እንጂ ሥርዓት የሚባል ነገር እንዳልተማረማ በደንብ ገብቶኛል፣" እጁን ወዲያና ወዲህ እያወናጨፈ አባቴ አጓራ። "ቂጡ ላይ መለጥለጥ ያስፈልገዋል!"

እነዚህ እኔን ምን እንደሚያስፈልገኝ የተናገራቸው የመጨረሻ ቃላት ከዚህ ቀደም እየጮኸ ከተናገራቸው ጋር ሲነጻጸሩ የበፊቶቹ ምንም ማለት ናቸው ይቻላል። እነዚህ የመጨረሻዎቹ ቃላት በእውነት ደሜ ፈልቶ በውስጤ እንዲንተከተክ አደረጉት።

"የራስህን ቂጥ ለጥልጥ!" በምፀት እኔም ጮኽኩ። "የራስህን ቂጥ ለጥልጥ! ዝምበል ብዬሃለሁ ዝምበል!"

እዚህ ላይ የነበረው ትዕግስት በሙሉ ተሟጦ አለቀና ወደኔ እየበረረ በአየር ላይ መጣ። ከአንዲት እናት ፍርሃት የተሞሉ ዓይኖች ሥር አንድ የተከበረ ጦርነትን የሚያክል ነገር ላይ ደርሶ የተመለሰ ጨዋ ሰው ያደርገዋል ተብሎ የማይጠበቀውን ነገር ለማድረግ የቃጣ ቢሆንም፤ ያ ሁሉ ዛቻ እና እንደዛ ተስፈንጥሮ በአየር ላይ የመምጣቱ ነገር ትንሽ እኔን ነካ ከማድረግ ያለፈ ሌላ ውጤት አላስገኘም። ይህም ሆኖ ግን ማንነቱ በማይታወቅ እንግዳ ሰው ያውም በእኔ ቅንነት የተሞላ የምልጃ ጸሎት ተሳክቶለት ከጦርነት የሚያክል ነገር ወጥቶ የኛ ትልቁ አልጋ ላይ መድረስ በቻለ እንግዳ ሰው እንዲህ መደፈሬ ያደረሰብኝ ከፍተኛ ውርደት ሙሉ በሙሉ እንደ እብድ እንድሆን አደረገኝ። አንዘፈዘፈኝ፣ መልሶ መላልሶ አንዘፈዘፈኝ፣ በባዶ እግሬ በንዴት ተፍጨረጨርኩ። አባቴ ጉስቁልቁል ብሎ አጭር ግራጫ የጦር ሠራዊት ካናቴራውን ብቻ እንዳደረገና የሰውነቱ ጸጉር ከላይ እስከ ታች ቀጥ ብሎ እንደቆመ፣ ልክ ሊገለኝ የፈለገ ያክል እንደ ተራራ ከላዬ ላይ ቆሞ በንዴት ተውጦ አፈጠጠብኝ። ይመስለኛል፣ ያን ጊዜ ነው እሱም በኔ እንደሚቀና ፍንትው ብሎ የታየኝ። እማማ የሌሊት ልብሷን እንደለበሰች ቆማለች። ልቧ በእኔና በእሱ መካከል ለሁለት የተከፈለባት ትመስላለች። መስላ እንደምትታየው ቢሰማት ብዬ ተመኘሁላት። አዎ፣ ይህን ሁሉ ጣጣ ያመጣችው እሷ ስለሆነች ቢያንስባት እንጂ አይበዛባትም። እንኳንም እንደዛ ሆነች።

ከዚያ ቀን ጠዋት ጀምሮ ሕይወቴ ገሃነመ እሳት ሆነ። አባቴ እና እኔ የለየልን እና የታወቀልን ጠላቶች ሆንን። አንዳችን በአንዳችን ላይ የማያቋርጥ ጥቃት መሰንዘራችንን ቀጠልንበት፤ እሱ እኔ ከእናቴ ጋር ሊኖረኝ የሚችለውን ጊዜ ሊሰርቅ ይሞክራል እኔም የእሱን ጊዜ እሰርቃለሁ። እሷ እኔ አልጋ ላይ ተቀምጣ ተረት ተረት ስትነግረኝ ጦርነቱ ሲጀመር ድሮ እኔ ክፍል ውስጥ ትቶት የሄደውን ቡትስ ጫማ እፈልጋለሁ ብሎ ምክንያት በመስጠት መኝታ ቤቴን ያተራምሳል። እሱ ከእናቴ ጋር ሲያወራ፣ በሚያወሩት ነገር ምንም ዓይነት ደንታ እንደማይሰጠኝ ለማሳየት ከመጫወቻዎቼ ጋር ጮኽ ብዬ እያወራሁ እጫወታለሁ።

