ፍቼ ጫምባላላ በዓል በዩኔስኮ የሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ባሕላዊ ቅርስ ዝርዝር ላይ በዩኔስኮ ተመዘገ

ከውክፔዲያ

ተመዘገ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

DECEMBER 4, 2015ARCCHPRLEAVE A COMMENT

የማይዳሰሱ (ኢንታንጀብል) ባህላዊ ቅርሶችን የሚመለከተው የዩኔስኮ አካል በይነ መንግሥታዊው ኮሚቴ (Intergovernmental Committee) 10ኛ ስብሰባውን ከኅዳር 20 እስከ ኅዳር 24 ቀን 2008 ዓ.ም. በናሚቢያ መዲና ዊንድሆክ በተደረገው 10ኛ የዩኔስኮ ጉባዔ ለውሳኔ ከቀረቡት 35 (ሠላሳ  አምስት) ባሕላዊ ቅርሶች መካከል የሲዳማ ብሔር የአዲስ ዓመት ዘመን መለወጫ የሆነው ፍቼ ጫምባላላ በዓል በሰው ልጆች ወካይ ቅርስ ዝርዝር ውስጥ (Representative List of Intangible Cultural Heritage of Humanity)   የ2003 የኢንታጀብል ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ ዓለም አቀፍ ስምምነት መስፈርቶችን አሟልቶ በመገኘቱ አባል አገሮች ውይይት ካደረጉበት በኋላ ፍቼ ጫምባላላ ተመዝግቧል፡፡ ይህም ከመስቀል በዓል ቀጥሎ የኢትዮጵያ ሁለተኛው የማይዳሰስ ዓለም አቀፍ የሰው ልጆች ወካይ ቅርስ ሆኖ ሕዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም በአገሩ ሰዓት አቆጣጠር 9፡40 በፋይል ቁጥር (01054) በውሳኔ ቁጥር 10.com.10.b.16 ተመዝግቧል፡፡


በምዝገባው ላይ ስድስት ዓባላት ያሉት የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድንን በመምራት በጉባዔው ላይ የተገኙት የፌዴራል ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ መዓዛ ገ/መድህን እንዲሁም የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር  አቶ ዮናስ ደስታ ሲሆኑ የፍቼ ጫምባላላ በዓል በመመዝገቡ የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ለጉባዔው በንግግር ገልጸው ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ለደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ እንዲሁም የቅርሱ ባለቤት ለሆነው የሲዳማ ሕዝብ እንኳን ደስ ያላችሁ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡



ተጨማሪ ማብራሪያ

  1. ኢትዮጵያ የኢንታጀብል ባህላዊ ቅርሶቿን በዩኔስኮ ከማስመዝገብ አኳያ ያለችበት ደረጃ አጭር ማብራሪያ


በ2003 (እ.ኤ.አ) በዩኔስኮ የፀደቀው የኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን (Safeguarding of the Intangible Cultural Heritage Convention) መሰረት ኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርስ ማለት ግለሰቦች፣ቡድኖችና ማህበረሰቦች ባህላቸው አድርገው የተቀበሏቸው ድርጊቶች፣ ውክልናዎች፣ መገለጫዎች፣ እውቀት፣ ክህሎት እንዲሁም ከእነዚህ ጋር የተያያዥ የሆኑ መሳሪያዎች፣ ቁሶች፣ እደጥበባትና ባህላዊ ሥፍራዎችን የሚያካትት ነው፡፡ በዚህ ኮንቬንሽን የኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች በአምስት ክፍሎች ተመድበዋል፡፡እነሱም አፋዊ ትውፊቶችና መገለጫዎች (Oral traditions and expressions)፤ ማህበራዊ ክንዋኔዎች፣ ሥነ-ስርዓቶችና ፌስቲቫሎች (Social practices, rituals and festive events)፤ሀገር በቀል እውቀቶች ወይም ስለ ተፈጥሮና ዓለም እውቀትና ትግበራ (Knowledge and practices concerning nature and the universe)፤ትውፊታዊ የዕደ ጥበብ እውቀቶችና ክህሎቶች (Traditional craftsmanship) እና ሀገረሰባዊ ትውን ጥበባት (Performing arts) ናቸው፡፡


ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሀገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች የየራሳቸው መለያ የሆኑ ባህላዊ እሴቶችና ቅርሶች ባለቤት በመሆናቸው ኢትዮጵያ በኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች ሀብት የበለጸገች ናት ማለት ይቻላል፡፡


