Jump to content

መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ

ከውክፔዲያ
መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ
የቤተርክስቲያኑ ዋና በር ፊት ለፊት፣ ጎንና ጎን የመንግስት መስሪያ ቤቶች
መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ is located in ኢትዮጵያ
{{{alt}}}
መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ

9°02′ ሰሜን ኬክሮስ እና 38°49′ ምሥራቅ ኬንትሮስ


የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሕንፃ የመሠረት ድንጋይ ታኅሣሥ ፲፭ ቀን ፲፱፻፳፬ ዓ/ም ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሲያስቀምጡ የእስክንድርያ ኮፕት ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ዮሐንስ እና የሀገር ጳጳሳትም በተገኙበት ልዩ ጸሎት እና ቡራኬ ተሠጥቶ ተመረቀ። ቤተ ክርስቲያኑ ሲታነጽ ቀዳሚ ዓላማው ለአገራቸው ነፃነት ሲታገሉ ለተሰው አርበኞች መካነ መቃብር እንዲሆን ታቅዶ ነው።

የደብሩም ስም የሚያመላክተው ይኼንኑ እንደሆነ ነው። ታላቁ ምሁር ዓለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መንበር የሚለውን ቃል በቁሙ ወንበር፣ ግርንቡድ፣ መኖሪያ፣ ማረፊያ፣ መቀመጫ፣ ዙፋን፣ አትሮንስ፣ ድንክ፣ እረፍት፣ መደብ፣ ለመቀመጫ የተለየ ከፍ ያለ ቦታ እንደሆነ ሲገልጹ፤ ጸባኦት ደግሞ ሰራዊት፣ ጭፍራ፤ የጦር ሕዝብ፤ ብዙ ወታደር፤ ያርበኛ ጉባኤ፤ የዠግና ማኅበር እንደሆነ ያብራራሉ።[1]

ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በጥንታዊት ኢትዮጵያ ክርስቲያናዊ ባህል መሠረት አብዛኛዎቹ ንጉሠ ነገሥቶቿ ካሠሯቸው አብያተ ክርስቲያናት በመጀመሪያ ያሠሯቸው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ፈጣሪ አምላክን “በአካል ሦስት፣ በባሕሪ አንድ” ምልክት የቅድስት ሥላሴን ቤተ ክርስቲያን ነው።

ለምሳሌ፦

  • ፩ኛ/ በፍጹም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያንነታቸው “ቆስጠንጢኖስ” የተባሉት እና አምልኮተ ጣዖትን አጥፍተው የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት የወሰኑት ዓፄ ዘርአ ያዕቆብ ከአሳነጿቸው አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በጣም ትልቅና ታሪካዊ የሆነውን በሸዋ ውስጥ ያለውን የደብረ ብርሃን ሥላሴን ቤተ ክርስቲያን አሠርተዋል።
  • ፪ኛ/ በጎንደር መንግሥት የዜማንና የስብሐተ እግዚአብሔር ውሳኔን የሰጡት ዓፄ ኢያሱ አድያም ሰገድ ካሠሯቸው አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ ያለውን ቤተ ክርስቲያን አሳንፀው በቅድስት ሥላሴ ስም ሰይመውታል።
  • ፫ኛ/ ዓፄ ዮሐንስንጉሠ ነገሥት እንደተባሉ ወዲያውኑ በአድዋ ከተማ የሚገኘውን የደብረ ብርሃን ቤተ ክርስቲያን አሳንፀው በቅድስት ሥላሴ ስም ሰይመውታል።

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም እንዲሁ ንጉሠ ነገሥት በተባሉ በመጀመሪያው ዓመት የሕንፃውን ሥራ አስጀምረው ሲፈጸም በቅድስት ሥላሴ ስም እንዲጠራ አደረጉ።

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት 'ኢትዮጵያ፡- ነጠላ እና ጋቢ' በሚል ጽሑፉ ላይ የቅድስት ሥላሴ ታቦት የመጣው በግራኝ ጊዜ ከፈረሰው ከወሎው መካነ ሥላሴ እንደሆነና ከዚያ ተወስዶ ወግዳ መኖሩን፣ ከወግዳ ራስ ጎበና አምጥተው ሸዋ አዲስ ዓለም ፍየታ እንዳኖሩት ከዚያም ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ደግሞ አዲስ አበባ አራት ኪሎ እንዳመጡት ይዘግባል፡፡[1] Archived ኖቬምበር 7, 2011 at the Wayback Machine

