Jump to content

የዑር ንጉሣዊ ጨዋታ

ከውክፔዲያ
የብሪታኒያ ቤተ መዘክር ውስጥ የዑር ንጉሣዊ ጨዋታ

«የዑር ንጉሣዊ ጨዋታ» (ወይም በጥንት «የሃያ ሕዋስ ጨዋታ») በሠንጠረዥ የሚጫወት ጥንታዊ ጨዋታ ነው። ቢያንስ ከ2220 እስከ 185 ዓክልበ. ግድም በመካከለኛው ምሥራቅ ይታወቅ ነበር። አሁንም በዘመናዊ ሥነ ቅርስ ውጤት አጨዋወቱ እንደገና ይቻላል።

ጨዋታው ባለ ሃያ ሕዋሳት ገበታ ላይ በዛህራ የሚካሄድ የእሽቅድድም ጨወታ ነው። እንግዲህ ትንሽ እንደ ዘመናዊ ባክጋሞን ይመስላል። ዛህራ ግን የሀረም ቅርጽ አለው። ሁለት ገበታዎች በዑር ንጉሣዊ መቃብሮች መካከል (2220 ዓክልበ. ግድም) ስለ ተገኙ፣ «የዑር ንጉሣዊ ጨወታ» ተብሎ በመታወቅ ሂዷል። በጥንታዊ ግብጽ ደግሞ በፈርዖን ቱታንኻመን መቃበር (1330 ዓክልበ. ግድም) ተገኝቷል። በግብጽም የጨወታው ስም «አሠብ» ይባል ነበር።

ከ1000 ዓክልበ. በኋላ የሠንጠረዡ መንገድ መጨረሻ ቀና ሆነ፣ የህዋሳት ቁጥር ግን ፳ ሆኖ ቀረ። ለምሳሌ በአሦር ንጉሥ 2 ሳርጎን (715 ዓክልበ.. ግድም) ቤተ መንግሥት ውስጥ በተገኘ ሐውልት ላይ እንዲህ አይነት ሠንጠረዥ ተቀርጾ ይታያል።

በ185 ዓክልበ. ግድም በተጻፈ ባቢሎናዊ ጽላት ላይ፣ የጨወታ ደንቦች ይገለጻሉ። ምልክቶቹ በመንገዱ ላይ ስንት ሕዋሶች ወደፊት መራመድ የሚችሉ ዛህራን በመጣል ይወሰናል። በሌላው ተጫዋች ምልክት ላይ ቢጨርስ፣ ያው ምልክት ከገበታው ይወገዳል፣ እንደገና ከመጀመርያ መግባት አለበት። የአበባ ስዕል ባለው ህዋስ ላይ ቢጨርስ ግን፣ ምልክቱ ጸት ይላል፣ ከሌላው ተጫዋች ምልክት ሊወገድ አይችልም። ስለ አጨዋወቱ ዝርዝሮች ግን አሁን ልዩ ልዩ ግምቶች አሉ።

የውጭ መያያዣዎች

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]