ማልኮም ኤክስ

ማልኮም ኤክስ (Malcolm X 1917-1957 ዓም) በአሜሪካ አገር ታዋቂ የብሔራዊ መብቶች እንቅስቃሴ መሪ ነበር።
በመጀመርያ በአንድ አነስተኛ ክፍልፋይ «ኔሽን ኦፍ ኢስላም» («የእስልምና ብሔር») ውስጥ አባል ሆነና የልደቱን ስም ማልኮም ሊተል የባርያ ፈንጋይ ቤተሠብ ስም ብሎት ወደ «ማልኮም ኤክስ» ቀየረው። ክፍልፋዩ «ኔሽን ኦፍ ኢስላም» ቢባልም፣ ትምህርቱ ግን እንደ እስልምና በፍጹም አይመስልም። መሪያቸው ስለ መሥራቹ አምልኮት ይሰብክ ነበርና ነጮች ሁሉ አጋንንት እንደ ነበሩ ያስተምር ነበር። ከጊዜ በኋላ ማልኮም ኤክስ ሀሣቡን ቀይሮ ከ«ኔሽን ኦፍ ኢስላም» ለቅቆ ወጣ፣ እምነቱም ወደ ሱኒ እስልምና ቀየረ። የሌሎችን ሰብአዊ መብት ለመከልከል ያሠበው ሁሉ ማናቸውም ዘር ቢሆን እሱ ጋኔኑ ነው ብሎ ያስተምር ጀመር። በዚህም ውቅት ወደ መካና ወደ አፍሪካም ጎብኞ ነበር።
ኔሽን ኦፍ ኢስላም እንቅስቃሴ ግን ከርሱ ጋር ስለ ተጣሉ በየጊዜ ዛቻ ያወሩበት ነበር። በ1965 እ.ኤ.አ. በገሐድ ሲናገር በጥይት ተተኩሶ ሞተ። የኔሽን ኦፍ ኢስላም ሤራ እንደ ነበረ የሚያስቡ አሉ። ማልኮም ኤክስ ዛሬ እንደ በጣም ጀግና፣ አስተዋይና ተወዳጅ ጸባይ ያለው ተናጋሪ ይታወሳል።