አሦር (የሴም ልጅ)

ከውክፔዲያ

አሦር (ዕብራይስጥ፦אַשּׁוּר /አሹር/) በብሉይ ኪዳን ኦሪት ዘፍጥረት (የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ) ምዕራፍ 10 መሠረት ከኖኅ ልጆች መካከል የሴም ሁለተኛ ልጅ ነበረ። የጥንታዊ አሦር ሀገርና ሕዝብ አባት መሆኑ ይታመናል።

በዘፍጥረት 10፡11 መሠረት ይህ አሦር ከሰናዖር ወጥቶ «ነነዌን፥ የረሆቦትን ከተማ፥ ካለህን፣ በነነዌና በካለህ መካከልም ሬሴንን ሠራ፤ እርስዋም ታላቂቱ ከተማ ናት።»

አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ግን ከፊተኛው ቁጥር ከ10፡10 በመውሰድ አድራጊው እንደ ናምሩድ ቆጥረውት፣ ናምሩድ እራሱ ወደ አሦር (ወደ ሀገሩ) ወጥቶ እኚህን ከተሞች እንደ ሠራ ይላሉ። ቢሉም፣ «ወደ» የሚል ቃል በእብራይስጡ መጽሐፍ የለም።

1ኛው ክፍለ ዘመን ዓ.ም. የኖረው አይሁዳዊ ታሪክ ጸሐፊ ፍላቭዩስ ዮሴፉስ እንዲህ ብሎ ጻፈ፦ «አሦር በነነዌ ከተማ ኖረ፤ ተገዦቹንም 'አሦራውያንን' ብሎ ሰየማቸው፤ እነርሱም ከሌሎች ይልቅ ዕድለኛ አገር ሆኑ።» (Antiquities, i, vi, 4).