Jump to content

መሐሙድ አህመድ

ከውክፔዲያ
(ከመሃሙድ አህመድ የተዛወረ)

ማህሙድ አህመድ፣ ኢትዮጵያዊ ዘፋኝ።

ማህሙድ አህመድ እና የሙዚቃ ህይወቱ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የተወለደው ሚያዚያ 30, በ1933 ዓ.ም. አዲስ አበባ መርካቶ በአሜሪካን ግቢ አካባቢ ነው፡፡ ሥራንም ሆነ ሕይወትን በራሱ መጋፈጥ የጀመረው ገና በሕፃንነቱ ነው፡፡ አባቱ በሚሠራበት ግሪክ ክለብ አብሮ በመሔድ ቅርጫት ኳስና የቴኒስ ሜዳዎቹ ላይ ይሠራም ነበር፡፡ በስድስት ዓመቱም ሊስትሮ ሆኖ መሥራት ጀመረ፡፡ በትምህርት ቤት ቆይታው ብዙ ጐበዝ እንዳልነበር ፈገግ ብሎ የሚያወራው ማህሙድ ቤተሰቦቹንና ራሱን መርዳት እንዳለበትም የተረዳው ገና በሕፃንነቱ ነው፡፡

የሙዚቃ ሕይወቱ ሀ ብሎ የተጀመረው አንድ ክለብ ውስጥ ሳንድዊች እንዲያቀርብ በተቀጠረበት ጊዜ ነው፡፡ እንደ አጋጣሚም ሆኖ በዚያው ክለብ ውስጥ ጥላሁን ገሠሠ ይዘፍንበት የነበረ ቦታ ነበር፡፡

በአንድ አጋጣሚም ሁሉም ድምፃውያን ወደ ድሬዳዋ ሔደው ሙዚቀኞቹ ያለ ድምፃዊ እየተለማመዱ ነበር፡፡ የተፈራ ካሣን ‹‹አልጠላሽም ከቶ››ን የተዘራን ‹‹ይሔም አለ ለካ››ንና የጥላሁን ዘፈን እየተለማመዱ ነበር፡፡ በድምፅ መዝፈን እንደሚፈልግም ጠየቃቸው፡፡

‹‹በጣም ቀጭን ነበርኩ እናም ‘ትችያለሽ? ወይ›› ብለው ጠየቁኝ፣ እናም እሞክራለሁ አልኩ›› በማለት ማህሙድ ይናገራል፡፡ ‹‹አልጠላሽም ከቶ›› የሚለውን ዘፈን በሚዘፍንበት ሰዓት የኮንጐ ዘማቾች በቦታው ነበሩ እናም አስደነቃቸው፡፡ እንደገናም እንዲዘፍን ተጠየቀ፡፡ የክለቡ ባለቤት በቦታው የነበረ ሲሆን አድናቆት በተሞላ ድምፅም ‹‹የአላህ ያለህ በጣም ጥሩ መዝፈን ትችላለህ!›› እንዳለው ማህሙድ ያስታውሳል በዚህም አጋጣሚ ከአስተናጋጅነት ወደ ዘፋኝነት ተቀየረ፡፡ የቤቱ ባለቤትም ሙሉ ልብስ ገዛለት፡፡


ጥላሁንና ሌሎቹ ዘፋኞች በተመለሱበት ወቅት የእሱ መዝፈን በጣም ነው ያስገረማቸው፤ የግጥም ደብተርም ሰጡት፡፡ መዝፈን በጀመረበት ወቅት የተለያዩ ዘፋኞችን ሙዚቃ በመዝፈን ነበር፡፡ በዚህም ክለብ ነበር ‹‹አላወቅሽልኝም›› የሚለው የመጀመሪያው ዘፈኑ የሆነው ግጥም የተሰጠው፡፡ ክብር ዘበኛ መቀጠር ፍላጐቱ የነበረ ሲሆን መጀመሪያ ግን ፖሊስ ኦርኬስትራና ምድር ጦር ለመቀጠር ጠየቀ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶችም እንደማይቀጥሩት ነገሩት፡፡ መቶ አለቃ ግርማ ሐድጉም (በኋላ ሻለቃ) ክብር ዘበኛ መቀጠር ይፈልግ እንደሆነ ጠየቁት፣ እሱም ተስማማ ከመቀጠሩ በፊት ግን በሕዝብ ፊት ዘፍኖ ማለፍ ነበረበት፡፡ የዚያን ጊዜ የነበረውን እያንዳንዷን ጥቃቅን ነገር በጥልቅ ያስታውሳል፤ የታምራት ሞላን ‹‹ተስፋ አትቁረጪ›› እንዲሁም ‹‹አላወቅሺልኝም››ን ሲዘፍን የተመልካቹ መልስ ለየት ያለ ነበር፡፡