አንድ ቀን ማታ ከሥራ ወደ ቤት ሲመለስ እና ያ የእሱን ሳጥን ከፍቼ በወታደራዊ ባጆቹ፣ ጉርካ ቢላዎቹ እና የጦር ሠራዊት በትሮቹ ስጫወት ሲያገኘኝ እጅግ አሳፋሪ የሚባል የቅሌት ድርጊት ፈጸመ። እናቴ ከተቀመጠችበት ብድግ አለችና ሳጥኑን ከእኔ ቀማችኝ።

"ካልፈቀደልህ በቀር በዳዲ መጫወቻዎች በጭራሽ መጫወት የለብህም። ትሰማለህ ላሪ!" ቆጣ ብላ አምርራ ተናገረች። "ዳዲ ባንተ መጫወቻ ይጫወታል እንዴ? አይጫወትም።"

በሆነ ምክንያት አባቴ ልክ በሆነ ነገር የነረተችው ያህል አተኩሮ ከተመለከታት በኋላ እየተሳደበ ፊቱን ዞር አደረገ። "ስሚ መጫወቻ አይደሉም፣" አጓራ፣ የሆነ ነገር አንስቼ እንደሆነ ለማየት ሳጥኑን መልሶ ዝቅ አድርጎ ተመለከተው። "አንዳንዶቹ ዕቃዎች በጭራሽ በቀላሉ የማይገኙ ናቸው፣ ዋጋቸውም አይቀመስም።"

ግን ጊዜ እየገፋ ሲሄድ እናቴን እና እኔን መነጣጠሉ እንዴት ይዋጣለት እንደነበረ ይበልጥ ግልፅ እየሆነልኝ ሄደ። ከዚህ ሁሉ የከፋው ደግሞ ስልቱን ስለሚቀያይር በቀላሉ ላውቅበት አለመቻሌ ወይም እናቴ ምኑን እያየች ወደሱ እንደምትሳብ ግልፅ ሊሆንልኝ አለመቻሉ የእኔን የተስፋ የመቁረጥ ስሜት ይበልጥ አፋፋመው። በእያንዳንዱ እሷን ሊማርኩ ይቻላሉ በሚባሉ መንገዶች ሁሉ ከእኔ ይብሳል እንጂ አይሻልም። አነጋገሩ ያልተገራ የባለገር ዓይነት ነው። ሻይ ሲጠጣ ፉት ሲል ድምፅ አውጥቶ እያፏጨ ነው የሚጠጣው። ምናልባት ወደሱ እንድትሳብ የሚያደርጋት ያ የሚያነበው ጋዜጣ ሊሆን ይችላል ብዬ ለተወሰነ ጊዜ አስቤ ነበር። ስለዚህ ለእርሷ ወሬዎችን ለመንገር እንድችል የተወስኑ ቁርጭራጭ ዜናዎችን አቀናብሬና ራሴ አዘጋጅቼ ሞከርኳት። አልተሳካም። ቀጥዬ ምናልባት ያ ጭሱ ሊሆን ይችላል ብዬ አሰብኩ። ይህን እንኳ እኔም ራሴ የሆነ የሚስብ ነገር እንደሆነ አምንበታለሁ። እሱ እስኪይዘኝ ቀን ድረስ ቤት ውስጥ ላያቸው ላይ እየተነፈስኩ የእሱን ፒፓዎች ይዤ ጎርደድ ጎርደድ አልኩባቸው። ሌላው ሳይቀር ሻይ ስጠጣ እንደሱ ሻዩን ስምግ አፌን ማስፏጨት ጀመርኩ። ግን እናቴ በጣም እንደሚያስጠላብኝ ነገረችኝ እንጂ ያተረፍኩት ነገር የለም። ምሥጢሩ የተቆለፈው እዚያ ለጤና አደገኛ ከሆነው አብሮ መተኛት ጋር ሙሉ በሙሉ ከተያያዘ ያልታወቀ ነገር ላይ ያለ ይመስላል። ስለዚህ ወደ የእነርሱ መኝታ ቤት ባሻኝ ጊዜ ዘው ብሎ በመግባት እና አስፈላጊውን ጩኸት በመፍጠርና ከራሴ ጋር በማውራት ተቃውሞዬን ይፋ አደረግኩት። ስለዚህ እያየሁዋቸው እንደሆነ ስለማያውቁ የሆነ እኔ የማላውቀውን ነገር ሲያደርጉ ለማየት ሞከርኩ። ግን እኔ የሚታየኝ ምንም የሚያደርጉት ነገር አልነበረም። በመጨረሻ እኔው ራሴ ተሸነፍኩ። ምሥጢሩ ያለው ትልቅ ሰው ከመሆን እና ለሰዎች ቀለበት ከመስጠት ጋር የተያያዘ ይመስላል። በመሆኑም ይህ ለእኔም እስኪሆንልኝ ድረስ ታግሼ መጠበቅ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። እንዲህም ሆኖ ግን አሁን ላይ ራሱ ጊዜዬን እየጠበቅኩ እንደሆነ እንጂ ትግሉን በቃኝ ብዬ በተሸናፊነት እንዳልተውኩት ለራሴ ርግጠኛ ለመሆን ፈልግኩ።

