መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር

ከውክፔዲያ

መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር በቢትወደድ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ተጽፎ በ፲፱፻፲፮ ዓ.ም. የታተመ መጽሐፍ ነው። ይህ መጽሐፍ ከመስራት የተነሳ የሰው ልጅ እንዴት ከተፈጥሮ ጥገኝነት ተላቅቆ ከኋላ ቀር አኗኗር ወደ ተሻለ ሕይወት እንደሚለወጥ የሚያስረዳ ሲሆን የዓለም ሕዝቦች የዕውቀታቸውና የሀብታቸው ደረጃ ከፍና ዝቅ ያለ መሆኑ ምክንያቱ ከጦርነት የተነሳ ነው ይላል። ጦርነቱንም የሚነሱ ነገሥታትና አለቆቹ ሁሉ ልባቸው ሀብት እንደፈለጉ አይገልፅም። ነገር ግን ስም ለመፈለግና ለማግኘት ወይም ሀይማኖቱን ለማስፋፋት ወይም የተጠቃውን ለመርዳት አስመስለው ይነሳሉ። የጦርነት ሁሉ ፍፃሜ ምኞት ግን መዝረፍና ማስገበር ነው። ይህንንም ሲሉ ዕውቀታቸው የሰፋ ነገሥታትም ቢሆኑ መዝረፍን አይተዉም። አዘራረፋቸው ግን የዕውቀት አዘራረፍ ነው እያለ በሰፊው ያወሳል።

አክሱም ዘመነ መንግሥት የእስራኤልና የአህዛብ ወገን ተብሎ የሁለት ዓመት ጦርነት በመፍጀቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍ ወዳለው ደረጃ እንዳይደርስ ዋና መሰናክል ሆኗል።

ዋጋ ማለት የስራ መለኪያ ነው። ዕውቀት ከጉልበት ይከበራል። ዕውቀት የሌለው ሕዝብ ሁሉ ለብቻው መንግሥት ቢኖረውም ባይኖረውም ዕውቀት ያላቸው ሕዝቦች ይገዙታል። ሰው ሲፈጠር ጌታና ድሀ ሆኖ አልተፈጠረም። ድህነትና ጌትነት የተለየው በሰው ዕውቀት ነው። የሀብት መለኪያ ሥራ ነው። ስለዚህ ሀብት ማለት የተከማቸ ሥራ ማለት ነው።

አርነት ያለው ሕዝብ ማለት ዕውነተኛ ትርጉሙ ለብቻው መንግሥት ያለው ማለት ብቻ አይደለም፣ ራሱንም የቻለ ሕዝብ ማለት ነው እንጂ። የኢትዮጵያ ሕዝብ እስከዛሬ ድረስ ገና ራሱን አልቻለም። እስቲ የሰራነውን እንይ እንዴት የተሠራና ማን ያመጣው ነው? ጭቅጭቅና ጦር ቅድሚያ የሚበዛው በስራ ባልሰለጠኑ ሕዝቦች ውስጥ ነው። ስለዚህም ሕዝቡ ሲሰለጥን የሹሞቹን ዕርዳታና ቸርነት የሚፈልግበት ምክንያት ሁሉ ያንሳል።

ሕዝቡ እንዲረዳና እንዲበረታ የፈለገ መንግሥት ከሁሉ ነገር በፊት የባላገሩ ትዳር እየተሻለ እንዲሄድ መጣር አለበት። ስለዚህ የሕዝብ ማሰልጠኛ ት/ቤቶች በየአይነቱ ማቋቋም፣ ሕዝቦችን የሚያቀራርብ የመጓጓዣ መንገድና ምድር ባቡር መስራትና የውጭ ኢንቨስተርን በደስታ ተቀብሎ ማስተናገድ፣ እነዚህን ከተከተለ የመንግሥት ሀብትና ሀይል እያደገ ይሄዳል ብለው በመቀጠልም ስለ ትምህርት ጥቅም ሲጽፉ ትምህርት በሌለበት ሀገር ለስርዓት የሚሆን መሠረት አይገኝም። ስርዓት የሚገኘው በትምህርት ነውና ትምህርት የሌለው ሕዝብ ስርዓት አይወድም አይጠቅመውም በማለት ያብራራሉ።

ስለ ገንዘብ አጠቃቀም ደግሞ ሲጽፉ ሕዝቡ ገንዘቡን በቤት ውስጥ ከማስቀመጥ ይልቅ በባንክ አስቀምጦ በባንክ ኖት መጠቀምን መልመድ አለበት። የባንክ ስራ በሞኖፖል መሆን የለበትም። ለደሀ ሕዝብ ከትልቁ የለውጥ መሳሪያ ይልቅ ትንንሹ የለውጥ መሳሪያ ያስፈልጋል (ከ.ሩብ፣ ከአለድ እና ከብር በመተመን መገዛዛትን ያሻል)። የኢትዮጵያ መንግሥት የለውጥ መሳሪያ ወርቅ እንዲሆን ቢጥርበትና እንዲሁም የገንዘብ ደንብ ማውጣት አለበት በማለት የደንብን አስፈላጊነት በጽሁፋቸው ይገልጻሉ።

ማጣቀሻ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]