በመሆኑም በ1987 የፀደቀው የኢፌዲሪ ህገ መንግሥት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህላዊ እሴቶቻቸውን በነፃነትና በእኩልነት የመግለጽ፣ የማሳደግና የመንከባከብ መብት አጎናጽፏቸዋል፡፡ በተጨማሪም በ199ዐ የፀደቀው የባህል ፖሊሲና በ1992 ዓ.ም. የወጣው የቅርስ ጥናትና አጠባበቅ አዋጅ ኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች በእኩልነት እንዲታወቁና፣ እንዲመዘገቡ ተጠንተው፣ ተጠብቀውና ተዋውቀው ለዘለቄታዊ ማኀበራዊና የቱሪዝም ልማት እንዲውሉና ባህላዊ ይዘታቸውን ጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉበትን አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የኢንታጀብል ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ ስምምነትን እ.ኤ.አ  ፊብሯሪ 24, 2006 ፈርማለች፡፡


በኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በአንደኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ሶስት ኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶችን በዩኔስኮ የሰው ልጆች ወካይ ቅርስ ዝርዝር ውስጥ ለማካተት የሚስችሉ ተግባራትን አከናውኗል፡፡


በ2004 በጀት ዓመት የመስቀል በዓል አከባበርን በዩኔስኮ ማስመዝገብ የሚያስችል የጥናት ሰነድ ተዘጋጅቶ ለዩኔስኮ የተላከ ሲሆን በአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ ከህዳር 23-28 ቀን 2006 ዓ.ም በተካሄደው 8ኛው የዩኔስኮ የኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ የኢንተርገቨርንመንታል ኮሚቴ መደበኛ ጉባዔ ውሳኔ መሰረት የመስቀል በዓል አከባበር በዩኔስኮ የሰው ልጆች ወካይ ኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርስ ዝርዝር (Representative List of Intangible Cultural Heritage of Humanity) ውስጥ ተካቷል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ፡-

http://www.unesco.org/culture/ich/index.php?lg=en&pg=665


በ2006 የበጀት ዓመት የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል የሆነው ፊቼ ጫምበላላን በሰው ልጆች ወካይ ኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርስ ዝርዝር ውስጥ ለማስመዝገብ የሚያስችል የጥናት ሰነድ (ኖሚኔሽን ፋይል) ተዘጋጅቶ ለዩኔስኮ የተላከውና ህዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም የተመዘገበው የተደረገው  ፊቼ ጫምበላላ ሰነዶች በሚከተለው የዩኔስኮ ድረ ገጽ ላይ ለመላው ዓለም ተለቀው ይገኛል፡፡

http://www.unesco.org/culture/ich/en/10b-representative-list-00779?lg=en&pg=00011&inscription=11


በተመሳሳይም በ2007 የበጀት ዓመት ኦሮሞ ህዝብ የማንነት መገለጫ የሆነው የገዳ ስርዓትን በሰው ልጆች ወካይ ኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርስ ዝርዝር ውስጥ ለማካተት የሚያስችል የኖሚኔሽን ሰነድ ተዘጋጅቶ ለዩኔስኮ መጋቢት 2007 ዓ.ም ተልኳል፡፡ የኖሚኔሽን ሰነዱ በሚከተለው የዩኔስኮ ድረ ገጽ ላይ ለመላው ዓለም ተለቀው ይገኛል፡፡

http://www.unesco.org/culture/ich/index.php?lg=en&pg=00774


በአጠቃላይ ኢትዩጵያ በአንደኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ሶስት ኢንታንጀብል ቅርሶች በሰው ልጆች ወካይ የቅርስ ማኀደር ውስጥ ለማስመዝገብ የሚስችሉ የኖሚኔሽን ጥናት ሰነዶችን አዘጋጅታ ለዩኔስኮ ልካለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እ.ኤ.አ በ2014 ኢትዩጵያ 24 አባል ሀገራት ባሉት የኢንታጀብል ባህላዊ ቅርሶች የኢንተርገቨርንመንታል ኮሚቴ (Intergovernmental Committee for the Safeguarding of Intangible Cultural Heritage) አባል ሁና ተመርጣለች፡፡ስለሆነም እ.ኤ.አ እስከ 2018 ድረስ በኮሚቴነት ትሰራለች ማለት ነው፡፡

  1. የፊቼ-ጫምባላላ በዓል ምንነት

በርካታ የማንነታችን መገለጫ ከሆኑ አኩሪ ባህሎቻችን ውስጥ አንዱ የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል (ፊቼ ጫምባላላ) ነው፡፡ ይህ በዓል በክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ የተሰጠው ትኩረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡


