ቤሪክ
ቤሪክ ወይም ቤሪግ በስዊድን አፈ ታሪክ የጎጣውያን ንጉሥ ነበረ።
የጎጣውያን ታሪክ ጸሐፊ ዮርዳኔስ 543 ዓ.ም. በጻፈው ጌቲካ ዘንድ፣ በጥንት ጎጣውያን ከንጉሣቸው ቤሪግ ጋራ ከስካንዲናቪያ ወጡ፤ ባልቲክ ባሕርን ተሻግረው በማዶ የተገኙትን ሕዝብ ኡልመሩጋውያንን አሸነፉና አገሩን ይዘው ሠፈሩበት። ከዚያ በኋላ ጎረቤቶቻቸውንም ቫንዳሎችን አሸነፉ። ቤሪክና ተከታዮቹ ለጥቂት ዓመታት በዚያ አገር ገዙ፤ ከቤሪክ አምስተኛው ንጉሥ ፊሊመር የጋደሪክ ልጅ ወደ እስኩቴስ እስከ መራቸው ድረስ።
ዮርዳኔስ እንዳለው የቤሪክ ሕዝቦች በሦስት መርከቦች ደርሰው ቀስ የሚሉት በሦስተኛው መርከብ ሁነው «ጌፒዶች» (በጎጥኛ «ቀስ የሚሉ») ተብለው ተሰደቡ። ይህ በታሪክ የታወቀው የጌፒዶች ወገን ነበር።
የስዊድን ታሪክ ጸሐፊ ዮሐንስ ማግኑስ 1546 ዓ.ም. ስለ ቤሪክ ብዙ ይጨምራል። በ1722 ዓክልበ. ግድም የስዊዶችና የጎጦች ነገዶች አዋሐደ፤ ነገር ግን የሕዝብ ቁጥርና የወንበዴ ቁጥር ለአገሩ ይበዛ ነበር። ከባልቲክ ማዶ የነበሩት ሕዝቦች፣ ኤስቶናውያን፣ ሊቮናውያን፣ ፊንላንዳውያን፣. ኩሬቴስና ኡልመሩጋውያን ሲሆኑ የጎጣውያን ጓደኞች አልነበሩም። ስለዚህ በ1683 ዓክልበ. ግድም በኲሩን ሁሙልፍን በስዊድን «የውስጥ ጎጣውያን» ንጉሥ አድርጎ፣ ሌላውን ግማሽ «የውጭ ጎጣውያን» ከቤሪክ ጋራ ባልቲኩን ተሻገሩ። ከሦስቱ መርከቦች አንድ በኤስቶኒያ ጠረፍ፣ አንዱም በኩሬቴስ ጠረፍ፣ ሦስተኛውም በኡልመሩጋውያን ጠረፍ ላይ ቦታን መፈልግ ታሠበ። ሆኖም በአውሎ ንፋስ ምክንያት ሦስቱ መርከቦች ሁሉ በኡልመሩጋውያን መካከል (በኋላ ፕሩሲያ በተባለ አውራጃ) ደረሱ። ሦስተናው መርከብ «ጌፒዶች» የተሰየሙ በዚያው ሰዓት ነበር ይለናል። ኡልመሩጋውያን ተሸንፈው ቤቶቻቸውን አቃጠሉና ወደ ቫንዳሎች ሸሹ። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ጎጣውያን አጠገብ የተገኙት የፖላንድና ፖመራኒያ ዙሪያዎች እንዲሁም ከቫንዳሎች ብዙ መሬት ይዘው ሠፈሩበት። በዚህ አገር ቤሪክ መጀመርያው «የውጭ ጎጣውያን» ንጉሥ ሆኖ ተከታዩ ጋፕቱስ ነበር።