Jump to content
አማርኛ ውክፔድያን አሁኑኑ ማዘጋጀት ትችላላችሁ - ተሳተፉበት!

ናራም-ሲን (አካድ)

ከውክፔዲያ
ሉሉቢ ላይ የናራም-ሲን ድል መታሰቢያ

ናራም ሲን ከ2049 እስከ 2030 ዓክልበ. ግድም ድረስ (ኡልትራ አጭር አቆጣጠር) የአካድ ንጉሥ ነበረ። የማኒሽቱሹ ልጅና ተከታይ ነበር። አያቱ ታላቁ ሳርጎን የአካድ መንግሥት መስራች ሆኖ ነበር። የሱመር ነገሥታት ዝርዝር ቅጂዎች ለ56 ዓመታት እንደ ገዛ ሲሉ፣ በሥነ ቅርስ ከዘመኑ በተገኙት ሰነዶች 20 የዓመት ስሞች ብቻ ይታወቃሉ። የአከታተላቸው ቀደም-ተከተል ግን አይታወቅም። ከነዚህ መካከል ብዙዎች ስለ ዘመቻዎቹ ናቸው፦

  • «ናራም-ሲን ማሪዳባንን ያጠፋበት ዓመት»
  • «ናራም-ሲን በአዙሂኑም ላይ ዘምቶ ያሸነፈበት ዓመት»
  • «ናራም-ሲን ሻቡኑም ያጠፋበት ዓመት»
  • «ኡሩክና ናግሱ ድል የሆኑበት ዓመት»
  • «ናራም-ሲን በሱባርቱ በአዙሁኑም ላይ አሸንፎ ዳሂሻታልን የማረከበት ዓመት»
  • «ናራም-ሲን እስከ ጤግሮስኤፍራጥስ መነሻዎች ደርሶ ሸናሚንዳን ድል ያደረገበት ዓመት»
  • «ንጉሡ ወደ ደብረ አማና ለውጊያ የሄደበት ዓመት»
  • «ናራም-ሲን ወደ አርዘ ሊባኖስ ተራሮች የሐደበት ዓመት»
  • «ናራም-ሲን በአማና አገር ድል አድርጎ የአርዘ ሊባኖስ ዕንጨት ያቆረጠበት ዓመት»
  • «ናራም-ሲን በሲሙሩም ላይ የዘመተበት ዓመት»
  • «ናራም-ሲን በሲሙሩም ላይ ድል አድርጎ የሲሙሩም አለቃ ባባን እና የአራሜ አለቃ ዱቡልን የማረከበት ዓመት»

አንድ ባቢሎናዊ ዜና መዋዕል ስለ ናራም-ሲን ይህን መረጃ አለው፦[1]

«ናራም-ሲን፣ የሳርጎን ልጅ፣ ወደ አፒሻል ገሠገሠ፤ በግድግዳው ቀዳዳ አድርጎ የአፒሻል ንጉሥና ሚኒስትር የሆነውን ሪሽ-አዳድን ማረከ። ወደ ማጋን ገስግሦ የማጋንን ንጉሥ ማኑ-ዳኑ ማረከ።»

ናራም-ሲን ደግሞ ሉሉባውያንን ከነንጉሳቸው ሳቱኒ አሸንፎአቸው፣ ድል ማድረጉን ለማስታወስ የታወቀ ጽላት አስቀረጸ።

በአንድ ታሪክ መሠረት፣ የኪሽ ሰዎች አመጹበትና ኢጱር-ኪሺ አለቃቸው አደረጉ። ከዚያ የሲሙሩም ገዥ ፑቲማዳል፣ የናማር ገዥ ኢንጊ፣ የአፒሻል ገዥ ሪሽ-አዳድ፣ የማሪ ገዥ ሚጊር-ዳጋን፣ የማርሐሺ ገዥ ሑፕሹምኪፒ፣ የማርዳማን ገዥ ዱሕሱሱ፣ የማጋን ገዥ ማኑ፣ የኡር ገዥ ሉጋል-አኔ፣ የኡማ ገዥ ኢር-ኤንሊላ፣ የኒፑር ገዥ አማር-ኤንሊላ ኢጱር-ኪሺን እንደደገፉት ይጠቀሳል። ናራም-ሲን ግን አመጸኞቹን ፱ ጊዜ እንዳሸነፋቸው ይላል።

ሌላ ጽላት ደግሞ ናራም-ሲን የሚከተሉትን አሸንፎ ያዙ፦ የጉቲዩም ንጉሥ ጉላዓን፤ እንዲሁም ካክሙም፣ ሉሉቡም፣ ሐሑም፣ ቱሩኩምካነሽአሙሩ፣ ዴር፣ አራሪ፣ ካሳውያንሜሉሓአራታ፣ ማርሐሺ፣ ኤላም፣ አፑም፣ አርማኑምሐና። የጉቲዩም ንጉሥ ጉላዓን ሥራዊት ከናራም-ሲን ሥራዊት 90 ሺህ ቢገድልም የናራም-ሲን 360 ሺህ ወታደሮች ድል አደረጉ ይላል።

በሌላ ጽላት ዘንድ ናራም-ሲን ከ17 ነገሥታት ትብብር ጋር ተዋጋ፣ አሸነፋቸውም፤ ከነርሱም ስሞቻቸው ሊነብቡ የሚችሉ፦ የኩጣ ንጉሥ አንማና-ኢላ፣ የፓኪ ንጉሥ ቡናን-ኢላ፣ የኡሊዊ ንጉሥ ላፓና-ኢላ፣ የሐቲ ንጉሥ ፓምባ፣ የካነሽ ንጉሥ ዚፓኒ፣ የአሙሩ ንጉሥ ሑዋሩዋሽ፣ የማርሃሺ ንጉሥ ቲሸንኪ፣ የላራክ ንጉሥ ኡር-ላራክ፣ የኒኪ ንጉሥ ኡር-ባንዳ፣ የቱርኪ ንጉሥ ኢልሹናኢል፣ የኩሻራ ንጉሥ ትሽቢንኪ፣ የአርማኒ ንጉሥ ማዳኪና ናቸው።

ናራም-ሲን በልጁ ሻርካሊሻሪ ተከተለ።

ቀዳሚው
ማኒሽቱሹ
አካድ ንጉሥ
2049-2030 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
ሻርካሊሻሪ
  1. ^ "ABC 20". Archived from the original on 2006-02-28. በ2013-09-25 የተወሰደ.