‹‹የኤልቪስ ፕሪስሊን ዳንስም እየደነስኩ ነበር፣ እናም የተመልካቹ መልስ የማይታመን ነበር፤›› በማለት ማህሙድ ይገልጻል፡፡

መቶ አለቃ ግርማም ወታደር ሆኖ እንዳይቀጠር መከሩት፣ የክብር ዘበኛ ሰዎችም በወታደርነትና ሙዚቀኝነት 120 ብር እንክፈልህ ብለው ጠየቁት፡፡ እሱ ግን ባለመስማማቱም በሙዚቀኝነት ብቻ በ1955 ዓ.ም. አካባቢ ተቀጠረ፡፡ ለአሥራ አንድ ዓመታትም ያህልም በዚህ ቦታ ሠርቷል፡፡

‹‹ለዚህ ያበቃኝ፣ የማውቀውን ነገር ሁሉ ያስተማረኝ ለእኔ ወንድሜ ጥላሁን ገሠሠ ነው፡፡ ሌሎችም ሙዚቀኞች እንዲሁ በእኔ ላይ አሻራ ጥለዋል፤›› ይላል ማህሙድ፡፡

በዚያን ወቅት ሙዚቀኞች አንድ ላይ ይሰባሰቡበት የነበሩ ብዙ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ክብር ዘበኛ ይሠራ በነበረበት ወቅት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ይደረግ የነበረው የሙዚቀኞች ውድድር አንዱ ነው፡፡

የተለያዩ ባንዶች እንደ ምድር ጦር፣ ክብር ዘበኛና የፖሊስ ኦርኬስትራ ባንዶች ከድምፃውያኖቻቸው ጋር ይመጣሉ፡፡ እያንዳንዱም ድምፃዊ አንድ ወይም ሁለት ዘፈን ይዘፍናል፡፡ ይሔም ለሙዚቀኞች ጥሩ አጋጣሚ እንደነበር ይናገራል፡፡ ከአሥራ አንድ ዓመታት ቆይታም በኋላ በተለያዩ ክለቦች መሥራት ጀመረ፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የነበረው ያገኘው የነበረው 60 ብር አምስት እህቶቹና ወንድሞቹ በአጠቃላይ ቤተሰቦቹን መደገፍ አልቻለም፡፡

በወቅቱ አባቱ ሥራ ያልነበራቸው ሲሆን እናቱ ብቻ ነበረች የምትሠራው፤ መጨረሻ ላይ ከክብር ዘበኛ በለቀቀበት ወቅት ደመወዙ 250 ብር ደርሶ ነበር፤ ከዚያም ከአይቤክስ ባንድ ጋር ተጠቃልሎ ራስ ሆቴል ተቀጥሮ መሥራት ጀመረ፡፡

በሙዚቃ ሕይወቱ ውስጥ ብዙ ውጣ ውረዶችን እንዳሳለፈ የሚናገረው ማህሙድ ዘመኑ ለሙዚቀኞችም ሆነ ለሙዚቃ ዕድገት የተመቻቸ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ እንደሚናገረው ከሆነ ይሔ ዕድገትም የተገኘውና እዚህ መድረስ የተቻለው በዱሮ ሙዚቀኞች መስዋዕትነት ነው፡፡

‹‹እነዚህ ሙዚቀኞች አሻራቸውን ጥለው ማለፍ ችለዋል፤›› የሚለው ማህሙድ በዚያን ጊዜ የነበሩት ሙዚቀኞች ምንም እንኳን ችሎታው ቢኖራቸውም የሙዚቃ ትምህርት ቤት አልሔዱም፡፡ የዚያን ጊዜውንም በማስታወስ ለሙዚቀኞች እንዴት ከባድ እንደነበር ይናገራል፡፡ ሙያውም እንዴት ይናቅ እንደነበርም ያስታውሳል፡፡

በ1963 ከአይቤክስ ባንድ ጋር ራስ ሆቴል በሚሠራበት ወቅት ‹‹ኩሉን ማን ኳለሽ››፣ ‹‹አምባሰል››፣ ‹‹ችቦ አይሞላም ወገቧ›› እና ‹‹አልማዝ ምን ዕዳ ነው›› የመሳሰሉ ዘፈኖችን ይዘፍን ነበር፡፡ እነዚህ ዘፈኖች ከአንዳንድ ወገኖች ከፍተኛ ትችትም አጋጠመው፡፡ የዱሮ ዘፈኖችን በአዲስ መልክ ትጫወታለህ ለማለት አንድ ጋዜጠኛ ‹‹ፍራሽ አዳሽ›› ብሎ የጠራውን አጋጣሚም አሁንም አይረሳውም፡፡

