Jump to content

ስንዱ ገብሩ

ከውክፔዲያ
ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ
ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ

ወይዘሮ ስንዱ ገብሩየመጀመሪያዋ ሴት የፓርላማ ተመራጭ፣ የጦር አርበኛ፣ ፀሐፊ- ተውኔት፣ ደራሲ፣ የመጀመሪያዋ ሴት ዲፕሎማት የነበሩት እና ሚያዝያ ፲፪ ቀን ፳፻፩ ዓ/ም በ፺፫ ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩን የክብርት ዶክቶር፣ ወይዘሮ ስንዱ ገብሩን ማንነት የሚዘክር “ዝክረ - ስንዱ ገበሬ”፣ በሚል ዝግጅት በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት በኢትየጽያ የሴቶች ማኅበራት ቅንጅት (ኢሴማቅ)፣ ከኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ማኅበር፣ ከኢትዮጵያ ሴት መገናኛ ብዙኀን ማኅበር፣ ከኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበረና፣ ከጾታዊ ጥቃት መከላከያ ማኅበር ጋር በትብብር የተዘጋጀ ዝክር ተከናውኗል።

ልደትና የወጣትነት ዘመናት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ በሸዋ ክፍለ ሀገር በመናገሻ አውራጃ በአዲስ ዓለም ከተማ ጥር ፮ ቀን ፲፱፻፰ ዓ/ም ተወለዱ። አባታቸው ታዋቂው ዲፕሎማት፣ የመጀመሪያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዘደንት፤ ጣሊያኖች ከኢትዮጵያ ከወጡ በኋላ ደግሞ የምክር ቤቱ ፕሬዘደንት የነበሩት በዳግማዊ ምኒልክ ሹመትም የመጀመሪያው የጎንደር ከተማ አስተዳዳሪ የነበሩት ከንቲባ ገብሩ ደስታ ሲሆኑ ታናሽ እህታቸው ደግሞ የውብዳር ገብሩ (አሁን ታዋቂዋ ሙዚቀኛ እማሆይ ጽጌ ማርያም) ናቸው።

ዕድሜያቸው ለትምህርት በደረሰበት ወቅት እቤታቸው አስተማሪ ተቀጥሮላቸው የአማርኛን ትምህረት ከፊደል መቁጠር እስከ ዳዊት መድገም በቤታቸው ተማሩ። ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ሄደው በስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት በመግባት እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምረዋል።

ከንቲባ ገብሩ ወጣቷን ስንዱ ገብሩን እያስከተሉ ወደ ቤተ መንግሥትም ሆነ ሌላ ሥፍራዎች ይወስዷቸው እንደነበረና ከጊዜው አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንንም ጋር እንዳስተዋዋቋቸው ተዘግቧል። አልጋ ወራሹም የወጣቷን ብልህነትና ትጋት በማድነቅ ወደ ፈረንጅ አገር ተልከው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ባዘዙት መሠረት ወይዘሮ ስንዱ በ፲፱፻፳፩ ዓ/ም (ፊታውራሪ አመዴ በ፲፱፻፲፱ ዓ/ም ይላሉ) ወደ ስዊስ ለትምህርት ቢሄዱም ኑሮው ስላልተመቻቸውና ትምህርት ይሰጥበት የነበረውን የጀርመንኛ ቋንቋ ስላልወደዱት ወደ ፈረንሳይ አቅንተው ትምህርታቸውን ቀጠሉ። በመጨረሻም በስዊስ እና በፈረንሳይ ሁለት ትምህርት ቤቶች በመዘዋወር በዲፕሎማ ተመረቁ። እዛው የሕግ ትምህርት ለመቀጠል ጀምረው የነበረ ቢሆንም፤ ፍላጎታቸው ወደ ሥነ-ጽሑፍ በማዘንበሉ በአጠቃላይ ለአምስት ዓመታት እዛው ተምረው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።

ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱም በአዲስ አበባ በቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት ቤት ውስጥ የፈረንሳይኛ ቋንቋን፣ ሀይጅን፣ ቁጥርንና የአማርኛ ድርሰት አጻጻፍን ማስተማር ጀመሩ። በዚህ ሁኔታ አንድ ዓመት እንደቆዩ ለብላታ ሎሬንሶ ታዕዛዝ ተዳሩና ባለቤታቸው የሐረርጌ ክፍለሀገር አስተዳዳሪ ሆነው በመሾማቸው ወደዚያው ከባለቤታቸው ጋር አቀኑ። ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላም ብላታ ሎሬንሶ የፍርድ ቤት ሹምና የዜና ስርጭት ኃላፊ ሆነው በመሾማቸው ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ አብረዋቸው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።

የፋሺስት ኢጣልያ ወረራ ዘመናት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ፋሺስቶች ኢትዮጵያን በወረሩ ጊዜ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወደ እንግሊዝ ሀገር ሲሰደዱ ብላታ ሎሬንሶ ታዕዛዝም አብረው ከጃንሆይ ጋር ሄዱ። ወይዘሮ ስንዱ ግን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እና ሆለታ ውስጥ ከሚገኙ ወደ መቶ የሚጠጉ የጦር መኮንኖች ጋር ተቀላቅለው ፋሺስቶችን ለመፋለም ወደ ቦሬ ሄዱ። እዚያም የመትረየስ አተኳኮስ ትምህርት ተማሩ። ወደ ነቀምት በመሄድም ሕዝብን እየሰበሰቡ ስለ ነፃነት ማስተማሩን ተያያዙት። በዚህ ወቅት በባንዳዎች ጠቋሚነት በፋሽስት እጅ ከመውደቅ ለጥቂት አምልጠው ጎሬ ላይ ከልዑል ራስ እምሩ ጦር ጋር ተቀላቀሉ። ከዚያም በጦርነቱ የሚጎዱ አርበኞችን ለማከም የሚሆን ቀይ መስቀል ለማቋቋም መፈለጋቸውን ለራስ እምሩ አማክረው በተሰጣቸው ፭ መቶ ብር አቋቁመው አርበኞችን መርዳት ጀመሩ። ወዲያው ግን እርሳቸው ተቀላቅለውት የነበረው የጥቁር አንበሳ ጦር ሲመታ በጣልያን ሠራዊት እጅ ተማርከው በእስር ወደ አዲስ አበባ አመጧቸውና የቁም እስረኛ ሆኑ።

የካቲት ፲፪ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ/ም ግራዚያኒን ለመግደል በተደረገው ሙከራ ወንድማቸው መሸሻ ገብሩ አሉበት በመባል ይታሰሱ ስለነበር ወንድማቸውን ከአደጋ ለማዳን ሲሞክሩ በድጋሚ በፋሺስቶች እጅ ወደቁ። በወቅቱ ግራዚያኒ ይኖርበት የነበረው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ውስጥ ታሰሩ። ቀጥሎም ወደ አስመራ፣ ከዚያ ወደ ምጽዋ ተወሰዱ። ከምጽዋ ወደብ ሦስት መቶ ወንዶችና ስምንት ሴቶች (እማሆይ ጽጌ ማርያምን ጭምር) ሆነው በመርከብ “አዚናራ” ወደተባለች የኢጣሊያኖች እስር ቤት ተወስደው ዘጠኝ ወራት ታሰሩ።

ከእስር በኋላም ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ በእንደዚህ ያለ ተግባር ላይ እንዳይሰማሩ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም፤ ማስፈራሪያው ሳይበግራቸው አርበኞችን በግጥም፣ በወኔ ቀስቃሽ ጽሑፎች በማበረታታት፣ መረጃ በማቀበል፣ መሣሪያ በማዳረስ የጀግንነት ተግባር ፈጽመዋል።

