መሐሙድ አህመድ

ከውክፔዲያ
Jump to navigation Jump to search
መሐሙድ አህመድ

መሐሙድ አህመድ (፲፱፻፴፫ ዓ.ም. ተወለደ[1]) ታዋቂ ኢትዮጵያዊ ዘፋኝ ሲሆን ብዙ ዘመናዊ የሙዚቃ ስራወችን በማቅረብ ይታወቃል። መሐሙድ በድምፁ ታላቅነት በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካና በአውሮፓ ትልቅ ክብርና ዝና ያለው አርቲስት ነው።[1]

የህይወት ታሪክ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

መሐሙድ አህመድ በአዲስ አበባ ከተማ አሜሪካን ግቢ (መርካቶ) በ፲፱፻፴፫ ዓ.ም. ተወለደ። በየዓመቱ በሚመጣው የቡሄ ጨዋታ ላይ የድምፁን ምንነት ያሳወቀው መሐሙድ በወቅቱ እነ ጥላሁን ገሠሠ የሚያሰሙትን ዘፈን በሚማርበት የአርበኞች ት/ቤት ውስጥ ሲዘፍን የሰሙት አስተማሪው ድምፁን ስለወደዱለትና በየዓመቱ በሚከበረው የወላጆች ቀንም ይዘፍን ስለነበር ወደ ሙዚቃው ዓለም በዚሁ የተነሳ ለመግባት ችሏል።[1]

እነ ጥላሁን ገሠሠ፣ ታምራት ሞላተዘራ ኃ/ሚካኤል እና ሌሎችም በሚጫወቱበት አሪዞና በሚባል የምሽት ክበብ ውስጥ በሌላ ሥራ ተቀጥሮ ይሠራ ስለነበር የእነዚህን አንጋፋ ዘፋኞች ሙዚቃ በማጥናትና በመዝፈን ይጫወት ስለነበር የዘፈን ችሎታውን ያዩት ግብፃዊ የምሽት ክበቡ ባለቤት አበረታትተውት እነ ጥላሁንን በማጀብ እንዲሠራ ፈቀዱለት። ሻለቃ ግርማ ሀድጉ ግጥምና ዜማ ፈልገው አውጥተውለት የመጀመሪያውን «ጭቅጭቁ ቀርቶ» የሚለውን ዘፈን ዘፈነ።[1]

ከዚያም አሪዞና ሲዘጋ ሾፌሮች ቡና ቤት ወደ ሚባለው የምሽት ክበብ በመሄድ የነ ገላን ተሰማና የታምራት ሞላን ዘፈኖች ሲጫወት ለመቀጠር እንዲችል በአዳራሹ ውስጥ ለተሰበሰበው ሕዝብ ለፍርድ ይቀርባል። በዚህን ጊዜ «ተስፋ አትቁረጪ» እና «የቡጊ ጨዋታ» የተባሉትን ዘፈኖች ደጋግሞ ተጫውቶ ለመቀጠር ቻለ። በተመሳሳይ ሁኔታም ጃንሜዳ በሚገኘው የክብር ዘበኛ የሠራዊቱ ሆስፒታል ውስጥ ለሠራዊቱና ለቤተሰቦቻቸው በየ፲፭ ቀናት የሙዚቃ ትርኢት ስለሚቀርብ ከዚያም ለድጋሚ ፈተና ቀርቦ በ፲፱፻፶፭ ዓ.ም. በሲቪልነት ተቀጠረ። መሐሙድ ካለፈባቸው የችግር ሕይወት በተጨማሪ የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ትልቁ ት/ቤቱ እንደነበረም ይናገራል።[1]

የሥራዎች ዝርዝር[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የመሀሙድ የመጀመሪያ ዘፈኑም «አላወቅሽልኝም» የተባለው የጉሮሮው መክፈቻ ሲሆን «ጠይቀሽ ተረጂ» እና «የፍቅር አዳራሽ» የተባሉት ዘፈኖቹም ለመድረክ ከመቅረባቸው በፊት ለግሩንዲንግ ተሽጠው በቴፕ የተቀረፁ ሥራዎቹ ነበሩ።[1]

በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ አሻራቸውን መጣል ከቻሉ ስመ ጥሩ ዘፋኞች ውስጥ አንዱ ማህሙድ አህመድ ነው፡፡

በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተወዳጅነትን፣ ተደናቂነትን፣ ተፈቃሪነትን ማትረፍ የቻለ ፈርጥ እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ፡፡ ሙሉ ሕይወቱን በሙዚቃ ያሳለፈው ማህሙድ በሙዚቃው ይተነፍሳል፣ ይናገራል፣ ሰውን ያዝናናል፡፡ ከአርባ ዓመታት በላይ በቆየውም የሙዚቃ ሕይወቱ የተለያዩ ትውልድን በሙዚቃው አንድ ላይ ማምጣት የቻለ ትልቅ አርቲስት ነው፡፡ በተለያዩ ኮንሠርቶች በሚዘፍንበትም ወቅት በተለያዩ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች ብሔራዊ መዝሙር በሚመስል መልኩ አብረውት በመዝፈንም በዘፈኑ አንድነትን ያሳያሉ፡፡

ማህሙድ የዝና ጣራ ላይ መድረስ ችሏል፡፡ በሕዝቡ ዘንድ ከመወደዱና ከመፈቀሩ በተጨማሪ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይም ዝናው ናኝቷል፡፡ የሰዎችን ልብ ከማሸነፉ በተጨማሪ ከኮንሠርቱ በፊት ቲኬቶቹ ተሸጦ የሚያልቅበት አጋጣሚም ተደጋጋሚም ነው፡፡ የተለያዩ ሽልማቶችንም ለማሸነፍም ችሏል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የቢቢሲ ወርልድ ሚዩዚክ አዋርድ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ምንም እንኳን ይሔን ያህል የጣራ ዝና ላይ ቢሆንም ትሁት፣ ሰዎችን የሚያከብርና በቀላሉም የሚግባባ ሰው ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ነበር የሰላም ዓለም አቀፍ ሙዚቃ ፌስቲቫል አካል ሆኖ ከያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋር ሙዚቃ ሕይወቱን ያካፈለው፡፡ አዳራሹ በተማሪዎች ተሞልቶ የነበረ ሲሆን ለብዙዎች ማህሙድን ማየት ትልቅ ነገር ነው፡፡ በተለይም በአካል ተገኝቶ ከእነርሱ ጋር ማውራቱ እንደ ዕድልም ነው ያዩት፡፡ በሚያስደንቅ ሁኔታ ግን ማህሙድ በስሜት ተሞልቶ ከተማሪዎቹ በላይ ያለቀሰበት ሁኔታ ታይቷል፡፡ በሳግ በተቆራረጠ ድምፅም እዚህ ቦታ ላይ መገኘቱ ለእሱ ልዩ እንደሆነም ተናግሯል፡፡

‹‹ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ከተማሪዎች ጋር ስለሙዚቃ ሕይወቴ ሳወራ፤ ዛሬ ብሞትም ምንም አይመስለኝም፡፡ በጣም ዕድለኛ ነኝ፡፡ እግዚአብሔርም በሕይወት ያቆየኝ ለዚህ ይመስለኛል፤›› ብሏል፡፡