የሕንፃው ግንባታ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የሕንፃው ግንባታ ልዩ መልክ ባለው እቅድ ተገንብቶ በሮችን መገጣጠምና ጌጣ ጌጥ ነገሮችን ማስገባት ሲቀር በ፲፱፻፳፰ ዓ/ም ፋሺስት ኢጣልያ አገራችንን በግፍ ለመውረር ስለተነሳ ሥራው መቆም ግድ ሆነበት። የፋሺስት ኢጣልያም ጠቅላላ ኃሣብ የኢትዮጵያን ሙሉ ክብር ፈጽሞ ለመግፈፍ እና የእራሱን አሻራ ለማላከክ ስለነበር፣ የዚህን ካቴድራል የአሠራር ጥራት እና የቦታውንም አቀማመጥ ምቹነት በመገንዘብ የካቶሊክ ካቴድራል ለማድረግ ወሰነ። ሆኖም በግድ እና በግፍ ወሰደው ላልመባል ግምቱን ሰጥቶ መውሰድን መርጦ የጊዜውን የቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች በማስፈራራት ግምት ከፍዬ ልውሰደው ሲል ጠየቃቸው። ያገኘው መልስ ግን <<ዛሬ መብቱ ያንተ ነው። በግድ ለመውሰድ ትችላለህ፤ ግን በፈቃዳችን አናደርገውም>> የሚል ቆራጥ መልስ በመሆኑ፣ እጠላት እጅ ሳይገባ ቀረ።

የምርቃቱ ሥነ ሥርዓት[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

፲፱፻፴፫ ዓ/ም በተገኘው ድል ንጉሠ ነገሥቱ ሲመለሱ፣ የሕንፃው ሥራ እንደገና ተጀምሮ በቅልጥፍና ተሠርቶ ካለቀ በኋላ “መንበረ ጸባኦት” ተብሎ በቅድስት ሥላሴ ስም ተሰይሞ ጥር ፯ ቀን ፲፱፻፴፮ ዓ/ም፤ መሳፍንት፣ መኳንንት፣ ሊቃውንት፣ የሴት ወይዛዝር፣ የጦር ሠራዊት በተገኙበት ተመረቀ። ካቴድራሉ መታሰቢያነቱም በ፭ቱ የጠላት ወረራ ዓመታት ለተዋጉት አርበኞች ሆነ። ቅዳሴ ቤቱ ከተባረከ በኋላ በባህር የተጣሉትን፤ በገደል የወደቁትን እና በማይታወቅ ቦት የረገፉትን አርበኞች ዐጽም ተሰብስቦ በዚሁ ዕለት በልዩ የጸሎት ሥነ ሥርዓትና በታላቅ የሰልፍ አጀብ ተቀበረ።

የቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን የመጀመሪያ ቅርጽ

በካቴድራሉ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሚከተለውን ዐዋጅ አስነገሩ።

“እጅግ ከፍ ያለው የዓለም ሁሉ ገዥ እግዚአብሔር ለኢትዮጵያና ለሕዝባችን ለእናና ለአርበኞቻችን በየጊዜው ካደረገልን ፣ ወደፊትም ከሚያደርግልን ከታላላቅ ችሮታ ከሚቆጠሩት ሥራዎች አንደኛውን ዛሬ ስለፈጸመልን ልናመሰግነው ይገባናል።

ለንጉሠ ነገሥት ቤተ ዘመዳችን ደንበና የዕረፍት ሥፍራ እንዲሆን በመሠረትነው የክብር ቦታ በሥራቸውና በመሥዋዕትነታቸው ውለታቸውን ልንመልስላቸው የተገባቸው አገልጋዮች ደንበኛ የርስት ተካፋይ እንዲሆኑ ፈቀድን። የሚገባቸውን ፈጽመው ማረፋቸውን ስንመሰክርላቸው በዐጽማቸው ፊት የክብር ሰላምታ እንሰጣለን።”

