ኩሽ (የካም ልጅ)

ከውክፔዲያ

ኩሽ (ዕብራይስጥ፦כּוּשׁ) በኦሪት ዘፍጥረት ምዕ. 10 መሠረት ከኖህ ልጆች መካከል የካም በኩር ልጅ ነበረ። የኩሽ ልጆች ሳባኤውላጥሰብታራዕማሰብቃታ ሲሆኑ ከዚህ በላይ የናምሩድ አባት ይባላል።

የአይሁድ ታሪክ መምህር ፍላቭዩስ ዮሴፉስ (100 ዓ.ም. ገደማ) እንደ ጻፉት፣ «ከካም አራት ልጆች፣ እድሜ የኩሽን ስም ከቶ አልጎዳምና፤ እርሱ የነገሠባቸው ኢትዮጵያውያን ዛሬውም ቢሆን በራሳቸውና በእስያም ሰዎች ሁሉ ዘንድ 'ኩሻውያን' ይባላሉና።»

ከጥንት ጀምሮ ታሪካዊው የኩሽ መንግሥት በአሁኑ ስሜን ሱዳን እንደ ኖረ ሊጠራጠር አይችልም። ይኸው ስያሜ ከቅድመኞቹ የግብጽ መዝገቦች ከ2 መንቱሆተፕ ዘመን (ከ2092 ዓክልበ.) ግድም ጀምሮ ታውቋል። በኋለኛ ዘመን «ኩሽ»ና የግሪክ ትርጉሙ Αιθιοπία (/አይቲዮፒያ/) ከሳህራ ደቡብ ላለው ምድር በሰፊው ይጠቀም ነበር። ደግሞ በአፍሪቃ ቀንድ ዙሪያ የሚኖሩት 'ኩሺቲክ ሕዝቦች' (ሶማሌአፋርኦሮሞ፣አገው፣ቅማንት፣ስልጤ፣ጉራጌ፣ሲዳማ፣ጋሞና ሌሎች) ይህን ስም ከዚሁ ኩሽ ተቀበሉ፤ ከተወላጆቹ መሃል ተቆጥረው ነው። አብዛኛው ጊዜ ኩሺቲክ የሚባሉ የቤጃ ሕዝብም ከኩሽ የደረሰ ልዩ የትውልድ ልማድ አላቸው።

1760 ዓ.ም. ያሕል ኢትዮጵያን የጎበኘው የስኮትላንድ መንገደኛ ጄምስ ብሩስ እንዳለው፣ «ሀበሾቹ ከድሮ ጀምሮ የተወረሰ ትውፊት አላቸው»፤ እሱም፦ ከማየ አይህ ቀጥሎ የካም ልጅ ኩሽ ከነቤተሠቦቹ በአባይ ወንዝ ላይ ተጉዘው ገና ሰዎች ሳይኖሩበት የአትባራ ሜዳ አገኙ። ከዚህም ሜዳ የኢትዮጵያን ደጋ አይተው ተነሡበትና አክሱምን ሠሩ። በኋላ ጊዜ ወደ ሜዳው ተመልሰው መርዌን ሠሩ። በብሩስ ዘመን የኖሩ አውሮፓዊ ሊቃውንት ግን ኩሽ ወደ አፍሪካ የገባ በባብ ኤል መንደብ እንደ ነበር ስለ አመኑ፣ ይህን ታሪክ አልተቀበሉም ነበር።[1]. በተጨማሪ፣ በመጽሐፈ አክሱም መሠረት ኩሽ የርስቱን ድርሻ ለማመልከት የአክሱምን ታላቅ ሀውልት እንዳቆመ፣ ልጁም ኢትዮጲስ በዚያ እንደተቀበረ ይታመናል። አቶ ብሩስም በኖረበት ዘመን ይህ መጽሐፍ በኢትዮጵያ ከክብረ ነገሥት ጋር እኩል ሆኖ እንደ ከበረ ጽፎ መሰከረ።

በኢትዮጵያ ታሪካዎ ልማድ ዘንድ፣ አባቱ ካም ከሞተ በኋላ ኩሳ በኢትዮጵያ ለ50 ዓመት ነገሠ፣ ከዚያ ሃባሢ ለ40 አመት፣ ሰብታ ለ30 አመት ነገሡ።

ፋርስ እስላም ታሪክ ጸሐፊ ሙሐመድ እብን ጃሪር አል-ታባሪ907 ዓ.ም. እንደ ጻፈው የኩሽ ሚስት የቲራስ ልጅ ባታዊል ሴት ልጅ ቃርናቢል ስትሆን «ሀበሾችን፣ ስንዶችንና ሕንዶችን» ወለደችለት።

  1. ^ Bruce, Travels to Discover the Source of the Nile, p. 305