Jump to content

ቱዲያ

ከውክፔዲያ

ቱዲያአሦራዊው ነገሥታት ዝርዝር መሠረት መጀመርያው የታወቀው የአሦር ንጉሥ ነበር። ከአሥራ ሰባቱ «በድንኳን የኖሩ ነገስታት» አንደኛው ነው።

የኤብላ ጽላቶች ተገኝተው መጀመርያ ሲተረጎሙ የቱዲያ ሕልውና እርግጥኛ መስሏል። ከኤብላ ጠቅላይ ሚኒስትር ከኤብሪዩም ጋራ ስምምነት እንደ ተዋዋለ ይዘገባል። በዚህ ውል ዘንድ አሦር በኤብላ ግዛት አንድ ካሩም ወይም ጥገኛ የነጋዴ ሠፈር እንዲያቆም ተፈቀደ። ኤብሪዩም የኤብላ ዋና አማካሪ ወይም ሚኒስትር የሆነው ለ፲፭ ዓመታት (ከ2107-2092 ዓክልበ. አካባቢ) መሆኑ ይታወቃል። መረጃው ለእንቆቅልሹ ሁሉ በፍጹም ቢስማማም፣ ሆኖም በኋላ ስለዚሁ ውል ያሳተሙት የሥነ ቅርስ መምኅሮች እንደሚሉት፣ ይህ ንባብ የተሳተ ነበርና «የአሦር ንጉሥ ቱዲያ» ሳይሆን፥ ያልተሰየመ «የአባርሳል ንጉሥ» ነበር የተዋወለው። ይህ «አባርሳል» ከተማ መታወቂያ ግን አልተገኘም። በ2070-1600 ዓክልበ. ግ. የአሦር መንግሥት ብዙ ካሩምሐቲ ያስተዳደረው እንደ ነበር ይታወቃል። በዚህ ሰነድ የቱዲያ ስም ማንበብ ስኅተት ከሆነ እኚህ መምኅራን እንደሚሉ የቱዲያ ሕይወት እንደገና አጠያያቂ ሆኗል።

ከዚያ ትንሽ በፊት በማሪ የነገሠው ንጉሥ ኢብሉል-ኢል (2127-2115 ዓክልበ. ግድም) በአንድ ሰነድ «የማሪና የአሹር ንጉሥ» ይባላል። ስለዚህ ከአሦር መጀመርያው ንጉሥ ቱዲያ አስቀድሞ አሹር የማሪ ግዛት እንደ ነበር ይመስላል።

ቀዳሚው
ማሪ ንጉሥ ኢብሉል-ኢል
አሦር ንጉሥ
2115-? ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
አዳሙ