ማህሙድ ከልጅነቱ ጀምሮ ያጋጠመውን ውጣ ውረድ በማስታወስ አሁን ያለበትን ደረጃም እግዚአብሔርን በማመስገን ተናግሯል፡፡

የተወለደው በ1933 ዓ.ም. አዲስ አበባ በአሜሪካን ግቢ አካባቢ ነው፡፡ ሥራንም ሆነ ሕይወትን በራሱ መጋፈጥ የጀመረው ገና በሕፃንነቱ ነው፡፡ አባቱ በሚሠራበት ግሪክ ክለብ አብሮ በመሔድ ቅርጫት ኳስና የቴኒስ ሜዳዎቹ ላይ ይሠራም ነበር፡፡ በስድስት ዓመቱም ሊስትሮ ሆኖ መሥራት ጀመረ፡፡ በትምህርት ቤት ቆይታው ብዙ ጐበዝ እንዳልነበር ፈገግ ብሎ የሚያወራው ማህሙድ ቤተሰቦቹንና ራሱን መርዳት እንዳለበትም የተረዳው ገና በሕፃንነቱ ነው፡፡

የሙዚቃ ሕይወቱ ሀ ብሎ የተጀመረው አንድ ክለብ ውስጥ ሳንድዊች እንዲያቀርብ በተቀጠረበት ጊዜ ነው፡፡ እንደ አጋጣሚም ሆኖ በዚያው ክለብ ውስጥ ጥላሁን ገሠሠ ይዘፍንበት የነበረ ቦታ ነበር፡፡

በአንድ አጋጣሚም ሁሉም ድምፃውያን ወደ ድሬዳዋ ሔደው ሙዚቀኞቹ ያለ ድምፃዊ እየተለማመዱ ነበር፡፡ የተፈራ ካሣን ‹‹አልጠላሽም ከቶ››ን የተዘራን ‹‹ይሔም አለ ለካ››ንና የጥላሁን ዘፈን እየተለማመዱ ነበር፡፡ በድምፅ መዝፈን እንደሚፈልግም ጠየቃቸው፡፡

‹‹በጣም ቀጭን ነበርኩ እናም ‘ትችያለሽ? ወይ›› ብለው ጠየቁኝ፣ እናም እሞክራለሁ አልኩ›› በማለት ማህሙድ ይናገራል፡፡ ‹‹አልጠላሽም ከቶ›› የሚለውን ዘፈን በሚዘፍንበት ሰዓት የኮንጐ ዘማቾች በቦታው ነበሩ እናም አስደነቃቸው፡፡ እንደገናም እንዲዘፍን ተጠየቀ፡፡ የክለቡ ባለቤት በቦታው የነበረ ሲሆን አድናቆት በተሞላ ድምፅም ‹‹የአላህ ያለ መዝፈን ትችላለህ!›› እንዳለው ማህሙድ ያስታውሳል በዚህም አጋጣሚ ከአስተናጋጅነት ወደ ዘፋኝነት ተቀየረ፡፡ የቤቱ ባለቤትም ሙሉ ልብስ ገዛለት፡፡

ጥላሁንና ሌሎቹ ዘፋኞች በተመለሱበት ወቅት የእሱ መዝፈን በጣም ነው ያስገረማቸው፤ የግጥም ደብተርም ሰጡት፡፡ መዝፈን በጀመረበት ወቅት የተለያዩ ዘፋኞችን ሙዚቃ በመዝፈን ነበር፡፡ በዚህም ክለብ ነበር ‹‹አላወቅሽልኝም›› የሚለው የመጀመሪያው ዘፈኑ የሆነው ግጥም የተሰጠው፡፡ ክብር ዘበኛ መቀጠር ፍላጐቱ የነበረ ሲሆን መጀመሪያ ግን ፖሊስ ኦርኬስትራና ምድር ጦር ለመቀጠር ጠየቀ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶችም እንደማይቀጥሩት ነገሩት፡፡ መቶ አለቃ ግርማ ሐድጉም (በኋላ ሻለቃ) ክብር ዘበኛ መቀጠር ይፈልግ እንደሆነ ጠየቁት፣ እሱም ተስማማ ከመቀጠሩ በፊት ግን በሕዝብ ፊት ዘፍኖ ማለፍ ነበረበት፡፡ የዚያን ጊዜ የነበረውን እያንዳንዷን ጥቃቅን ነገር በጥልቅ ያስታውሳል፤ የታምራት ሞላን ‹‹ተስፋ አትቁረጪ›› እንዲሁም ‹‹አላወቅሺልኝም››ን ሲዘፍን የተመልካቹ መልስ ለየት ያለ ነበር፡፡

