የሂንዱ ሃይማኖት
የሂንዱ ሃይማኖት ወይም ሂንዱኢዝም የሕንድ አገር ዋና ሃይማኖት ነው። እስከ 1998 ዓ.ም. ድረስ በይፋ በኔፓል የመንግሥት ሃይማኖት ሆኖ ነበር።
የሂንዱ ሃይማኖት መንስኤ በ1500 አክልበ. ገደማ ወደ ሕንድ የወረሩት አርያኖች ነገዶች ያመኑበት በርግ ቬዳ የተገለጸው «ቬዲክ ሃይማኖት» ነበር። ይህ ቬዲክ ሃይማኖት ከኗሪዎቹ ከድራቪዲያን ብሔሮች እምነቶች ጋራ ሲቀላቀል አንድላይ የሂንዱ ሃይማኖት ሠርተዋል። ከዚህ የተነሣ ሁለቱ ጥንታዊ ልሳናታቸው ሳንስክሪትና ታሚልኛ አንድላይ እንደ ቅዱሳን ወይም እንደ አማልክት ቋንቋዎች ይቆጠራሉ።
ሆኖም የሂንዱኢዝም ታሪክ ብዙ ተቃራኒ ፈሳሾች ያሉበት ወንዝ ይመስላል፤ በዚህም ወንዝ ውስጥ በብዙ ተቃራኒ ጣኦታት አማልክት የሚያምኑ ፈሳሾች አሉ፣ አማልክት ሁሉ የአንድያው ፈጣሪ አካላት ብቻ ናቸው የሚሉም ፈሳሾች፣ ምንም ነፍስ ወይም መንፈስ መኖሩን የሚክዱም ፈሳሾች ደግሞ ተገኝተዋል። በዛሬውኑ ሂንዱኢዝም በአማልክት አከፋፈል ረገድ አራት ዋና ክፍሎቹ ቫይሽናቪስም፣ ሻይቪስም፣ ሻክቲስምና ስማርቲስም ይባላሉ። በነዚህም ሁሉ ውስጥ አያሌ ጥቃቅን ንዑስ-ክፍሎች በልዩ ልዩ ትምህርቶች ይመደባሉ። ከዚህም በቀር በፍልስፍናዎች ረገድ ስድስት ዋና ዋና የሂንዱኢዝም ፍልስፍናዎች አሉ፣ እነርሱም ሳምኽያ፣ ዮጋ፣ ኛየ፣ ቫይሸሺካ፣ ሚማምሳ፣ እና ቨዳንታ ይባላሉ። ከ፮ቱ ዋና ፍልስፍናዎች ውጭ ደግሞ እጅግ ብዙ ልዩ ልዩ ተቃራኒ ፍልስፍናዎችና ትምህርቶች ተነስተዋል፤ ከነዚህም መካከል ሁለቱ ቡዲስምና ጃይኒስም ለየራሳቸው እንደ ተለዩ ሃይማኖቶች ተቆጥረዋል።
ከ700 ዓክልበ. ግድም ጀምሮ የሰምሳረ ትምህርት በሕንድ አገር በሰፊ ተቀበለ፤ እነዚህስ እምነቶች ሁሉ በሰምሳረ (ተመላሽ-ትስብዕት) ያምናሉ። እንደ «አብርሃማዊ ሃይማኖቶች» (በተለይ አይሁድና፣ ክርስትና፣ እስልምና) በሙታን ትንሳኤ ለፍርድ ቀን የሚያስተምሩ ሳይሆን፣ «ሰምሳረ» ማለት በእምነታቸው ከመሞት በኋላ ሕያዋን ዳግመኛ ከማሕጸን በተመላሽ ትስብዕት በመታየታቸው የሚሉ ናቸው። ይህን ትምህርት መጀመርያው የገለጸው ፈላስፋ ያጅኘቨልክየ የተባለው እንደ ነበር ይመስላል። በሂንዱኢዝም ደግሞ ኅብረተሠብ በአራት አጠቃላይ ወራሽ መደባት ወይም «ቫርናዎች» ይከፈላል፤ እነርሱም ብራህሚን (ቄሳውንትና አስተማሮች)፣ ክሻትሪያ (ወታደሮችና ገዢዎች፣ ገበሬዎች)፤ ቫይስያ (ነጋዴዎች)ና ሹድራ (ሠራተኞች፣ አገልጋዮች) ናቸው።