ማኒሽቱሹ

ከውክፔዲያ
«የማኒሽቱሹ ሐውልት»፣ በኪሽ ዙሪያ የርስት አከፋፈል ይዘግባል

ማኒሽቱሹ ከ2056 እስከ 2049 ዓክልበ. ግድም ድረስ (ኡልትራ አጭር አቆጣጠር) የአካድ ንጉሥ ነበረ። የታላቁ ሳርጎን ልጅ ሲሆን የወንድሙ ሪሙሽ ተከታይ ነበር። እናቱ ምናልባት ንግሥት ታሽሉልቱም ነበረች። የሱመር ነገሥታት ዝርዝር ቅጂዎች ለ7 ወይም 15 ዓመታት እንደ ገዛ ሲሉ፣ በሥነ ቅርስ ከዘመኑ በተገኙት ሰነዶች ምንም የዓመት ስም ገና አልተገኘም።

በወንድሙ ሪሙሽ መሞት ማኒሽቱሹ ንጉሥ ሆነ። ዘመኑ በአንድ ጽላት እንዲህ ይተረካል፦

«ማኒሽቱሹ የዓለም ንጉሥ፣ አንሻንንና ሺሪሁምን (በአሁኑ ፋርስ) ሲያሸንፍ፣ የጦር መርከቦች የታችኛው ባሕር (የፋርስ ወሽመጥ) እንዲሻግሩ አደረገ። ባሕር ማዶ (በአሁኑ ኦማን?) የነበሩት ከተሞች 32 ሲሆኑ ተባብረው ለውግያ ተሠለፉበት፣ እርሱ ግን ድል አደረጋቸው። ከዚህ በላይ ከተማቸውን አሸንፎ ገዢዎቻቸውን መታቸው። ካስነሣቸው በኋላ አገራቸውን እስከ ማዕድን ቦታ ድረስ ዘረፈ። ከታችኛ ባሕር ማዶ ተራሮች፣ ጥቁር ድንጋያቸውን ቆፈረ፣ በጀልባዎቹ ላይ ጫናቸው፣ ወደ አካድ ወደቦች አመጣቸው፤ ሐውልትም አሠራ።» እንዲሁም «የማኒሽቱሹ ሐውልት» የሚሠራው ከጥቁር ድንጋይ ነው፤ ይህም ከኦማን ዘመቻ እንደ ተገኘ ይታስባል።

እንደ ወንድሙ ሪሙሽ ዘመን ግን የማኒሽቱሹ ዘመን በአመጽ እንደ ተሞላ ይመስላል። ሪሙሽም በግድያ እንደ ሞተ፣ ማኒሽቱሹ ደግሞ በራሱ ሎሌዎች እጅ ተገደለ። ልጁ ናራም-ሲን ተከተለው።

ቀዳሚው
ሪሙሽ
አካድ ንጉሥ
2056-2049 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
ናራም-ሲን