ከድል በኋላ ወይዘሮ ስንዱ ለሁለት ዓመታት ደሴ ከተማ የሚገኘው የወይዘሮ ስኂን ትምህርት ቤት አስተዳዳሪ በመሆን፣ በኋላም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰውም የእቴጌ መነን ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህርነት፣ ከዚያም የመጀመሪያዋ ሴት ርዕሰ መምህር ሆነው አገልግለዋል። በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት በነበሩበት ወቅት፤ “ኮከብ ያለው ያበራል ገና”፣ “የየካቲት ቀኖች”፣ “የኑሮ ስህተት” የሚሉ ትያትሮችን ሠርተው አቅርበዋል።

የመጀመሪያዋ ሴት የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባል

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

፲፱፻፵፰ ዓ/ም እስከ ፲፱፻፶፪ ዓ/ም ድረስ የመጀመሪያዋ የሴት የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባልና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል ሊቀ መንበር ሆነው አገልግለዋል። በዚህ ምክር ቤት አባል በነበሩበት ጊዜ ብቸኛዋ ሴት ከመሆናቸውም ባሻገር የሴቶች እኩልነት በማይከበርበት ጊዜ እና “የወንድ ዓለም” በገነነበት የታሪክ ምዕራፍ የሴቶችን ሰብዓዊ መብት ለማስከበርና እኩልነትን በሕግ ለማስተማመን ብዙ የታገሉ ሴት ነበሩ። ስለዚህ ጊዜ ሁኔታዎች ምስክርነት ከሰጡት በከፊሉ፦

“… የቤተሰብ ሕጉ በእርሳቸው ጊዜ ሲወጣ፣ የመኖሪያ ስፍራ የመምረጥን መብት በተመለከተ ለባል የተሰጠውን መብት ተከራክረው ተቀባይነት ቢያጡም የፍትሕ ብሔር ሕጉ ላይ ሴቶች ባገቡት ወንድ ስም ይጠሩ የሚለውን በመቃወም እንዳይፀድቅ ያደረጉና ያስቀየሩ ሴት ስለሆኑ ቀዳማይት ታጋይ እላቸዋለሁ። …”

ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ፤ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ።

“… የተፈጠሩበትን ዘመን፣ ሁኔታና አካባቢ አልፈው ዓላማቸውን ያሳኩ አንቱ ለተባለላቸው የአገልግሎቶችና የሥራ አይነቶች ከውጊያ እስከ ውሳኔ ሰጪነት በመቀመጥ ፈር ቀዳጅ ናቸው። በተቀመጡበት ሥልጣንም፣ ለተነሱበት ዓላማ ለሴቶች የእኩልነት ጥያቄ የከፈሉት አስተዋጽኦና ተግባራት በታሪክ የዘመኑ ታላቅ ሰው ያደርጋቸዋል …”

ወይዘሮ ሳባ ገብረ መድኅን፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ዳይሬክተር።

እራሳቸውም በጊዜው የዚሁ ሸንጎ አባል የነበሩት ፊታውራሪ አመዴ ለማ ደግሞ ስለዚህ ጉዳይ ትዝታቸውን ሲያካፍሉን፦

“የፍተሐ ብሔሩ ሕግ ቀርቦ ስንከራከር፣ ምን ይላል ፍትሐ ብሔር ውስጥ ያን ጊዜ ሲወጣ፣ ‘የቤቱ ሹም ባል ይሆናል። ሚስት ለባሏ ታዛዥ መሆን አለባት። እንዲህ እንዲህ የሚል ሴቶችን የሚጫኑ አንቀጾች አሉ። ይሄንን ወይዘሮ ስንዱ የዚያን ጊዜ ቀደም ብለው የነቁ ስለነበረ “እንዴ! ለምን አንድ ጊዜ እኛን ንጉሠ ነገሥቱ እኩል ናችሁ ካሉን በኋላ በእራሳችን ስምምነት እንጂ በሕግ ሴቶችን የሚጨቁን ሕግ መግባት የለበትም” ብለው ተከራከሩ። እሺ ድምጽ ይሰጥበት ሲባል አንድ ሰው ብቻ ደገፋቸው። ተናደዱ። “እናንተ እዚህ ምክር ቤት የመጣችሁ ወንዶች፤ ስትመረጡ ሴትና ወንደ ነበር የመረጣችሁ፣ ግን ልትመክሩ የመጣችሁት ለወንዶች እንጂ ለሴቶች እንዳልሆነ ታዝቤአችኋለሁ። ይህ ዛሬ እናንተ የሰጣችሁት ውሳኔ፣ ከአንድ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ብዙ ሴቶች ገብተው ይገለብጡታል እና ዘለቄታ የለውም።”

