Jump to content

የአክሱም ሐውልት

ከውክፔዲያ
የአክሱም ሀውልት በትግራይ ክልል በ2001 ዓ.ም.

የአክሱም ሃውልት (እንግሊዝኛ: Obelisk of Axum) ወይም Rome Stele እየተባለ በተለምዶ የሚጠራው በኢትዮጲያአክሱም ከተማ የሚገኝ የአለማችን ረጅሙ ትክል ድንጋይ ሃውልት ነው። ይህ ሀውልት 1700 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን የ24 ሜትር (78 ጫማ) ርዝመት አለው። 160 ቶን የሚመዝነው ይህ ግዙፍ ድንጋይ መሠረቱ አከባቢ ሁለት የሀሠት በር መሣይ ፍልፍሎች አሉት። የዚህ ሀውልት ጌጥ ይህ ብቻም አይደለም በያንዳንዱ ጎን የመስኮት ቅርጽ የያዙ ፍልፍሎች ሲኖሩት በመጨረሻው ጫፍ ላይ ደግሞ በብረት ፍሬም የታገዘ የግማሽ ክብ ነው::

በአክሱም ዘመነ መንግስት እንዲገነባ የተደረገው ይህ ሀውልት ወይም በእንግሊዝኛው "stele" የሚባለው በአክሱም ከተማ ከሌሎች መሠል ሀውልቶች ጋር ኢንዲቆም የተደረገው በ4ኛው ምዕተ አመት አካባቢ ሲሆን። ይህም የጥንታዊ አክሱም ምን ያህል ስልጣኔ እንደነበራት ጠቋሚ ነው። ከኩሻይቲክ የሜሮይ አገዛዝ የተወሰደ እንደሆነ የሚነገርለት ይህ ሀውልቶችን የማቆም ስራ አሁንም ድረስ በአከባቢው ተመሳሳይ ስራዎችን መመልከት ይቻላል። እነዚህ ሀውልቶች የሚቆሙት በመሠረታቸው ለሚቀበሩ ንጉሳዊ ቤተሠቦች ነው:። በዚህም ከፍተኛ ስልጣን የነበራቸው መሳፍንቶች መቃብር ላይ የሚቆሙት ሀውልቶች በብዛት በተፈለፈሉ የሀሰት በር እና መስኮቶች ያጌጡ ናቸው። እንዲሁም የሟቹ ንጉሳዊነት በቀነሠ ቁጥር በመቃብሩ ላይ የሚቆሙት ሀውልቶችም ውበት (የሚፈለፈሉት የሀሰት በር እና መስኮት መሠል ቅርጾች ብዛት) በዚያው ልክ ይቀንሳል። ለዚህም ነው ብዛት ያላቸው ቅርጽ አልባ ሀውሎቶችን በየቦታው መመልከት የሚቻለው። ትልልቅ የሚባሉት ደግሞ አነስተኛ ቁጥር አላቸው።

የሰሜኑ የአክሱም ሀውልቶች ፓርክ በመካከል ላይ የንጉስ ኢዛና ሀውልት እና መሬት ላይ ተጋድሞ የሚገኘው ታላቁ የአክሱም ሀውልት

ከሀውልቶች ሁሉ በመጨረሻ በ4ኛው ክፍለ ዘመን እንደቆመ የሚታወቀው የንጉስ ኢዛና ሀውልት ነው። አብዛሀኛዎቹ ትክል ድንጋዮች በመሰረት ጥንካሬ ማነስ የወደቁ ሲሆን ከነዚህም መካከል ተጠቃሽ የሚሆነው በእርዝመቱ ተወዳዳሪ የሌለው (የ33 ሜትር ርዝማኔ ያለው) ታላቁ ሀውልት በመሬት ላይ መውደቁ ነው። በሀውልቶቹ ላይ የደረሱት ችግሮች ብዙ ናቸው። ከነዚህም ውስጥ በተደጋጋሚ የሚከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ (የአክሱም ከተማ ለመሬት መንቀጥቀጥ በአንፃራዊ ሁኔታ የተጋለጠች ነች። በ19ኛው ምዕተ-አመት ከዋና ዋናዎቹ የንጉስ ሀውልቶች መካከል የንጉስ ኢዛና ሀውልት ብቻ ሳይወድቅ ተገኝቷል።

በ1928 ዓ.ም ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ ይህን ሀውልት በጊዜው በነበረው የፋሽስት ኢጣሊያ ገዝ ትዕዛዝ መሰረት የጣልያን ወታደሮች የኣክሱምን ሓውልት ከወደቀበት ኣንስተው ወደ ሮም ወሰዱት። በዚህ ጊዜ የፋሺስት አገዛዝ እንደ ጦር ምርኮ እና የሮም ግዛት መስፋፋት ምልክት አድርጎ በመውሰድ በሮም አደባባይ ላይ እንዲተከል አድርጓል።

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዳለቀ ጣልያን የዘረፈችውን የኣክሱም ሃውልት ለኢትዮጵያ እንድትመልስ በተስማማችው መሠረት ላለመፈጸም እስከ የካቲት ፲፱፻፷፮ ዓ.ም. ብዙ ግለሰቦች ቢማጸኑም ኣሻፈረኝ ኣለች። የመጨረሻውም ምክንያት ጣልያን ገንዘብ፣ ኣሜሪካ ኣውሮፕላን ስለከለከሉ ነበር። በእነዚህ ምክንያቶች ያልተደሰቱት ዶ/ር ኣበራ ሞላ ኢንተርኔትን በመጠቀም የመላኪያ ገንዘብ ለማስባስብና ሐውልቱንም በትናንሹ ኣስቆርጦ መላክ እንደሚቻል ለጣሊያኖች ካሳወቁ በኋላ ኣጣብቂኝ ውስጥ የገቡት ጣልያኖች እራሳቸው ወጪውን ከፍለው ከወሰዱበት እንደሚመልሱት ተስማሙ። በእዚሁ መሠረት የጣልያን መንግሥት ወደ ኣሥር ሚሊዮን ዶላር ኣውጥቶ ሐውልቱ ኣክሱም ከተማ ተመልሶ ተተክሎ ነሓሴ ፳፱ ቀን ፳፻ ዓ.ም. ተመርቋል።

የውጭ መያያዣዎች

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የሓውልቱ ከሮም ወደ ኢትዮጵያ ኣመላለስ

[1] [2] [3] Archived ማርች 15, 2012 at the Wayback Machine [4] Archived ኤፕሪል 3, 2012 at the Wayback Machine [5] Archived ኤፕሪል 3, 2012 at the Wayback Machine [6] [7]


በ"Wikimedia Commons"
(የጋራ ፎቶዎች ምንጭ)
ስለ Obelisk of Axum የሚገኛኙ
ተጨማሪ ፋይሎች አሉ።