ማዴ

ከውክፔዲያ

ማዴ ወይም ማዳይ (ዕብራይስጥ፦ מדי /ማዳይ/፤ ግሪክ፦ Μηδος /ሜዶስ/) በኦሪት ዘፍጥረት 10 መሠረት የያፌት ልጅና ከኖህ 16 ልጅ ልጆች አንዱ ነው።

ዮሴፉስና በሌሎች የድሮ ጸሐፊዎች ዘንድ፣ ማዴ በስሜን-ምዕራብ ፋርስ የኖሩት የሜዶን ሰዎች (ወይም «ሜዴስ»[1]) አባት ነበረ። በግሪክ «ሜዶን» የተባለው ሕዝብ በአሦርኛና በዕብራይስጥ «ማዳይ» ይባል ነበርና። እንዲሁም ዛሬ በአካባቢ የሚኖሩት ኩርዶች እስካሁን ከሜዶን ሰዎችና ከማዳይ እንደተወለዱ ይላሉ። ሜዶን ከ700 ዓክልበ. ግድም ጀምሮ ሲታወቅ፣ በአካባቢያቸው የሌሎች ብሔር ስሞች ማቲዬኔ (650-617 ዓክልበ. ግድም)፣ ማናይ (850-650 ዓክልበ. ግድም) እና ሚታኒ (1507-1307 ዓክልበ. ግድም) ደግሞ ከማዴ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ታሥቧል።

መጽሐፈ ኩፋሌ ውስጥ ስሙ «ማዳይ» ሲጻፍ፣ የሴምን ልጅ ስለ አገባት በራሱ ርስት (በማጎግና በደሴቶቹ መካከል፣ ወይም ስሜን አውሮፓ፤ 9፡22) ከመኖር ይልቅ በሴም ዘር መካከል መኖር ፈለገ። ስለዚህ የሚስቱን ወንድሞች ኤላምአሦርአርፋክስድ ለምኖ በመጨረሻ ከሴም ልጆች ርስት መካከል አንድ አገር ተቀበለ። ይህ አገር ስም በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ «መቄዶን» ሲጻፍ (10፡21)፣ በጥንታዊ ቅጂዎች (በግሪክ፣ እብራይስጥ፣ አራማይስጥ) ወዘተ) ግን «ሜዶን» ነው። በነዚህ ቅጂዎች «ሜዶን» ደግሞ በ9፡10 ሲጠቀስ ስሙ በአማርኛ ትርጉም «መእዳይ» ሆኖ ይጻፋል። በዘመናት ላይ ቅጂዎችን የሠሩት ካህናት በአንዳንድ ስፍራ የሜዶንና የመቄዶን ስሞች በደንብ አለዩምና።

በ8፡37 ደግሞ በአማርኛ ትርጉም የአርፋክስድ ልጅ ቃይንም ሚስት የያፌት ልጅ የአበዳይ ልጅ ሜልካ ነበረች ሲለን፣ በድሮ ልሳናት ግን በ«አበዳይ» ፋንታ «ማዳይ» ይላል። በዚህ ትውልድ መሠረት አብርሃምሰሎሞንኢየሱስ ሁላቸው የሴም ወይም የካም ዘር ብቻ ሳይሆን የያፌት ዘር ደግሞ አለባቸው።

በሊቃውንት ዘንድ የሜዶን ሕዝብ የሕንዳዊ-ኢራናዊ ቋንቋዎች ቤተሠብ አባሎች ነበሩ። ሚታኒ በጥንት ዘመን ከአራስ ወንዝ ዙሪያ ተነሥቶ ሶርያን የወረረ ሕዝብ ነበረ። በሶርያ ሑርኛ ተለመዱ፤ ስሞቻቸው ግን የሕንዳዊ-ኢራናዊ ቋንቋዎች ዘመዶች እንደነበሩ ይገልጻል። የሜዶን ሰዎች የዞራስተር (ዛራጡሽትራ) ሃይማኖት ተከታዮች ሆነው ከሁሉ ጥንታዊ በሆኑት መጽሐፍታቸው ዘንድ፣ መጀመርያ መኖርያቸው አገር «አይርያነም ቫኤጃህ» ሲባል በአራስ ወንዝ ሸለቆ አካባቢ ተገኘ (ቡንዳሂሽን 29፡12)። ይህ አውራጃ በኋላ አራን ተባለ፤ ከዚህም በላይ ይህ ወንዝ በአራራት ተራራ አጠገብ ይመንጫል።

በተጨማሪ በስሜን በርማ (ምየንማ) በተገኘው ጂንግፖ (ካቺን) ነገድ እምነት ዘንድ፣ እነሱ «ማዳይ» ከተባለ ጥንታዊ ቅድመ-አያት ተወለዱ።

  1. ^ «መጽሐፍ ቅዱስ መደበኛ ትርጉም ከማጥኛ ጽሑፊች ጋራ» እንዳለው «ማዴ ባኋላ ሜዴስ የተባሉት ናቸው።»