ተእያ ትክል ድንጋይ
ጢያ ክስታኔ የኢትዮጵያ ማእከላዊ ክልል
የጢያ ትክል ድንጋይ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በጉራጌ ዞን በተለይም ከአዲስ አበባ ወደ ቡታጂራ በሚወስደው መንገድ 88 ኪሎ ሜትር ርቃ ከምትገኘው ሶዶ ወረዳ በጥያ ከተማ ይገኛል፡፡ ጢያ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ ከምድር ሰቅ (ኢክዌተር) 8026′ ሰሜን 38037′ ምሥራቅ እንደሆነ የዩኔስኮ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ የጢያ ታሪካዊ ድንጋይ በቁጥር 44 የሚደርሱ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 32 ያህሉ ልዩ ልዩ ቅርጾች ምስሎች ያሉባቸው ናቸው፡፡ ሁሉም ድንጋዮች የተለያየ ርዝመት፣ ስፋትና ውፍረት አላቸው፡፡ ይሁንና በሌሎቹ ሥፍራዎች ማለትም በአገር ውስጥ በስልጢ ወይም በግብፅ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በሩቅ ምሥራቅ፣ በአውሮፓና በላቲን አሜሪካ እንደምናያቸው የመቃብር ድንጋዮች አንድም አራት ማዕዘን ወይም ድቡልቡል አይደሉም፡፡ በአብዛኛው ከታች ሰፋ ብለው ወደ ላይ እየሾጠጡ የሚሄዱ ናቸው፡፡ የአንዳንዶቹ ትክል ድንጋዮች ቁመትም ከ1-5 ሜትር ሊረዝም እንደሚችል የአርኪዮሎጂ አጥኚዎች ሥራዎች ያመለክታሉ፡፡ በድንጋዮቹ ላይ የተቀረጹት ምስሎችም የጎራዴ ወይም የሰይፍ ወይም የጩቤ፣ የጦር፣ የትራስ እንጨት፣ ክብ ዳቦ ወይም ፀሐይ መሰል ቅርጾች፣ የግማሽ ጨረቃ ምስሎች እጆቹን ወደላይ የዘረጋ ሰው ክንዶች ናቸው፡፡
በቅድመ ታሪክ ይኖሩ የነበሩት ኢትዮጵያውያን ድንጋዮቹን ለምን እንደተከሏቸው ባይታወቅም ትልቅ የጦር መሪዎች፣ ገዥዎችና ታላላቅ ሰዎች የተቀበሩባቸው ሥፍራዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገመታል፡፡ ሊቃውንቱ ይህን ግምት የወሰዱት በአሁኑ ጊዜ በሶዶ፣ በስልጢና በጌድኦ ካሉት የመቃብር ድንጋዮች እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡ ምንም እንኳን ትክል ድንጋዮቹ መች እንደተተከሉ በትክክል ማወቅ ባይቻልም አንዳንድ አጥኝዎች ከ800 ዓመት በፊት እንደተተከሉ ይገምታሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ከቅድመ ታሪክ በፊት የነበሩ ኢትዮጵያውያን የተሠሩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገምታሉ፡፡ የተወሰኑ ትክል ድንጋዮቹ ለብዙ ዓመት ሳይወድቁ የቀሩበትን ምክንያት ሲያብራሩም ከመሬት በታች ስምንት ሜትር ርዝመት ስላላቸው እንደሆነ ይገልጣሉ፡፡ በድንጋዮቹ ላይ ያለው የሰይፍ ብዛት ሟች ምን ያህል ልጆች እንዳሉት እና ምን ያህል አውሬ እንደገደለ ያሳያሉ፡፡