‹‹የኤልቪስ ፕሪስሊን ዳንስም እየደነስኩ ነበር፣ እናም የተመልካቹ መልስ የማይታመን ነበር፤›› በማለት ማህሙድ ይገልጻል፡፡

መቶ አለቃ ግርማም ወታደር ሆኖ እንዳይቀጠር መከሩት፣ የክብር ዘበኛ ሰዎችም በወታደርነትና ሙዚቀኝነት 120 ብር እንክፈልህ ብለው ጠየቁት፡፡ እሱ ግን ባለመስማማቱም በሙዚቀኝነት ብቻ በ1955 ዓ.ም. አካባቢ ተቀጠረ፡፡ ለአሥራ አንድ ዓመታትም ያህልም በዚህ ቦታ ሠርቷል፡፡

‹‹ለዚህ ያበቃኝ፣ የማውቀውን ነገር ሁሉ ያስተማረኝ ለእኔ ወንድሜ ጥላሁን ገሠሠ ነው፡፡ ሌሎችም ሙዚቀኞች እንዲሁ በእኔ ላይ አሻራ ጥለዋል፤›› ይላል ማህሙድ፡፡

በዚያን ወቅት ሙዚቀኞች አንድ ላይ ይሰባሰቡበት የነበሩ ብዙ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ክብር ዘበኛ ይሠራ በነበረበት ወቅት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ይደረግ የነበረው የሙዚቀኞች ውድድር አንዱ ነው፡፡

የተለያዩ ባንዶች እንደ ምድር ጦር፣ ክብር ዘበኛና የፖሊስ ኦርኬስትራ ባንዶች ከድምፃውያኖቻቸው ጋር ይመጣሉ፡፡ እያንዳንዱም ድምፃዊ አንድ ወይም ሁለት ዘፈን ይዘፍናል፡፡ ይሔም ለሙዚቀኞች ጥሩ አጋጣሚ እንደነበር ይናገራል፡፡ ከአሥራ አንድ ዓመታት ቆይታም በኋላ በተለያዩ ክለቦች መሥራት ጀመረ፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የነበረው ያገኘው የነበረው 60 ብር አምስት እህቶቹና ወንድሞቹ በአጠቃላይ ቤተሰቦቹን መደገፍ አልቻለም፡፡

በወቅቱ አባቱ ሥራ ያልነበራቸው ሲሆን እናቱ ብቻ ነበረች የምትሠራው፤ መጨረሻ ላይ ከክብር ዘበኛ በለቀቀበት ወቅት ደመወዙ 250 ብር ደርሶ ነበር፤ ከዚያም ከአይቤክስ ባንድ ጋር ተጠቃልሎ ራስ ሆቴል ተቀጥሮ መሥራት ጀመረ፡፡

በሙዚቃ ሕይወቱ ውስጥ ብዙ ውጣ ውረዶችን እንዳሳለፈ የሚናገረው ማህሙድ ዘመኑ ለሙዚቀኞችም ሆነ ለሙዚቃ ዕድገት የተመቻቸ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ እንደሚናገረው ከሆነ ይሔ ዕድገትም የተገኘውና እዚህ መድረስ የተቻለው በዱሮ ሙዚቀኞች መስዋዕትነት ነው፡፡

‹‹እነዚህ ሙዚቀኞች አሻራቸውን ጥለው ማለፍ ችለዋል፤›› የሚለው ማህሙድ በዚያን ጊዜ የነበሩት ሙዚቀኞች ምንም እንኳን ችሎታው ቢኖራቸውም የሙዚቃ ትምህርት ቤት አልሔዱም፡፡ የዚያን ጊዜውንም በማስታወስ ለሙዚቀኞች እንዴት ከባድ እንደነበር ይናገራል፡፡ ሙያውም እንዴት ይናቅ እንደነበርም ያስታውሳል፡፡

