መደብ:18ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ

ከውክፔዲያ

ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ (ጥር ፮ ቀን ፲፰፻፲፩ ዓ.ም. - ሚያዝያ ፮ ቀን፲፰፻፷ ዓ.ም.)[1] ከ፲፰፻፵፯ ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞታችው ድረስ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነበሩ። በትውልድ ስማቸው ካሳ ኃይሉ ሲባሉ፣ በፈረስ ስማቸው አባ ታጠቅ፣ በወታደራዊ ስማቸው መይሳው ካሳ እና እንዲሁም አንድ ለናቱ ተብለው የሚታወቁ የ19ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ወታደርና ፖለቲከኛ ነበሩ።

ቴዎድሮስ ጥር ፮ ቀን ፲፰፻፲፩ ዓ.ም. ሻርጌ በተባለ ቦታ ቋራ ውስጥ፣ ከጎንደር ከተማ በስተ ምዕራብ ተወለዱ። የተወለዱትም አገሪቷ በባላባቶች ተከፋፍላ በምትመራበት-ዘመነ መሳፍንት በሚባለው ወቅት ነበር። አባታቸው ደጃዝማች ኃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ የቋራ ገዢ ነበሩ። ዓፄ ቴዎድሮስ በህጻንነታቸው የቄስ ትምህርት ከቀሰሙ በኋላ፣ የአጎታቸውንና በኋላም ለጥቂት ጊዜ የጎጃሙን ጦር መሪ የጎሹ ዘውዴን ጦር ተቀላቀሉ። በዚሁ የውትድርና ዘመናቸው ከፍተኛ ችሎታን ማስመዝገብ ስለጀመሩና ዝናቸው ስለተስፋፋ በ፲፰፻፴፱ ዓ.ም. በወይዘሮ መነን ሊበን አምዴ አነሳሽነት የልጇን የራስ አሊ አሉላን ልጅ፣ ተዋበች አሊን ተዳሩ፤ እንዲሁም በደጃዝማችነት ማዕረግ የቋራ አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ። ቴዎድሮስ ግን በ፲፰፻፵፬ ዓ.ም. አጠቃላይ የዘመነ መሳፍንት ሥርዓትን በመቃወም በሰሜናዊ ባላባቶች ላይ ዘመቻ ጀመሩ። በኒህ ተከታታይ ዘመቻወች የገጠሟቸውን ባላባቶች ስላሸነፉ፣ መጀመሪያ የራስ ማዕረግን በኋላም የንጉሥ ማዕረግን በአንድ ዓመት ውስጥ ተቀዳጁ። በየጊዜው በሚያደርጉት የተሳካ ዘመቻ የዘመኑን ባላባቶች ኃይል በመሰባበር የካቲት ፫ ቀን ፲፰፻፵፯ ዓ.ም ንጉሥ ካሳ - ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ተብለው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሆኑ።

ሥርዓተ ንግሡ የዘመነ መሳፍንት መቃብር በመሆን የዘመናዊ ኢትዮጵያን ታሪክ "ሀ" በማለት ጀመረ። ዓፄ ኃይለ ስላሴ እስከ ፈጸሙት ድረስ ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ሥራም በዚሁ ወቅት ተጀመረ። ዓፄ ቴዎድሮስ ሰሜናዊ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አንድ ለማድረግ የሞከሩት፣ አጠቃላይ በታሪክ የሚታወቀውን የኢትዮጵያ ክፍል ነበር - ለዚህም ዋቢ ወደ ወሎና ወደ ሸዋ ያደረጓቸው ዘመቻወች ይጠቀሳሉ።