የጢያ ትክል ድንጋይ የአውሮፓውያንን ዓይን መሳብ ከጀመረ ብዙ ዓመትን ያስቆጠረ ሲሆን ኢጣሊያውያን የአርኪዮሎጂ ባለሙያዎች ጥልቅ ጥናት ባያካሂዱም ከ70 ዓመት በፊት ኢትዮጵያን ወርራ በነበረችበት ጊዜ የመጡ ተመራማሪዎች ስለድንጋዮቹ መኖር ዘግበዋል፡፡ የዛሬ 84 ዓመት ወደኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው ጀርመናዊ አጥኚም በዚህ ሥፍራ በኩል አልፎ እንደነበረና የጎራዴ ምስል ያላቸው የድንጋይ ትክሎች እንዳየ በጥናቱ አመልክቷል፡፡ ከዚህ አጥኚ ቀደም ሲልም ኑቪለ እና ፔር ዛይስ (Neuville and Pere Azais.) የተባሉ አውሮፓውያን ጥያን መጎብኘታቸውን የዩኔስኮ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
ትራቭል አፍሪካ በተሰኘው የጎብኝዎች የኢንተርኔት መረጃ ምንጭም ጢያ የሚገኙት ትክል ድንጋዮች አዳዲ ማርያም ከተባለው ከድንጋይ ፍልፍል የተሠራው ቤተ ክርስቲያን፣ ሀረ ሸይጣን ከተባለው ክሬተር ሐይቅ፣ ከመልካ አዋሽ መስመር ጋር ስለሚገኙ ለጎብኝዎች በአንድ ጉዞ ብዙ ታሪካዊ ቦታዎችን ለመጎብኘት ያስችለዋል በማለት አስፍሯል፡፡ ፊሊፕ በሪግ የተሰኙት አጥኚም የጥያ ትክል ድንጋይ ጥንታዊነትን ለዓለም በማስተዋወቅ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ይታወቃል፡፡ የፈረንሳይ አርኪዮሎጂ ባለሙያዎች መረጃ እንደሚያመለክተው የጢያ ትክል ድንጋይ ባለበት ቦታ ዕድሜያቸው ከ18-30 የሚገመቱ ብዙ ወጣቶች በአንድ ላይ የተቀበሩበት ሥፍራ ነው፡፡
የፈረንሳይ ሊቃውንት እንደሚሉት ሥፍራው የመቃብር ቦታ ከሆነ ከዓለም የመቃብር ሥፍራዎች አኳያ የምንመለከተው ይሆናል፡፡ በኦክስፎርድ ጁኔር ኢንሳይክሎፒዲያ (ቅጽ 12፡1957) ‹‹ቱምስ›› (tombs) በሚል ርዕስ ሰፍሮ እንደምናገኘው ደግሞ በጥንታዊት ግሪክ ሦስት ዓይነት የመቃብር ዓይነቶች ነበሩ፡፡ እነሱም ‹‹ስቴል››፣ ‹‹ሙስሊየም››እና ‹‹ሳርኮፋገስ›› የሚባሉት ናቸው፡፡ ‹‹ስቴል›› የሚባለው የመቃብር ዓይነት የሟቹ ምስል ቁም ለቁም የተቀረጸበት ወይም የቤተሰቡ አጠቃላይ ሁኔታ የሚያመለክት ድንጋይ ተቀርጾ የሚተከልበት ሲሆን ይህም ከክርስቶስ ልደት በፊት ከስድስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የነበረ ነው፡፡
ትራቭል አፍሪካ የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚያወሳው ከጥያ ጋር የሚመሳሰሉ ትክል ድንጋዮች በሶዶ ወረዳ 160 ሥፍራዎች ሲኖሩ ከነዚህም ድንጋዮች በኢማም አሕመድ ኢብራሂም (አሕመድ ግራኝ) እንደተተከሉ በአፈ ታሪክ ቢነገርም በትክክል ማን እንደተከላቸው ግን አይታወቅም፡፡ የአርኪዮሎጂ አጥኚዎች እንደሚሉት የጢያ ትክል ድንጋዮች ከሰሐራ በታች ካሉ ትክል ድንጋዮች ከአክሱም በስተቀር በዕድሜ የሚበልጣቸው የለም፡፡
ከላይ የተጠቀሱትን ምክንያቶች መሠረት በማድረግ ቦታው እ.ኤ.አ ከ1980 ጀምሮ በዓለም የቅርስ መዝገብ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
Advertisements