Jump to content

ኅሩይ ወልደሥላሴ (ብላቴን ጌታ)

ከውክፔዲያ
(ከኅሩይ ወልደ ሥላሴ የተዛወረ)
የብላቴን ጌታ ኅሩይን ሞት የሚያሳውቅ ደብዳቤ

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴኢትዮጵያ መኻል አገር በሰሜን ሸዋ በመርሐ ቤቴ አውራጃ በታች ቤት ወረዳ ረመሸት ቀበሌ ደን አቦ ገዳም በተባለ ሥፍራ በ ፲፰፻፸፩ ዓ.ም ተወለዱ። ሲወለዱ የተሰጣቸው ስም ገብረመስቀል ነበር። በቤተ ክህነት ትምህርት እንጦጦ ራጉኤል ደብር መጥተው የመጻሕፍትን ትርጓሜ በዘመኑ ከነበሩት የደብሩ ሊቃውንት ዘንድ ተምረው አጠናቀዋል። እዚህ ነው አንዱ መምህራቸው «አንተ የቀለም ቀንድ ስለሆንክና በምግባርህም የተመሰገንህ ነህና፡ ኅሩይ የተባለውን ስሜን ሸልሜያሃለሁ፡ ከንግዲህ ኅሩይ እየተባልክ ተጠራ!» አሏቸው። [1]

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ሃያ አንድ መጻሕፍትን የደረሱ ሲሆኑ፤ የመጨረሻው መጽሐፋቸው «የኢትዮጵያ ታሪክ፡ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል» ለመጀመሪያ ጊዜ በ ፲፱፻፺፱ ዓ.ም የልጅ ልጃቸው ወይዘሮ ሠናይት ተክለማርያም አሳተሙት። የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር እና የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በመተባበር ጳጉሜ ፪ ቀን ፳፻፬ ዓ/ም በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ የተመረቁትን እና ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ እንዲሁም የደራስያን፤- ቀኝ-ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤን፤ ነጋድራስአፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ፣ እና አቶ ተመስገን ገብሬን ምስል የተቀረጸባቸውን አራት ቴምብሮችን ገበያ ላይ አውለዋል።[2] ደራሲው ፋሽሽት ኢጣልያ ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጋር አብረው ወደ እንግሊዝ አገር ስደት ላይ እንዳሉ በስልሳ ዓመታቸው መስከረም ፱ ቀን ፲፱፻፴፩ ዓ.ም. አረፉ።

ሥርዓተ ቀብራቸው መስከረም ፲ ቀን እዚያው እንግሊዝ አገር ሲፈጸም ንጉሠ ነገሥቱ የሚከተለውን ንግግር አደረጉ።

«አሁን የአዳምን ልጆች ወግ ሲቀበል የምታዩት ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ በአገራችን ሥርዓት በመልካም አያያዝ ያደገ ከኢትዮጵያም ከፍ ካሉት ሊቃውንት የሚቆጠር ነው። ብልሃቱንና ትጋቱንም ለመልካም ሥራ የሚያገለግሉ መሣሪያዎች ስላደረጋቸው በመንግሥታችን ሥራ ለመመረጥና ወደ ታላቁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ለመድረስ በቃ። በየጊዜው የጻፋቸው ከፈትኛ ባህሪውን የሚገልጹ መጻሕፍት፤ ይልቁንም በቤተ ክህነትና በታሪክ እውቀት በዓለም ሊቃውንት ዘንድ የታወቀና የተከበረ አደረጉት። ለምታውቁት ሰው ከታሪኩ ከዚህ የበለጠ ልነግራችሁ የሚያስፈለግ አልመሰለኝም።

በአጭሩ ከጠባዩ ትልቅነት የሚሰማኝን ለመናገር ሳስብ ጊዜውን ሁሉ ቁም ነገር በመሥራት ማሳለፉ፤ ከራሱ ይልቅ የተቸገሩትን ለመርዳት መጣሩ፤ እውነትን፣ ፍርድንም ማክበሩና በአገር ፍቅር መቃጠሉ ትዝ ይሉኛል።

አገልጋዬና ወዳጄ ኅሩይ! በተቻለህ ስለአገርህ ሥራህን በሚገባ ፈጽመህ በምትሰናበትበት ጊዜ ታላቅ ነህ ሳልልህ ብቀር ሥራዎችህ ቀድመውኝ ይናገራሉ። በክፉ አድራጊዎች የሚገፋ የዓለምን ፀጥታ የሚያናውጥ ነፋስ ምንም ቢያንገላታህና በታላቅ ፈተና ላይ ቢጥልህም ሊያሸንፍ አልቻለም። ታላቅና ቸር በሆነው ጌታ በተመደበው ሕግ ግን መታዘዝ ግድ ሆነብህ። ይህም ለያንዳንዳችን የሚደርሰን ዕድል ነው። አንተም እስከ መጨረሻ ከታገልክ በኋላ ዛሬ ደከመህ፣ አንቀላፋህም። በሥጋ ብትለየንም ስምህና ሥራህ በመካከላችን ይኖራሉ።

ኅሩይ! እግዚአብሔር ሲያስበን አጥንቶችህና መንፈስህ የሚሰፍሩበትን ቦታ እስኪያዩና ከአባቶችህ እስኪቀላቀሉ ድረስ በእንግድነት በመጣህበት በዚህ ሥፍራ በሰላም ዕረፍ።» [3]

  1. ^ የኢትዮጵያ ታሪክ፡ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ - ፲፱፻፺፱ ዓ.ም
  2. ^ ‘ሪፖርተር’ Ethiopian Reporter, “የአራት ደራስያን መታሰቢያ ቴምብሮች ታተሙ” 09 SEPTEMBER 2012
  3. ^ የኢትዮጵያ ታሪክ፡ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ - ፲፱፻፺፱ (1999) ዓ.ም