በዘመነ ንግሣቸው ዓፄ ቴዎድሮስ አገሪቱን የሚያሻሽሉ ሥርዓቶችን ለአገራቸው አስተዋውቀዋል። ከነዚህም ውስጥ፡ ባርነትን የሚያግድ አዋጅ፣ የመጀመሪያው መንገድ ግንባታ፣ የሥርዓተ ንዋይና የፖለቲካ ሥርዓቱን በማዕከላዊ መንገድ ማዋቀር፣ የባላባት የተከፋፈለ "ሁሉ-በሁሉ-ጦርነት ሥርዓት"ን በማስቀረት ብሔራዊ ውትድርናን ማስተዋወቅ ይጠቀሳሉ። በዘመነ መሳፍንት እንደልባቸው ይፈልጡ ይቆርጡ በነበሩ ባላባቶች ዘንድ እኒህ ለውጦች እጅግ የተጠሉ ሆኑ። በ፲፰፻፶ ዓ.ም. ብዙወቹ ባላባቶች አመጽ ማነሳሳት ጀመሩ። በ፲፰፻፶፪ ዓ.ም ንጉሠ ነገሥቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ርስት የነበረውን መሬት ለገበሬወች በማከፋፈላቸው ከሃይማኖት መሪወች ጋር ተጣሉ። ይህን ተከተሎ በየቦታው አመጽ በሚነሳበት መካከል አውሮፓውያን ሚሲዮኖችም ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር በተነሳሳ አለመግባባት ምክንያት በዓፄው ታሰሩ።

በመጋቢት ወር ፲፰፻፷ ዓ.ም ላይ የእንግሊዝ መንግሥት በሮበርት ናፒየር የሚመራ፣ በጊዜው እጅግ ግዙፍ የተባለ ኃይልን አሰናድቶ አውሮፓውያን እስረኞችን ለማስፈታት ጦር ላከ። መጋቢት ፭ ቀን ፲፰፻፷ ዓ.ም ይህ ጦር በመቅደላ ምሽግ ላይ በሚገኘው፣ በአመጽ በተዳከመ የንጉሱ ጦር ላይ ጥቃት አደረሰ። በውጊያው መሃል ንጉሠ ነገሥቱ እጃቸውን እንዲሰጡ ቢጠየቁ እስከመጨረሻው አሻፈረኝ በማለት በሽጉጣቸው እራሳቸውን ገድለው በጀግንነት አለፉ። ዓፄ ቴዎድሮስ ያሰቡትን ለውጦች በሙሉ በተግባር ቢፈጽሙ ኖሮ በእርግጥም ታላቅና የሰለጠነ ሀገር መሪ ሊሆኑ ይችሉ እንደነበር ታሪክ ተመራማሪወች ይስማማሉ። ዕቅዳቸው በዚህ መልኩ ቢሰናከልም፣ እጅግ ድንቅ መሪ፣ የተዋጣላቸው ወታደርና የተባበረች ዘመናዊ አገር ራዕይ አብሳሪ እንደነበሩ ያሰሯቸው አውሮጳውያን ሳይቀር ሳይመሰክሩ አላለፉም።

የዙፋን ስማቸው «ቴዎድሮስ»ን የወሰዱት ከፍካሬ ኢየሱስ ከተገኘ ትንቢት ነበረ። በዚያው ትንቢት በኩል፣ በዓለም መጨረሻው ክፍለ ዘመን፣ ተወዳጁ፣ የጥንቱ ዘመን ንጉስ ቀዳማዊ ቴዎድሮስ እንደገና ተነስቶ አገሪቱን ለ፵ ዓመታት ይገዛል የሚል ነበር። "ቴዎድሮስ" የሚለው ስም ከግሪክ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም «ጤዎስ ዶሮስ»፣ 'የአምላክ ስጦታ' ማለት ነው።

ንዑስ-መደቦች

በዚሁ መደብ ውስጥ አንድ ንዑስ-መደብ አለ፦

የመደብ (ካቴጎሪ) «18ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ» ይዞታ ፦

በዚሁ መደብ ውስጥ (ከ2 በጠቅላላ) የሚከተሉት 2 መጣጥፎች አሉ።