በዚሁም ሥነ ሥርዓት ላይ ለልዩ ልዩ የጦር ሠራዊት መለዮ የሚሆነው ሰንደቅ ዓላማ በዚህ ካቴድራል እንዲውለበለብ ፈቀዱ። ይህም በጦር ሜዳ ለወደቁት አርበኞች፣ ለሕያዋኑ ጦር ሠራዊት መታሰቢያ እና የጦሩ መለያ የሚሆን ነው።

የቅድስት ስላሴ ቤ/ክርስቲያን ፎቶግራፍ በድሮ ዘመን

ስለዚህም ንጉሠ ነገሥቱ በሚከተለው ምስክር ወረቀት የተረጋገጠውን ሽልማትም አደርጉ።

ኢትዮጵያን ከጠላት ለመከላከል በጦር ሜዳ ላይ ለወደቁት ጦረኞቻችን መታሰቢያ እንዲሆንና በጦር ሠራዊታችን ውስጥ ሆነው ለኢትዮጵያ ለተከላከሉና ለረዱ፤ ወደፊትም ለሚከላከሉና ለሚረዱ ፣ ለታማኝ ዜጎቻችን ሁሉ በመልካም ፈቃዳችን ውለታቸውን በልዩ ለመግለጥ ምኞታችን ስለሆነ፤ በሕገ መንግሥታችን በ ፲፭ኛው ክፍል የተመለከተውን ዓይተን ይህንን ለመፈጸም፦

ታላቁን የሥላሴን ኒሻን ኮርዶን ሸልመናቸዋል። አዲስ አበባ ጥር 21 ቀን ፲፱፻፴፯ ዓ/ም ጸሐፌ ትእዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ፣ የጽሕፈት ሚኒስትር

፪ኛው የቅጽል ሥራ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

መንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከተስፋፋ በኋላ አሁን የያዘውን ቅርጽ እንደያዘ

፲፱፻፴፮ ዓ/ም የተመረቀው የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ የአዲስ አበባ ሕዝብ ብዛይ እየጨመረ ሲሄድ በመጥበቡ በ፲፱፻፴፱ ዓ/ም አዲስ ቅጽል ሥራ ተጀምሮ አሁን ያለውን መልክና ሥፋት ሊያገኝ ችሏል። የአሁኑ ሕንፃ ወለል ስፋት ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ፴፯ ሜትር ሲሆን ከሰሜን ወደደቡብ ፳፯ ሜትር ነው። ቁመቱም መካከሉ ላይ ፴፭ ሜትር ነው። በውስጡ ካሉት ዓምዶችና ከቅድስቱ ጀምሮ ያለው ሕንፃ በመጀመሪያው ጊዜ የተሠራው ያልተነካ ነው። በሰሜንና በደቡብ ያሉት ግንቦች ግን በ፲፱፻፴፱ ዓ/ም የተቀጠሉት ግንቦች ናቸው።

የካቴድራሉ አሠራር[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በመቅደሱ ውስጥ ሦስት መንበሮች ይገኛሉ። የተሠራበትም ዋጋው ፸፭ ሺ ብር ሲሆን፣ መካከለኛው በአጋእዝተ ዓለም ቅድስት ሥላሴ የተሰየመ ነው። መንበሩ ከወርቅ፣ ከብር፣ ክዝሆን ጥርስ፣ ከወይራ እንጨት ነው። ልዩ ልዩ የሥዕል ጌጣ ጌጦች ፤ በምሥራቅ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሞኖግራምና ዘውድ፣ በቀኝ እና በግራው መላእክትም አሉበት። ከፍ ብሎ ከአጎበሩ ላይ ደግሞ ክብር የተሠራ ምሴተ ሐሙስን የሚያስታውስ ማዕድ ይገኛል። በደቡብ ደግሞ በከርሠ ሐመሩ ላይ የንግሥት ሳባ ኒሻን፣ በአጎበሩ ግን የጰራቅሊጦስ ሥዕል ይገኛል። በአጎበሩ ተሸካሚ ዓምዶች ላይ የኢየሱስ ክርስቶስ የሕይወት ታሪክና የስንዴ ቅርጽ ይገኝበታል።