ብለው ተናደው ይሄን ተናግረው ወጡ። ይላሉ

ሌላው የዚህ ሸንጎ አባልና ለብዙ ዘመናት የወይዘሮ ስንዱ ጓደና የነበሩት አቶ ጠንክር ተድላ፦ ሴቶችን በተመለከተ ጉዳይ ባል ከሚስቱ እውቀት ውጭ ከ አምሥት መቶ ብር በላይ እንዳይበደር የሚል ሃሣብ አቅርበው በጋለ ስሜት እንደተከራከሩና ውጤቱም ይህ ቁም ነገር ሕግ ለመሆን የበቃ መሆኑን ይመሰክራሉ።

ሌላው ብዙ የተሟገቱበትና ውጤታማ የሆኑበት ጉዳይ በጊዜው ቀርቦ የነበረው ‘እንደ ፈረንጆች’ ተለምዶ የኢትዮጵያም ሴቶች ባል ሲያገቡ የባላቸውን አባት ስም እንዲጠቀሙበት የሚል ያልተሳካ የሕግ ረቂቅ ነበር።

ሌላ አስተዋጽዖዎች

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበር ፕሬዝዳንት፣ የሕዝባዊ ኑሮ እድገት ዋና ፀሐፊነትና አስተዳዳሪነት፣ በምዕራብ ጀርመን ለሦስት ዓመት የትምህርት አታሼ በመሆን አገልግለዋል። ወይዘሮ ስንዱ ከአሥር በላይ የግጥምና ልብ ወለድ መጻሕፍት የጻፉ ሲሆኑ ሠላሳ ሁለት ጽሑፎቻቸው በ[[አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ] ይገኛሉ።

የድርሰት ሥራዎች

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]
  • ኮከብህ ያውና ያበራል ገና
  • በግራዚያኒ ጊዜ የየካቲት ቀኖች (፲፱፻፵፯ ዓ/ም)
  • የታደለች ህልም (፲፱፻፵፰ ዓ/ም)
  • ርእስ የሌለው ትዳር (፲፱፻፵፰ ዓ/ም)
  • የኔሮ ስህተት (፲፱፻፵፰ ዓ/ም)
  • ከማይጨው መልስ (፲፱፻፵፱ ዓ/ም)
  • ፊታውራሪ ረታ አዳሙ (፲፱፻፵፱ ዓ/ም)


የመጀመሪያዋ የሴት ፓርላማ አባል፣ የሴት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ ጀግናና ፀረ-ፋሺስት አርበኛ፣ ፀሐፊ ተውኔት፣የመጽሐፍ ደራሲ፣ እና የመጀመሪያዋ የሴት ዲፕሎማት ስንዱ ገብሩ (የክቡር ዶክተር) ሰኞ ሚያዝያ ፲፪ ቀን ፳፻፩ ዓ/ም በተወለዱ በ ፺፫ ዓመታቸው ሕይወታቸው አልፎ በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተቀብረዋል።

ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ ላበረከቷቸው አስተዋጽዖዎች የወርቅ ሜዳሊያ፣ የንግሥት ሣባ የወርቅ ኒሻን፣ የቀይ መስቀል የወርቅ ሜዳሊያ እና በኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ዘመን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተሰጥቷቸዋል።

  • Ethiopia Zare (ሰኞ ግንቦት 3 ቀን 2001 ዓ.ም. May 11, 2009)
  • [1] Archived ሴፕቴምበር 29, 2007 at the Wayback Machine «History of Ethiopian Theater» በዮናስ ኃይለ መስቀል. ፌብሩዋሪ 20 ቀን 2007 ታይቷል።