አንድ ቀን ማታ ክፋቱን ተሞልቶ፣ አናቴ ላይ ቆሞ ካንባረቀብኝ በኋላ አዘናግቼ ዋጋውን ሰጠሁት።

"ማሚ፣" አልኩ፣ "ሳድግ ምን እንደማደረግ ታውቂያለሽ?"

"አላውቅም የኔ ልጅ" መልስ ሰጠችኝ። "ምን ታደርጋለህ?"

"አንቺን አገባሻለሁ፣" ረጋ ብዬ መልሱን ሰጠኋት።

አባቴ የሆነ ነገር ሲቀፈውና ቀልቡ ሲገፈፍ ታየኝ፣ ግን ምንም አላለኝም። እያስመሰለ እንደሆነ እንጂ ውስጡ ብግን ብሎ እንደተቃጠለ በደንብ ዐውቄበታለሁ።

እና እናቴ ምንም ይሁን ምን በተናገርኩት ነገር በጣም ደስ አላት። አንድ ቀን አባቴ በእሷ ላይ ያለው የበላይነት እንደሚያበቃ በማወቋ ምናልባት እፎይታ ስሜት የተሰማት መስሎ ተሰማኝ።

"ደስ የሚል ነገር አይሆንም?" ፈገግ ብላ ተናገረች።

"በጣም ደስ የሚል ነገር ይሆናል፣" በራስ መተማመን መንፈስ መናገሬን ቀጠልኩ። "ምክንያቱም በጣም ብዙ ብዙ ልጆች ይኖሩናል።"

"ልክ ነህ የኔ ልጅ" በጽሞና ተሞልታ በእርጋታ ተናገረች። "በቅርቡ አንድ ማሙሽ ልጅ የሚኖረን ይመስለኛል፣ ከዚያ በኋላ አብሮህ የሚሆን ጓደኛ አታጣም።"

በዚህ ነገር እንዳሰበችው ደስ አላለኝም። ምክንያቱም ምንም እንኳ እሷ ራሱን ያን ያክል ለአባቴ ራሷን አሳልፋ የሰጠች መሆኗ ቢታወቅም የኔን ምኞት ከግምት ለማስገባት እየሞከረች እንደሆነ በግልፅ ያታያል። ከዚህ ጐን ለጐን የጌነይ ቤተሰቦች ባሉበት ሁኔታ የእኛ የበላይ እንደሆኑ እንዲቀጥሉ ያደርጋቸዋል። ምንም እንኳ መጨረሻው እንዳዛ ሆኖ ባያልቅም። ከሥር መሠረቱ ለመጀመር ያክል፣ ከልክ በላይ በጣም ብዙ ጉዳይ አለባት – ያንን የተባለውን አሥራ ሰባት ፓውንድ ከስልሳ ከየትም አታመጣውም ብዬ አስባለሁ – እንዲሁም አባቴ ማታ ማታ አምሽቶ ቢመጣም ለኔ የፈየደልኝ ነገር የለም። እኔን በእግራችን ለመሸራሸር ይዛ መውጣቷን ትታዋለች፣ ልክ እንደ እሳት ዝምብላ ትፋጃለች ሲላትም ከመሬት ተነስታ ትገርፈኛለች። አንዳንድ ጊዜ እነዚያን በርከት ያሉ ልጆች ስለ መውለዳችን ምንም ባልተናገርኩ ይሻል ነበር እላለሁ ለራሴ – ለሌላ ነገር ሳይሆን በራሴው ላይ መከራን ለማምጣት ብቻ የሚያስችል ብልህ አእምሮ ያለኝ መስሎ ይሰማኛል።