በየ፬ቱ ማዕዘን ላይ የኪሩቤልና የሱራፌል ቅርጽ ወይም በአራቱ ወንጌላውያን የሚመሰሉት የሰው፣ የአንበሳ፣ የላም እና የንስር ቅርጽ ከብዙ ዓይንና ከየስድስቱ ክንፍ ጋር ይገኛል።ይሄ ሥራ በኢትዮጵያውያን አርቲስቶች የተሠራ ሲሆን በቤተ መንግሥቱ ልዩ ግምጃ ቤት ሹም በብላታ አድማሱ ረታ ተጠባባቂነት ነው።

ከዋናው መቅደስ በስተቀኝ በቅድስት ማርያም የተሰየመው መቅደስ ይገኛል። ከዋናው መቅደስ በስተግራ ደግሞ በመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ የተሰየምው መቅደስ ይገኛል።የመቅደኡ ግንብ በሞላ በሞሴይክ የተሠራ ነው። ከቅድስቱ ውስጥ በቀኝ እና በግራ ከእንጨትና ከዝሆን ጥርስ የተሠሩ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እና የእቴጌ መነን ወንበሮች (ዙፋናት) ይገኛሉ። እንዲሁም በዚሁ በቅድስት ውስጥ በቀኝ ለሴት ወይዛዝር፣ በግራ ለወንድ መኳንንት የተለየ የክብር መቀመጫ ይገኝበታል።

ኢየሱስ ክርስቶስዮርዳኖስ ሲጠመቅ

የቤተ ክርስቲያን ጌጣ ጌጥ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በሰሜንና በደቡብ በየመስኮቱና በየግንቡ የቅዱሳንና የመላእክት፤ የቅድስት ማርያም ሥዕል ይገኛል። በተለይ ግን በቅድስቱ ውስጥ ከግንቡ ላይ ከምሥራቅ ከፍ ብሎ ሥዕለ ሥቅለት፣ ዝቅ ብሎ ከበሩ ራስ ላይ ምስለ ፍቁር ወልዳ ይገኛሉ ። በዚህም ሥዕል ቀኝና ግራ ግርማዊ ጃንሆይና ግርማዊት እቴጌ እንደተማፀኑ ያመለክታል። ቀኝና ግራ ባሉት መቅደሶችላይ ያሉት ሥዕሎች ደግሞ ፩ኛው ጥምቀትን ፪ኛው ኪዳነ ምሕረትን ያመለክታሉ።

በደቡብ በኩል ደግሞ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴኢትዮጵያን ጉዳት ለዓለም መንግሥታት ማኅበር ያመለከቱበትን የጀኔቭ ጉባኤ የሚያመለክት ሥዕል ይገኛል።

በሰሜን በኩል ደግሞ የንጉሠ ነገሥቱን ወደ ኢትዮጵያ መመለስና በኦሜድላ ላይ ሰንደቅ ዓላማውን ሲተክሉ ያሳያል። በምዕራብ በኩል የኢትዮጵያ ሰማዕታት ዐጽም ከልዩ ልዩ ቦታዎች ተሰብስቦ በክብር ወደዚህ ቅዱስ ቦታ መግባቱን የሚያመለክት ሥዕል ይገኛል።

ሌሎች ሥዕሎች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በአቶ አገኘሁ እንግዳ፤ በአቶ እምአላፍ ኅሩይ፤ አቶ አለፈለገ ሰላም እና አቶ መዝሙር ዘዳዊት የተሣሉ፦

  • ፩ኛ/ የኢየሱስ ክርስቶስን ዕርገት የሚያመለክት ከፍ ብሎ ከኮፖላው ላይ
  • ፪ኛ/ የኢየሱስ ክርስቶስን ዳግመኛ ምጽዐት የሚያስታውስ ሥዕል
  • ፫ኛ/ የሀገርና የውጭ አገር ቅዱሳን ሥዕሎች ይገኛሉ።


ማጣቀሻዎች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  1. ^ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ "መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሓዲስ" (፲፱፻፵፰ ዓ/ም))

ዋቢ ምንጭ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]