‹‹አላዘንኩም፡፡ የዱሮ ዘፈኖችን አዲስ ሕይወት በመስጠት ዘፍኛለሁ፡፡ ፍራሽም እንደ አዲስ ሲታደስ ይተኛበታል›› ይላል፡፡ ማህሙድ ከዚህም በተጨማሪ ‹‹ዓባይ ማዶ››፣ ‹‹ደኑን ጥሰሽ›› እና ‹‹የት ነበርሽ›› የሚሉት ዘፈኖቹም የተለየ ርዕዮተ ዓለም ያስተላልፋሉ በሚልም ተወቅሶ ነበር፡፡

ማህሙድ አህመድ እና አለም አቀፍ እውቅና

በሚያዚያ ወር 1976 አ.ም የፈረንሳይ የቴአትር ቡድን አባላት በመላው አፍሪካ በሚገኙ የፈረንሳይ የባህል ማእከላት እየተዘዋወሩ የተለያዩ ትርኢቶችን ያቀርቡ ነበር:: በዚህ ወቅት ነበር የፍራንሲስ ፋልሴቶ የቅርብ ወዳጅ የነበረ አንድ ፈረንሳያዊ ከቴአትር ቡድኑ ጋር በስቴጅ ማናጀርነት ወደ አዲስ አበባ የመጣው:: ይህ የፍራንሲስ ወዳጅ ታዲያ በአዲስ አበባ ጎዳና ሲዘዋወር የመሃሙድን ሙዚቃ በጎዳና ላይ ይሰማና ይወደዋል:: በጊዜው ደግሞ ፍራንሲስ ፋልሴቶ እና ጉዋደኞቹ ከመላው አለም የተለያዩ ሙዚቃዎችን በመሰብሰብ አብረው ማዳመጥ፣ መወያየት እና ፉክክር ያደርጉ ነበር:: ይህ ፈረንሳያዊ የመድረክ ባለሙያ ታዲያ የመሃሙድን ሙዚቃ እንደሰማ ወዲያው ወደሙዚቃ ቤቱ ይገባና ሸክላውን በመግዛት ወደ ፈረንሳይ ሲመለስ ለፍራንሲስ ይሰጠዋል:: ፍራንሲስም ከወዳጆቹ ጋር ሙዚቃውን መስማት ይጀምርና እጅግ በጣም የተለየና በጣም አዲስ አይነት ሙዚቃ ይሆንበታል:: ወዲያውም ያንን ሙዚቃ በበርካታ ካሴቶች ይቀዳና ለሚያውቃቸው የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጆች ዲጄዎች እና ሙዚቃ ተንታኞች ይልክላቸዋል:: በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናቶች ታዲያ ከሁሉም ያገኘው ምላሽ እጅግ የሚያስደንቅ ነበር:: ከየት ይህን ሙዚቃ እንዳመጣውና እጅግ በጣም እንደወደዱት እንዲያ ያለ ሙዚቃም ሰምተው እንደማያውቁ ይገልፁለታል:: በእንዲህ ያለ ሁኔታ ነበር ከመሃሙድ ጋር ለመስራት የወሰነው:: ይህ በሆነ በወሩ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ማህሙድን ፈልጎ በማግኘት በርካታ ስራዎችን ሊሰሩ ችለዋል:: ይህ አጋጣሚ ነበር እንግዲህ ኢትዮጲክስ የተሰኙትን እነዚህን 30 አልበሞች እንዲደመጡ ምክንያት የሆነው:: ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ሙዚቃን ያሳተመው የውጪ ሃገር አሳታሚ ክሬመርስ የተባለው የቤልጂየም ሬከርድ ሌብል የመሃሙድን 2 ዘፈኖች የያዘ ኤልፒ (LP) በ1976 አ.ም አካባቢ አሳተመ። በወቅቱ ይህ ሬከርድ በጣም ጥሩ የሚዲያ ዳሰሳዎችንም አግኝቶ ነበር:: (ኒዮርክ ታይምስን ጨምሮ) የአለም ምርጥ 10 ወርልድ ሚውዚክ ቻርት ውስጥም ለመግባት ችሎ ነበር:: ይህ ማለት እንግዲህ ከፍራንሲስ ፋልሴቶ በፊት መሆኑ ነው:: ነገር ግን በአልበም ደረጃ እንጂ አለም አቀፍ መድረኮች ላይ በመጫወት እና በመላው አለም ሙዚቃዎቹ ተደማጭነት እንዲያገኙ ያደረገው ፍራንሲስ ፋልሴቶ ነው::