መከራውም በርግጥ ቀላል መከራ አልነበረም! ሶኒ በእጅግ አስቀያሚ ዋይታ እና ሁከታ መካከል ወደ ቤታችን መጣ – ያን ሁሉ ግርግር እና ጩኸት ሳያበዛ መምጣት እንኳ አልቻለም – እና ገና ካየሁት ቀን ጀምሮ ጠላሁት። በጣም አስቸጋሪ ሕፃን ነበር – እኔን እስከሚያገባኝ ድረስ ሁልጊዜም አስቸጋሪ ልጅ ነበር – እና ከልክ በላይ ትኩረት እንዲሰጠው ይፈልጋል። እናቴ የሱ ነገር ሲነሳ እንደ ጅል ያደርጋታል፣ እና መቼ ጉራውን ዝም ብሎ እየነፋ እንደሆነ እንኳ ለይታ ማወቅ አልቻለችም። እንደ ጓደኛ ከታየ፣ ከእርባና ቢስም የከፋ ዓይነት ከንቱ ፍጡር ነው። ሙሉ ቀን እንቅልፉን ይለጥጣል፣ እና እሱን ከእንቅልፉ ላለመቀስቀስ ቤት ውስጥ በእግሮቼ ጣቶች ቀስ ብዬ መሄድ ነበረብኝ። አሁን ጥያቄው አባቴን መቀስቀስ ወይም አለመቀስቀስ አይደለም። አዲሱ መፈክር "ሳኒን እንዳትቀሰቅስው!" የሚል ሆኗል። ሕፃኑ በትክክለኛው ሰዓት ለምን እንደማይተኛ ሊገባኝ አልቻለም፤ ስለዚህ እናቴን ጀርባዋን በሰጠችን ቁጥር ቀስ ብዬ እቀሰቅሰው ነበር። አንዳንድ ጊዜ እንቅልፍ እንዳይወስደው በተጨማሪ ቆንጠጥ ሁሉ አደርገውም ነበር። አንድ ቀን እናቴ ይህን እያደረግኩ እጅ ከፍንጅ ያዘችኝና ያለ ምንም ርህራሄ ሙልጭ አድርጋ ገረፈችኝ።

አንድ ቀን ማታ አባቴ ከሥራ መመለሱ ነበር። ከፊት ለፊት ባለው የግቢያችን መናፈሻ ላይ ባቡር ባቡር እየተጫወትኩ ነበር። ልክ መምጣቱን ያላወቅኩ መስዬ ጨዋታዬን ቀጠልኩ፤ ልክ ከራሴ ጋር የማወራ አስመስዬ ድምፄን ከፍ አድርጌ ፦ "ሌላ ልጅ ከአሁን በኋላ እዚህ ቤት ከመጣ፣ እኔ ከዚህ ቤት እወጣለሁ።" ብዬ ተናገርኩ።

አባቴ ደንግጦ የሞተ ሰው ያክል ደርቆ ቀረ እና ዞር ብሎ ተመለከተኝ። "ምንድን ነው ያልከው አንተ?" ሲል ጠየቀኝ ኮስተር ብሎ።

"ከራሴ ጋር እያወራሁ ነበር፣" መልስ ሰጠሁት፣ መፍራቴ እንዳይታወቅብኝ ድምፄን ጥረት እያደርግኩ። "የግል ምሥጢር ነው።"

