ሚኒሊክ ሆስፒታል

ከውክፔዲያ


ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል በአገሪቱ የህክምና አገልግሎት ታሪክ ውስጥ ፈር ቀዳጅ ነው። በታሪክ ሲነገር የሚሰማው የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ምስረታ ጊዜና ለበዓሉ የታተመ መጽሄት ላይ የሰፈረው መረጃ የሚገልጸው የተቋቋመበት ወቅት ለየቅል ነው። ሆስፒታሉ የተሰየመው በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ነው፡፡ የግንባታ ሥራው ከ1890ዓ.ም እስከ በ1891ዓ.ም ተከናውኖ የተወሰኑ ክፍሎቹ ለአገልግሎት በቅተዋል፡፡ ሙሉ ቁመና የያዘው ደግሞ ከአስር ዓመት በኋላ በ1902ዓ.ም ነው፡፡በዚህ መልኩ የህዝብ ጤናን ለመጠበቅ የተመሠረተው ሆስፒታል በረጅም ጊዜ የአገልግሎት ዘመኑ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች እየተስፋፉ መጥተዋል፡፡የተገልጋዩም ቁጥር ጨምሯል፡፡ይሁን እንጂ ሆስፒታሉ በሀገሪቷ ብቸኛ በመሆኑ የህክምናውን ጫና ተሸክሞ ነው ያለፈው ማለት ይቻላል፡፡ ከምስረታው ጀምሮ ማስፋፊያዎች ባለመከናወናቸው፣ በቂ በሆነ የሰው ኃይል ባለመደራጀቱና በተለያዩ ተጽዕኖዎች ውስጥ እንዲያልፍ መገደዱ ለውጡን አዝጋሚ አድርጎታል፡፡ ሆስፒታሉ 62ሺ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ቢሆንም ባዶ መሬቱን በአግባቡ አልተጠቀመበትም፡፡ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥባቸው ክፍሎችም በተበታተነ ቦታ ነው የተገነቡት፡፡ ይሄም ሆስፒታሉን ለአገልግሎት ምቹ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ የአገልግሎት ዘመናቸው ረጅም ከመሆኑ ጋር ተያይዞም የክፍሎቹ ጣሪያ የሚያፈሱ፣ ግድግዳቸውና ወለላቸውም ያረጁ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ለረጅም ጊዜ እድሳት ስላልጎበኛቸው አገልግሎቱን ጎዶሎ አድርጎታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሆስፒታሉ በሀገሪቷ ፈር ቀዳጅ ቢሆንም እስካሁንም የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ አልነበረውም፡፡ በዚህ ምክንያት ይዞታውንና ደህንነቱን ለማስጠበቅ ተቸግሮ ቆይቷል፡፡ በሆስፒታሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ይስተዋሉ የነበሩትን በርካታ ችግሮች ለማቃለል ከ2001ዓ.ም ወዲህ በአይነት፣ በመጠንና በጥራት ለመለወጥ ጉዞ ጀምሯል። በአመራሩና በፈጻሚው ተነሳሽነት የሚገለጹ የለውጥ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው ይነገራል፡፡ ያልነበረውን ይዞታ ካርታ ከማግኘቱ በተጨማሪ የሆስፒታሉንም አጥር በግንብ አጥሯል፡፡ አስር ነባር የህክምናና የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ክፍሎች እድሳት ተደርጓል፡፡ከዚህም ባለፈ 356 የህሙማን አልጋዎችን የሚይዝ ዘመናዊ የህክምና መስጫ ባለ ሰባት ፎቅ ህንፃ አስገንብቷል፡፡እነዚህ ሁሉ እንቅስቃሴዎች የከተማ አስተዳደሩ ትኩረት መስጠቱን እንደሚያሳይ ተገልጿል፡፡ ሆስፒታሉ በእነዚህ ሁሉ ለውጦች ታግዞ የምስረታ በዓሉን ሲያከብር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። በጡረታ የተገለሉ የሆስፒታሉ ሠራተኞችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታዳሚ ሆነዋል፡፡ የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ክበበው ወርቅነህ እንደገለጹት፤ ሆስፒታሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ የአይንና የአስክሬን ምርመራ አገልግሎቱ የታወቀ ነው፡፡ በተለይም በአስክሬን ምርመራ ብቸኛው ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት ረጅም ዓመታት ጠቅላላ ህክምና፣ ከአንገት በላይ፣ የውስጥ ደዌ፣የነርቭ የአጥንትና የጥርስ የህክምና አገልግሎቶችን በመስጠት ህሙማንን ሲረዳ ቆይቷል፡፡ አዲሱ የማስፋፊያ ህንጻ መገንባታ ደግሞ አገልግሎቱን በተሻለ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ አስችሎታል፡፡ከዚህ በፊት ይሰጡ ያልነበሩ የህናቶች የድህረና የቅድመ ወሊድ ክትትሎችና የማዋለድ፣ እንዲሁም የህጻናት የህክምና የኩላሊት እጥበት አገልግሎቶችን ለመጀመር አስችሎታል፡፡ ሆስፒታሉ በውስጥ አደረጃጀቱም ተለውጧል፡፡ ወቅቱ የሚጠይቀውን ዘመናዊ የህክምና መስጫ መሳሪያዎች አሟልቷል፡፡ ሙያቸውን አክብረው የአገልጋይነት ስሜት ያላቸው ሙያተኞች ለማፍራትም የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ እራሱን ለለውጥ አዘጋጅቷል፡፡ ሆስፒታሉን ጽዱና ምቹ በማድረግ በኩል ቀድሞ ከነበረው ኋላቀር ተገልጋይ ተኮር የአገልግሎት አሰጣጥ በመላቀቅ ዘመናዊ የሆነ የሆስፒታል አገልግሎት ሥርዓት ለመከተል ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ እንደ አቶ ክበበው ገለጻ፤ ሆስፒታሉ በተመላላሽና ተኝቶ ህክምና በሚሰጠው አገልግሎት ለተወሰኑ ህሙማን ብቻ ነበር አገልግሎቱን ሲሰጥ የቆየው፡፡ ህሙማንም ተራ በመጠበቅ ይንገላታሉ፤ በተለይም ደግሞ በተኝቶ ታካሚዎች ላይ ችግሩ የከፋ ነበር፡፡ ወረፋ በመጠበቅ የሚሞቱም ነበሩ፡፡አሁን በተደረገው ማስፋፊያ ግን ቁጥራቸው በቀን እስከ 500 የሚደርስ ተገልጋዮችን ለማስተናገድ አቅም ተፈጥሯል፡፡ለተኝቶ ታካሚዎችም እድሉን ማስፋት ተችሏል፡፡ የሆስፒታሉ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ይክፈለው ወልደመስቀል እንዳብራሩት፤ ከሦስት አመታት በፊት ከ50 በታች የነበረው የሆስፒታሉ የመኝታ አገልግሎት ወደ 75 በመቶ አድጓል፡፡ በዚህም ውስንነት የነበረበትን የቀዶ ህክምና አገልግሎት ለማሻሻል ተችሏል፡፡ የአደረጃጀትና የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በቦርዱ በኩልም ከፍተኛ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡የአንድ ለአምስት የለውጥ ሠራዊት አደረጃጀትም ለለውጡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ሆስፒታሉ በአሁኑ ጊዜ ከ600 በላይ በሚሆኑ የህክምናና የአስተዳደር ሠራተኞች ተደራጅቷል ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው በበኩላቸው፤ በከተማዋ የሚገኙት አብዛኞቹ ሆስፒታሎች ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠሩ መሆናቸውን በማስታወስ በእርጅና ምክንያት አገልግሎታቸው ተደራሽ ሳይሆኑ መቆየታቸውን ይናገራሉ። በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ ችግሩን ለመቅረፍ በተለይ ከ2001ዓ.ም ጀምሮ ለለውጥ በመነሳሳት ከፍተኛ በጀት መድቦ የማስፋፊያና አዳዲስ ግንባታዎችን ጀምሯል፡፡አቶ አባተ «የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታልም አንዱ ማሳያ ይሆናል» ብለዋል፡፡ እንደ ምክትል ከንቲባው ገለጻ በከተማው በሌሎች አራት ሆስፒታሎችም ተመሳሳይ የማስፋፊያ ሥራ ተከናውኗል፡፡ በዚህ ዓመት በኮልፌ ቀራኒዮ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶና ቦሌ ክፍለ ከተሞች አዳዲስ ሆስፒታሎች ይገነባሉ፡፡ በየወረዳው አንድ ጤና ጣቢያ እንዲገነባ በተያዘው እቅድም አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም 93 ያህል ጤና ጣቢያዎች ለመገንባት ተችሏል፡፡ ከ2000ዓ.ም በፊት በከተማው የነበረው የጤና ጣቢያ 24 ብቻ ነበር፡፡ የከተማ አስተዳደሩ በጤናውና በተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎች ያደረገውን ጥረት በመልካም አስተዳደር ላይ የሚስተዋሉትን ችግሮች በመፍታት ተመሳሳይ ጥሩ ውጤት ለማስገኘት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚንቀሳቀስ ነው የተናገሩት፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ እንደገለጹት፤ የህክምና አገልግሎቱን ከፍ ለማድረግ መንግሥት የተለያዩ የማሻሻያ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ በጤናው ዘርፍ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አራት ዋና ዋና ግቦች ተቀምጠዋል፡፡ የመጀመሪያው ዘርፉን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ተብለው ከተቀመጡት ግቦች አንዱ በሀገር ደረጃ ንቅናቄ መፍጠር ነው። ከገንዘብ ይልቅ ሙያው የሚጠይቀውን ህይወት ለማትረፍ ቅድሚያ የሚሰጥ ርህራሄ ያለው የህክምና ባለሙያ ለማፍራት እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡ ሁለተኛው ዕቅድ መረጃን መሠረት ያደረገ አገልግሎት እንዲኖር ማስቻል ነው፡፡ ቁጥሩ የሚልቀውን የህመም አይነት ከመለየት ጀምሮ የመድኃኒት ፍላጎትና የግብአት አቅርቦት በመለየት በመረጃ የተደገፈ ተግባር ይከናወናል። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የወረዳ ትራንስፎር ሜሽንን በመተግበር የጤና ጣቢያ አገልግሎትን ማሻሻል ነው፡፡አራተኛው እቅድ በአጠቃላይ የአገልግሎት ጥራትን በማስጠበቅ አገልግሎቱን ወደላቀ ደረጃ ማድረስ ነው፡፡ ለተግበራዊነቱም ሁሉም የየድርሻውን መወጣት እንዳለበትና በተቋማቱም ዘላቂ ንቅናቄ እንዲፈጠር አሳስበዋል፡፡ እንደ ዶክተር ከሰተብርሃን ማብራሪያ፤ እነዚህ ቁልፍ የሆኑት የጤና ልማት ግቦች ዘርፉን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ከፍተኛ ድርሻ አላቸው፡፡ በሀገር ደረጃ ንቅናቄ በመፍጠር በኩል ከገንዘብ ይልቅ ሙያው የሚጠይቀውን ህይወት ለማትረፍ ቅድሚያ የሚሰጥ ርህራሄ ያለው የህክምና ባለሙያ ማፍራት ነው፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው «ሰማንያ በመቶ የሚሆነውን የበሽታ ምንጭ በመከላከል አመርቂ የሆነ ውጤት በማስመዝገብ ላይ ብንሆንም ዘመኑ የሚጠይቀውን የህክምና አገልግሎት በመስጠት የተገልጋዩን ፍላጎት በማሟላት ላይ ግን ብዙ ይቀረናል» ብለዋል። ያም ሆኖ ጅምሮቹ ዘርፉን ወደተሻለ አገልግሎቶች የሚያደርሱ መሆናቸውን ነው የገለፁት፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሆስፒታሎች መሠረተ ልማቶች በማስፋፋት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡ ሙያውን የእርካታ ምንጭ አድርጎ መነሳሳት እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን በጤናው ልማት የተተገበሩትን ምርጥ ተሞክሮዎች በመቀመር ሁለተኛውን በተሻለ ደረጃ ለመፈጸም የሚያስችሉ ሥራዎች መሠራታቸውን የጠቆሙት አቶ ደመቀ፤ ኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ቱሪዝም ተጠቃሚ እንድትሆን በነቃ ተሳትፎ መንቀሳቀስ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ በሀገር ደረጃ የታቀደውን የጤና ልማት ፕሮግራም ወደ ተግባር ለመለወጥ ዘርፉን በተማረ የወጣት ኃይል በመምራት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እየተከናወነ ያለው ተግባርንም አድንቀዋል፡፡ የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታልን አገልግሎት ለማሻሻል የተሰሩት ሥራዎችም ሆስፒታሉ እድሜው በሚመጥነው የለውጥ ጎዳና ላይ መድረሱን የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል በህክምና አገልግሎቱ ብቻ ሳይሆን ታዋቂ ጋዜጠኛ፣ የስፖርት ባለሙያም በማፍራት ባለታሪክ ነው፡፡ ለአብነትም ታዋቂው ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ በሆስፒታሉ የመርፌ መውጋት የህክምና አገልግሎት ሰጥቷል። በስፖርቱ የሚታወቁት ይድነቃቸው ተሰማም ሆስፒታሉን አስተዳድረዋል፡፡ በዚህ መልኩ ከአንድ አዛውንት እድሜ በላይ በማስቆጠር ባለታሪክ የሆነ ሆስፒታል ብዙ ለውጦችን ቢያስመዘግብም ያልተፈቱ ውስጣዊና ውጫዊ የሆኑ ተግዳሮቶች እንዳሉበት በሆስፒታሉ ዙሪያ የተዘጋጀው የህትመት ውጤት ያመለክታል፡፡ ውጫዊ ችግሮቹ የመብራት መቆራረጥና የመሠረተ ልማት አለመሟላት ይጠቀሳሉ፡፡ በውስጣዊው ደግሞ ኃላፊነትን መሸሽ፣ ተቀናጅቶ አለመንቀሳቀስ፣የቅንነትና አገልጋይነት ስሜት አለመኖር፣ የሰው ኃይል አለማሟላት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ናቸው፡፡ እነዚህን ያልተሻገራቸውን ችግሮች ፈትቶ እንደቀዳሚነቱ በአገልግሎቱም ልቆ ባለታሪክነቱ እንደሚቀጥል እምነት ተጥሎበታል፡፡