ሞሳሕ

ከውክፔዲያ

ሞሳሕ (ዕብራይስጥ፦ משך /ሜሼክ/) በኦሪት ዘፍጥረት ዘንድ የያፌት ልጅ የኖህም ልጅ ልጅ ነበረ። በመጽሐፈ ኩፋሌ ደግሞ ስሙ «ሞስክፍ»፣ «ሞሳኮ» ተጽፎ ይታያል።

አይሁድ ታሪክ ጸሐፊው ፍላቪዩስ ዮሴፉስ መሠረት (1ኛው ክፍለ ሸመን የጻፈ)፣ ከሞሳሕ የተወለደው ሞሶኬኒ የተባለ ብሔር ነበር። «አሁን ቀጴዶቅያውያን ሲሆኑ የከተማቸው ስም ማዛካ የቀድሞ ስማቸው ትዝታ ነው» ብሎ ጻፈ።

ይህም ብሔር ለጥንት ግሪካውያን ጸሐፍት (ከ550 ዓክልበ. ጀምሮ) «ሞስኮይ» ተብሎ ይታወቅ ነበር። ያንጊዜ የሞስኮይ ሕዝብ በአሁኑ ቱርክጂዮርጂያአርሜኒያ አገራት ውስጥ እንደ ኖረ ጻፉ።

ከዚያ በፊት፣ ከአሦራውያን ጎረቤቶች መካከል ሲሆኑ ሙሽኪ በሚል ስያሜ ይታወቁ ነበር። እኚህ ሙሽኪ በአሦር ንጉሥ 2 ሳርጎን ዘመን (700 ዓክልበ. ግድም) በኪልቅያ (በደቡብ አናቶሊያ) ሲገኙ የታባል መንግሥት ተባባሪዎች ነበሩ። ሙሽካውያን እና ታባላውያን በ1190 ግድም የኬጥያውያን መንግሥትን ወርረው ያፈረሱት ናቸው። ሌላ ስማቸው «ብሩጊ» ሲሆን ከመቄዶን (አውሮጳ) ወደ ትንሹ እስያ ተሻግረው ከ«ብሩጊ» ወደ «ፍሩጊ» ቀይረውት አገሩ ለነርሱ ፍርግያ እንደ ተባለ ይታመናል።

በቅዱስ አቡሊድስ ዜና መዋዕል (226 ዓ.ም.) የሞሳሕ ተወላጆች እልዋርያውያን ነበሩ (እልዋርያ የአሁኑ አልባኒያና ቀድሞ ዩጎስላቪያ ሲሆን)።

በተጨማሪ በአንዳንድ አስተሳሰብ፣ የሞሳሕ ልጆች ምናልባት ለግብጽ ታሪክ የታወቀውን መሽወሽ ሕዝብ ያጠቀልል ነበር። «መሽወሽ» ኬጥያውያንንም ግብጽንም በ1190 ከወረሩት ከ«ባሕር ሕዝቦች» መካከል ይቆጠሩ ነበር። ከ1390 ዓክልበ. ያህል ጀምሮ መሽወሽ በሊቢያ ቀሬናይካ እንደ ተመሠረቱ ይመዘገባል። አንድ የመሽወሽ ቅርንጫፍ ግብጽን ወርሮ ከ1000 እስከ 740 ዓክልበ. ድረስ በጥቂት ሥርወ መንግሥታት (ከኩሻውያን በፊት) ግብጽን ይገዙ ነበር። እስካሁንም በስሜን አፍሪካ የሚገኙት በርበሮች ሕዝቦች ራሳቸውን «ኢማዚቀን» ሲሉ፣ ይህ ስም ከግብጽኛ «መሽወሽ»፣ ከግሪክ «ማዙወስ»፣ ከሮማይስጥ «ማዛከስ» ግንኙነት እንዳለው ይታወቃል።

በጆዮርጂያ የቆዩት የሙሽኪ ነገዶች እስካሁን በዚያ ሲገኙ ስማቸው መስከጢ፣ መስክ፣ ወዘተ. በሚል ስያሜዎች ይታያል። እንደ ጂዮርጂያና አርሜኒያ ሕዝቦች ልማድ፣ ከሞሳሕ ያፌት የተወለዱ ብቻ ሳይሆን፣ ከቶቤልና ከቴርጋማ ጋሜር ዘር ጋር ተከለሱ።

1490 ዓ.ም. አኒዩስ ዴ ቪቴርቦ የተባለ ጣልያናዊ መነኮሴ ባሳተመው ጽሑፍ ዘንድ፣ የባቢሎን ታሪክ ጸሓፊ ቤሮሶስ (290 ዓክልበ.) ስለ ኖኅ ልጆች ብዙ መዝገቦች አቅርቦ ነበር። በዚህ በኩል፣ በናምሩድ 13ኛው ዓመት የያፌት ልጅ ሳሞጤስ የሰፈረበት ሀገር በኋለኛ ጊዜ ጋሊያ እና ፈረንሳይ የተባለው ክፍል ሆነ። ከአኒዩስም ቀጥለው የጻፉት ሊቃውንት ይህ ሳሞጤስ መታወቂያና የሞሳሕ ማንነት አንድላይ ሲሆን፣ ከጋሊያ በላይ በታላቅ ብሪታንያ ደግሞ መጀመርያው የነገሠ ነው የሚል ዝርዝር ጨመሩ። ዛሬ ግን አብዛኛው መምህሮች የአኒዩስ መጽሐፍ እንደ ሐሣዊ መረጃ ይቆጥሩታል።

16ኛው ክፍለ ዘመን ዓ.ም. ጀምሮ አንዳንድ የአውሮጳ ሊቅ የሞሳሕ ልጆች በመስኮብ ሠፈሩ የሚል አሣብ አቀረቡ። እንዲሁም አንድ የሩስያ ተውፊት (ከ17ኛው ክፍለ ዘመን የታወቀ) እንደሚለው፣ የመስኮብ መስራች «ንጉሥ ሞሶክ ያፌት» ሲሆን፣ ለርሱና ለሚስቱ «ክቫ» ስሞች ስሙ «ሞስክቫ» (መስኮብ) ሆነ።

ትንቢተ ሕዝቅኤል 38 እና 39፣ ሞሳሕ ይጠቀሳል። «በጎግ ላይና በማጎግ ምድር ላይ፣ በሞሳሕና በቶቤል ዋነኛ አለቃ ላይ» ይላል።

ሴም ልጅ አራም ልጆች አንዱ «ሞሶሕ» ሲባል በ1 ዜና መዋዕል ግን ስሙ «ሞሳሕ» ተጽፏል። ይህ ከያፌት ልጅ ሌላ ሰው መሆን አለበት።