ርግ ቬዳ
ሪግ-ቬዳ (ሳንስክሪት፡= ऋग्वेद /ርግቬዳ/ «የምስጋና ዕውቀት» ) በሂንዱ ሃይማኖት ታሪክ ከሁሉ ጥንታዊ የሆነ እምነት ጽሁፍ ነው። የተቀነባበሩበት ቋንቋ በጣም ጥንታዊ የሳንስክሪት አይነት ሲሆን፣ ይህ ቋንቋ የተነገረው ምናልባት ከ1700-1100 ዓክልበ. ያህል እንደ ሆነ ይታመናል። የጽሕፈት እውቀት (ዴቫናጋሪ ፊደል) ከዚያ በኋላ ወደ ሕንድ የደረሰው ሲሆን፣ ግጥሞቹ በቃል ድምጽ ብቻ ተወርሰው እንደ ታወሱ ይታመናል። በአሥር መጻሕፍት ወይም «መንደላ» ይከፈላሉ፤ ከነዚህም፣ መንደላዎቹ 2-7 ከሁሉ ጥንታዊ እንደ ሆኑ ይታመናል።
ግጥሞቹ ባብዛኛው አርያኖች በዚያን ጊዜ የታመኑባቸው አማልክት ምስጋና መዝሙሮች ናቸው፤ ከነዚህ አማልክት ዋናዎቹ ኢንድራ፣ ሚትራና አግኒ («እሳት») ናቸው። ሌሎች የተፈጥሮ ባሕርዮች እንደ ጣኦታት እራሳቸው ከፍ ከፍ ተደረጉ፦ ቨሩና (ውሃ)፣ ሱርያ (ፀሐይ)፣ ቫዩ (ንፋስ)፣ ድያውስ (ሰማይ)፣ ፕርጢቪ (ምድር) ናቸው። ከነዚህም ጣኦታት፣ የኢንድራ፣ ሚትራ፣ ቨሩና ወዘተ. ስሞች ደግሞ በሚታኒ ጽላቶች (ከ1500-1300 ዓክልበ. ሶርያ አካባቢ) ተገኝተዋል፤ ሚጥራ በተጨማሪ በአቨስታ (የፋርስ ዞራስተር ሃይማኖት መጽሐፍ) ይገኛል። እነዚህ ሁለት ብሔሮች፣ ሚታኒ እና ጥንታዊ ፋርስ፣ በርግ ቬዳ መሠረት ሕንድን ከወረሩት አርያን ወይም ሳንስክሪት ነገዶች ጋራ በቋንቋም ሆነ በእምነት በኩል ቅርብ ዝምድና እንደ ነበራቸው ግልጽ ነው።