Jump to content

መሠረተ ልማት

ከውክፔዲያ

መሠረተ ልማትእርሻንና የኢንዱስትሪን ክፍላተ ኢኮኖሚ የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ቅርንጫፎችን በጥቅሉ ለማመልከት በኢኮኖሚ ነክ ጽሑፎች ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሥራ ላይ የዋለ ቃል ነው። በመሠረተ ልማት ውስጥ የሚጠቃለሉት መንገዶች፣ ወደቦች፣ ድልድዮች፣ አውሮፕላን ማረፊያዎች፣ መጋዘኖች፣ ቦዮች፣ የኃይል ማመንጫዎች፣ የባቡር ሃዲዶች፣ ልዩ ልዩ የመገናኛ አውታሮች፣ የውሃና ፍሳሽ ተቋሞች፣ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶችና የመሳሰሉት ናቸው።

ቃሉ በመጀመሪያ ያመለክት የነበረው በግንባር የተሰለፉ ወታደሮችን የሚያግዙና ድጋፍ ሰጪ የሆኑ እንደ ስንቅ ዝግጅት እንደ መሣሪያ ማከማቻ ቦታዎች እንደ ተዋጊ አውሮፕላን ማረፊያዎችና የመሳሰሉትን ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ተቋሞችን በማመልከት ትርጉሙ ከልማት ጋር ሊያያዝ ችሏል።

በመሠርተ ልማት ውስጥ የሚጠቃለሉ ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ተቋሞች የአንድን ሀገር ቂሳዊ ሀብት በማሳደግ ረገድ በሚጫወቱት ሚና ምርታዊና ኢምርታዊ መሠረተ ልማት ተብለው ይከፈላሉ። ምርታዊ መሠረተ ልማት የሚባሉት ከቁሳዊ ምርት ጋር በቀጥታ የተገናኙ እንደ መንገዶች እንደ ባቡር ሃዲዶች እንደ ኃይል ማመንጫዎችና እንደ መጋዘኖች የመሳሰሉትን ሲያጠቃልል፣ በኢምርታዊ መሠረተ ልማት ውስጥ የሚጠቃለሉት ደግሞ ከቁሳዊ ምርቱ ጋር ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የሚገናኙ እንደ ትምህርትና እንደ ጤና አገልግሎቶች የመሳሰሉት ናቸው።