Jump to content

የእጅ መድፍ

ከውክፔዲያ
የሞንጎሎች የነሓስ እጅ መድፍ፣ 1280 ዓም ግድም፣ ቻይና

የእጅ መድፍ ከሁሉ ጠብመንጃ አይነቶች አስቀድሞ የተፈጠረው ሲሆን የጠመንጃና የመድፎች ሁሉ አባት ሊባል ይችላል።

መጀመርያው የእጅ መድፍ የተሠራው 1120 ዓ.ም. አካባቢ በቻይና አገር ነበር። ባሩድ በቻይና ተገኝቶ ጥቅሙ እንደ የጦርነት መሣርያ በ1036 ዓም ዉጂንግ ዞንግያው በተባለ ጽሑፍ ተጻፈ። ከዚህም በፊት የእሳት ፍላጻ896 ዓ.ም. ጀምሮ፣ የነበልባል ጦር ከ950 ዓ.ም. ግድም ባሩድን ይጠቅሙ ነበር። «የነበልባል ጦር» እንደ ተራ ጦር ሳይሆን ጥቂት ጠጠሮች በባሩድ ተተኩሰው ጭምር ያቀረበ መሣርያ ነበር።

በ1120 ዓ.ም. የተሳለ በስርቿን የተገኘ የዋሻ ስዕል መጀመርያ የእጅ መድፍ ያሳያል። ለጊዜው ይህ ቴክኒክ የቻይናውያን ምስጢር ብቻ ሆኖ ቆየ። ከ1211 ዓም ጀምሮ ግን ሞንጎሎች በመድፍ እርዳታ ግዛታቸውን ያስፋፉ ጀመር። ሞንጎሎችም በ1233 ዓም በሞሂ ውግያሀንጋሪ መድፎች በአውሮጳውያን ሠራዊት ላይ መጀመርያ ተኮሱ። ዓረቦች ከዚያ ቀጥሎ ምስጢሩን እንዳገኙ ይመስላል፤ በ1252 ዓ.ም በአይን ጃሉት ውግያ በዛሬው እስራኤልማምሉኮችግብጽ በሞንጎሎች ላይ መድፎች እንደ ነበሩዋቸው፤ እንዲሁም በእስፓንያካስቲል ንጉሥ 10ኛው አልፎንሶ1254 ዓም ኒዬብላን ከተማ በሠራዊት ሲከብብ፣ ዓረቦቹ በመድፍ ተከላከሉዋቸው።

መጀመርያዎቹ እጅ መድፎች የተሠሩ ከቀርቀሃ ሲሆን ከ1280 ዓ.ም. ያህል ጀምሮ ከነሓስ ሊሠሩ ጀመር። ባሩድ በበርሚል ገብቶ ድንጋይ ሲጨመር ከዚያም እሳት ሲነካው በበርሚል አቅጣጫ ይፈነዳል። በቅርብ ጊዜ ውስጥ መድፍ በሕንድም ሆነ በጣልያን ይሠራ ጀመር፤ በ1300ዎቹ ውስጥ በመላው አውሮጳና እስያ ተስፋፋ።