የፊቼ ጫምባላላ በዓል በርካታ ባህላዊ ክንዋኔዎችን በውስጡ የያዘ ነው፡፡ ለአብነትም በዓሉ የሲዳማ ብሔር የአዲስ ዘመን መቀበያ ከመሆኑም ባሻገር በዓሉ ዘመዳሞች የሚገናኙበትና የሚጠያየቁበት፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች የተፈጠሩ አለመግባባቶች ተፈተው እርቅ የሚወርድበት፣ ሀገር በቀል የሆኑ ዕውቀቶች ማለትም ባህላዊ የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት በብሔሩ ባህላዊ ሊቃውንቶች የሚከወንበት፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የሥነ ምህዳር እውቀቶች ለወጣቱ ትውልድ የሚተላለፉበት እንዲሁም ባህላዊ የምግብ አዘገጃጀት የሚከወንበት በዓል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በዓሉ የተለያዩ ሀገረሰባዊ ጭፈራዎች የሚከወንበት በዓል ነው፡፡

  1. የፊቼ ጫምባላላ በዓል የዩኔስኮ ምዝገባ ሂደት

የደ/ብ/ብ/ህ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም የብሔሩ አባላት ያቀረቡትን ጥያቄዎች መሰረት በማድረግ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ከ2005 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ የፊቼ ጫምባላላ ኢንታጀብል ባህላዊ ቅርስ በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የሚያስችሉ የጥናት ሰነዶች ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም ከሲዳማ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና መንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ጋር በቅንጅት ተዘጋጅቷል፡፡ የተዘጋጀውም የኖሚኔሽን ሰነድ መጋቢት 2006 ዓ.ም ለዩኔስኮ እንዲላክ ተደርጓል፡፡ ይህ የኖሚኔሽን ፋይል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቀው ከሰኔ 2006 ዓ.ም ጀምሮ በዩኔስኮ ድህረ ገፅ ላይ ተጭኖ ይገኛል፡፡


በዩኔስኮ ድህረ ገፅ ላይ ተጭኖ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቀው በመደረግ ላይ ያሉት ሰነዶች የሚከተሉት ናቸው፡፡

  1. National Inventory document– የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ በቅርስነት መመዝገቡን የሚያረጋግጥ ሰነድ፤
  2. ICH-02 Nomination Form– ስለ ፊቼ ጫምባላላ ሰፋ ያለ መረጃ የያዘ የኖሚኔሽን ሰነድ፤
  3. Video– ፊቼ ጫምባላላን ለዓለም ሕዝብ ለማስተዋወቅ የ1ዐ ደቂቃ ቪዲዮ፤
  4. Photographs- ፊቼ ጫምባላላን የሚያመለክቱ 10 ፎቶግራፎች፤
  5. Consent of the Community– የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ያለምንም ተጽእኖ ወይም ግፊት በራሳቸው ተነሳሽነት ፊቼ ጫምባላላ በዩኔስኮ እንዲመዘገብላቸው መስማማታቸውን የገለጹበት የጽሑፍ ሰነድና ይህንንም ከስማቸው አኳያ በፊርማቸው ያረጋገጡበትን ሰነድ ያትታል፡፡


ይህ ተጠንቶ የተላከው የኖሚኔሽን ሰነድ  የፊቼ ጫምባላላ  ኢንታጀብል ቅርስ ሰነድ ዩኔስኮ የሚጠይቀውን ሂደት ጠብቆና የተለያዩ የግምገማ መስፈርቶችን አልፎ በዩኔስኮ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት  እ.ኤ.አ ከNovember 30 – December 04/2015 ድረስ በናሚቢያ በሚካሄደው 10ኛው የዩኔስኮ የኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ የኢንተርገቨርንመንታል ኮሚቴ መደበኛ ጉባዔ  ላይ ቀርቧል፡፡ ለምዝገባ ውሳኔ በጉባዔው ላይ 35 የኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች የቀረቡ ሲሆን ከነዚህም አንዱ ፊቼ ጫምባላላ ቅርስ ነበር፡፡ በጉባዔው 23 የኢንታጀብል ቅርሶች እንዲመዘገቡ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ከነዚህም አንዱ ፊቼ ጫምባላላ   ነው፡፡


የፊቼ ጫምባላላ መመዝገብ ሀገራችን ኢትዩጲያ ቀደም ሲል ካስመዘገበቻቸው ዘጠኝ የታንጀብል (ተዳሳሽ) አለም አቀፍ ቅርሶች በተጨማሪ ሁለት የኢንታጀብል ባህላዊ ቅርስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስመዝገብ ችላለች ማለት ነው፡፡