ዞር ብሎ ምንም ነገር ሳይናገር መንገዱን ወደ ቤት ቀጠለ።

ልብ አድርጉ እንግዲህ፣ እኔ ያሰብኩት ዝም ብሎ እንደ ማስጠንቀቂያ ሆኖ እንዲያገለግል ነበር፤ ነገር ግን ያስገኘው ውጤት በጣም ያልተጠበቀ ስኬት ነበር። አባቴ ለእኔ ደግ ይሆንልኝ ጀመረ። ይሄንን መረዳት በርግጥ እችል ነበረ። ምክንያቱም እናቴ ከሶኒ ጋር ስትታይ በጣም ታስጠላለች። ሌላው ሳይቀር በገበታ ሰዓት እንኳ ሳይቀር ከመዐድ ላይ ትነሳና ከሆነ የጅል ፈገግታ ጋር በሕፃን አልጋው ላይ ታፈጣለች፣ እና አባቴም ልክ እንደሷ እንዲያደርግ ትጠይቀዋለች። ይህንን ሲጠይቅ ሁልጊዜም ትህትና አይጎድለውም፣ ግን ስለ ምን ጉዳይ እያወራች እንዳለ ለማወቅ ግራ እንደተጋባ ለማየት ትችላላችሁ። ሶኒ ሌሊት ስለሚያለቅስበት የአለቃቀስ ሁኔታ ቅሬታውን ያሰማል። እሷ ግን ችላ ብላ ታልፈውና ሶኒ የሆነ ነገር ካልሆነ በቀር እንደማያለቅስ ለማስረዳት ትሞክራለች – ይኼ የሚያበግን ቅጥፈት ነበር፣ ምክንያቱም ሶኒ ምንም የሚሆነው ነገር አልነበረውም። የሚያለቅሰው ትኩረት ለመሳብ ሲፈልግ ብቻ ነው። ምን ያክል እንዲህ ያለ ተራ ጭንቅላት ያላት ሴት እንደሆነች ስትታይ፣ በእውነት በጣም ነው የምታመው።

አባቴ ያን ያክል የሚሰብ ዓይነት ሰው አልነበረም፤ ቢሆንም ግን የተሻለ አእምሮ ነበረው። የሶኒ ተንኮልን ለይቶ ዐውቆበታል እና አሁን እኔም ልክ እንደሱ ተንኮሉ እንደገባኝ ተረድቶቷል። አንድ ሌሊት ከእንቅልፌ ነቃሁ። አልጋዬ ላይ ሌላ ሰው ተኝቶ ነበረ። ለአንድ የሆነ ምንነቱ የማይታወቅ አፍታ ጊዜ እናቴ መሆን እንዳለባት የርግጠኛነት ስሜት ተሰማኝ። ወደ ልቧ በስተመጨረሻ ተመልሳ፣ አባቴን እስከ ወዲያኛው ተሰናብታ ወደኔ የመጣች መሰለኝ። ሆኖም ግን በቅዠቴ መሃል ሶኒ ሲያለቅስና እናቴ "ይኸው የኔ ቆንጆ! እሺ . . . እሺ ተኛ የኔ እናት! አይዞህ!" ስትል ከዚያኛው ክፍል ሰማሁዋቸው፤ ስለዚህ አጠገቤ ያለችው እሷ እንዳልሆነች ታወቀኝ። አባቴ ነበር አጠገቤ የተኛው። እንቅልፍ አልወሰደውም፣ ቁና ቁና ይተነፍሳል፣ በግልፅ እንደሚታየው በንዴት እስከ መጨረሻው ግሎ በግኗል። ከትንሽ አፍታ በኋላ ምን እንደዚያ እንዳበገነው ተገለፀልኝ። አሁን የእሱ ተራ ነበር። እኔን ከትልቁ አልጋ እንድባረር ካደረገኝ በኋላ፣ አሁን ደግሞ እሱ ራሱን በራሱ አባሯል። እናቴ አሁን ከዚያ መርዛማ ከሆነ ቡችላ ሶኒ በቀር ሌላ ምንም ደንታ የሚሰጣት ሰው የለም።

ለአባቴ በጣም አዘንኩለት። እኔም እሱ ያጋጠመውን መከራ ከዚህ ቀደም አልፌዋለሁ፣ እንዲያውም ሌላው ሳይቀር ያንን መከራ የተቀበልኩት ዕድሜዬ ገና እምቦቅቅላ በነበረበት ዘመን ነበር። የራሱን ጸጉር ጫር ጫር እያደረግኩለት ቀስ ብዬ በለሆሳስ፦ "ይኸው የኔ ቆንጆ! እሺ . . . እሺ ተኛ የኔ እናት! አይዞህ!" ማለት ጀመርኩ።

ምንም ዓይነት የተቃውሞ ምላሽ አልሰጠም። "አንተም አልተኛህም?" እንደ መነፋነፍ ብሎ ተናገረ።

"እንዴ አይዞህ፣ በእጅህ አድርገህ እቀፈኝና እንተቃቀፍ፣ ማቀፍ አትችልም?" አልኩት፣ እሱም እንዳልኩት በራሱ መንገድ እንደ ምንም ዕቅፍ አደረገኝ። በከፍተኛ ጥንቃቄ ብላችሁ ሁኔታውን ልትገልፁት የምትችሉ ይመስለኛል። በጣም ቀጫጫ ነው፤ ቢሆንም ባዶ እጅ ከመቅረት ግን ይሻላል።

