ሻንግ ሥያንግ

ከውክፔዲያ

ሻንግ ሥያንግ (ቻይንኛ፦ 上庠) በቻይና አፈ ታሪክ ዘንድ በጥንት በቤተ መንግሥት ከተማ የተገኘ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ነበረ።

እንኳን ከ«ሻንግሥያንግ» አስቀድሞ፣ በቅድመኞቹ አፈ ታሪካዊ ነገስታት ዘመኖች ከ2350 ዓክልበ. ጀምሮ «ቸንግ ጁ» የተባለ ትምህርት ተቋም በቤተ መንግሥት እንደ ነበር ተጽፏል።

ንጉሥ ያው ወይም ንጉሥ ሹን ምናልባት 2060 ዓክልበ. ግድም «ሻንግ ሥያንግ» (ላይኛ ወይም ከፍተኛ አቅርቦት) ለመኳንንት ጡረተኞች አቆመ፣ እንደዚህም «ሥያ ሥያንግ» (下庠 ታችኛ አቅርቦት) ለተራ ሕዝብ ሽማግሎች አቆመ። የመኳንንት ልጆች ለምክር ወይም ለትምህርት ወደ «ሻንግ ሥያንግ» መምህሮች ይሄዱ ነበር፣ የተራ ሕዝብም ልጆች ወደ «ሥያ ሥያንግ» ሄዱ። ንጉሥ ሹን ደግሞ ልዩ የሙዚቃ ክፍል መጀመርያ እንደ መሠረተ ይጻፋል።

እንዲሁም በሥያ ሥርወ መንግሥት (2000-1600 ዓክልበ. ግድም) ከፍተኛው ተቋም «ዶንግ ሹ» እንደ ተባለ ተጽፏል። በሻንግ ሥርወ መንግሥት (1600-1054 ዓክልበ.) ደግሞ ከፍተኛው ተቋም «ዮው ሥዌ» ይባል ነበር።

በሚከተለውም ዦው ሥርወ መንግሥት (1054-229 ዓክልበ.) በዋና ከተማቸው ውስጥ አምስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነበሩዋቸው፦ 1) ሻንግ ሥያንግ፣ 2) ዶንግ ሹ፣ 3) ቸንግ ጁ፣ 4) ጉ ዞንግ (የሙዚቃ ተቋም)፣ 5) ፒ ዮንግ ወይም ታይሥዌ (ማዕከለኛው ከፍተኛ ተቋም) ነበሩ።

በዚሁ ዘመን ተቋማት የ«ስድስቱ ሞያዎች» አስተማሩ፦ ሊ (禮 ሥርአተ ቅዳሴ)፣ ይዌ (樂 ሙዚቃ)፣ ሼ (射 ቀስትን ማስፈንጠር)፣ ዩ (禦 ሠረገላ መንዳት)፣ ሹ (書 ሥነ ጽሑፍ ወይም ጽሕፈት)፣ ሹ (數 ሥነ ቁጥር) ነበሩ።

የጪን ሥርወ መንግሥት (229-214 ዓክልበ.) መሥራች ጪን ሽኋንግ ከመምህራን ብዙዎቹን ገደለ፣ ከመጻሕፍትም ብዙዎቹን አቃጠለ ይባል ነበር። በመሆኑም ለ220 ዓመት ያህል የከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንዳልተመሠረተ ይመስላል።

ሃን ሥርወ መንግሥት ዘመን ንጉሥ ፒንግ ሃን አዲስ ቤተ መንግሥታዊ ተቋም በ6 ዓክልበ. መሠረተ (ታይሥዌን ይዩ)።