አሹር (ከተማ)
አሹር (ቃልአት ሺርቃት) | |
---|---|
የአሹር ከተማ አርማ | |
ሥፍራ | |
መንግሥት | የአሦር መንግሥት ሚታኒ (1440-1366 ዓክልበ.) |
ዘመን | ከ2380 እስከ 622 ዓክልበ. |
ዘመናዊ አገር | ኢራቅ |
ጥንታዊ አገር | አሦር |
አሹር የአሦር ጥንታዊ ዋና ከተማ ነበር። ፍርስራሹ በጤግሮስ ወንዝ ምዕራብ ዳርቻ አሁን ሊታይ ይችላል። «አሹር» የሚለው ስም ደግሞ በአካድኛ (አሦርኛ) ማለት የአገሩ አሦር ስም እና የአረመኔ ሃይማኖታቸው ዋና ጣኦት አሹር ነበር። በዕብራይስጥም «አሹር» ማለት ወይም አገሩ ወይም አሦር (የሴም ልጅ) ሊሆን ይቻላል።
አሹር ከተማ የተሠራው ከ2380 ዓክልበ. አስቀድሞ ይሆናል። በ2115 ዓክልበ. ግ. ኢብሉል-ኢል «የማሪና የአሹር ንጉሥ» ተባለ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ (2106 ዓክልበ. ግ.) መጀመርያው አሦራዊ ንጉሥ ቱዲያ ከኤብላ ሚኒስትር ኤብሪዩም ጋር ስምምነት እንደ ተዋዋለ ይታወቃል። በ1980 ዓክልበ. ገደማ ጥንታዊው የአሦር ንጉሥ ኡሽፒያ የአሹር ቤተ መቅደስ መስራች እንደ ነበር ይተረካል። በዚህ ወቅት አሹር የአሦር ከተማ-አገር መቀመጫ ሆነ። 1 እሽመ-ዳጋን በ1678 ዓክልበ. ከሞተ በኋላ የባቢሎን ንጉሥ ሃሙራቢ ሥልጣን ያዘ፤ የአሹር ነገሥታት ለትንሽ ጊዜ ለባቢሎን ተገዥ ቢሆኑም በይፋ በነፃነት ገዙ። ከ1440 ግድም አሹር በሚታኒ ንጉሥ ሻውሽታታር ተዘርፎ ከዚያ እስከ 1366 ዓክልበ. ድረስ የአሹር ነገሥታት ለሚታኒ ይገዙ ነበር። በ1366 ዓክልበ. ግን 1 አሹር-ኡባሊት የሚታኒ ሰዎችን አባረራቸውና የአሦር መንግሥት ይስፋፋ ጀመር። በኒኑርታ-አፒል-ኤኩር ዘመን (በ1195 ዓክልበ. ገደማ)፣ አንድ የምድር መንቀጥቀጥ በአሹር የነበረውን መቅደስ በሙሉ አጠፋው።
በ887 ዓክልበ. 2 አሹር-ናሲር-ፓል የአሦርን ዋና ከተማ ከአሹር ወደ ካልሁ አዛወረው። የአሦር መንግሥት በ622 ዓክልበ. በወደቀበት ጊዜ የአሦር ጠላቶች ባቢሎን፣ ሜዶንና እስኩቴስ ሰዎች አሹርን አጠፉት። ሆኖም በኋላ አዲስ መንደር በሥፍራው ቆሞ እስከ 14ኛው ክፍለ ዘመን ዓ.ም. ድረስ ይቆይ ነበር።