ሻርካሊሻሪ

ከውክፔዲያ
«ሻርካሊሻሪ፣ የአካድ ንጉሥ፤ ጸሓፊው ኢብኒ-ሻሩም አገልጋዩ ነው።» የሚል ማኅተም

ሻር-ካሊ-ሻሪ (አካድኛ፦ «ንጉሥ-ሁሉ-ነገስታት»፣ «የነገስታት ሁሉ ንጉሥ») ከ2030 እስከ 2013 ዓክልበ. ግድም ድረስ (ኡልትራ አጭር አቆጣጠር) የአካድ ንጉሥ ነበረ። የናራም-ሲን ልጅና ተከታይ ነበር። የሱመር ነገሥታት ዝርዝር ቅጂዎች ለ24 ወይም 25 ዓመታት እንደ ገዛ ሲሉ፣ በሥነ ቅርስ ከዘመኑ በተገኙት ሰነዶች 18 የዓመት ስሞች ብቻ ይታወቃሉ። የአከታተላቸው ቀደም-ተከተል ግን አይታወቅም። ከነዚህ መካከል አንዳንድ ስለ ዘመቻዎቹ ናቸው፦

  • «ሻርካሊሻሪ በአሙሩ ላይ በባሳን ያሸነፈበት ዓመት»
  • «ሻርካሊሻሪ በውግያ ከአክሻክ ፊት ተዋግቶ ኤላምንና ዘሃራን ድል ያደረገበት ዓመት»
  • «ቀንበሩ በጉቲዩም ላይ የተገደደበት ዓመት»
  • «ሻርካሊሻሪ የጣኦታት ቤተ መቅደስ በባቢሎን ሠርቶ የጉቲዩም ንጉሥ ሻርላግን የማረከበት ዓመት»

ከሻርካሊሻሪ ዘመን ቀጥሎ የአከታተል ቀውስ እንደ ተነሣ ይመስላል። የሱመራዊ ነገስታት ዝርዝር «ከዚያስ ማን ንጉሥ ነበረ? ማን ንጉሥ አልነበረም!» በማለት ሁኔታውን ይመስክርልናል። አራት ሰዎች - ኢርጊጊ፣ ኢሚ፣ ናኑም እና ኢሉሉ ለ፫ ዓመታት ለአካድ ዘውድ እንደ ተወዳደሩ ይላል። ከዚያም ንጉሥ ዱዱ እና ልጁ ሹዱሩል ይጠቀሳሉ። በዚያው ዘመን የአካድ ኃይል ቶሎ ደክሞ ጠላቶቹ ጉታውያን ያስቸግሩት ጀመር።

ቀዳሚው
ናራም-ሲን
አካድ ንጉሥ
2030-2013 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
ኢሉሉና ፫ ሌሎች