ታምራት ሞላ
ታምራት ሞላ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ ዘፋኝ ሲሆን ብዙ ዘመናዊና ባህላዊ የሙዚቃ ስራወችን በማቅረብ ይታወቃል። በ፳፻ ዓ.ም የካንሰር በሽታ የተገኘበት ድምጻዊ ታምራት በህክምና ከህመሙ ሙሉ በሙሉ እንደ ተሻለው አሳውቆ የነበረ ቢሆንም ህመሙ እንደገና አገርሽቶበት በተወለደ በ፮፱ አመቱ በየካቲት ፬ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። የቀብር ሥነ ሥርዓቱም በዕለቱ በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተሰቦቹ ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ ፣ የሙያ አጋሮቹ እና አድናቂዎቹ በተገኙበት ተፈጸሟል [1]።
ታምራት ሞላ በ፲፱፻፴፮ ዓ.ም. በጎንደር ክ/ሀገር ተወለደ። ታምራት የ፩ኛ ደረጃ ትምህርቱን እዚያው ጎንደር ከጨረሰ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት አድቬንቲስት ሚስዮን ትምህርት ቤት በመግባት ትምህርቱን ተከታተለ። ከ፲፱፻፶፩ ዓ.ም. በቀድሞ ክብር ዘበኛ በወታደርነት በመቀጠር እስከ ፲፱፻፶፬ ዓ.ም. ጃዝ፣ ሳክስፎንና ሌሎችንም የሙዚቃ መሳሪያዎች መጫወት ጀመረ። በድምፁም ጭምር ስሜቱን ለማርካት በ፲፱፻፶፭ ዓ.ም. በምድር ጦር ኦርኬስትራ ተቀጠረ።[2]
ታምራት ለመጀመሪያ ጊዜ ካዜማቸው ዘፈኖቹ «ታምሜ ተኝቼ» እና «ዘውትር ብርቅነሽ» የተሰኙትን ዘፈኖቹን ለመጀመሪያ ጊዜ በመድረክ ላይ ሲያሰማ በተመልካቾች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን አትርፈውለት ነበር።[2]
ታምራት እስካሁን ድረስ የዘፈናቸው ዘፈኖች በርካታ ቢሆኑም «አስታውሺኝ»፣ «መሞት አለ ለካ»፣ «የለችም» እና «ጊዜው ለጨነቀው» የተሰኙት ዜማዎቹ የተዋጣላቸው ከመሆናቸው ባሻገር በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነት ያላቸው ናቸው።[2]
ታምራት ከነዚህ ስራዎች በተጨማሪ ሙሉ በሙሉ በአንታራም ግጥም በተሞላው «ሰበቡ» በተሰኘ ዘፈኑ ይታወቃል።
- ^ "ዝነኛው ድምጻዊ ታምራት ሞላ ከዚህ አለም በሞት ተለየ". thearadaonline.com (፭ የካቲት ፳፻፭). Archived from the original on 2013-02-26. በ፭ የካቲት ፳፻፭ የተወሰደ.
- ^ ሀ ለ ሐ "ናሽናል ቢብሊዮግራፊ ቡድን፣ የአንጋፋ አርቲስቶች መዝገበ የሕይወት ታሪክ፣ መጋቢት ፳፻፣ ገጽ 22-23". Archived from the original on 2011-09-29. በ2010-12-16 የተወሰደ.
- ^ "ብሔራዊ ቢብሎግራፊ (መዝገበ ቀረፀ ድምፅ ወምስል)፤ ሰኔ ፲፱፻፺፰ ዓ.ም.". Archived from the original on 2011-07-20. በ2010-12-16 የተወሰደ.