ለገና በዓል ጊዜ በጣም ምርጥ የሆነ የባቡር መጫወቻ ከነ የባቡሩ ሃዲድ በራሱ ፍላጎት ገዝቶልኝ መጣ።

[1] እንደ Wikipedia እና Oxford Advanced Learners’ Dictionary ኤዲፐሳዊ ቅናት የሚለው አገላለጽ ከክርስቶስ ልደት በፊት በአምስተኛው ክፍለ ዘመን ኖሯል ተብሎ በአፈ ታሪክ የሚታመነውን ከግሪኩ ኤዲፐስ የሚባል ንጉሥ ስም የተገኘ ሲሆን ጥሬ ትርጉሙ አንድ ወንድ ልጁ በእናቱ ላይ የሚኖረው ወሲባዊ ፍላጎትን እና በዚህም የተነሣ የሚከሰተው ልጁ በአባቱ ላይ የሚኖው ክፉ የቅናት ስሜትን ይወክላል። የቃሉ አመጣጥ አስቀድሞ እንደ ተገለጸው መነሻው ኤዲፐስ ስለተባለው የግሪክ ንጉሥ የሚያወራው አፈ ታሪክ ሲሆን በዚህ ትርክት መሠረት የኤዲፐስ አባት ላዩስ ከአማልክት ጋር በሚነጋገርበት ጊዜ ልጁ እሱን እንደሚገድለው እና በአባቱ ዙፋን ላይ እንደሚነግሥ ንግርት ይነገረዋል። ይህ እንዳይፈጠር አባትየው ላዩስ ልጁን ኤዲፐስን እንዲሞት በማሰብ ራቅ አድርጎ በመውሰድ ተራራማ አካባቢ ይጥለዋል። ሆኖም ግን የተጣለውን ልጅ አንድ እረኛ ያገኘውና ወደ ቤቱ ወስዶ ያሳድገዋል። ከብዙ ዓመታት በኋላ ኤዲፐስ ወደ ትውልድ አገሩ ይመለሳል። የገዛ ወላጆቹን ማንነት አያውቅም ነበር። ስለሆነም ኤዲፐስ የገዛ አባቱን ላዩስን ይገድልና እናቱን ጆካስታን ሚስት አድርጎ ያገባታል። በዚህ ታሪክ ላይ በመመርኮዝም ኤዲፐስ ሬክስ (Oedipus Rex) የሚባለው ተወዳጅ እና ዝነኛ ተውኔት ከክርስቶስ ልደት በፊት በ429 ገደማ በሶፎክልስ ተጽፎ ከዚያም ወደ የተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ በዓለም ዙሪያ በመድረክ ላይ ሲታይ እስከ አሁኑ ዘመን ድረስ ቆይቷል። አሁንም ገና በመታየትም ላይ ነው። ከዚህ ባሻገር፣ በዘመናዊው ሥነ አእምሮና ሥነ ልቦና ጥናት ኤዲፐሳዊ ቅናት (Oedipus complex ወይም ብዙ አባባሉ ባይዘወተርም Oedipal complex በመባል የሚታወቀው የባሕሪ መገለጫ) ትርጉሙ ሕፃን ሴት ከሆነች ከአባቷ፣ ወንድ ከሆነ ደግሞ ከእናቱ ጋር ወሲብ ለመፈጸም የሚገፋፋቸው ደመ ነፍሳዊ ግን ተለዋዋጭ ውስጣዊ ስሜት አላቸው ብሎ የሚከራከር የፍልስፍና እሳቤ ጽንሰ ሐሳብ ነው። …ኤዲፐሳዊ ቅናት የሚለው ሳይንሳዊ ትንታኔ በመጀመሪያ መሰጠት ሲጀምር አንድ ወንድ ልጅ በእናቱ ላይ የሚያድርበትን ወሲባዊ ድብቅ ስሜት የሚገልፅ ቃል ነበር። “ኤዲፐሳዊ ቅናት” የሚለውን ቃል አገጣጥሞ የፈጠረው ሲግመንድ ፍሩድ የተባለው የሥነ ልቦና ሊቅ እና ፈላስፋ ሁለቱም ወንድ እና ሴት ሕፃናት ከወላጆቻቸው ጋር የሚኖራቸውን ድብቅ ስሜት ይወክላል ብሎ ያምናል።

Frank O'Connar's "My Oedipus Complex" translated into Amharic by Brook Beyene