በ1963 ከአይቤክስ ባንድ ጋር ራስ ሆቴል በሚሠራበት ወቅት ‹‹ኩሉን ማን ኳለሽ››፣ ‹‹አምባሰል››፣ ‹‹ችቦ አይሞላም ወገቧ›› እና ‹‹አልማዝ ምን ዕዳ ነው›› የመሳሰሉ ዘፈኖችን ይዘፍን ነበር፡፡ እነዚህ ዘፈኖች ከአንዳንድ ወገኖች ከፍተኛ ትችትም አጋጠመው፡፡ የዱሮ ዘፈኖችን በአዲስ መልክ ትጫወታለህ ለማለት አንድ ጋዜጠኛ ‹‹ፍራሽ አዳሽ›› ብሎ የጠራውን አጋጣሚም አሁንም አይረሳውም፡፡

‹‹አላዘንኩም፡፡ የዱሮ ዘፈኖችን አዲስ ሕይወት በመስጠት ዘፍኛለሁ፡፡ ፍራሽም እንደ አዲስ ሲታደስ ይተኛበታል›› ይላል፡፡ ማህሙድ ከዚህም በተጨማሪ ‹‹ዓባይ ማዶ››፣ ‹‹ደኑን ጥሰሽ›› እና ‹‹የት ነበርሽ›› የሚሉት ዘፈኖቹም የተለየ ርዕዮተ ዓለም ያስተላልፋሉ በሚልም ተወቅሶ ነበር፡፡

የማህሙድ ዓለም አቀፍ ዕውቅና የመጣው ፍራንሲስ ፋልሴቶ ኢትዮጲክስ የሚለውን የሙዚቃ ስብስብ ካወጣ በኋላ ሲሆን ማህሙድም ውለታውን የረሳ አይመስልም፡፡

ፋልሴቶ ፈረንሣዊ ፕሮሞተር ሲሆን የማህሙድን ‹‹መላ መላ›› የሚለውን ዘፈን ሬዲዮ ላይ ሰምቶ አብረን እንሥራ ብሎ ጠየቀው፣ ማህሙድ መጀመሪያ ላይ ተጠራጥሮ እንደነበር ያስታውሳል፡፡

እየተደራደሩ ባሉበት በ1960ዎቹ አካባቢ ማህሙድ ወደ ፈረንሣይ አቅንቶ ሙላቱ አስታጥቄ ጋር አብሮ ዘፍኗል፡፡ በዚያችው ከተማም ማይክል ጃክሰን በዚያው ምሽት ዘፍኗል፡፡ ከተመለሰም በኋላ ነው ኢትዮጲክስ የወጣው፡፡

በዚሁ መድረክ ላይ አዲስ እየሠራው ያለውን ‹‹አብራኝ ናት›› ስለሚለው ዘፈኑም ተናግሯል፡፡ አዳራሽ ውስጥ እየጠቆመ ምን ያህል እንደሚያፈቅራትም ተናግሯል፡፡ ‹‹አብራኝ ናት ከልጅነት እስከ ዕውቀት አብራኝ ናት፡፡ እዚሁ አለች በመንፈስም በሥራዎቼም ውስጥ አብራኝ ናት፡፡ እዚህ ለመድረሴም ምክንያት እሷ ናት፡፡ ትመክረኛለች፤ ከዓመታት በፊት ‹‹አልማዝ አልማዝዬ›› ብዬ ዘፍኘላታለሁ፤ አሁን ደግሞ ‹‹አብራኝ ናት ብዬ›› እዘፍንላታለሁ፤›› ብሏል፤ ማህሙድ፡፡

ማጣቀሻዎች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  1. ^ ናሽናል ቢብሊዮግራፊ ቡድን፣ የአንጋፋ አርቲስቶች መዝገበ የሕይወት ታሪክ፣ መጋቢት ፳፻፣ ገጽ 23-24